>

“ከጅብ ጅማት የተወጠረ ክራር.....” (አሰፋ ታረቀኝ)

“ከጅብ ጅማት የተወጠረ ክራር…..” 

አሰፋ ታረቀኝ

ትህነግን ከሽብርተኝነት ፍረጃ ነጻ ለማድረግ በተጠራው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተደረገውን ውይይት ተከታትያለሁ፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነትና የጸጥታ አማካሪ ተብለው የተሰየሙት ሰው የሰጡትን አስተያየት ሳዳምጥ፣ ከብዙ አመታት በፊት ዶ/ር መረራ ጉዲና በኢህአደግ ፓርላማ ያሰሙት ቀልድ ታወሰኝ፡፡ በወቅቱ የተሰጠው ሹመት ያልጣማቸው ዶ/ር መረራ “አቅም የሌለውን ሰው የአቅም ግንባት ሚንስትር፣ አፍ የሌለውን ሰው አፈጉባኤ አድርጋችሁ ትሾማላችሁ” ነበር ያሉት፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንድህ አይነቱን ትህትና የራቀውና ጠብ ጫሪ የሆነ ሰው ለምን የደህንነትና ጸጥታ አማካሪ አድርገው አጠገባቸው አስቀመጡት? ሰውየው ለእንድህ አይነቱ ያልታረመና መረን የለቀቀ ንግግር ብቻ ነው የተፈለግው ወይስ ከዚህም የከፋ እቅድ ይኖር ይሆን?

ዛሬም ይህንን የተወናበደ ትርክት የሙጥኝ እንዳሉ ናቸው፡፡ “የትግራይ ህዝብ ሰላም ያስፈልገዋል” ካሉ በኋላ “ መለኪያው እኔ ነኝ የሚል መንፈስ፣ ጨፍልቆ የመግዛት ፍላጎት፣ አንተ እኔን ካልመሰልክ፣ እናንተ እኛን ካልመሰላችሁ ደረጃችሁ አይመጥነንም የሚለው ዝንባሌ……የሚያስፈራቸዉ አሉ”እያሉ ተውረገረጉ፡፡ ከአካላዊ ልዩነታቸው በስተቀር ነገረ ሥራቸው ሁሉ አቶ መለስ ዜናዊን አስታወሰኝ፡፡ የዚኽ ሁሉ ዛቻና ማስፈራሪያ ኢላማ የሆነው የአማራ ሕዝብ መሆኑ አጭርና ግልጽ ነው፡፡ ክግርግዳ ጋር ታስሮ ባለቤቱ እፊቱ የተደፈረችበት አባወራ፣ ሴት ልጃቸው በፊታቸው የተደፈረችባቸው ወላጆች፣ ላምና በሬዎቻቸው እንደሰው በጥይት የተረፈረፉባቸው የጎንደር፣ የወሎና የአፋር ህዝብ፣ የአቶ ረድዋን ሁሴንን ንግግር ሲሰሙ ምን ይሰማቸው ይሆን? የአማራውስ ህብረተሰብ አሁን እየከፈለ ካለው በላይ እንድከፍል ይጠበቅበት ይሆን? ሰወች ለምን ይሆን ከማይዘልቅ ታሪክ ጋር ተጣብቀው የሚቀሩት? አቶ ረድዋንና የኦሮሞ አክራሪዎች ማንሳት የማይፈልጉት ወይም የሚፈሩት አንድ ሀቅ አለ፡፡ እነሱ ተኝተው በሚያንኮራፉበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ እንደዚህ መቀጠል የለባትም፣ብለው ለለውጥ የተነሱትና እሳቱን ያቀጣጠሉት የአማራው ብሄር ተወላጆች ናቸው፡፡ ወንድማማቾቹ የንዋይ ልጆችና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ጉራጌአም ኦሮሞም አልነበሩም፡፡ ሁለቱ ከሸዋ ሌላው ከጎንደር ነበሩ፡፡

 ከህዋህት ማእድ የተቋደሰ ሁሉ አማራውን ለማሸማቀቅ የሚሄድበትን ርቀት ሳይና በጊዜ ውስጥም አለመቀየራቸውን ስመለከት፣ የአበው ተረት ትዝ አለኝ፤ “ ከጅብ ጂማት የተወጠረ ክራር ሲገርፉት እንብላው እንብላው ይላል”፡አቶ ረድዋንና መሰሎቻቸው በሌለ ነገር ላይ እንደተንጠለጠሉ የክፍለ ዘመኑ ሁለተኛ አጋማሽ ሊጀምር ነው፡፡ አቶ ረድዋን እደመቀበት ገብተው ማጨብጨብ ልዩ መታውቂያቸው እንደሆነ ከህዋህት ዘመን ጀምሮ እናውቃቸዋለን፡፡ ከህዋት በላይ ትግሬ እንደነበሩት ሁሉ፣ ከኦሆድድ በላይ ኦሮሞ ሆነው ለመታየት ሲደነፉ አየናቸው፡፡ ንግግራቸው ተፈናቅሎ በየካምፑ የሚሰቃየውን አማራ ያሳዝነው አያሳዝነው ጉዳያቸው አልነበረም፡፡ “እኔን ካልመሰላችሁ ደረጃችሁ አይመጥነኝም” አቶ ረድዋን፣ በጽሁፍ ነው ወይስ በድርጊት አማራው እንድህ ያለው? አንድ ህዝብ እንድህ ተደርጎ ይዘለፋል? ምናለበት ለልጆቸዎ አሳፋሪ ታሪክ ትተው ባያልፉ? የአራት ከፍለ ሀገር ህዝብ እንድህ በጅምላ ይወንጀላል?ለትግራይ ወንድሞቻችንስ ይጠቅማቸዋል? 

በልጅነቴ የሰማሁትን አንድ ተረት የዚህ ጽሁፍ መዝጊያ ላድርገው፡፡ ተረቱም እንድህ ይነገራል፤ “ ሦሥት በአስማት ጥበብ የተራቀቁ ጓደኞች መንገድ ሲሄዱ፣ ከአሞራና መሰል አውሬወች የተረፈ የአንበሳ አጥንትና ቁርጥራጭ ቆዳ ያያሉ፤ ከአስማተኞቹ አንደኛው፣ የዚህን አንበሳ አጥንት በአስማት ኅይል እገጣጥመዋለሁ ይላል፤ ሌላኛው ይነሳና እኔ ቆዳውንና ጸጉሩን እንደነበረ አድርጌ እመልሰዋለሁ ይላል፤ ሦሥተኛው አስማተኛ እናንተ ያላችሁትን ከሠራችሁ፣ እኔ ነፍሱን እመልሳታለሁ ይላል፡፡ ከማን አንሼ ትግል ገጠሙና እንደፎከሩት አንበሳውን ከሞተበት ቅስቅሰው ሦሥቱም በአንበሳው ተበሉ”፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ ሳያቅማማ አንገቱን ደፍቶ እየኖረ ያለ አማራ የኦሮሞው አክራሪና የነሱ ማእድ ተቋራሾች የዘለፋና የጥይት መለማመጃ አድርገውታል፡፡ የከንቲባዋን ethnic profiling, የሽመልስ አብዲሳን ያልተቋረጠ ጸረ አማራ ድንፋታ፣ የባሕል ሚንስትሩን ልሙጥ የሆነ የታሪክ “ትንተና” ታዝበን ሳንጨርስ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነትና የጸታ አማካሪ፣ ህዋህት ለጫረው ጦርነት አማራውን እኩል ተጠያቂ ከማድረግ አልፈው በሁሉም ዘንድ በ “ጨፍላቂነት እንደሚታይ ለማረጋገጥ “ይሉሽን በሰማሽ” በሚል አለቦታው በተሰነቀረ ተረት አጅበውታል፡፡ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ለምን እልባት ሳይሰጠው መዘግየት እንዳስፈለገ የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ  ጸረ አማራ ድንፋታ ፍንጭ ይሰጣል፡፡

አማራ መከዳቱንና ብቻውን መሆኑን፣ አልፎ ተርፎም እንድመናመን የተፈለገ መሆኑን የተረዳ ዕለት፤ የደንፊዎቹም፤ የኢትዮጵያም ዕጣ እንደ ሦሥቱ አስማተኞች እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ በመድረካቸውም በጥይታቸውም ኢላማ አደረጉትና መጨረሻው አስፈራኝ፡፡ 

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይታደጋት፡፡

Filed in: Amharic