>

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዘመናት በአገራችን ኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ጸንቶና ልዩነቶች ተወግደው እንዲኖሩ አርአያና ምሳሌ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥራና በአንድ መዋቅራዊ አስተዳደር ጸንታ መኖሯ የሚታወቅ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተከሰቱ ባሉ አለመግባባቶች መነሻነት ከአገራችንም አልፎ ጸንቶ በቆየው የቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ መዋቅር ላይ እየተከሰቱ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ነው፡፡ 

በዚሁ ምክንያት በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ መዋቅርና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት መካከል አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ግንኙነት መቋረጡን ተከትሎና በጦርነቱ ምክንያት ሁሉም የባንክ ተቋማት ሥራቸውን በማቆማቸው በየጊዜው እንደሌሎች አህጉረ ስብከት ለትግራይ አህጉረ ስብከት ይላክ የነበረው በጀት መላክ አልተቻለም፡፡ ይህም በጦርነቱ ከደረሰው ጉዳት በላይ በመዋቅሮቻችን ሥር ተመድበው ይሰሩ የነበሩ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶችና አገልጋይ ሠራተኞች ላይ የበጀት እጥረት አጋጥሞ ቆይቷል፡፡

ምንም እንኳን በባንክ መዘጋት ለአገልጋይ ሠራተኞች በጀት መላክ ባይቻልም የደመወዝ መክፈያ የባንክ ሂሣባቸው በአዲስ አበባ ከፍተው ሲገለገሉ የቆዩት አባቶች ማለትም፡

– ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ የመቐለ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ 

– ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና

– ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሽሬ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከጦርነቱ በኋላ እስከአሁን ድረስ ያለምንም መቆራረጥ ወርኃዊ ደመወዛቸው ወደ ባንክ ሂሣባቸው ሲገባ የቆየና እየገባ ይገኛል፡፡

– የብፁዕ አቡነ መርሐክርስቶስ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የባንክ ሂሣብ ግን በዚያው በሚኖሩበት አካባቢ የተከፈተ በመሆኑና በአካባቢው የባንክ አገልግሎት በመቆሙ በጀቱን ማድረስ ያልተቻለ ነው፡፡ በዚህም የዋናው መ/ቤት በእጅጉ ያዘነና በአገሪቱ የተከሰተው ጦርነት ሰላማዊ እልባት አግኝቶ መንግስታዊ መዋቅራዊ ግንኙነቱ እንደተጀመረ የተከሰቱ ችግሮችንና የደረሰውን የጉዳት መጠንና ማዕከል ያደረገ ውይይት በማድረግ ተገቢና ችግር ፈቺ በጀት ለመመደብ ይቻል ዘንድ ለሁሉም የትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃነጳጳሳት በቁጥር 197/897/2015 በ1/6/2015 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪ አስተላልፋለች፡፡

ቢሆንም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ፈቺ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ሲገባ በክልሉ የተከሰተውን ችግር ቤተ ክርስቲያናችን እንዳላዘነችና የጉዳቱ ቀጥተኛ ተጠቂ መሆኗን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ምላሽ አዘል መግለጫ እንደደረሰን ጉዳዩን በጽሞናና በትዕግስት በማየት በጥናት ላይ የተመሰረተ ችግሩን ሊፈታ የሚችል የአቀራራቢ ሽማግሌ ልዑካንን ለመመደብ በዝግጅት ላይ እያለን መጋቢት 13 ቀን 2015ዓ.ም. የቤተ ክርስቲያናችንን ጸንቶ የቆየ ተቋማዊ አንድነትና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀትን በሚንድ መልኩ “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት” ጽ/ቤት የሚል አዲስ ሕገወጥ ክልላዊ መዋቅር በመፍጠርና ያለምንም በቂ ማስረጃ ዋናው መ/ቤት በጀት እንደከለከለ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ እንዳገደ በአጠቃላይ በክልሉ በሚገኙ አህጉረ ስብከት ላይ አቅዶ ችግር እንደፈጠረ የሚያስመስልና ሕገ-ቤተ ክርስቲያኑን የጣሰ መግለጫ ከመሰጠቱም በላይ በሕገ-ቤተ ክርስቲያኑ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው በሁሉም አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ሊመደቡ የሚችሉት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ መሆኑ እየታወቀ ሆን ተብሎ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሥራ ላይ እያሉና ሲኖዶሳዊ አንድነቱ ጸንቶ ባለበት ሀኔታ ላይ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውጭና ያለቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ አሠራርን በጣሰ ሁኔታ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሊቃነ ጳጳሳት ተመድበው በሚሠሩባቸው የውጭ ዓለማት አህጉረ ስብከት ላይ ሊቃነ ጳጳሳት ከቀኖና ውጭ ራሳቸውን በራሳቸው በመመደብ መግለጫ መስጠታቸውን በመገናኛ ብዙኃን በመስማታችን በእጅጉ አዝነናል፡፡

በመሆኑም የእምነትና የታሪክ መሠረት በሆነው በታላቁ የትግራይ አህጉረ ስብከት እንዲህ ዓይነት መዋቅርን የሚንድና ቤተ ክርስቲያናችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ በዓለም መላውን የእምነቱን ተከታዮች የሚያሳዝን አድራጐት ለታሪካዊ ለትግራይ ሕዝብና ሊቃውንት የማይመጥን አድራጎት ከመሆኑም በላይ ለቤተ ክርስቲያናችን መዋቅራዊ አንድነትና መስፋፋት ተጋድሎ የፈጸሙ የቀደሙ ቅዱሳን አባቶቻችንን ያሳዘነ መሆኑን ለተከበረው የትግራይ ሊቃውንትና ሕዝብ የተሰወረ እንዳልሆነ በጽኑ እናምናለን፡፡

በመሆኑም ከላይ በዝርዝር ለመግለጽ እንደሞከርነው ፡-

1. በትግራይ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከት በጀት እንዳይላክ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነ አንድም ውሳኔ የሌለና በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት የባንክ አገልግሎት በመቆሙ የተከሰተ የግንኙነት መቋረጥ መሆኑ ታውቆ በጀቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ከአህጉረ ስብከት ጋር በመነጋገር ለመላክ ዝግጁ መሆናችንን እናሳውቃለን፡፡

2. በክልሉ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የደረሰውን ጉዳትና ችግር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰማትን ሐዘንና በችግሩም ወቅት ለአህጉረ ስብከቱ በበጀት ተደራሽ ባለመሆናችን ያስከተለው ችግር ያሳዘነን መሆኑን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ ገልጸን እያለንና የተከሰተው ጦርነት እንዲቆም በጸሎትና በምሕላ ስንማጸን መቆየታችን ወደጐን ተትቶና ተዘንግቶ ቤተ ክርስቲያናችን የጦርነቱ ደጋፊ በሚያስመስል መልኩ የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት የሌለውና ቤተ ክርስቲያናችንንም የማይገልጽ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡   

3. እናት ቤተ ክርስቲያን በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዳጩ ሆሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሕገወጥ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ፈተና ለመፍታትና የቤተ ክርስቲያናችንን ሲኖዶሳዊ አንድነትን ለማጽናት በከፍተኛ ኃላፊነት እየሠራች ባለበት ሁኔታ ለዚህ የቤተ ክርስቲያናችን ተልዕኮና ተቅማዊ አንድነት መጽናት በጸሎትም በሐሳብም ልንታገዝ ሲገባ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አበው የእምነትና የታሪክ መሠረት በሆነው የትግራይ ሊቃውንት እንዲህ ዓይነት ድርጊት መከሰቱ ለአገሩም ሆነ ለሕዝቡ የሚመጥን አድራጐት ባለመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን፡፡

4. በክልሉ ያለው አጠቃላይ መዋቅራዊ ችግሮችን በሚመለከትና አጠቃላይ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተከሰቱትን ችግሮች ተወያይቶ ለመወሰን መጋቢት 21 ቀን 2015ዓ.ም. በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 3 የሕግ ድንጋጌ መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ የተጠራ ስለሆነ በክልሉ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድባችሁ በመሥራት ላይ የምትገኙ ሊቃነጳጳሳት በጥሪው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ላይ እንድትገኙና ክልላዊ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ውይይት ላይ በመሳተፍ የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከአደራ ጭምር ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

5. የተከበራችሁ በትግራይ ክልል የምትገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እናት ቤተ ክርስቲያን በአባቶቻችሁ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ጸንታ እስከአሁን መቆየቷን ለእናንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ በመሆኑም በአገራችን በተከሰተው ፖለቲካዊ ችግር ዘመናትን በጽናት የተሻገረችውን እናት ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አንድነቷ መፍረስ ሲኖዶሳዊ ልዕልናዋ መጣስ የሌለበት መሆኑን በጽናት እንደምታምኑ እምነታችን የጸና ነው፡፡

ስለሆነም በሚያልፍ ችግር የማያልፍ ታሪክ ጥለን ማለፍ ስለሌለብን እንደቀደሙ አባቶቻችሁ አበው ሊቃውንት ለቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ አንድነት አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል በጽናት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ በቀደሙ አባቶቻችን ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

6. የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስቱም በክልሉ ተፈጥሮ የቆየው ችግር በሰላማዊ መንገድ በውይይት በመፈታቱ እናት ቤተ ክርስቲያን የተሰማትን ደስታ እየገለጸች አስቀድሞ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን የተመራው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለቀረበው የሰላም ጥሪ እናት ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተች እናስታውሳለን፡፡

በመሆኑም በተከሰተው ችግር የተፈጠሩ ጉድለቶች ካለ ጉድለቶችን ለማረምና ችግሮቹን ለመፍታት ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን የጸና አቋም እየገለጽን በክልሉ የተከሰተውን ተቋማዊ አንድነትን የሚጥስና ቀኖና የጣሰ አደረጃጀት እንዲቆም የበኩሉን ሚና በመጫወት ለቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ አንድነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም መላው በትግራይ ክልል የምትገኙ ምእመናንና ምእመናት በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተከሰተው ፈተና እንዲወገድና አንድነቷ ጸንቶ እንዲኖር በጸሎትና በምሕላ ጸንታችሁ ስታግዙ እንደቆያችሁት ሁሉ አሁንም በክልሉ የተከሰተውን ቀኖናዊ ጥሰትና ሕገወጥ አደረጃጀት ቆሞ እናት ቤተ ክርስቲያን በአንድነቷ ጸንታ እንድትኖር እንደአሁን ቀደሙ በጸሎትና በምሕላ ጸንታችሁ የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ እየጠየቅን የኢፌዴሪ መንግስትም እንደአሁን ቀደሙ በሲኖዶሳዊ አንድነት ላይና በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ የተጋረጠው ችግር ልዩ ትኩረት በመስተጠና የበኩሉን ሚና በመጫወት የቤተ ክርስቲያናችንን ሲኖዶሳዊ አንድንትና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀት ጸንቶ እንዲኖር አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

መጋቤት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. 

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic