>
5:31 pm - Thursday November 12, 9435

ይድረስ ለኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት! (ፊልጶስ)

ይድረስ ለኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት!


ይኽን መልዕክት ለመተየብ ከመጀመሪ በፊት፤ ለአገሬ መከላከያ ሠራዊትና  ለአረንጓዲ፣ ቢጫ፤ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን ያለኝን አክብሮት ተንበርክኬ  በመግለጽ ነው። እንደ አንድ  ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤ ይኽን  መልዕክት  ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋና ምክንያት ደማችሁን እያፈሰሳችሁ፤ አጥታችሁን እየከሰከሳችሁ የህይወት መሰዋትነት እየከፈላችሁ ያሰከበራችኋት  ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን፤ ፓለቲከኞች በፈጠሩት የጎሳ ፓለቲካ ምክንያት አገራችን እጅግ አደግኛ ሁኔታ ላይ መሆኗና እናንተን በቀጥታ ስለሚመልከታችሁ ብቻ ሳይሆን፤ ለቀባሪ ማርዳት ባይሆንብኝ ፤ አገርንና ህዝብን የመታድግ ኃላፊነት በእናንተ ላይ የወደቀ በመሆኑ ነው።
 
መቼም እናንተ የምትኖሩቱን ህይውትና የምትከፍሉትን መሰዋአትነት  ለመጻፍ መሞከሪን በበጎ እንደምታዮልኝ እምነቴ ነው። የምጽፈው መልዕክትም ሁሉም ዜጋ የሚያውቀውና የተለመደ ቢሆንም ማስታወሱ ግን  በዚህ  ፈተኝ ወቅት ክፋት የለውም ብየ አምናለሁ።  ይህም የተከበረውን   የአገር መከላከያ ሠራዊት ክብር መንካት  ሆኖ እንደማይቆጠርብኝ  ተስፋ አለኝ።

የሰው ልጅ  ለአገሩና ለወገኑ ከነፍሱ የበለጠ የሚሰጠው በምድር ላይ የለም። ነፍሱን አስይዞ ለወገኑና ለአገሩ የሚኖር ኃይል ቢኖር  ደግሞ መከላከያ ሠራዊት ነው።  መከላከያ ሠራዊት ከመላው ህዝብ የተውጣጣ  የህዝብ ልጅ ነው። ስለሆነም  ስለምቾት ሳያስብ፣ ለመኖር ሳይጓጓ ፤  በቀበሮ ጎድጓድ ፣ አፈር ሆኖ፣ አፈር ለብሶ ሁሌም በተጠንቀቅ  ወገኑን ይጠብቃል። አገሩን ከጠላት ይከላከላል።

በብዙ የዓለማችንና የሰለጠኑ አገሮች መከላከያ ሠራዊት ቋሚ፣ የተክበረና  ዘመናት ያስቆጠረ ተቋም ነው። በክብርና  በቋሚነት ከትውልድ – ትውልድ  ዘመናት መሻጋር የቻለው ደግሞ ”ፓለቲካን” ለፓለቲከኞች ትቶ፤ ምንም አይነት ልዮነት ሳያደርግ    ከህዝብ ጋር መቆሙና የህዝብ ልጅነቱን ማስመስከሩ ነው።  የአገር አንድነትንና ህዝብን ከመጠብቅ ውጭ ፤ ለፓለቲካው ገለልተኛ  መከላከያ ሠራዊት ያላቸው  አገሮች የበለጸጉና ህዝባቸውም በሰላም የሚኖር ነው።

ዛሬ አገራችን በባሰ ድህነትና ርስ-በርስ ጦርነት ላይ ትገኛለች። የዚህ ሁሉ መዘዝ ፓለቲካኞቻችን  ሥልጣን ላይ ለመቆየትና ለሚፈጽሙት ወንጀል ተጠይቂ ላለምሆን   ህዝብን በቋንቋና በጎሳ ከፋፍለው በመግዛታቸው  መሆኑ የሁላችንም ሃቅ ነው።

ባለፋት ሁለት ዓመታት ከህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ (ወያኔ) ጋር የተደረገው ጦርነት የደረሰውን እልቂትና የተከፈለውን  መሰዋአትነት ከእናንተ  ከመከላከያ ሠራዊት የበለጠ የሚያውቀው ምድራዊ ኃይል የለም። ጥቅምት 24 ቀን  2013  ወያኔ በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ በደርቅ ለሊት የፈጸመው ጭካኔና ግፍ  ውድ ህይወታችሁ እንደ ቅጠል ረግፏል።  የዚህ ጦርነት የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ ከሆነው ከስሜን ዕዝ ጀምሮ ፣ መላው ሠራዊትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዕር ሊጽፈው ፤ አንደበት ሊናገረው የማይችል መከራና ስቃይ ደርሶበታል። አሁንም እየደረሰበት ነው።

ታዲያ እልቂቱ በሰሜኑ  ክፍል ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ በጎሳ በተደራጁና በራሱ በመንግሥትም የሚዘገንን  ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ግድያ፣ ሰቆቃና መፈናቀል  ደርሷል። አሁንም ከዋና ከተማችን  አዲስ አበባ ጀምሮ  በመላውም የአገራችን ክፍል ተባብሶ ቀጥሏል። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ በዋናነት የጎሳ ፓለቲካና  ቋንቋ  መሰረት ያደረገው ክልል መሆኑን ማንም አይዘነገውም።

ዛሬ ደግሞ  ከህዝባዊ ወያኔ  አርነት ትግራይ  ጋር  ተደረገ የተባለ ስምምነት ገና ባልተተገበረበትና እነሱም ለአዲስ ጦርነት እየተዘጋጁ ባለበት ሰዓት መንግሥት  ”—ልዮ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት—-” በሚል የተጀመረው ያልታሰበ ውሳኔ፤ከእናንተ ጋር በአንድ ጉድጓድ የተዋደቀውንና አብሮ መሰዋአት ከከፈለው የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖ ጋር ግጭት ገብቶ ክቡር የሰው ልጅ ህይወት እያለፈ ነው።  ሰላማዊ ህዝብ እየተጎዳ ነው። ” ለአንድ አገር አንድ መከላከያ  ሠራዊት ” የሚለው የሁላችንም የብዙዎቻችን እምነት ቢሆንም፤ ይህ ግን  መንግሥት  ከህዝብ ጋር ሳይማከርና አሁንም የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ ባለበት ሰዓት፤ ያለግዜው የመጣ ውሳኔ በተለይ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት በማጣቱ ፤ ህዝባዊ አመጽ   በተለያዩ ከተሞችና ቦታዎች ተቀጣጥሏል።

 በርግጥ ይህ ህዝባዊ አመጽ ”ልዮ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት” የሚለው  ክብሪት ሆኖ ያቀጣጣጥለው እንጅ፤  የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ከደር እስከ ዳር  በጎሳ ገዥዎችና ካድሪዎች በሚያደርሱበት ጭቆና፣  ስደትና ግድያ አስመርሮት፤  አሁን ያለው መንግሥት በቅቶታል። በመንግሥትና በህዝብ መሃከል መተማመን ከጠፋና ህዝብም  ከመንግሥት ማግኘት የሚገባውን መሰረታዊ ደህንነት አጥቶና የተገባለት ቃል ሁሉ ተክዶ   ”መንግሥት የለም”  ብሎ ካመነ ውሎ አድሯል።

ስለዚህም አሁን ለህዝባዊ አመጽና መብቱን ለማስከበር ሲነሳ ፤ መንግሥት  ደግሞ ሥልጣኑን ለማሰጥበቅ፡ የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ በኃይል ለመደምሰስና ለማፈን ወስኗል።  ለዚህ ደግም አምባገነኑ አገዛዝ ”ህገ-መንግሥቱን ” በማስከበር ስም እናንተን፤  ከህዝብ አብራክ የወጣችሁትን የህዝብ ልጆች የአገር መከላከያ ሠራዊትን  እየተጠቀመባችሁ  መሆኑን እያየንና እየሰማን ነው።

የተከበራችሁ የአገር መከላከያ ሠራዊት! ፤ አሁን የተነሳው ህዝባዊ አመጽ የፓለቲካ መፍትሄ  እንጅ  ኃይል አይመልሰውም። ህዝባዊ አመጹና እምቢተኝንቱ  ለነጻነትና ለእኩልነት ብሎም ለአገር እንድነት የሚደረግ የመላው ኢትዮጵያዊ  የፓለቲካ ትግል ስለሆነ ፤ እናንተን በትህትና የምንጠይቀው እጃችሁን በወግኖቻችሁ ላይ እንዳታነሱና የፓለቲካውን ጥያቄ ለመንግሥት እንድትተውት ነው።
   
ባለፈው በህዝባዊ አርነት ትግራይ- ወያኔ አገዛዝ ዘመን የህዝብን ጥያቄ ለማዳፈን ብዙ ደም ፈሷል። ግን ወያኔን ከሥልጣን ለመቆየት አላስቻለውም። አሁንም መንግሥት የህዝብን ጥያቄ እንደማይመልስ የታወቀ  ነው።  ኃይል መጠቀሙ ለበለጠ ውስብስብ ችግር እንጅ መፍትሄ እንደማያመጣ የታመነ ነው።ትርፋ ሌላ እልቂት፣ ሌላ ውድመትና የአገር እንድነትን  ለበለጠ ችግር ማጋለጥ ነው።

ገዥው መንግሥት አሁንም  እንደ ወያኔ የጎሳ”ካርድ” እየተጫውተና ወደፊትም  ስልጣኑ  መሸርሸር ሲጀምር በበለጠ እንደሚጠቀምበት የታወቀ  ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ መከላከያ ሠራዊትንም ከህዝብ ጋር ለማጋጨትና የወገኑን ደም እንዲያፈስ  ማንኛውንም ሴራ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም።

የአገር መከላከያ ሠራዊትን ከቻለ ከህዝብ ጎን ሆኖ የህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ያግዝ ፤ ያለያ ግን በገለልተኝነት ህዝብ መጭውን ዘመኑን ራሱ እንዲወስን ይፈቀድለት። የኋላ -ኋላ ህዝብ ያሸንፋልና።  የትላንት ገዥዎችም ሆኑ የአሁኖቹ የብልጽግና ገዥዎች በሥልጣን ላይ ለምቆየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማያጋጩት ህዝብ፣ የማይገቡበት የጎሳ ዓይነት፣ የማይፈጥሩት ማደናገሪያና ማባባያ እንደ ሌለ የታወቀ ነው። ግን ቋሚ አገርና ህዝብ እንጅ ፤ ዘላለማዊ ሥልጣን  የለምና የተከበረው የአገር መከላከያ ሠርዊታችን ቅድሚያ ለአገር እንደነትና ለህዝብ ደህንነት በመስጠት ታሪካዊ ግዴታ እንዲወጣ   እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጥሪ  አደርጋለሁ። ከህዝባችሁ ጎን እንደምትሰለፍምና ኢትዮጵያን ሁላችንም በእኩልነትና በአንድነት የምታስተናግደን አገር እንደምናደርጋ እምነቴ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!
ፊልጶስ
ሚያዝያ 2015

E-mail; Philiposmw@hotmail.com

Filed in: Amharic