>

የአቶ ታዲዮስ መንፈሳዊ ጥንካሬ (አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም - አዲስ አበባ)

የአቶ ታዲዮስ መንፈሳዊ ጥንካሬ 

  አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም ( አዲስ አበባ)

መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 3ኛ የጸረ ሽብር ወንጀል ችሎት የአንጋፋው የታሪክ ተመራማሪና ጋዜጠኛ አቶ ታዲዮስ ታንቱ የፍርድ ሂደት የሚታይበት ቀጠሮ ግዜ በመሆኑ ከረፋዱ 3፡30 ላይ ለመታደም በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ቀደም ብዬ ተገኝቼ ነበር፡፡ የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል ከመጡ ቤተሰቦችና ሌሎች ግለሰቦች ጋር አግዳሚ ወንበር ላይ በመጠባበቅ ላይ እንዳለሁ አቶ ታዲዮስን የያዘው የማረሚያ ቤቱ አውቶብስ የግቢውን ትልቅ በር አቋርጦ ሲገባ አስተዋልኩ፡፡ ወዲያውኑ በሰንሰለት የተቆራኙ የህግ ታራሚዎች ተራ በተራ መሳሪያ ባነገቱ የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች እየታጀቡ በተለምዶ አንበሳ ማሰሪያ ተብሎ በሚጠራው ጊዚያዊ ማቆያ ሲወሰዱ ተመለከትኩ፡፡ ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ ግን መንፈሰ የሚያነቃቃ፣ ሞራልን የሚገነባ አንድ ሰው ከሌላ የህግ ታራሚ ጋር በሰንሰለት ተቆራኝቶ በመንፈሳዊ ጥንካሬ ሲራመድ ተመለክትኩ፡፡ ያ ሰው ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ ነበር፡፡ በእውነቱ ለመናገር የጋሼ ታዲዮስ መንፈሳዊ ልእልና እና የህሊና የበላይነት በስፍራው የነበሩትን እውነተኛ ኢትዮጵያውያንን ፈገግ ያሰኘና ያስደሰተ ነበር፡፡ የዚህ ሰው አረማመድ በ80ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኝ አዛውንት አይመስልም ነበር፡፡ ቀልጠፍ ብሎ ሲራመድ፣ በፊቱ ላይ ይነበብ የነበረው የሞራል የበላይነት፣ኮስታራነት በስፍራው የነበሩትን ሁሉ አስገርሟል፡፡ የሶየውን ሞራል ለመስበር፣ ህሊናውን ለማድማት ብዙ ሴራ የሸረቡትን የጎሳ አምበሎች ያሳፈረ ነበር፡፡( ከሴራቸው ውድቀት መማር ከቻሉ ለማለት ነው፡፡) በአጭሩ የጋሼ ታዲዮስ መንፈስ አልተሰበረም፡፡ አይገባቸውም ወይም እንዲገባቸው አይፈልጉም እንጂ ሶየው በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ለሚወዱት ኢትዮጵያውያንም ሆነ በጎሳ ፖለቲካ አቅላቸውን ለሳቱ አሳሪዎቹ ልበሙሉነቱን አሳይቷቸዋል፡፡  ጋሼ ታዲዮስ ለእውነት ብሎ፣በእውነት ምክንያት በዘረኞችና አምባገነኖች እንደ ጥጃ ሲታሰር እና ሲፈተ የነበረ ጎምቱ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ያ/ የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ድምጻዊ እና ተወረግራጊ ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ (ነብሱ በሰላም ትረፍ)

ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ፣

ለእውነት እሞታለሁ፡፡

ብሎ በዛ ጥኡም ድምጹ አንጎርጉሮ እንዳለፈው፡፡ ጋሼ ታዲዮስ ለእውነት ብለው ብዙ መከራን ተቀብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት እና የብዙ ሺህ አመታት ታሪክ ባለቤትነት ጽኑ አቋም ያላቸው ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ በተለይም ባለፉት 5 አመታት የአማራ መከራ አላባራ በማለቱ እኚህ ሰው በግልጽ በአደባባይ የሚፈጸመውን ግፍ በማጋለጣቸው በአገዛዙ ጥርስ ተነክሶባቸው ቆይተዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በዚህ የአዛውንት የእድሜ ዘመናቸው ከአንድም ሁለቴ ሶስቴ በግፈኞች ዘብጥያ ተወርውረው ለወራቶች ከታሰሩ በኋላ ተለቀው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ካለፈው አመት ክረምት መግቢያ ጀምሮ በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ አጥንትን ሰርስሮ በሚገባው እና ዘላለማዊ በሆነው የስንኝ ቋጠሯቸው ነግረውን እንዳለፉት ( ከገባን ማለቴ ነው)

እምዬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡

የኢትዮጵያን መራር እውነታ ነግረውናል፡፡ በ1983 ዓ.ም. በዱር በገደሉ፣በሰሜን ኢትዮጵያ በረሃ እና ቀይ ባህር የተዋደቁ የአንድነት ሀይሎች የትም ተበትነው ገንጣይና አስገንጣዮች የሀገር መሪዎችና ብቸኛ ሀብት ዘራፊዎች ከሆኑ በኋላ ነበር የእኛ ነገር እያከተመ የመጣው፡፡ እነኚህ ጎሰኞች የሀገር ዋርካዎችን ካጠፉ በኋላ በኢትዮጵያ ሀብትና ነብረት ብቸኛ አዛዥና ናዛዥ በመሆናቸው የተነሳ ኢትዮጵያን እያዳከሙ አሁን የደረስንበት እጅግ አስፈሪ ግዜ ደርሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምትገኝበት በዚህ አስጨናቂ ግዜ እና ሀገሪቱ የሰው ምድረበዳ እየሆነችበት በምትገኝበት ግዜ እንደ አቶ ታዲዮስ ታንቱ ያሉ ጎምቱ ሰዎች ለኢትዮጵያ ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማታቸውን አላቆሙም፡፡ ኢትዮጵያ በምትገኝበት በዚህ አስጨናቂና ጨለማ ዘመን ሶየው አንጸባራቂ ኮከብ ሆነው ከፍ ብለው ታይተዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ታሪክ ጠበቃ፣ ቅርሶች እንዳይጠፉ፣ ተሟጋች፣ በዜጎች ላይ በተለይም በአማራዎች ላይ የተፈጸመውን ግፍ በጓዳ ሳይሆን በአደባባይ፣ በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው በማውገዝ የኢትዮጵያዊነት ግዴታቸውን ሁሉ የተወጡ ታላቅ ሰው ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ጋሼ ታዲዮስ ለኢትዮጵያ ታሪክ መከበር ፣ በአንድ ህዝብ ( በተለይም በወለጋና ሌሎች አካባቢዎች በሚኖረው የአማራ ወገናችን ላይ) የተፈጸመውን ግፍ ፍንትው አድርገው በማቅረብ፣ ግፍ የተፈጸመበት ህዝብም እራሱን መከላከል እንዳለበት ታሪክን በማጣቀስ በማስተማራቸው የተቆጣው አገዛዝ የታሪክ እውቀት አለን ባዮችን ደጋፊዎችን በታወቀ መገናኛ ብዙሃን አቅርቦ ማከራከር ሲገባውን እኚህን ታላቅ የታሪክ ሰውና አንጋፋ ጋዜጠኛ በአዛውንት የእድሜ ዘመናቸው ለአንድ ግዜ ሳይሆን ለተደጋጋሚ ግዜ ወህኔ ቤት በመወርወር ስቅየትን እንዲቀበሉ ማድረጉ የግፍ ግፍ ነው፡፡

ትላንት ኢትዮጵያን ለማጥፋት እስከ ሲኦል ድረስ ቢሆን እንሄዳል ያሉ፣በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ዋና መሃዲስ እና በሙስና የተጨማለቁት፣ እነ አቶ ስብሐት ነጋ በአደባባይ ደረታቸውን ነፍተው በሚሄዱበት ሀገር ፣ እነ አቶ ታዲዮስ ታንቱን የመሰሉ የእውነት ጠበቆች በእገረሙቅ ታስረው ማየት በእውነቱ ያማል፡፡ የኢትዮጵያንም እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡

አቶ ታዲዮስ በእለቱ ፍርድ ቤት የቀረቡት ጠበቆቻቸው በምስክርነት የጠየቋቸው ሰዎችን ቃል ለማሰማት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ገሚሱ በህመም፣ሌሎች ደግሞ ለመምጣት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ምስክሮች ተሟልተው አልቀረቡም ነበር፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የአቶ ታዲዮስ ጉዳይ ከሰኞ መጋቢት 25 ቀን እስከ እሮቡ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚታይ ሰምቻለሁ፡፡

እንደ መደምደሚያ

የአቶ ታዲዮስን የፍርድ ሂደት ለመከታተል የተገኙት ባለቤታቸውና አንዲት ሴት ልጆቻቸው፣ ከእኔ ጋር ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ በችሎቱ ተገኝተው የነበረው፡፡ በተረፈ 3ቱም ጠበቆቻቸው ነበሩ፡፡ በእውነቱ ለመናገር ለኢትዮጵያ ህዝብና ታሪክ መከበር ሲል፣ በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለን ወንጀልና ግፍ በአደባባይ በማውገዙ ምክንያት በግፍ እስር ላይ ለሚገኙት ጋሼ ታዲዮስ የፍርድ ሂደት ችሎት ላይ ታዛቢ መጥፋቱ ሲታሰብ በእውነቱ ህሊናን ያደማል፡፡

በሀገራችንም ያለውን ከባድ መከራና ፍጹማዊ አምባገነንትን ማሳያም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ጥቂትም ቢሆኑ ነጻ ጋዜጠኞች የት ገቡ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ ለህግ የበላይነት መከበር ቆመናል የሚሉ የመብት አስከባሪዎች የት ገቡ የአቶ ታዲዮስ ጉዳይ ያሳስበናል የሚሉ እንዴት 10 ሰዎች እንኳን ጠፉ፡፡ እስቲ ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡ በእኔ በኩል የህዝቡ የፍርሃት መጠን ከፍ በማለቱ እና ህዝቡ በሌሎች በብዙ መከራዎች ውስጥ የተዶለ በሆኑ እንደ አቶ ታዲዮስ የመሰሉ የግል ጀግኖቹን እየዘነጋ የመጣ መሰለኝ፡፡ ይህ ግን በፍጹም መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ አቶ ታዲዮስ ለኢትዮጵያ ሲሉ በኢትዮጵያ ምክንያት በግፍ የታሰሩ ሰው ናቸው፡፡ መስከረም አበራ የተባለች ጥንታግ ጋዜጠኛና ፖለቲካ ተንታኝ በአንድ ወቅት እንደነገረችን አቶ ታዲዮስ የሚጠይቃቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሰው ናፈቀኝ ያሉት እንደው ዝም ብለው አይመስለኝም፡፡ ሰውማ አጠገባቸው ሞልቶ ተርፏል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ የአቶ ታዲዮስ ጥያቄ ወደ እስር ቤት እየተመላለሱ የሚይቋቸውን ሰዎች ይሻሉ፡፡ የታሪክ መጽሐፍትን የሚያቀብላቸውን የህሊና ሰው ይፈልጋሉ፡፡ የፍርድ ሂደቱ የተዛባ እንዳይሆን ታዛቢ የህሊና ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች በፍርድ ቤት የቀጠሮ ቀናቸው ተገኝተው ሚዛናዊ ምልካታቸውን እንዲከውኑ ይሻሉ፡፡ ምን ያህል ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ናቸው በተቀጠሩበት የፍርድ ቤት የቀጠሮ ግዜ ተግኝተው የነበረው መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ኢትዮጵያውያን እተወዋለሁ፡፡

በመጨረሻም ከእድሜ ጫና በቀር የጋሼ ታዲዮስ መንፈሳዊ ጥንካሬ የእርሳቸውን ጉዳይ ለሚከታተሉ ሁሉ የመንፈስ እርካታን የሚሰጥ መሆኑን በማስታወስ እሰናበታለሁ፡፡

Filed in: Amharic