ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
*…. የአማራ ወጣት – የማይወይበውን ጀግንነትህን የምታስመሰክርበት ጊዜው አሁን ስለሆነ በየአካባቢህ ተደራጅተህ ከልዩ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ባልደራስ ጠየቀ
የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ህወኃት ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ህዝብ ትክሻ ላይ እንዲራገፍ እንደማይፈልግ ከተለያዩ ተግባሮቹ መገንዘብ ተችሏል፡፡ በህወሃት እና በኦህዴድ/ብልፅግና መካከል ያለው ልዩነት የሥልጣን ሽኩቻ እንጅ የፖለቲካ አመለካከት እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ ዛሬ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች የአማራ ህዝብ ቀጣይ ጥቃት እንዲፈፀምበት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የአማራን ልዩ ኃይል፣ ፋኖን እና ሚሊሻውን ለማፍረስ ቀን ከሌት እየባዘኑ ይገኛሉ፡፡
አማራ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ ሀገሩን በደሙ ያቆመ፣ የሀገርን እና የሕዝብን አንድነት ያስጠበቀ፣ የጀግንነት አኩሪ ታሪክ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ዳሩ ግን ያለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት ለአማራ ህዝብ የህማማት ጊዜያት ሆነውበታል፡፡ በጽንፈኛ አክራሪዎች ታርዷል፤ ቤትና ንብረቱ ወድመውበታል፤ ከቀየው ተፈናቅሏል፤ ከኢኮኖሚ ባለቤትነትና ከፖለቲካ ሥልጣን ተገልሏል፡፡ ከመኖሪያው ተፈናቅሎ በተለያዩ ሥፈራዎች የተበተነውም የሚመገበው፣ የሚለብሰውና የሚያድርበት ተቸግሮ በስቃይ ላይ ይገኛል፡፡ ሰሞኑንም በንፁሀን ህይወት ላይ በሚቆምሩ ፖለቲከኞች ምክንያት የአማራን ህዝብ ትጥቅ አስፈታለሁ በማለት ሀገሪቱን መውጫ ወደሌለው መቀመቅ እያስገቧት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናጋው የጎሳ ፖለቲካ፣ ህገ መንግስቱ እና የክልሎች አከላለል ባልተቀየረበት ሁኔታ ልዩ ኃይሉን ማፍረስ ከቃላት በዘለለ ወንድማማችነትን ሊያስገኝ እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ‹‹የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎች ሳይፈርሱ የአማራን ልዩ ኃይል ብቻ መርጦ ማፍረስ የአማራን ሕዝብ ለጥቃት ማጋለጥ ነው›› በማለት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን ለማሰማት ወደአደባባይ የወጣውን ኗሪ ክቡር ህይወት መቅጠፍ በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ይህ ድርጊት የፖለቲካውን መስመር ወደ መራራ ትግል ይመራዋል እንጅ አያስቆመውም፡፡ ዜጎችንም ማሰር ትግሉን አያዳክመውም፡፡ የልዩ ኃይሉን ደመወዝ እና ምግብ ማቋረጥም ትግሉን አይጎትተውም፡፡
ስለዚህ፡-
➢መላው የአማራ ህዝብ – ከብልፅግና የፋሽስት አገዛዝ ነፃ እስክትወጣ ድረስ መከታ የሆነህን ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያ በምግብ አቅርቦት እንድትደግፍ፣
➢መላው የአማራ ህዝብ የንግዱ ማህበረሰብ – በክብር እና በሰላም እንድትኖር የታደገህን እና አሁንም እየታደገህ ያለውን ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ እንዳይራብ ድጋፍ እንድታደርግ፣
የመከላከያ ሰራዊት – ሰሜን ዕዝ ሲጨፈጨፍ እና ሲኖ ትራክ በጭንቅላቱ ላይ ሲነዳበት እና በግፍ ሲታረድ ከጎንህ በቆመው የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ፣ ሚሊሻ እና ህዝብ ላይ ቃታህን እንዳትስብ፣
➢አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን – የጥቁር ህዝብ ህይወት ግድ ይለኛል /Black lives matter/ የሚለው ማህበራዊ ንቀናቄ በጥቁሮች ላይ የሚፈፀመውን አድልዎ የሚቃወም ንቅናቄ ሲሆን፣ በዚህ ንቅናቄ ላይ ከጥቁሮች በተጨማ ነጮችም ተሳታፊዎች እንደነበሩ የዓለም ታሪክ ያስረዳል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም በአማራ ላይ ሲደርስበት የነበረውን እና እየደረሰበት ያለውን የዘር ማጥፋትና ማፅዳት፣ አድልኦ እና ጭቆና በመቃወም የአማራ ሕዝብ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንድትቀላቀሉ፣
➢የአማራ ወጣት – የማይወይበውን ጀግንነትህን የምታስመሰክርበት ጊዜው አሁን ስለሆነ በየአካባቢህ ተደራጅተህ ከልዩ ኃይሉ ጎን እንድትቆም፣
➢የአማራ ህዝብ እና የሀገሬ ጉዳይ ግድ ይለኛል የምትሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን – ሃገርን ከመበታተን የማዳን ትግሉን ተቀላቅላችሁ ይህን ዘረኛ ሥርዓት በመገርሰስ ሂደት የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታበረክቱ የአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ