>

መለካውያን እና ዐላውያን አገዛዞች የሠለጠኑባት የኢኦተቤክ (ከይኄይስ እውነቱ)

መለካውያን እና ዐላውያን አገዛዞች የሠለጠኑባት የኢኦተቤክ

ከይኄይስ እውነቱ

ርግማን ይሁን ተካክሎ መበደል፤ የማይቀር ትእዛዝ ይሁን የትንቢት መፈጸሚያ መሆን ጥንታዊት፣ ርትዕት፣ ብሔራዊት፣ ኵለንታዊት፣ የኢትዮጵያ ዓምዷና ውዱዳ የሆነችው የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሠላሳ ዓመታት በላይ በዐላውያንና በመለካውያን ስትገዘገዝ ቆይታ በጭራቅ ዐቢይና አገዛዙ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ከመንፈስ ቅዱስ በተለዩ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ባሉና ዓለማዊ ምቾትና የሥልጣን ፍትወት ባሰከራቸው ምንደኞችና ሐሳውያን ‹አባቶች› አማካይነት ዶግማዋ (መሠረተ እምነቷ)÷ ሥርዓቷና ቀኖናዋ ተጥሶ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ሳይሆን የመለካውያኑን ፈቃድ አስፈጽማለች፡፡ 

በቅድሚያ አንዳንድ አንባብያን እንዳይደናገሩና ሐሳብን ለማጥራት ዐላውያንና መለካውያን የሚሉትን ቃላት በሊቃውንት የተሰጣቸውን ፍቺ እናስቀምጣለን፡፡ ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት› በተባለው ታላቁ ሥራቸው ዐላዊን ወንጀለኛ÷ እንቢተኛ÷ ሽፍታ÷ ከሀዲ÷ ውልን ቃል ኪዳንን አፍራሽ÷ መልካም ምክርን ትምህርትን የሚለውጥ የሚገለብጥ በማለት ሲፈቱት፤ መለካዊ ማለት ደግሞ ንጉሣዊ/አገዛዛዊ÷ ከኳደሬ (ከዝቅተኛው የመንግሥት ሥልጣን) እስከ ንጉሥ/መሪ ያለው ሹም፤ የንጉሥ/የአገዛዝን ፈቃድ ለመፈጸም ንጉሥ/አገዛዝ ያቆመው ወይም የሰበሰበው ጉባኤ፤ እንደ ማኅበረ ኬልቄዶን ያለውን ማለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የኬልቄዶን ጉባኤ የተባለው በዛሬዋ ቱርክ ኢስታንቡል በምትገኘው የኬልቄዶን ከተማ እ.አ.አ. በ451 ዓ.ም. በተደረገ ጉባኤ አንዲት የነበረችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት የተከፈለችበት የዐላውያንና መለካውያን ፈቃድ ለማስፈጸም የተካሔደ የእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን የሥጋና መለኮት ተዋሕዶ የካደ ምንታዌነትን ያመጣ (የክርስቶስ አካልና ባሕርይ የተለያዩ ናቸው፤ ክርስቶስ ኹለት ባሕርይ ኹለት ህላዌ ባንድ አካል የሚል የኑፋቄ ትምህርት) የክህደት ትምህርት የተቀበለ ጉባኤ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአምስቱ አኀት የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት የተወገዘና ጉባኤ ከለባት (የውሾች ጉባኤ – የተተፋውን የኑፋቄ ትምህርት የመለሰ) ተብሎ የሚታወቅ ጉባኤ ነው፡፡ የኢኦተቤክ እና የቀሩት አኀት ኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት (የእስክንድርያ፣ የሶርያ፣ የአርመን እና የሕንድ) የሚቀበሉአቸው በኒቂያ፣ በቊስጥንጥንያ እና በኤፌሶን የተካሄዱት ሦስቱን ዓለም አቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶሶ የወሰኑትን ሃይማኖት ብቻ ነው፡፡

በቅርቡ በልሳነ እንግልጣር ባቀረብኹት ጽሑፍ  በርክበ ካህናት (በሲኖዶስ ስብሰባ) ጊዜ ዐላውያኑን እና መለካውያኑን ወክለው ከቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ሥርዓትና ቀኖና ውጭ እንዲመለሱ በተደረጉት የአገዛዙ መልእክተኞች አማካይነት የመለካውያኑን ፈቃድ በሚያስፈጽም መልኩ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የሚደረግ ከሆነ ሲኖዶሱ ግዙፍ የሆነ ምናልባትም የቤተ ክርስቲያኒቱን ብቻ ሳይሆን የአገርን ህልውና የሚነካ ታሪካዊ ስሕተት እንደሚፈጽም እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያኗ ልጅነቴ አሳስቤ ነበር፡፡ የፈራሁት የደረሰ ይመስለኛል፡፡ የእኔ ‹የጨዋው› ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ የሚገኙና በቤተ ክህነቱ ዕውቅና የተቋቋመ ዐቢይ ኮሚቴ የሰጠውን መግለጫ ችላ ማለት፤ በብዙ ምርምርና ጥናት የቀረበውን የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ማሻሻያ ከመደርደሪያ ወርዶ ተግባራዊ እንዳይሆን መወሰን፤ መምህራን፣ ካህናትና ምእመናን ባንድነት ሆነው የኤጲስ ቆጳሳቱ ሹመት ለጊዜው ይዘግይ ብለው ፊርማ አሰባስበው ያስገቡትን አቤቱታ ለሲኖዶሱ አጀንዳ ሆኖ እንዳይቀርብ መደረጉ ለመለካውያውኑ ከተደረገ ትብብር ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን የዐላውያኑ ዛቻና ማስፈራሪያ ሳያግዳቸው ቤተ ክርስቲያንን በጐሣ/በዘር ማደራጀት የሥርዓትና የቀኖና ጥሰት ብቻ ሳይሆን ዶግማን መተላለፍ እንደሆነ ገልጸው ቢያሳስቡም ቤተ ክህነቱም ከመለካውያኑ ጋር ባንድነት አውግዞአቸዋል፡፡ መለካውያኑ ደግሞ ዘብጥያ አውርደዋቸዋል፡፡ 

ሲኖዶሱ ከመንፈስ ቅዱስ የተፋታው እነዚህን በመሠረተ እምነት፣ ሥርዓትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ተከሰው በመለካውያኑ ትእዛዝ እንዲመለሱ ሲወስን ነው፡፡ ለመሆኑ ይህንን ውሳኔ የትኛው የቅዱሳት መጻሕፍት አስተምሕሮ፤ የትኛው የሥርዓት መጻሕፍት (ዲዲስቅልያ – የሐዲስ ኪዳን የሥርዓት መጽሐፍ) እና የትኛው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን (ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5) የሚደግፈው ሆኖ ነው ያስተላለፋችሁት? የክህደቱን መንገድ በዚህ ውሳኔ ጀምራችሁታል፡፡

እንደ አንድ የተዋሕዶ እምነት ተከታይ እነዚህን ዶግማ፣ ሥርዓትና ቀኖና ተላላፊዎች እንኳን በአባትነት ልቀበላቸው እንደ ግለሰብም አገርና ቤተ ክርስቲያን አፍራሽ ነውረኞች መሆናቸውን ነው የማውቀው፡፡ በመሆኑም የነ አካለ ወልድ ወንጀለኛ ቡድን ብዬ ነው የምጠራው፡፡ ታሪክም በዚህ መልኩ እንደሚመዘግበው አልጠራጠርም፡፡ ለአገርና ለቤተ ክርስቲያኗ ተቆርቋሪ በሆኑና ከአገዛዙ ውጭ በሚገኙ መደበኛና ማኅበራዊ መገናኛ በዙኃን  እንደሰማነው የሲኖዶሱ ጉባኤ በሦስት ተከፍሎ ነበር የሚለውን አልቀበልም፡፡ ከመነሻው የአንድ መናፍቅ ዱርዬ ትእዛዝ ተቀብለው ያንን የጐሣ አጀንዳ የመንፈስ ቅዱስ ጉባኤ በነበረው ሲኖዶስ ላይ አንሥተው ሲነጋገሩ ጉባኤው የመንፈስ ቅዱስ መሆኑ አክትሞ የዐላውያንና የመለካውያን ሆኗል፡፡ ይህም ሆኖ ቀኖናን የሚመለከት የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በሙሉ ሲኖዶስ (unanimously) የሚወሰን በመሆኑ ለቤተ ክርስቲያኗ ዶግማ፣ ሥርዓትና ቀኖና ቆመናል የሚሉ አባቶች ቢኖሩ ማድረግ የሚገባቸው ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በጉባኤ ኬልቄዶን እንዳደረገው ይህንን ዳግማዊ ጉባኤ ከለባት ረግጠው መውጣት ነበረባቸው፡፡ እንደ ዓለማዊ የሲቪል ሰርቪስ መ/ቤት መልቀቂያ አቅርቤ አልተቀበሉኝም የሚባልበት አገልግሎት አይደለም፡፡ እምነቱም ሆነ ታማኝነቱ ለሰማያዊው ንጉሠ ነገሥት መሆን ነበረበት፡፡ ይህንን ሊያደርጉ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ 

በፍጥረት መጀመሪያ በዓለመ መላእክት ሳጥናኤል የእግዚአብሔርን ክብርና ቦታ ይገባኛል፤ በመሆኑም ለኔ የባሕርይ ስግደት ልትሰግዱ ይገባል ባለበትና ሽብር በነገሠበት ወቅት ከሳጥናኤል ጋር የቆሙ፤ የፈዘዙ እና ‹ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ አምላክነ› አምላካችንን እስክምናገኘው ባለንበት ጸንተን እንቁም ያሉ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል የሚመሩ መላእክት ነበሩ፡፡ አሰላለፋቸውን ከሳጥናኤል ጋር ያደረጉትና የፈዘዙት ከክብራቸው ተዋርደው መልአከ ጽልመት ሆነው ወደ ጥልቁ ሲወርዱ በእምነታቸው ጸንተው ከቅዱስ ገብርኤል ወገን የሆኑት ብርሃናውያን መላእክት እግዚአብሔር አምላክ ድንቅ ብርሃኑን አፍስሶላቸው ያም ዕውቀት ሆኗቸው በሃይማኖታቸው ጸንተው ዘላለማዊ ክብር ተጎናጽፈዋል፡፡ ዛሬ በተግባር እንዳየነው እስከ መጨረሻው ጸንቶ ከእውነት ጎን የቆመ አልተገኘም፡፡ በትርያርኩን ጨምሮ ኹሉም (ቅጥረኞቹም፣ ፍዞቹም፣ የተንገዳገዱትም) ተካክለው የመለካውያኑ ፈቃድ ፈጻሚዎች ሆነዋል፡፡ የክህደቱን በር ወለል አድርገው በመክፈት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለውድቀት አመቻችተዋል፡፡ በቀጣይ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ አብያተ ጣዖታት እንዲከፈቱ መንገዱን ጠርገዋል፡፡ 

አንዳንድ የዋሆች አባቶችም እኮ ሰዎች ናቸው በማለት የስንፍና ንግግር ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ አዎ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሲመነኩሱ ለዚህ ዓለም ሞተዋል፡፡ ከራሳቸው ይልቅ የእግዚአብሔርን ክብር ለማስቀደም፤ የእግዚአብሔርን በጎች መንጋውን በለመለመ መስክ ለማሰማራት ቃል ገብተዋል፤ ከዐላውያንና ከመለካውያን እንዲሁም ከመናፍቃን የሚመጣባቸውን መከራ መስቀል በመሸከም እግዚአብሔር በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ ወስነዋል፤ የቤተክርስቲያኒቷን መሠረተ እምነት (ዶግማ)፣ ሥርዓት፣ ቀኖና እና ትውፊት እስከ ሰማዕትነት ደርሰው ለማስከበር ቃል ገብተዋል፡፡ እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ቄርሎስ፣ መላእክት ዘበምድር የተባሉት እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም እኮ ሰዎች ናቸው፡፡ መልካሙን ገድል ተጋድለው፣ ሃይማኖታቸውን ጠብቀው፣ አእላፋትን በምግባር በሃይማኖት አፍርተውና ሩጫቸውን ፈጽመው ነው የተዋሕዶ ከዋክብት ለመሆን የበቁት፡፡ ቅድስናና ብፅዕና ያለ ዋጋ በብላሽ አይገኝም፡፡ 

በተቃራኒው የአሁኖቹ ‹አባቶች› በተለይም አፈንጋጮቹ እንደ ዐላውያኑና መለካውያኑ የመንፈስ ቅዱስን ሥልጣን በጉልበትና በጠመንጃ አፈ ሙዝ ለማግኘት ሠርተዋል፡፡ ለመሆኑ ባሳለፍነው ሠላሳ ኹለት ዓመታት ውስጥ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ በመንፈሳዊ ብቃትና በችሎታ የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ከጠቅላላው አንድ በመቶ ይገኙ ይሆን? ይህ ጸሐፊ ራሱ ምስክር የሆነበት ከአሜሪካ ዶላር ተሸክመው መጥተው የመንፈስ ቅዱስን ሀብት የገዙ የሉም? ከአናጕንሲጢስ እስከ ሊቀ ጳጳስ የሹመት ሥርዓቱ በግልጽ ባይነገርም ጐሣና ገንዘብ አልነበረም? አሁንስ ለውጥ አለ? በዘመነ ወያኔ ከገጠር አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አብዛኞቹ ካንድ ጐሣ የተገኙ አልነበሩም? ብዙዎች ‹አባቶች› ተብዬዎች እየተኩነሰነሱ ያሉት በዓለሙ ምቾትና ተድላ ደስታ ውስጥ አይደለም? በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመዘገበችው መበለት ‹ትዳራቸውን› በሚሰጡላት ምእመናን ከብት አይደለም እንዴ የሚንቀባረሩት? ምእመናን እኮ ያውቃሉ፡፡ ትናንት (የዛሬ ሦስት ወር ገደማ) ለቤተክርስቲያናችን ህልውና ክቡር ሕይወታቸውን የገበሩትን የሻሸመኔ ሰማዕታት እንዴት እንዘነጋለን? የምእመናኑ ፍላጎት እኮ ሥልጣነ ክህነታችሁን እስካላፈረሳችሁ ድረስ ሌላው ነውር በንስሓ ይስተካከላል፤ ቢያንስ የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና እስከ ዶግማዋ፣ ሥርዓቷ፣ ቀኖናዋና ትውፊቷ አቆዩልን ነው ጥያቄአቸው፡፡ እናንተ ግን በዚህ ልትታመኑ አልቻላችሁም፡፡ መለካውያኑ ይዘንባችኋል የሚሉትን ነውር እናንተን በማስፈራራት የሚፈልጉትን ለማስፈጸም ቢጠቀሙ እንኳን የነውሩ መጋለጥ ከቤተ ክርስቲያኗ ህልውና ይበልጣል? ዛሬ ለዓለም ምውት ነን ያሉ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጳሳት ደመወዝ ለዕጓለ ማውታ ማሳደጊያ ነው የሚውለው? እንኳን ደመወዙ ሥር በሰደደው ንቅዘት የቤተ ክርስቲያኗ ሀብት እነዚህን ‹መነኰሳት› የቅንጡ መኪናዎች፣ የቪላና ሕንፃዎች ባለቤት ከማድረግ አልፎ ለዘመዶቻቸው ድርጅት መክፈቻ፣ በውጭ አገር ማኖሪያና ማስተማሪያ መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር መሆኑ ከምእመናን የተሰወረ ይመስላችኋል? ይባስ ብሎ ደግሞ አኅጉረ ስብከቶችን ማስተዳደሩ የገንዘብ ምንጭ መሆኑና ከእኔ አኅጉረ ስብከት ከሚቀነስብኝ የቤተክርስቲያን ዶግማ፣ ሥርዓትና ቀኖና ቢጣስ ይቀላል የሚሉ ደፋሮች መነሣታቸው እውነትም ቤተ ክህነቱም እንድ ቤተ መንግሥቱ ለይቶለት በስብሷል የሚያሰኝ ነው፡፡

ኧረ ተዉ! ምእመኑን ባታፍሩ እንኳን እግዚአብሔርን ፍሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዋናነት የክርስቲያኖች አንድነት መሆኑን ዘንግታችሁ ምእመኑ አያገባውም አላችሁ፡፡ ከምእመኑ የምንፈልገው የኛ ሥልጣን እንዳይነካ ሰማዕትነት እንዲከፍል፤ እኛ ምቾታችን እንዳይጓደል ወተቷ እንደማይነጥፍ ላም ሁሌም የምታልቡትን ገንዘብ ፈላጊ ሆናችሁ፡፡ በዚህ ሁናቴ እንዴት አድርገን ብፁዕ ወቅዱስ ቀርቶ ‹አባት› እንበላችሁ?

እኛስ ምእመናን የልጅነት ድርሻና ኃላፊነታችንን ተወጥተናል? በጭራሽ! ከሦስት ወራት በፊት መለካውያኑ በቤተ ክርስቲያናችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ቤተ ክርስቲያናችን ማቅ ለብሳ ሲኖዶሱን ለመገልበጥ ሙከራ ሲያደርጉ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ሕይወት ኗሪ ሆነን በጾም በምሕላ ያሳየነው መንፈሳዊ ኅብረት የአንድ ጊዜ ተግባር አድርገን ቁጭ ብለናል፡፡ ከዛ በኋላ በመለካውያኑ የተፈጸመውን ድራማ በሚገባ ተከታትለናል፡፡ በብሔራዊ በዓላችን በዓድዋ ድል ክብረ በዓል ጊዜ በታላቁ ገዳም በገነተ ጽጌ (በአራዳ) ቅዱስ ጊዮርጊስ የተፈጸመውን ፍጹም ድፍረት፣ ንቀትና በዚህም በካህናትና በምእመናን ላይ የደረሰውን አደጋ እናውቃለን፡፡ በዚህ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶች መልስ ምን እንደሆነ ዓይተናል፡፡ በፍርሀት ተሸብበው መለካውያኑ እየዛቱብንና ሊከሱን እየተዘጋጁ ነው ምን አድርጉ ትሉናላችሁ እያሉ ሲቆጡ አስተውለናል፡፡ በመጨረሻም የመለካውያኑ ቅጥረኞችን ከዶግማ፣ ሥርዓትና ቀኖና ውጭ ማዕርጋቸውን ጠብቀው እንደመለሷቸውና በግንቦቱ ርክበ ካህናት ወቅት የመለካውያኑን ቅጥረኞች በኤጲስ ቆጶስነት ለመሾም ቀጠሮ ይዘው እንደነበር እናውቃለን፡፡ ይህን በሚገባ እያወቅን የነሱን ትእዛዝ ሳንጠብቅ ቤተ ክርስቲያናችን መጠበቅ ሲገባን ‹አባቶች› ያልናቸውን አምነን ተቀመጥን፡፡ ውጤቱም ቤተ ክርስቲያናችንን ለመለካውያኑ ተላላኪዎች አሳልፎ መስጠት ብቻ ሳይሆን ሲኖዶሱም የጐሣ አገዛዙን ተከትሎ በጐሣ እንዲደራጅ በሩን የከፈተ ሆኗል፡፡ 

እንደለመድነው ቤተ ክርስቲያን ባለቤቷ ክርስቶስ ነውና አትፈረስም እያልን ለቸርነቱ ምክንያት የሚሆን ሥራ ሳንሠራ እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጥ? ኢትዮጵያ አገራችን ሀገረ እግዚአብሔር ናት አትፈርስም እያልን ስናላዝን ሕዝብ በግፍና በገፍ አልቆ፣ አሉ የምንላቸው የእሤት ሥርዓቶቻችን በሙሉ ተሸርሽረው አልቀው፣ ማኅበረሰቡ የተሸመነበት ድርና ማግ ተበጣጥሶ፣ የውርደትን ጥግ ኹሉ ዓይተን አሁን የቀረን ምንድን ነው? እኛ ጋር ያለው ኃይል ዐላውያኑና መለካውያኑ ጋር ካለው አይበልጥም? ለሰማዕትነቱ ሳስተን እንዳልሆነ ቢገባኝም፣ ሳይዘገይና ጩኸታችንም የማይጠቅም ከመሆኑ በፊት አሁን ልናደርገው አይገባም ወይ? አዲስ ድርጅት አያስፈልገንም፡፡ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናን፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ የልዩ ልዩ ማኅበራት ኅብረቶች አሉን፡፡ ከጸሎቱ ጎን ለጎን መለካውያኑን በተቃውሞ፤ የቤተ ክህነቱን ሰዎች ላይ ደግሞ ጫና በመፍጠር ሊመጣ ያለውን የከፋ ጥፋት ከጅመሩ ማስቀረት የለብንም? በትንቢት የሚታመን ትውልድ መሆን የለብንም፡፡ እኛ ባሮችህ የዐቅማችንን እንወጣለን፤ የአንተ የአምላካችን ቸርነትና እገዛ አይጓደልብን ማለት የክርስትናው መንገድ አይደለም?

Filed in: Amharic