>

“ለብሳ እማታውቀውን……..’’ (አሰፋ ታረቀኘ)

“ለብሳ እማታውቀውን……..’’

አሰፋ ታረቀኘ

የሥጋቱ መነሻ ምንጩ ባይታወቅም፣ “ኢትዮጵያ አትበተንም” የሚለው የጠቅላይ ሚንስትሩ አነጋገር ከማረጋጋት ያለፈ ፋይዳ እንደለለው መገንዘብ ከጀመርን ሰነበትን፡፡ ዛሬ ከአድስ አበባ ውቢቱ ጅማ ደርሶ መመለስ ከኦሮሞ ጎሳ መወለድን ና ኦሮሙኛ መናገርን ይጠይቃል፡፡ ዝዋይ ምሳ በልቶ ዲላ ወይም ክብረ መንግሥት አዳር ለማድረግ ታሪክ ሆኗል፡፡ በአምቦ አቋርጦ ወለጋ ከመሄድ ናይሮቢ መሄድ ይቀላል፡፡ ጎጃሜው ቴፒ፣ ወሎየው አጋሮ፣ የአሩሲና የአምቦ ልጆች ደሴና ባህር ዳር መሄድ አይችሉም፡፡ የመቀሌ ወጣቶች ወደ ደሴና ጎንደር፤ የጎንደርና የወሎ ወጣቶች ወደ መቀሌ ዝርው አይሉም፡፡

ከዚህ በላይ ሀገር መፍረስ ማለት ምን ይሆን?

ኦሮሚያ ተብሎ ከተከለለው የኢትዮጵያ ክፍል የተፈናቅለ፣ መተከልን ጨምሮ ወደ 800,d000(ስምንት መቶ ሽህ) የሚገመት አማርኛ ተናጋሪ ሕብረተሰብ በራሱ ሀገር ላይ በስደት ይኖራል፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራውና ለዘመኑ ነጣቂ ተኩላዎች ያልተመቸው የቦረና ኦሮሞ ከብቶቹና ግመሎቹ በድርቅ ሲረግፉበት ዘወር ብሎ ያየው የለም፡፡ ከሰወቹ አልፎ እንሰሶቹና የተከለው ዛፍ ሳይቀር በትህነግ መድፍና መትረየስ የረገፈበት አማራ፣ የሞተውንና በህይወት የተረፈውን ቆጥሮ  ሳይጨርስ፣ ጦርነት ታዝዞበታል፡፡ ቤተሰብ አስተዳድረው በማያውቁ ውርጋጥና ዘራፊዎች እጅ የወደቀው የኦሮሞ ሕዝብ የመከራውን ገፈት እየተጋተ ነው፡፡ የዘመኑ አጼ ቦካሳ(ሽመልስ አብድሳ) ታጣቂዎቹን እየላከ አማራን ያስገድላል፤ እዳው በኦሮሞ ሕዝብ ይመካኛል፡፡ የኦሮሞን ደግነት፣ ቸርነትና ፍትሕን የሚወድ ሕብረተሰብ መሆኑን የማናውቅ ይመስል፣ የሚሠሩትን አስቃቂ ግፍ፣ በኦሮሞ ስም ያደርጉታል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ፣ 

  • የድሆችን ቤት አፍርሱና ሜዳ ላይ ጣሏቸው አላለም፤
  • መስጅዶችን አፍርሱ አላለም፤
  • ቤተክርስቲያንን አውድሙ፣ ካሕናትን አሰቃዩ፣ ንዋየ ቅድሳትን አቃጥሉ አ ላለም፤

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከላይ ሆነው “ አይዟችሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም” ይሉናል፡፡ ሽመልስ አብድሳ ሕዝብ ያጎሳቁላል፤ ሐገር ይበትናል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ አካፋ ይዘው የአቅመ ደካሞችን ቤት ሲሠሩ በቪዲዮ ያሳዩናል፡፡ የሽመልስ አብዲሳ ታጣቂ ኅይል፣ በክረምት የድሆችን ቤት በግሬደር ያፈርሳል፡፡ አትጥበቡ ስፉ እንጂ ይሉናል፡፡ በሥራቸው የተሰገሰገው ዘራፊና ስግብግብ ቡድን ሁሉን ካልጠቀለልኩ ብሎ ሀገር ሲያወድም አይተው እንዳላዩ ያልፉታል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ አድስ የሚመስል ግን ያረጀ ዘዴ ተጀምሯል፡፡ “አማራው መንግሥት ሊገለብጥ ነው የሚል”፡፡ “ነፍጠኛ፣ ተስፋፊ፣ ጨቋኝ እየተባለ ድብደባ የጠናበትና እንደ አውሬ እየታደነ መገደል የሰለቸው አማራ ጠመንጃ አንስቶ ራሱን መከላከል ሲጀመር፣ “ በትግልህ የተጎናጸፍከውን ነጻነት ነፍጠኛ ሊነጥቅህ ተነሳስቷል” የሚል አድስ ውንጀላ ተጀምሯል፡፡ በቅርቡ ባደረጉት ደቡብ ምዕራብ ሪዞርት ምረቃ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩም ይህንኑ አባባል ጠቆም አድርገውታል፡፡

ሐገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን አጥብቀው  ኡኡ እሚሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ የሰሜኑ ጦኦርነት ከኦሮሚያና ከደቡብ አካባቢ ለዘመቱት መለዮ ለባሾች የአማራን ሕዝብ ሥነምግባር፣ ሐገር ወዳድነት፣ ሰው አፍቃሪነትና አክባሪነት እንዲያዩ እድል ከፍቶላቸዋል፡፡ የቆሰለውን ወታደር ከወደቀበት በማንሳት፣ ወደ ሆስፒታል በማጓጓዝ፣ ምግብ በማዘጋጅት፣ እተኙበት ላይ ምግብ በማቅረብና እጎናቸው ቁጭ ብሎ በማጉረስ ማንነቱን አስመስክሯል፡፡ እናቶች የወደቀ ሲያነሱ፣ ልጆቻቸው መሳሪያ አንስተው ከመደበኛው ወታደር ጎን ወድቀዋል፡፡ አንድ ጉድጓድ ገብተው አብረው አፈር ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጅ፣ ሐገርን ለመታደግ ሲፋለሙ የወደቁበት መሬት ደሙ ሳይደርቅ፣ ጠ/ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድና መንግሥታቸው በአማራው ሕብረተስብ ላይ ጦርነት አውጀዋል፡፡ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነና ለፓርቲ የማይታዘዝ መከላከያ መሥርተናል በተባል ማግስት፣ ፊልድ ማርሻሉና በአምባሳደርነት ገለል የተደርጉት ጀኔራል ባጫ ደበሌ ጭምር፣ በአማራ ፋኖ ላይ የውሸትና የውንጀላ ናዳቸውን ሲያዥጎደጉዱበት እሰማን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደት እየወሰዱን ነው? ይሕም አልበቃ ብሏቸው፣ ጦሩን እንደግፋለን የሚል ሰልፍ ሕዝብን ያለፍላጎቱ እያሰለፉ ናቸው፡፡ አማራው ጦሩን በሕይወቱ ደግፎ በተግባር አሳይቶታል፣ በሰልፍ ማሳየት አያስፈልገው ይሆናል፡፡ ነገርግን በጎሳ ላይ የተመሠረተውና ለወታደሩ የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ መልዕክቱ ለማን ነው?

ትህንግ ወልቃይትን ከበጌምድርና ስሜን፣ ራያን፣ ዋጃን፣ ዞብልንና ገሞጅን ከወሎ ቆርሶ መውሰዱ ሳያንሰው፣ መተከልን ከጎጃም ነጥቆ ለጉሙዝ ሰጠ፡፡ አማራ እንደ አፈር በግሬደር ተገፍቶ ወደ መቃብር የተሸኜበት መተከል!!! ይህንን ሁሉ የግፍ ጫና ተሸክሞ የተቀመጠን ሕዝብ አክሞ እንደማረጋጋት ፈንታ  በቁስል ላይ ጨው እንደመጨር አይነት ወታደር ያዘምቱበታል፡፡ ኦሮሙማ የአማራውን ህብረተሰብ ከመወንጀልና ከማፈናከል በስተቀር ያተረፈለት ነገር የለም፤ ሌላው ሕብረተሰብ ኦሮሞውን በጥርጣሬ እንዲያየው ከማድረግ ያለፈ ምንም ነገር ጠብ አላለልትም፡፡ እነ ሽመልስ አብዲሳና አድናቂወቹ እየዘረፉ ስለበለጸጉ፣ ሁሉም ኦሮሞ እንደዚያ እንድሰማው ይደሰኩራሉ፡፡  ጠቅላይ ሚንስትሩም የሚፈልጉትን በሽመልስና በአዳነች አበቤ እያስፈጸሙ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኢኮኖሚው በአፍጢሙ መደፋት፣ የአዛውንቶች ቤት መፍረስ፣ የህጻናት በጅብ መበላት፣ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ 

መንግሥት ቆሞ እያየና በአስፈጻሚነት እየተሳተፈ አማራውን አስጨፈጨፈ፤ አማራው እንደዘር ከመጥፋት ራሱን መከላከል ሲጀምር፣ መንግሥት ሊያፈርስ ነው ተባለ፤ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የወጡ እብዶች፣ ኢትዮጵያ ያላትን ሁሉንም በእጃቸው አስገብተው እያለ፣ አልበቃቸውም፡፡ የሌላትን ደግሞ ከየትም አታመጣም፡፡ የቀራቸው ነገር ቢኖር ‘ሁላችሁም ልቀቁልንና ኢትዮጵያን እኛ ብቻ እንኑርባት” ማለት ነው፡፡ የተያዘው ፕሮጀችት “ አማራው ተቀጥቅጦ አንገቱን ከደፋ፣ ሌላውን በኩርኩም ብሎ ጸጥ ማሰኘት ይቻላል ከሚል የተሳሳተ ግምት የመነጨ ነው፡፡

 ኦሮሞውን በተለይ፣ ኢትዮጵያን በአጠቃላይ ከኦሆድድና ከኦነግ የተቀናጀ እብደት ማዳን የሁሉም ብሔረሰቦች ኅላፊነት ነው፡፡ ዛሬ በአማራው ላይ፣ ነገ ሁሉም ስደተኛ የሆናል፡፡

እነዚ ሰወች ምንም አይነት ሀገር የመምራት ልምምዱና ራዕዩ ሳይኖራቸው፣ ልክ ትህነግ ሳያስበው መንግሥት እንደሆነው ሁሉ፣ በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ በትረ-ሥልጣን ላይ ቁጭ ያሉ ናቸው፡፡ አልቻሉበትምና ለነሱም ለሀገሪቱም ደህንነት ሲባል ለሚችሉት አስረክበው ገለል ቢሉ መልካም ነው፡፡

‘’ለብሳ እማታውቀውን የሰው ቀሚስ ለብሳ፣

ተመለሽ ቢሏት ወደት ተመልሳ’’ እንደተባለው ሆኗል፡፡

Filed in: Amharic