ሰይጣነሰብ አብዮት አህመድ
ብሩክ ደሳለኝ
በዓለሙ ሁሉ እየተከናወነ ያለው የሚያመለክተው ሰይጣን እጅግ መንቀዥቀዡን፣ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱንና የሰውን ልጅ አዋርዶ፣ ከሰው ተራ አውጥቶ የሰው ደም እየጠጣ፣ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሰውን ልጅ ወደ መቃብር እያወረደ፣ ለርሱ የገበሩትንም ከሞት በባሰ ጨምላቃ ድርጊቶችና ኑሮ እየነዳ በበሰበሰ አስተሳሰብና ስብእና እየተቆጣጠረ መሆኑን ነው፡፡ መጥኔ ይህን ላልተገነዘቡ፤ ተገንዝበውም ሆን ብለው በሰይጣናዊ መንገድ እየተጓዙ ላይ ላዩን ጤነኛ፣ ደስተኛ ለሚመስሉ ነገርግን እነቅልፍ እንደልባቸው ለማይወስዳቸው፣ ደም እየገበሩ እጃቸው በደም ለተነከረ ሁሉ፡፡
በሌላም በኩል እኛስ ብንሆን አለን ይባላል? ረጋ ብለን ስናየው በአሁኗ ሰዓት ኢትጵያውያን ነን የምንል ኢትዮጵያዊነቱ ቀርቶ ዕውን በሰውነት ደረጃ የምንቆም ነን? ይህን ሁሉ መዓት እያየን እየሰማን ዝም፣ ጭጭ! ከማን ጋር ነን? ከሰይጣን ወይስ ከእግዚአብሔር? አሁን የኛ ኑሮ ኑሮ ነው? ከሞቱት በላይ ነን ወይ? እግዚኦ! አይ የኛ ቅሌት በዚች ዛሬ ኢትዮጵያ በምትባል አገር የምንኖር ሰዎች! አይ ውርደት! አይ ውርደት! አይ ውርደት! ምን ዓይነት አዚም ነው የወረደብን? በዕውነትም መተት በአውሮፕላን ተረጨብን ይሆን እንዴ?
ወለጋ ሰው ተከቦ በጥይት ተቆላ – ዝም፣ ኧረ ባካችሁ ድረሱልን ከአገር ውጡ ብለው ቤታችንን፣ ጎተራችንን አቃጠሉብን – ዝም፣ ኧረ የወገን ያለህ ከበው ሊጨርሹን ነው ድረሱልን – ጭጭ፣ ኧረ ህጻናት ሴቶች ካህናት ታረዱ – ጭጭ፣ ኧረ ቤተክርስቲያን ተቃጠለ – ዝም፣ ኧረ ያገር ያለህ ቤታችንን በላያችን ላይ አፈረሱብን – ጭጭ፣ እረ ካህኑን በድንጋይ ወግረው ገደሉ- ጭጭ፡፡ ዝም – ጭጭ – ምጭጭ፡፡ የመጨረሻው መጨረሻ አማራን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ዘመቻ መጣልሃ! የሆነ ነገርማ ተደርጎብናል! ወይስ ቦቅቧቃ ሆነን ነው? መለየት እኮ አስቸገረ!
ህዝብ ይባልልኛል ደግሞ! አገር አገር የምትሆነው በህዝብ አይደለም በመሪ እንጂ! ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን አጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ግድያና ግፍ ያየ የሚገነዘበው፤ ህዝብ ያውም ለሺ ዓመታት ነጻ ነበርኩ ለሚል ህዝብ፣ አገር ማለት መሪ – መሪ ማለት አገር መሆኑን ነው፡፡ በቅርቡ ታሪካችን እንኳ ቴዎድሮስ በዚያ በኋላ ቀር ዘመን አገሩን ልክ አስገብተዋል፣ ዮሃንስ ተሰውተዋል፣ ሚኒሊክ ጥቁርን ሳይቀር አስከብረዋል፣ ኃይለስላሴም ኢትዮጵያን በመላው ዓለም የተከበረች አድርገዋል ከዚያ ወዲህ የመጡብን እርጉማን መንግስቱና መለስም ምንም እንኳ ምናምንቴዎች ቢሆኑም አገሪቷ ተንገላታም አገር ትመስል ነበር፡፡ አብዮት አህመድ ግን የሰይጣን መልእክተኛ ሳይሆን ሰይጣን አዕምሮውን የተዋሃደው ሰው ነው፡፡ ስለዚህም ሰይጣነ-ሰብ ብንለው ምንም ስህተት የለውም፡፡
እንደሚታወቀው የመጀመሪያው አብዮት የተካሄደው በሰማይ ሲሆን የመጀመሪያውም አብዮተኛ ሳጥናኤል የተባለው መልአክ ነበር፡፡ በሰማይ ሊያካሂድ ያሰበው አብዮት ከሽፎበት ቅዱስ ሚካኤል ቀጥቅጦት ወደ መሬት ሲጣል ከነኩታንኩንት አብዮቱ ምድር ላይ ተፈጠፈጠ፡፡ በሰማይ ያልታሳካለትን አብዮት መሬት ላይ ለሰው ልጅ አስተምሮ የኛም ኢትዮጵያ ፊቷን ከፈጣሪዋ በማዞሯና የሰይጣንን መንገድ በመከተሏ አብዮት አይቅርብኝ ብላ ንጉሷን በትራስ አፍና ገላ የሞቱላትን አርበኝች ረሽና እና አንድ ትውልዷን ቅርጥፍ አድርጋ በልታ፣ በእርስ በርስ ጦርነት ተማግዳ፣ ህዝቧን በበረት በበረት ከፋፍላ ይኸው ስምን መልአክ ያወጣዋልና አብዮት አህመድ የተባለ ሰይጣነሰብ ታዞባት ሰው ተዘቅዝቆ የሚሰቀልባት፣ የሰው ሥጋ የሚበላባት፣ ህጻናት ፣ ሴቶች ፣ ካህናት የሚታረዱባት፣ ካህን በዱላና በድንጋይ ተወግሮ የሚገደልባት ምድራዊ ሲኦል አደረጋት፡፡ የጥጋቡ ጥጋብ ደግሞ አማራን ሊጨርስ ተነስቷል፣ የራሱ መጨረሻ መሆኑን ማን በነገረው! አማራ ሃይማኖትና ታሪካዊ ንቃተ ህሊና ያለው፣በዕምነቱ የማይደራደርና በታሪኩ የሚኮራ ህዝብ ነው፡፡ በሃይማኖትና ታሪካዊ መሰረት ላይ የተገነባ ንቃተ ህሊና ያለውን ህዝብ፤ ያውም ከዚህና ከዚያ ተለቃቅሞ በምዕራባውያን ድጋፍ በተሰለፈ ግሪሳ ማጥፋት አይቻለም፡፡ ጠመንጃውንም ከሱ በላይ የሚተኩስ ለአሳር ነው! ሴራም ቢሆን የዛሬውን አያርገውና የዝንብ ጠንጋራ የሚየውቅ ሕዝብ ነበር እንደ አሁኑ በመንደር ሽማግሌ ነን ባይ የሰይጣነሰቡ ተላላኪዎች ከመሸወዱ በፊት፡፡
ሲጀመርም ሰይጣነሰቡ ያለምክንያት አብዮት አልተባለም፡፡ ስምን መልአክ ያወጣዋልና ምንም እንኳ ዛሬ ከክብሬ ብወርድም ቀድሞ የመላእክት ሁሉ አለቃ ነበርኩና የእርሱንስ ስም እኔ ላውጣው ብሎ ከእግዚአብሔር አስፈቅዶ ለከሸፈበት ሰማያዊ አብዮቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሳጥናኤል የዛሬውን የኢትዮጵያ መሪ አብዮት አህመድ ብሎ እርሱ ራሱ ሳይሆን አይቀርም ስሙን ያወጣለት፡፡ እኛው ራሳችን ከእግዚአብሔር መንገድ ፈቀቅ ብለን በሰራነው ሃጢአት ብዛት የታዘዘብን ይህ ሰይጣነሰብ በርኩሰት አባቱ በሳጥናኤል እየታገዘ በአዕምሮ ስንኩሉ ጋኔል ክብረት ደላላነት አጋንንት እያስጎተተ ይኸው አይተነው፣ ሰምተነው ቀርቶ አስበነው የማናውቀው ሰይጣናዊ ውርጂብኝ አምጥቶብን አገራችን ከመዓት የሚያወጣት ሰው አጥታ ዋይ ዋይ ትላለች፡፡
እርሱና ግብረ አበሮቹ ገና የንጹሃንን ደም ለመገበር ቢያሴሩም የአብነ ገብረመንፈስ ቅዱስ፣ የአቡነ ተክለሃይማኖት እና የፍጡነ ረድዔት ቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ይህን ሰይጣነሰብ ከነግብረ አበሮቹ እነደጉም አብንኖ እንደ ጢስ አትንኖ የሚያጠፋበት ጊዜ ደርሷል፡፡ ይልቁኑስ አብረው ከርሱ ጋር የርሱን እርጉም ትዕዛዝ የሚያስፈጽሙ ሁሉ በንነው ተንነው ከነዘርማንዘራቸው ከመጥፋታቸው በፊት በጊዜ ሰልፋቸውን ከህዝብ ጋር ቢያደርጉ ይሻላቸዋል፡፡ የሰይጣነሰብ አብዮት አህመድና ግብረአበሮቹ ቀናቸው አልቋል፡፡