>

ስለ ድምፃዊው ማስታወሻ (ጌታቸው አበራ)

 ስለ ድምፃዊው ማስታወሻ          

(ከ“ክራሬን ልቃኘው” እስከ “ለምን?”)

ጌታቸው አበራ

A picture containing text, human face, screenshot, chin

Description automatically generated
ድምፃዊ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው

ድምፃዊ ፋንታሁን ሸዋንቆጨውን የማውቀው በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እንማር ከነበርንበት ጊዜ ጀምሮ ነው። በወቅቱ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት፣ የዘመናዊና የባህል ሙዚቃን ከአካዳሚክ ትምህርቶች ጋር አጣምሮ ይሰጥበት የነበረ በመሆኑ፣ የትምህርቱ ብዛትና የሙዚቃ መሣሪያዎች ጥናት ናላችንን ሲያዞረው፣ በየክፍለ-ጊዜዎቹ መሃል አንዳንዴ የተወጠረ  አእምሯችንን ዘና ለማድረግ ስንሻ፣ ፋንታሁን ሸዋንቆጨውን ዙሪያውን ከበነው በሳቅና በሁካታ እናሳልፍ ነበር። ፋንትሽ እጅግ ሲበዛ ተማሪዎችን፣ በቀልዶቹና በትረካዎቹ እየመሰጠን፣ ከሚገባው በላይ እዚያው በመቆየታችን በመምህራን የተገሰፅንባቸው ጊዜያትም ነበሩ።

ፋንታሁን ሸዋንቆጨው ቀልድና ወግ አዋቂ ብቻ ሳይሆን፣ መረዋ ድምፅ እንዳለው የተረዳነው ደግሞ፣ ት/ቤቱ በአመት ሁለት ጊዜ ይሰጥ በነበረው የኮንሰርት ዝግጅት ላይ ነበር።ያኔ! የጥላሁን ገሠሠን “እንጉዳዬ ነሽ” እና “በሸዋ ላይ ደሴ…” የሚለውን ባህላዊ ዘፈን ሲያቀነቅን፣ “ምነው ዘፈኖቹ ቶሎ ባላለቁ፣ ምነው ደጋግሞ በዘፈነ…” እያልን፣ በተመስጦም እናዳምጠው ነበር። 

የያሬድ የሙዚቃ  ት/ቤት እና በወቅቱ በአገሪቱ ያቆጠቆጡት የቀበሌና የከፍተኛ ኪነቶች (የባህልና የዘመናዊ ሙዚቃ ቡድኖች)፣ የተፈጥሮ ስጦታውን በማውጣት፣ ለሙዚቃ ጅማሮው ጥርጊያ መንገድ እንደከፈቱለት ይታመናል። ዜማ ደርሶ የራሱን ዘፈን ያቀነቀነው ገና በጠዋቱ፣ የሙዚቃ ት/ቤት የአራተኛ ዓመት ተማሪ በነበርንበት ወቅት ነበር። እውቁ የክራር መምህራችን ጋሼ መላኩ ገላው፣ ግጥምና ዜማ ደርሰን እንድናመጣ፣ ለክፍሉ ተማሪዎች በሰጡት የቤት ስራ መነሻነት፡ ፋንትሽ ከማንኛችንም በላይ ጎልቶ የሚሰማና ዘመን ተሻጋሪ ሊሆን የበቃውን፣ “ክራሬን ብቃኘው” የምትለዋን ዜማ ፈጥሮ መጣ። 

“ብቻዬን ቁጭ ብዬ ክራሬን ብቃኘው – ለካስ ካንቺ በቀር ሕይወቴ ባዶ ነው”፤ በወቅቱ ተወዳጅነትን ያተረፈችለት ያቺ ዜማ በሙዚቃ መሣሪያዎች ተቀነባብራ፣ እሱ ክራሩን ይዞ እያዜመ በኢትዮጵያ ቲሌቪዥን ለመቀረጽና ለሕዝብ ለመድረስ በቃች። ብዙም ዜማዎች በሌሉትና ለድምፃዊያን አስቸጋሪ ነው በሚባለው በአምባሰል ቅኝት የተደረሰችው የፋንትሽ ዘፈን ከአያሌ ዓመታት በኋላ፣ እስካሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የመቅረቧ ሚስጢር ኃያልነቷንና ተወዳጅነቷን ገላጭ ነው። ያቺን ዜማ የአሁን ዘመን ወጣት ድምፃዊያንም፡ ለዘፈን ውድድር ይዘዋት ሲቀርቡም አስተውለናል። 

በጠዋቱ እውቅናን ያገኘው ድምፃዊ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው፣ በወጣቶች ከተገነባው የማሂራን እና የመዲና ባንድ (የሙዚቃ ቡድን) ጋር ከመጫወቱም በላይ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ቤት ውስጥም ስራዎቹን ለሕዝብ ለማቅረብ ችሏል። በብሔራዊ ቲያትር ቤት በሰራባቸው ዓመታት ከድምፃዊነቱም በሻገር፣ በአስተዳደር ክፍል እስከ የሙዚቃ ክፍል ኃላፊነት ቦታ ደርሷል። የባህል ቡድኖችን በመምራት፣ ወደ ተላያዩ የውጭ ሃገራት በመጓዝ የአገራችንን ሙዚቃና ውዝዋዜ አስተዋውቋል። 

በአገር ቤት እያለ በተደጋጋሚ የሙዚቃ አልበሞችን አበርክቷል። በስደት ላይ ባለበት አገርም አርፎ ቁጭ አላለም። የውጭ አገርና የኛኑ የሙዚቃ ባለሙያዎችን በማዋሃድ በየጊዜው የሙዚቃ ድርሰቶቹን በኮንሰርትም፣ በአልበምም በመስራት ላይ ይገኛል።፡ሙዚቃ ላትተወው፣ እሱም ላይተዋት የተማማሉ እስኪመስል ድረስ። 

ድምፃዊ ፋንታሁን ባመነበት ነገር ላይ ብርቱ ነው። እስከመጨረሻው እጅ የማይሰጥ! ሁሌም የሙዚቃ ስራዎቹ በተሟሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች (ሙሉ ባንድ) መሰራት እንዳለበት አጥብቆ ያምናል። ይህንን እምነቱንም እስከመጨረሻው ጠብቆ የኖረ፤ ዘፈን በአንድ ኪ-ቦርድ ‘በሚመረትበት’ በአሁኑ ዘመን እንኳን፣ ዘፈንን ያለ ሙሉ ባንድ ንክች አያረጋትም። 

ዛሬ ስለድምፃዊ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው ይህቺን ትንሽ ማስታወሻ ለመጫር ያነሳሳኝ፤ በቅርቡ አዲስ የሙዚቃ አልበም እንደሚያስመርቅ ዜናው ከወደ ካናዳ-ቶሮንቶ በመሰማቱ ነው። “ለምን?” የተሰኘው አዲሱ የሙዚቃ አልበሙ ጁን 16 ቀን 2023 በቶሮንቶ ከተማ ይመረቃል። “ለምን?”፣ የእናት አገር ጥያቄንም ያዘለ ይመስላል፤ የዘመናችን የሁላችንም ጥያቄ ሊሆን የሚገባውና በጋራም ለጥያቄው ምላሽ የምንሻበት ወይም መልሱን የምናፈላልግበት! “ጥያቂውንም” ለመስማት፣ መልሱንም ለማሰላሰል፣ የአልበሙ ምርቃት እለት መገኘትን፣ ከዚያም ባሻገር አልበሙን የራስ አድርጎ ማጣጣምን ይጠይቃል። በካናዳ ያላችሁ ወገኖች በእለቱ በስፍራው በመገኘት ወንድማችንን እንድታበረታቱልን በአክብሮት ተጋብዛችኋል። 

ወዳጄ ፋንትሽ! ለትውልድ የሚቀር ነገር ከሚያኖሩት መሃል ነህ ብዬ አምናለሁ። ዘወትር ባመንክበት ነገር ሁሉ በርታ! የረጅም ጊዜ የስራ ፍሬህን ለማየት በመብቃትህ እንኳን ደስ ያለህ!

Filed in: Amharic