>

አምሓራ - በቃ ተነስ! አታቅማማ! ታገል! ይህን ስታደርግ ራስህንም ኢትዮጵያንም ታድናለህ (ብርሐኑ ድንቁ)

አምሓራ – በቃ ተነስ! አታቅማማ! ታገል! ይህን ስታደርግ ራስህንም ኢትዮጵያንም ታድናለህ 

ብርሐኑ ድንቁ

የገበሬዎች አመጽ፣ የተማሪ እንቅስቃሴ፣ የመምህራን ተቃውሞ እንዲሁም የዋለልኝ የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ (On the Question of Nationalities in Ethiopia) የምትለዋ ትንሽ ጽሁፍ ተጣምረው ያፈነዱት የየካቲት 1966ቱ አብዮት የኃይለሥላሴን መንግሥት ከሥሩ ገረሰሰው። ክፍተቱን ተከትሎ ሥልጣን ላይ የወጣው የጊዜአዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መሬት ላራሹን (land to the tiller) ከግቡ ለማድረስ ሄድኩበት በሚለው መንገድ ያጠቃው የአምሓራን ነገድ ነው። መሬትም ለአራሹ ሳይሆን ለመንግስት ሆነና አረፈው። ደርግ ምንም እንኳን በዘረኝነት ላይ ያተኮረ አስተዳደርን የሚጸየፍ ቢሆንም ጉልታዊውን ሥርዓት ለመጣል ሲሞክር በተጓዳኝ ለኢትዮጵያ ታላላቅ ሥራዎች የሠሩትን ታላላቅ የአምሓራ ባለሥልጣናት፣ አርበኞችና ምሁራንን ኋላም በቀይ ሽብር ስም አምሓራዎችን አጠቃ። ከደርግ እልቂት ለመዳን በርካታ አምሓራ አገሩን ለቆ ተሠደደ። አምሓራው መጪውን ሁኔታ በቅጡ ተረድቶ መደራጀትና መታጠቅ ሲገባው ሲያቅማማና ሲያሰላስል – ሥልጣን ሕዝባዊ ወገነተኝነት በሌላቸው ሰዎች እጅ ገባች። ይህ ስህተት ነው እስከዛሬ የዘለቀውን ኢትዮጵያንና አምሓራውን ሠለባ ያደረገው። እስኪ አንኳር አንኳሩን ብቻ እንመልከተው።

በአምሓራ ነገድ ላይ የደረሰው መከራና ፍዳበህወሃትኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን

ሀ. ወያኔ ወደ አዲስ አበባ ጠጋ ስትል “ዘመቻ ዋለልኝ” ብላ በመደለል የዋለልኝን ጽሁፍ በወርቅ ቅብ አስለብዳ እንደ ባንዲራ እያውለበለበች ደካሞች፣ ሆዳሞችና የመገንጠል ናፋቂዎችን ቀልብ ሳበች።

ለ. ህወሃት ራሱን በራሱ ገዝግዞ የጣለውን ደርግ አሸነፍኩ ብላ ወደ ሚኒልክ ቤተ መንግሥት ሰተት ብላ የሽግግር መንግሥት ስታቋቁም አምሓራ ነገድን ካለተወካይ አስቀረችው። ከአማራ ክልል ውጭ ያለው አምሓራም የኅልውና አደጋ ተደነቀረብት።

ሐ. ህወሃት – ዋለልኝ “የውሸት ብሄረተኝነት ምንድነው? (What is fake Nationalism?!) የአምሓራ ወይንም የአምሓራና ትግሬ የበላይነት አይደለምን? (Is it not simply Amhara and to a certain extent Amhra-Tigre supremacy?) “ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ፣ ኢትዮጵያዊ ሙዚቃ፣ ብሄራዊ ልብስ ምን እንደሆን ማንንም ጠይቁ የአማራ ወይም የትግሬ ነው” ያለውን ሃሳብ ጠምዝዛ “ትግሬ ምንም ውስጥ የለበትም አምሓራ ነው የብሄር ብሄረሰቦች ገዥ” በማለት አምሓራን ነጥላ በጠላትነት አስፈረጀች።

መ. እነ አቶ ስብሃት በአንድ በኩል ደካማና ምርኮኞችን በሌላ በኩል ደግሞ የአምሓራ ሆዳምችን አመሰጣጥረው የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካን ሠሩ። ወያኔ የዋለልኝ ብሄር ብሄረሰብ ሃሳብ በሬት ለውሳ በአንድ በኩል የመመዝበርያ በሌላ በኩል ደግሞ አምሓራን ማስጠያ ስልት አደረገችው።

ሠ. የአምሓራውን ነገድ ጠቅላላ የብሄር ብሄረሰብ ጠላት ለማስመሰል የአገዛዙ የጀርባ አጥንት የሆነው ብአዴን “ከአምሓራ ክልል ውጭ ያሉት አምሓራዎች ሁሉ ነፍጠኞች ናቸው” ሲል በይፋ ለፈፈ። ደካሞችና ሆዳሞች ይህንኑ መመርያ ተከትለው በአርባጉጉ፣ በደኖና፣ በጉራፈርዳ፣ ወዘተ በአምሓራ ላይ ለመናገር የሚዘገንን ግፍ ፈጸሙ።

ረ. ወያኔ ከውስጥ ወደ ውጭ መታየት የነበረበትን የውጭ ጉዳይ መርህ ከውጭ ወደ ውስጥ በማድረግ ጥንታዊቷን የጀግኖች አገር ኢትዮጵያ ለምዕራቡ ዓለም አሳልፋ ሰጠች። ምዕራቡ ዓለም ከአድዋ ጦርነት በኋላ ነው አምሓራ ላይ ጥርሱን የነከሰው። የምዕራቡ ዓለም ምሁራን የከበርቴዎችን ጥቅም ለመጠበቅ በዴሞክራሲ ስም ይሸነግላሉ፣ አጸያፊ ባህሎችን ለማስፋፋት ደግሞ የሠባዓዊ መብት ጥያቄን ከፍ አድርገው ይጮሃሉ። ዴሞክራሲና ሠባዓዊ መብት ድጋፍ መስጫ (collaboration policy – supporting and helping policy) ወይንም የጣልቃ ገብነት መሳርያዎች ናቸው (tools of government intervention)።

በአምሓራ ነገድ ላይ የደረሰው መከራና ፍዳበኦሕዴድብልጽግና አገዛዝ ዘመን

ሀ. ህወሃት ሃያ ሰባት ዓመት መልካም ነገሮችን ስታመሰቃቀል ቆይታ ሙስናና ሌብነቱ አድቅቋት ሥልጣኑንም መሸከም አቅቷት እንደ እየሩሳሌም የምትሰግድለትን የሚኒልክን መናገሻ ከተማ አዲስ አበባ ትታ ወደ መቀሌ ስትፈረጥጥ ክፍተቱን ተከትሎ ሁለተኛው ኢሕአዴግ ማለትም ኦሕዴድ-ብልጽግና እንደ ዘበት ሥልጣኑ ማማ ላይ ወጣ።

ለ. አብይ አህመድ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” የሚል አዲስ የማፍዘዣ ስልት ይዞ ብቅ ሲል በውስጥም ውጭም ያሉ የአምሓራ ነገዶች ሠፊ ድጋፍ አደረጉለት።

ሐ. በርካታ የአምሓራ ልጆች ከየቦታውና ትምህርት ቤቱ ታግተው ደብዛቸው የጠፋው፣ ንብረታቸው የተቃጠለው፣ አስቃቂ በደል፣ ወዘተ፣ የደረሰባቸው አምሓራ ሠፊ ድጋፍ ባደረገለት የብልጽግና መንግሥት ነው።

መ. ኦሕዴድ-ብልጽግና ሥልጣኑን ለማጠንከር በከፈተው ጦርነት አምሓራንና አፋርን ከጎኑ አሰልፎ ህወሃትን ክፉኛ ቀጠቀጠ። ወያኔ ምዕራቡ ዓለም ቢተባበራትም ከመጣባት መዓት ለመዳን የሠላም ስምምነት ማድረጉ ብቻ እንደሚያዋጣት መላ ፈየደች። ኦሕዴድ-ብልጽግና ከአሳዳጊው አባቱ ከወያኔ ጋር በመስማማት አምሓራንና አፋርን አሳልፎ ሠጠ። አምሓራ ዛሬም በወያኔ፣ ብልድግና እንዲሁም አምሓራ ጠል ቡድኖች ዒላማ ውስጥ ነው።

ሠ. ኦሆዴድ-ብልጽግና አምሓራ ዜጋ፣ አምሓራ ቀሳውስትም ጭምር ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መመርያ ካስተላለፉ ቆይቷል።

ረ. የፕሪቶርያው እርቅ አምሓራን ያላካተተ ስውር ደባ ነው። ስምምነቱ ህወሃት ህገ መንግሥታዊ ግዛቶቼ የምትላቸውን የአምሓራ መሬቶች እንደገና በእጇ እንድታስገባ የሚያደርግ ነው። የምዕራቡ አገሮች በማንኛውም መንገድ የህወሃት የበላይነት እንዲመለስ ይጥራሉ። የትግራይን ሕዝብ በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ መማገድም ይሁን የአምሓራንና የትግራይን ሕዝብ እርስ በእርስ ማዋጋት የዘመኑ ክፋት ዋነኛ መገለጫ ነው።

ሰ. ዋለልኝ “ኢትዮጵያዊ ለመሆን አንድ ግለሰብ አማርኛ ማውራት፣ አማርኛ ዘፈን ማዳመጥ፣ የአማራና ትግሬ ኃይማኖት የሆነውን ኦርቶዶክስ ክርስትና መቀበልና በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የአምሓራና ትግሬን ሸማ ለብሶ መቅረብ አለበት” የሚል ሃሳብ ጽፎ ነበር። ይህንኑ የዋለልኝን ሃሳብ አጣሞ በማየት ዛሬ ፍጹማንና ምሉዓን የሚያደርጓቸው ባህርይን ያዘሉትን ግዕዝ ቋንቋን ወደ ላቲን ለመለወጥ ነው ሽር ጉድ የሚባለው። ለመሆኑ ከኢትዮጵያዊው ግዕዝ ፊደል ይልቅ የምዕራቡ ላቲን ፊደል ይሻላልን? ምዕራቡ ዓለም በግዕዝ ቋንቋና አሃዝ ቁጥር የተጻፉ ምሥጢረ-መጻህፍትን ከኢትዮጵያ ወስደው በታላላቅ ዩኒቨርሲቲያቸው እያስተማሩበት ነው።

ሸ. በኃይማኖት ስም የተደራጁ ገንዘብ በአቋራጭ ለማግኘት የሚመኙ ራስ ወዳዶች ለምዕራቡ ዓለም በማጎብደድ ጥንታዊዋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በአደባባይ መዝለፍ ጀመሩ። በፍርሃትና በማስተዋል በጥበብ የሚነገረውን የእግዚአብሄር ቃል ዋልጌው እንዳሻው ሲጠቀምበት ከዚህ የበለጣ ምን ድፍረት አለ።

ቀ. ዛሬ በኦሮምያ በአዲስ አበባም ጭምር የኢትዮጵያን ባንዲራ፣ የሚኒልክንና ጣይቱን ምስል ይዞ ወደ አደባባይ መውጣት የተከለከለው ነፍጠኛ ተብሎ በተፈረጀው አምሓራ ጥላቻ ምክንያት ነው።

በ. በኢትዮጵያ ያለውን የእስልምና ኃይማኖት ለማጥፋት ወያኔ-ኢሕአዴግ የጀመረውን ዘመቻ ኦሆዴድ-ብልጽግናም ቀጥሎታል። እስልምና እና ክርስትና የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጎጆ መደገፍያዎች ዳርና ዳር የቆሙ ሁለት ባላዎች ናቸው።

አምሓራአስተውልያለህበትን የቆምክበትን አረጋግጥ

ሀ. ኢትዮጵያ ወደድንም ጠላንም በኅልውና የነበረች፣ ያለችና የምትኖር አገር ነች። ሰው ይሞታል፣ ያልፋል እንጂ ኢትዮጵያ አትጠፋም። በጋራና በስምምነት መኖር አስተዋይነት ነው። ሃገር በጎም ጠማማም ታሪክ አላት። መልካሙን እያዳበሩ ጠቃሚ ያልሆነውን እያስወገዱ የሃገር ኅልውና ማስቀጠል አዋቂነትና ብስለት ነው። በኢትዮጵያና አምሓራ ላይ ያነጣጠረው ጥላቻና ዓለም አቀፍ ዘመቻ ራሱን የቻለ መንፈሳዊ ምክንያት እንዳለው ሁሉ ኦርቶዶክስ የሆኑትን አምሓራና ትግራይን እርስ በእርስ ማዋጋቱም ሆነ ቤተ ክርስትያናትና መስጅዶችን ማፈራረሱ የኢትዮጵያን የኅልውና ዜና መዋዕል ለመለወጥ የሚደረግ ደባ ነው።

ለ. እነመለስ ያበጃጁት የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ በተላላዎች አጃቢነት በጮሌዎች መሪነት አምሓራን መጉጃ የተቀነባበረ ሴራ ነው። አምሓራው በኅብረት በመቆም ብቻ ነው ከተጎነጎነበት ተንኮል የሚፈታው።

ሐ. ፌደራላዊ የተባለውን መንግሥታዊ ቅርጽ አጼ ሚኒክል ናቸው በሚገባ በሥራ ላይ ያዋሉት። ትህነግ ለአስተዳደር የማይመቹ ክልሎች ፈጥራ ከብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ጋር አቆራኘችው። ክልል – የአምሓራን መሬት ቆርሶ ወደ ትግራይ፣ ቤንሻንጉልና ኦሮምያ ማካተቻ ዘዴ ሲሆን ህገ-መንግሥት ተብዬው ደግሞ የባንዳዎችን ጥቅም ማስጠበቅያ የክፋት ሰነድ ነው።

መ. “እኔ ምን አገባኝ – ደልቶኝ እውጭ ነው የምኖረው – እምትል አምሃራ ሆይ! ካንተ ይልቅ የውጭ አገሩን ባይተዋርነትና ገፈት የሚሸከመው ልጅህ ነው። ዝም ብለህ በዋል ፈሰስ ጊዜ ከምታባክን ታገልና ጥለሃት የሄድካትን፣ በቅዱሱ ኪዳን መለኮታዊ ደም የታተመችውን ኢትዮጵያ ለልጅህ አስረክባት።

ሠ. “እኔ ትዳር፣ ልጆች፣ ንብረት አሉኝ – መታገል እፈራለሁ” ብለህ የምታቅማማ አምሓራ ሁሉ – እንኳንስ ያንተ ትዳርና ንብረት ይቅርና ሃገር ወደ አስፈሪ ምዕራፍ መሸጋገርዋን ገና አላወክምና ነው የተኛሐው? በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ዋስትናህን አሳጥተውሃል። አምሓራ ሆይ!  የየቀናቶቹን ክፉት ተረድተህ ዘመኑን በመዋጀት ራስህንም አገርህንም ታደግ ።

ረ. “እኔ ምን ገዶኝ፣ ወደ ውጭ እወጣለሁ፣ ሃገሪቱን ለቅቄ እሄዳለሁ” የምትል አምሓራ – ተስፋህን የጣልክባቸው የበለጸጉት አገሮች ራሳቸው መጪው ዘመን እያሳሰባቸው ነው። ሊከሰቱ የሚችሉ ፖለቲካና ምጣኔ-ኃብታዊው ችግሮችና ጦርነቶች እንኳንስ አዳዲስ ስደተኞችን ሊያስተናግዱ ይቅርና የተቀበሏቸውን እንኳን ማኖር እማይችሉበት ደረጃ ሊያደርሳቸው ይችል ይሆናልና እዛው አገርህ ላይ ቆይና ታግለህ ነፃነትህን አስከብር።

መደምደምያ

የኃይለሥላሴን መንግሥት በሕዝብ ተቃውሞና አመጽ ሲፈርስ አስተዳደሩን የሚረከብ ሕዝባዊ ኃይል አልነበረም። ተማሪው የጮኸለት ሕዝባዊ መንግሥት ሕልም ሆኖ በመቅረቱ ሥርዓት ከአምባገነንነት ወደ ዘረኝነት እየዘለለ ወደ ጽንፍ ዘረኝነት ተሸጋገረ። ይህ ደግሞ ከማንም በላይ የጎዳው የአምሓራን ነገድ ነው።

ዛሬም አዲስ ነገር የለም። ኦሕዴድ-ብልጽግና በቁም እያቃሰተ ነው። ብልሹ አስተዳደሩ፣ ምሬቱ፣ ህግ መጥፋቱ፣ የሙስናው መስፋፋት፣ የባለሥልጣናቱ ምዝበራ፣ ፍትህ መዛባቱ፣ የውጭ ምንዛሬ መሟጠጡና የምጣኔ ኃብት አጣብቂኝ፣ የኃይል አሠላለፍ መሰበጣጠር፣ የዲፕሎማሲው ክስረት፣ የኃያል አገሮች ጫና፣ የነዳጅ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የምግብ፣ የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት፣ የንብረት ታክስ ጫና፣ የትግራይ በጀትና የጡረተኞች ደሞዝ ጥያቄ፣ የበጀትና የፋይናንስ ቀውስ፣ የኢንቨስትሜንት እጥረት፣ የምዕራቡ የተጽዕኖ ኃይል፣ የእርዳታ መቋረጥ፣ ወዘተ፣ – ገዥዎችን ለከፋ ስጋት ዳርጓቸዋል። አሜሪካ የምልከው እርዳታ በይፋ ተመዝብሮ ተሸጧል በሚል እርዳታ ከልክላለች።

አምሓራ ልብ አርግ! ሕዝባዊ ኃይል በትግልህ ካልመሠረትህ ሌላ አበሳ ውስጥ ነው የምትዳረገው። አምሓራ በህብረት መቆም ካልቸለ የተቆለለ በቀልና ዛቻ ነው እንደተናደ ተራራ የሚከመርበት።

መከረኛው አምሓራ ሆይ! ወገንህ ተዘቅዝቆ ተሠቅሏል፣ ነፍሠ ጡር አማራ ሆዷ ተቀዶ ሽሉ ተጥሏል፣ የልጅህ ሥጋ ሲበላ ቆመህ ተመልክተሃል፣ የሞቱ ወገኖችህ በግሬደር እየተገፉ እጉድጓድ ተጥለዋል፣ አባትህ ሚኒልክ እመሠረቷት አዲስ አበባ እንዳትገባ ተከልክለሃል፣ ቤተ-እምነቶችና መኖርያ ቤትህ እየፈረሱ ነው፣ በቅርብ ቀን እንኳን መከላከያ ኃይል እደብረ ኤልያስ ገዳም ድረስ ሄዶ መነኮሳትን፣ የአብነት ተማሪዎችን፣ ምዕመናን እንዲሁም ለጸሎትና ጠበል የሄዱትን ክርስትያኖች ጨፈጭፏል።

አምሃራ ! በመንግሥተ ሠማያት ምስል የተሠራች አገር እያለህ ዘረኞች ሲዖል ሲያደርጓት ለዓመታት ዝም ብለሃል። ባንተ ላይ የደረሰውን ፍዳ፣ ሰቆቃ፣ የዘር ፍጅት፣ እገታ፣ ርሸና፣ ወከባ፣ የዘር ጥቃት፣ ወዘተ፣ ተዘርዝሮ አያልቅም። አሁንስ ስቃይ አልበቃህም? በቃ ተነስ! አታቅማማ! ታገል! ይህን ስታደርግ ራስህንም ኢትዮጵያንም ታድናለህ።ድል ለኢትዮጵያና አምሓራ ሕዝብ!

Filed in: Amharic