>

የሰንሹ ትምርት ላማራ ሕዝባዊ ኃይል፤ ማጥቃት መከላከል ነው (መስፍን አረጋ)

የሰንሹ ትምርት ላማራ ሕዝባዊ ኃይል፤ ማጥቃት መከላከል ነው

መስፍን አረጋ

“በጥበበኛ አዛዥ የሚመራ ጦር ሳይታሰብ ግድቡን ጥሶ በሚጎርፍ ደራሽ ውሃ ይመሰላል፡፡  ደራሽ ውሃ ከፍተኛ ቦታን እየለቀቀ፣ ወደ ዝቅተኛ ቦታ እያዘቀዘቀ፣ ዝቅዝቅ በመጉረፉ በሚያገኘው እየጨመረ የሚሄድ እንድርድረት (increasing momentum) እንቅፋቶቹን እየጠራረገ ረባዳን ያጥለቀልቃል፡፡  በጥበበኛ የጦር አዛዥ የሚመራ የጦር ሠራዊትም የጠላትን ጠንካራ ጎን እየራቀ፣ ደካማ ጎኑን እየሰነጠቀ፣ እየጎለበተ በመትመም፣ የጠላት ጦር ያልሰፈረበትን የጠላት ግዛት እንበለ ውጊያ በመቆጣጠር ይንቦራቀቅበታል፡፡  ደራሽ ውሃ ወደ መዳረሻው የሚወንዘው አወናነዙን ከመሬቱ አቀማመጥ ጋር እያዛመደ ፍጥነቱን፣ ስፋቱንና ጥልቀቱን በመለዋወጥ እንደሆነ ሁሉ፣ በጥበበኛ የጦር አበጋዝ የሚመራ ሠራዊትም ወደ ግቡ (goal) የሚያመራው የጠላቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ትልሙን (strategy) እና ስልቱን (tactic) እንዳስፈላጊነቱ በመለዋወጥ ነው፡፡”  ሰንሹ (Sun Tzu)

“ጦርነት ማለት በሽወዳ (deception) ላይ የተመሠረተ መጨፋጨፍ ማለት ነው፡፡  በመሆኑም ዋናው የድል ቁልፍ የሽወዳ ክሂሎት ምጥቀት ነው፡፡  የአጉል ጀብደኝነት ትርፉ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ነው፡፡  ስለዚህም ጠንካራ ስትሆን ደካማ፣ ደካማ ስትሆን ጠንካራ፣ ሩቅ ስትሆን ቅርብ፣ ቅርብ ስትሆን ሩቅ፣ ዝግጁ ስትሆን አልዝግጁ፣ አልዝግጁ ስትሆን ዝግጁ መስለህ ለጠላትህ ታይ፡፡  ጠላትህን እንቁ አሳይተህ እነቀው፡፡”  ሰንሹ (Sun Tzu)

መንደርደርያ

የአማራ ሕዝባዊ ኃይል፣ የአማራን ሕልውና ለማስቀጠል ከኦነግና ከወያኔ ጋር የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡  በዚህ የሞት ሽረት ትግል ላይ ደግሞ ሁሉም ፋኖ አማራ ሁሉም አማራ ፋኖ በመሆን እንደክሂሎቱ የበኩሉን ተጋድሎ ማድረግ አለበት፡፡  ከነዚህም ተጋድሎወች ውስጥ ደግሞ አንዱና ዋናው የአማራን ሕዝብ ተፈጥሯዊ የጦርነት ጥበብ በጦርነት ሳይንስ ማዳበር ነው፡፡  

የአማራ ሕዝብ ባማራነቱ የተካነውን እድሜ ጠገብ የጦርነት ጥበብ በሌሎች አገሮች (በተለይም ደግሞ በቻይናና በሩሲያ) የጦርነት ጥበቦች ካዳበረው፣ ማናቸውንም ጦርነት ባሸናፊነት የመወጣት እድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡  የቻይናው የጦርነት ሊቅ ሰንሹ (Sun Tzu) የጦርነት ጥበብ (Art of War) በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ ላይ በስፋት እንዳብራራው ደግሞ፣ የጦርነትን ጥበብ የተካነ፣ ትጥቁ እጅግም የሆነ ሠራዊት፣ እስካፍንጫው የታጠቀን ሠራዊት በቀላሉ ድል እንደሚመታ ነው፡፡  የዚህ ጦማር ዓላማ ደግሞ ከሰንሹ የጦርነት መርሖች ውስጥ አንዱ የሆነውን የማጥቃትና የመከላከል መርሕ መዘርዘር ነው፡፡ 

የኦነግ ሠራዊት ጨለማን ተገን አድርጎ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉትን ሕጻናትን፣ አረጋውያንና ደካሞችን ከማረድ በስተቀር፣ በዕድሜ ዘመኑ አንድም ቀን ድል ማድረግ ቀርቶ በቅጡ ተዋግቶ የማያውቅ፣ በትንሽ ብትር የሚንኮታኮት እንኩቶ፣ በፍንጥቅ እሳት ዐመድ የሚሆን ገለባ ሠራዊት ነው፡፡  እንዲህም ሆኖ ግን ጠላት አይናቅምና ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ባልተጠነቀቀበት ቦታ ላይ በድንገት ከተፍ ብሎ መከታተፍ ያስፈልጋል፡፡  በተለይም ደግሞ ማንም አይነካኝም ብሎ በመተማመን ተኮፍሶ በሚንጎባለልበት ቦታ ላይ (ለምሳሌ ያህል ወለጋ ላይ) ተሰውሮ ገብቶ እንብርቱን ወግቶ ቅንብቻውን ማስተንፈስ የግድ ነው፡፡ የጭራቅ አሕመድ ጃንደረባወች ተመስገን ጡሩነህና ደመቀ መኮንን የሚያሰማሯቸውን የአማራ ለምድ የለበሱ ብአዴናዊ የመስመር መኮንኖች በማስወገድ፣ የጭራቁን የግንኙነት መስመሩን መበጣጠስ ይዋል ይደር መባል የለበትም፡፡  የሰንሹ ትምህርት የሚያስተምረውም ይህንኑ ነው፡፡ 

የሰንሹ የማጥቃትና የመከላከል መርሖች

  1. ድል ማድረግ በራስ ሁኔታ፣ ድል መደረግ ደግሞ በጠላት ሁኔታ ይወሰናል፡፡  ስለዚህም ጠቢብ የጦር አዛዥ በራሱ በኩል ሊያከናውናቸው የሚገባውን ሁሉ በጥንቃቄ አከናውኖ አመችውን ጊዜ ነቅቶና ተግቶ በትእግስት ይጠባበቃል፡፡  ታላቆቹ ጦረኞች ትዕግስትና ጊዜ ናቸው፡፡  ጊዜ የሰጠው ቅል ዲንጋ ይሰብራል፡፡  
  2. ኢተረችነት በመከላከል ችሎታ፣ ረችነት ደግሞ በማጥቃት ችሎታ ይወሰናል፡፡  ጠላት ሲበረታ ተከላከል፣ ሲደክም አጥቃ፡፡
  3. ጠቢብ የጦር አዛዥ የሚያጠቃው መጠቃት ያለበትን እንጅ ለማጥቃት ሲል ብቻ አያጠቃም፡፡
  4. ጠቢብ የጦር አዛዥ የሚከላከለው መካላከል ያለበትን እንጅ ለመከላከል ሲል ብቻ አይከላከልም፡፡  
  5. ጠቢብ የጦር አዛዥ ሲያጠቃ የሚከላከል፣ ሲከላከል የሚያጠቃ ያስመስላል፡፡
  6. ጠቢብ የጦር አዛዥ ሲያስፈልግ እንደ እሳተ ገሞራ ከምድር ይፈነዳል፣ ሲያስፈልግ ደግሞ እንደ መብረቅ ከሰማይ ይበርቃል፡፡
  7. ጠቢብ የጦር አዛዥ ሲያስፈልግ እንደ ንፋስ ይፈጥናል፣ ሲያስፈልግ ደግሞ እንደ ተራራ ይቆማል፡፡ 
  8. ጠላት ሲረጋጋ ባሉባልታ አሸብረው፣ ሲያርፍ በትንኮሳ አዋክበው፡፡  ካጋም እንተጠጋ ቁልቋል ረፍት እየነሳህ፣ እዚህም እዚያም እየበሳሳህ፣ ዘላለም አስለቅሰው፡፡ 
  9. ጠላትህ ትይዝብኛለህ ብሎ የማያስበውን፣ ከያዝክበት ደግሞ ባስቸኳይ ሊያስለቅቅህ የግድ የሚያስፈልገውን ቦታ ሳይስበው በድንገት ያዝበትና ሥራህን ቶሎ ሠራርተህ ሳያስበው በድንገት በመውጣት ትሄድበታለህ ብሎ በማያስበው መንገድ ትሄድበታለህ ብሎ ወደማይገምተው ቦታ በፍጥነት ሂድ፡፡ 
  10. እንደ መብረቅ በድንገት በርቀህ እንደ አውሎ ንፋስ በድንገት ንፈስ ፡፡  መብረቅ ድንገት ይበርቃል እንጅ ከየት በኩል እንደሚበርቅ አይታወቅም፡፡  አውሎ ንፋስ በድንገት ነፍሶ የሚጠራርገውን ይጠራርጋል እንጅ ከወዴት እንደሚነፍስ አስቀድሞ አይታወቅም፡፡  ሲበርቅ ቢጨፍኑ ከመወጋት አይድኑ፡፡
  11. ጠንካራ ስትሆን ደካማ፣ ደካማ ስትሆን ጠንካራ፣ ሩቅ ስትሆን ቅርብ፣ ቅርብ ስትሆን ሩቅ፣ ዝግጁ ስትሆን አልዝግጁ፣ አልዝግጁ ስትሆን ዝግጁ መስለህ ለጠላትህ ታይ፡፡  ጠላትህን እንቁ አሳይተህ እነቀው፡፡  ሲጠናከር ሽሸው፣ ሲዳከም ተጋፈጠው፡፡  በግንባርህ ሲመጣብህ በጀርባው፣ በቀኝህ ሲመጣብህ በግራው እየተዟዟርክ አዋክበው፡፡  አወይ አተኳኮስ ወይ ደፋር መሆን፣ ሲሄድ መቀለቻ ሲዞር ግንባሩን፡፡
  12. ማጥቃትህ ስኬታማ እንደሚሆን እርግጠኛ ልትሆን የምትችለው ጠላትህ የማይከላከለውን ስታጠቃ ብቻ ነው፡፡  መከላከልህ ስኬታማ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን የምትችለው ጠላትህ የማያጠቃውን ስትከላከል ብቻ ነው፡፡  በማጥቃት የተካነውን መከላከል፣ በመከላከል የተካነውን ማጥቃት ትርፉ ትልቅ ሽንፈት ነው፡፡ 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic