>

በአገልጋዮቿ እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ እና በደል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሰጠ መግለጫ ።

በቅርቡ በተቋቋመው በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ በአገልጋዮቿ እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ እና በደል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሰጠ መግለጫ ።

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በተለያየ ዘመን በተነሱ ቅዱሳን ክርስትና እንዲሰበክ በማድረግ ለሺህ ዓመታት የሀገሪቱ የሃይማኖት፣ የታሪክ እና የሞራል ምንጭ ሆና ኖራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ራሷ የሆነው ክርስቶስን በመስበክ ያላመኑትን ከማሳመን፣ ያመኑትን ከማፅናት እና የፀኑትን ከመቀደስ ውጪ ሌላ ምድራዊ ዓላማ ሳይኖራት ነገስታቱንም ሆነ ምዕመኑን እኩል ንስሀ አባት መድባ አና ንስሀ አቀብላ፣ ቀድሳ አቁርባ እና ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም ለሁሉም እኩል ፍትሃት አድርጋ የምትሸኝ ሰውን በፆታው፣ በቋንቋው፣ በነገዱ እና በማንነቱ አድሎ ሳታደርግ የኖረች ናት። ሆኖም ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ውስጥ ያለአንዳች ማስረጃ የተፈጠሩ የሀሰት ትርክቶች እና እነዚህን ትርክቶች መሠረት ተደርገው በሰፊው ሲነዙ የነበሩ ሀሰተኛ መረጃዎች ቤተ ክርስቲያንን ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡ 

አሁን አሁን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ምእመናን በሃይማኖታቸው ብቻ ተለይተው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ አካላት ካህናት አባቶቻችን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋና ደሙን ቀድሰውና አክብረው ለሰዎች ድህነት ይሆኑ ዘንድ በተሰጣቸው ስልጣነ ክህነት ምእመናን ለርስት መንግሥተ ሰማያት የሚያበቁ ሁነው ሳለ በተለያዩ ጊዜ ለሞት እና ለእንግልት እንዲሁም ለስደት እና ለእስራት ሲዳረጉ ማዬት የእለት ተእለት ተግባር ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡ 

በአዲሱ መንግስታዊ መዋቅራዊ አደረጃጀት በአዲስ አበባ ዙርያ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሸገር ከተማ በሜጢ ሆርሲሳ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን የነበሩት ቄስ አባይ መለሰ በመጋቢት ፲ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ከቅዳሴ ወጥተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲሄዱ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በተፈጸመባቸው ድብደባ ሕይወታቸው ሊያልፍ መቻሉን ተረድተናል፡፡ 

መንግሥት የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ደህንነት የማስጠበቅ እና ዋስትና የመስጠት እንዲሁም ጭካኔ እና አረመኔያዊ ከሆኑ ጥቃቶች የመጠበቅ መንግሥታዊ ኃላፊነት ሊኖርበት ይህንን ባለመወጣቱ ምክንያት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ዜጎች በሕይወት የመኖር መብት በየእለቱ እየተሸረሸረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሀገረ ስብከታችን በቀሲስ አብይ መለስ ሞት የተሰማንን መሪር ኃዘን እየገለጽን የሚመለከተው የፌዴራል፤ የአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና የፍትህ አካል ጉዳዩን ልዩ ትኩረት በመስጠት ተገቢውን ምርምራ በማድረግ ይህንን አስነዋሪ እና ጭካኔ የተሞላበትን የግድያ ወንጀል የፈጸሙ ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ስር የሚተዳደሩ ቁጥራቸው ከዐሥራ ሦስት በላይ የሆኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በአዲሱ የከተማ ድንበር ማካለል ወደ ኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ክልል ውስጥ የተካለሉ ቢሆኑም ለዓመታት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገንብተው መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ 

፩ የኤርቱ ሞጀ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናትን ለማፍረስ ተሞክሮ ከእነዚህ ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በመሉ በአፍራሽ ግብረ ሀይል እንዲፈርስ ከመደረጉም በላይ የፈረሰውን ቤተ ክርስቲያን በውስጡ ከሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በሙሉ እንዲቃጠሉ እና እንዲወድሙ ተደርጓል፡፡ 

፪. በኤርቱ ሞጆ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን አጥሩን ማፍረስ ተጀምሮ ምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ባደረጉት ርብርብ የማፍረስ : ሒደቱ ለጊዜው ቢቆምም አሁንም ይህን ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሸገር ከተማ ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ስለሆነም ለሀገር ባለውለታ የሆነችን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በማሳደድ እና በማውደም ታሪካዊ መሠረቷን ለመናድ እና ከሌሎች ቤተ እምነቶች በመነጠል በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተፈጸመ ያለው አድሏዊ እና ኢ-ሕገ መንግስታዊ የሆነው ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲደረግ እያሳሰብን የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥትም የድርጊቱን ፈጻሚ አካላት ላይ ተገቢውን እርምት እንዲወስድ ስንል እንጠይቃለን፤ 

በመጨረሻም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የሚመለከተው ባለስልጣን አካል በየካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በገነተ ጽጌ ቅዱስ

ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመውን እና ሕገ ወጥ ተግባርን በተመለከተ የድርጊቱን ፈጻሚ አካላትን በ፭ ቀናት ጊዜ ውስጥ ተለይተው በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ለሕዝብ እንዲያሳጡት ጥሪ ያስተላለፈች ቢሆንም ይህ መግለጫ  አስከሚሰጥ ድረስ ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ተለይተው ተጠያቂ አለመሆናቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘነ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ቤተ ክርስቲያን ያቀረበችውን ጥያቄ ምላሽ ሊሰጥ ያልቻለ በመሆኑ የድርጊቱን መነሻ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት እና የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለይቶ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ በማዋቀር ወደሥራ የተገባ መሆኑን እያሳወቅን ኮሚቴው የደረሰበትን ጥቅል መረጃ በአጭር ቀናት ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ሪፖርቱን የሚያቀርብ እና የድርጊቱ ፈጻሚዎች ቤተ ክርስቲያንን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ እና አጥፊዎችም ለድርጊታቸው ተገቢውን ሕጋዊ ቅጣት እንዲያገኙ እየሠራን መሆኑን እናሳውቃለን። 

በመሆኑም፡ 

፩. መንግሥት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በመሆናቸው ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ በመንገድ ላይ ተደብድበው ሕይወታቸው እንዲያልፍ የተደረጉት የቄስ ዐብይ መለሰ ገዳዮችን ተከታትሎ ለፍርድ እንዲያቀርብ እና ችግሩን ከሥር ከመሠረቱ በመፍታት የአገልጋዮችንና የምእመናን መብት እንዲያስከብር

፪. በሸገር ከተማ አስተዳደር እየተፈፀመ ያለው አብያተ ክርስቲያናትን የማፍረስ ድርጊት በአስቸኴይ እንዲቆም እንዲደረግ፣ 

፫. የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት ቦታ ተመላሽ እንዲያደርግ እና የፈረሰውን ቤተ ክርስቲያንም በራሱ ወጪ እንዲያሠራ እንዲደረግ እንጠይቃለን። 

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን እና ምእመናት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባቶች ዘመነ ቤተ ክርስቲያንን በጉልበታችን፤ በዕውቀታችን እና በገንዘባችን የምናገለግልበት ብቻ ሳይሆን በአካላችን፣ በጤናችን እና በሕይወታችንም መስዋዕትነትን የምንከፍልበት የሰማዕትነት ዘመን ነው፡፡ ይህ የሰማዕትነት መከራም በሀገራችንና በየቤታችን እየመጣ ያለ የመከራ ዘመን በመሆኑ አብዝቶ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ፤ ሥጋችንን በጾም እና በስግደት በመግራት ከአባቶቻችሁ አባታዊ መመሪያ በመቀበል በሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ 

እግዚአብሔር ሀገራችንን እና ህዝቦቿን ይባርክ መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም 

ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ በትላንትናው ዕለት ቤተክርስቲያን ያደረገችውን ጥሪ በመቀበል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ  አህመድ በተገኙበት የተደረሰውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመቀበል በዛሬው  ዕለት ወደ እናት ቤተክርስቲያናቸው መመለሳቸውን የሚገልዕ ደብዳቤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በማቅረብ በይፋ ተመልሰዋል።

ቤተክርስቲያንም በተደረሰው ስምምነት መሰረት ወደ ሥራ የምትመልሳቸው ሲሆን ደመወዛቸውንም የምትከፈልና የታሸገውን ቤታቸውን በመክፈት እንደምታስረክባቸው የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ገልጿል።

Filed in: Amharic