>

የዐምሐራው ትግል የሚከሽፈው ጭራቁን ዐቢይ እና አገዛዙን ያዳመጠ ዕለት ነው (ከይኄይስ እውነቱ)

‹‹ልዩ ኃይል›› ማፍረስ የሚለውን የቅጥፈት ማደናገሪያ ትተን ጭራቁንና አገዛዙን ደምስሶ የዐምሐራውን ሕዝብ ህልውና እና ኢትዮጵያን መታደግ ቀዳሚ ዓላማችን ይሁን!!!

የዐምሐራው ትግል የሚከሽፈው ጭራቁን ዐቢይ እና አገዛዙን ያዳመጠ ዕለት ነው

ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ ማረስ የለም

ከእንግዲህ ወዲህ የዐምሐራው ሕዝባዊ ኃይልም (ፋኖ፣ ‹ልዩ ኃይል›፣ ሚሊሻ፣ ሌሎችም) ሆነ ሕዝቡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት አለ ብሎ ይህንን የወሮበሎች አገዛዝ እንደ መንግሥት ቈጥር የሚንቀሳቀስ ከሆነ ያን ጊዜ በገዛ እጁ የራሱን ጥፋት ያፋጥናል፡፡ የጭራቁን እና አገዛዙን ባሕርይ – ቅጥፈቱን፣ የለየለት ዋሾ መሆኑን፣ በአፉ እየሸነገለ ከዳተኛነቱን፣ የዐምሐራ ሕዝብ በተለይ፣ የኢትዮጵያ ባጠቃላይ ጠላት መሆኑን – አሁን ላይ ዐላውቅም አልተረዳሁም የሚል የዐምሐራ ትግል እንኳን ኢትዮጵያን የራሱን ህልውና ሊታደግ አይችልም፡፡

‹ልዩ ኃይል› የሚባል ሕገ ወጥ የጦር አደረጃጀት በደደቢትም ‹ሰነድ› ቢሆን ሕገ ወጥ ብቻ  ሳይሆን ላገር ህልውናና ለአብሮነት ጠንቅ እንደሆነ ገና ከማለዳው ብዙዎች ተናግረን ያዳመጠንም የለም፡፡ ጭራቁና ሌላው ዕብድ ሽመልስ የሚመኩበት ሕገ ወጥ ሠራዊት መከላከያን አኅሎና መስሎ ከመደራጀቱ በፊት አያስፈልግም ብንልም የጐሣ ሥርዓቱ ውጤት ሆኖ አሁን ላይ ከቊጥጥር ውጭ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህ የጐሣ ሥርዓት እስከ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ› እና ‹ክልል› የተባለው የአትድረሱብኝ መዋቅር በሕዝብ ትግል ከኢትዮጵያ ምድር ጠፍቶ ባገርና በሕዝብ ሉዐላዊነት፣ በግዛት አንድነትና ባንድ ሰንደቅደ ዓላማ ብሔራዊ መለያነት፤  በብቃትና በኢትዮጵያዊ ዜግነት መሠረት ላይ እውነተኛና አስተማማኝ የሀገር መከላከያ ኃይል እስኪገነባ ድረስ ይህ ሕገ ወጥ ኃይል መቀጠሉ የማይቀር ብቻ ሳይሆን ‹አስፈላጊም› ሆኖ ይታያል፡፡ ባጭሩ በኦሕዴድ የሚመራው የጐሣ አገዛዝ የሀገር መከላከያን አፍርሶ የሠላሳ ዓመት ህልውና ያለውንና ወያኔ የፈጠረለትን ኦሮሚያ የሚባል የኢትዮጵያ አንድ ግዛት የ‹ጦር ኃይል› በመከላከያ አቋም ገንብቷል፡፡ ይሄ በኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሀብትና በሀገር መከላከያ ስም ሠልጥኖና ታጥቆ፣ ከሚገባው በላይ አብጦ የሚገኘው ኃይል ለአገዛዙ ዋስትና ቢመስልም ሥሪቱና አመለካከቱ አገር አጥፊ ኃይል በመሆኑ በጊዜው ጊዜ በየአካባቢው ከተደራጁ ‹ልዩ ኃይሎች› ጋር ያለ ጥርጥር በጥንቃቄ መበተን ይኖርበታል፡፡ ጊዜው ግን  አሁን አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ጆሮውን ለጭራቁና ግብር አበሮቹ የሚሰጥ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በተለይም ዐምሐራው ሕዝብ የማይቀለበስ ታሪካዊ ስሕተት ፈጻሚ ይሆናል፡፡  

ሰሞኑን የአማራ ሕዝብ ብሎም የኢትዮጵያ አለኝታ ሊሆን የሚችለው ፋኖ አባላት ካሉበት ሆነው ቀጣፊው አገዛዝ የአካባቢ ‹ልዩ ኃይል›ን በማፍረስ የሐሰት ምክንያት (pretext) ዐምሐራውን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከቻለ ለማጥፋት ካልቻለ አሽመድምዶ ለማንበርከክ የሸረበውን ሴራ በሚመለከት የተሰማቸውን ስሜትና ትግሉ ምን መልክ መያዝ እንዳለበት በቊጭት ሲናገሩ አዳምጬአለሁ፡፡ ለነዚህ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ ያለኝን ታላቅ አክብሮት እየገለጽኹ በዚህ ንግግራቸው ውስጥ ከታዘብኹትና በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለ ስሕተት እንደሆነ በአክብሮት ለመጠቆም የምፈልገው ‹መንግሥት› ለመነጋገር/ለመደራደር ዝግጁ ከሆነ እኛም ዝግጁ ነን የሚመስል ንግግር አድምጬአለሁ፡፡ ምን ማለት ነው? የማይተካ ሕይወታችሁን ለሕዝባችሁ ለመስጠት ከቆረጣችሁና ዝግጁ ከሆናችሁ ጀግኖች ይህንን በጭራሽ አልጠብቅም፡፡ የዚህን አገዛዝ ፀረ-ዐምሐራነትና፣ ፀረ-ኦርቶዶክስ ተዋሕዶነት፣ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቅጥረኛና ባንዳ መሆን፤ ለእናንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል፡፡ ትግላችን ኹሉ ጭራቁን ዐቢይና አገዛዙን በጭራሽ ካለማመን መጀመር ይኖርበታል፡፡ ይህንን መልእክት ደጋግሜ ስናገር ቆይቼአለሁ፡፡ ባንድ ወገን አንድም ንጹሐ ሰው እንዳይሞት ከመፈለግ፣ በሌላ በኩል የዐምሐራን ሕዝብና ባጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚታደግ መልእክት በመሆኑ አሁንም በአጽንዖት ለመናገር አልሰለችም፡፡ 

ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያውያን ኹሉ ደጋግሜ እንደተናገርኹት በጐሣ አገዛዝ ውስጥ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል የሚባል ሊኖር አይችልም፡፡ እሳቤውም መዋቅሩም አይፈቅድም፡፡ ባለፉት 32 ዓመታት ባጠቃላይ፤ በተለይም ባለፉት 5 ዓመታት ኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት አልነበራትም፤ የላትምም፡፡ በአገር መከላከያ ስም የሚነግድ የኦነግ/ኦሕዴድ ሠራዊት   ግን አለ፡፡ ዛሬ ጭራቁ ዐቢይ ወደሚፈራው የዐምሐራ ሕዝብ ለወረራ የላከው የበግ ለምድ የለበሰ (የመከላከያን ስም የያዘና ልብሱን የለበሰ) የኦሕዴድን ‹ልዩ ኃይል› ነው፡፡ ይህንን ፈሪና አውሬ ኃይል እመ አምላክን እንድታምረው፡፡ በኃያ ሰባት ዓመታቱ ባጠቃላይ፣ ባለፉት 5 ዓመታት በተለይ በዐምሐራ ሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንት ላይ ለማየት፣ ለመስማትና ለመናገር የሚዘገንን ግፍ የፈጸመውን ኃይል ላይ አንዳች ርኅራኄ እንዳይኖርህ፡፡ በባለጊዜነት ላገር መከላከያ ሠራዊት ሊሆን የሚገባውን ሀብት (ስንቅና ትጥቅ) የያዘና ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልእኮ ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ የአውሬዎች ጥርቅም በመሆኑ መሥፍን አረጋ የተባለ ወንድሜ እንደመከረህ በፊት ለፊት ሳይሆን በደፈጣ/በሽምቅ ተፋለመው፡፡ የዐባይ በርሃ ሲሳይ አድርገው፡፡ መላ ኢትዮጵያ ግዛቱ የሆነው ዐምሐራው ለጊዜው ከልለው ባስቀመጡት አካባቢ ኹሉ ይህ በኢትዮጵያና ሕዝቧ ጥላቻ ላይ የተዋቀረው አጥፊ ኃይል መላኩ ስለማይቀር ‹የሀገር መከላከያ› መስሎህ ሳትዘናጋ ስም አጠራሩ ሳይቀር ድራሹ እንዲጠፋ አድርገህ ልኩን ልታሳየው ይገባል፡፡ 

ሌላው እስካሁን እንቆቅልሽ ሆኖ አልፈታ ያለኝ ጉዳይ ግን ዘላለማዊ አሽከርና የዐምሐራው ሕዝብ ተቀዳሚ ጠላት የሆነው ብአዴን የሚባል በድን ድርጅት በተለይም አመራሩን የዐምሐራ ሕዝብ የታገሠበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ጠላት እኮ ከሩቅ አይመጣም፡፡ ውስጥ ዐዋቂና እንደ መዥገር የተጣበቀ ጠላት ግን አደገኛ ነው፡ ይሄ ቆሻሻ ቡድን ለበጎ ሥራ በድን ቢሆንም ለጥፋት ግን ‹ሕያው› ነው፡፡ የዐምሐራ ሕዝብና የኢትዮጵያን ጠላቶች – ወያኔ ትግሬን እና ኦሕዴድ/ኦነግን – ለ32 ዓመታት በታማኝ ሎሌነት ሲያገለግል የኖረውን የነውረኞች ቡድን ከምድሩ ጀግና ሳይጠፋ የወንድ ክንድ ያላረፈበት ለምን እንደሆነ ምሥጢር ሆኖ ዘልቋል፡፡ 

በመጨረሻም በውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን (በተለይም የዐምሐራውና የጉራጌው ማኅበረሰብ አባላት) ትግላችን ባህል ሆኖብን እንደለመድነው ለመንቀል ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ኹሉም ኢትዮጵያውያን (ወርድ፣ ስፋት፣ ቊጥር ወዘተ. የሚባል አላስፈላጊ ቅጽል ሳይጨመርበት) በእኩልነት የሚታዩበት፣ የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበትና እኩል ተጠቃሚ የምንሆንበትን ሥርዓት መትከል ላይ እንዲሆን ትግሉን ባግባቡ እንድትመሩትና አቅጣጫ እንድታስይዙት በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሕይወቱን እየገበረ ያለው ወገናችን መሥዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆን አጥብቀን ልናስብበት ይገባል፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ዕርፍ ይዞ ወደ ኋላ አይታረስም እንዲሉ፣ የጠላትን አፍራሽ ወሬ ከቁብ ሳንቆጥር ሁለ ገብ ትግሉን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ አንድም ሰው ተመልካች መሆን የለበትም፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሁላችን በተሰጠን ጸጋ የበኩላችንን ጠጠር ማስቀመጥ ግዴታችን ነው፡፡ አንድ ጥግ ይዞ የደሀ ልጅ አልቆ እኔ በሰላም እኖራለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ ባይፈጠር ይሻለዋል፡፡ አንድ ቀን የያዝኸው ‹ጥግ› መሐል ሆኖ ተልካሻ ሞት እንደምትሞት ልታስብ ይገባል፡፡ በርግጥም መሐሉ ዳር የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

Filed in: Amharic