>

ይድረስ ለዐዲስ ድምፅ ሚዲያ አዘጋጅ፤ (ከይኄይስ እውነቱ)

ለአንድ ዓላማ በተሰልፈን ወገኖች መካከል የምክክር እንጂ የአተካራ ጊዜ የለንም

ከይኄይስ እውነቱ

ይድረስ ለዐዲስ ድምፅ ሚዲያ አዘጋጅ፤

ኢትዮጵያችን በዐምሐራው ሕዝብ የህልውና ትግል አማካይነት ዕጣ ፈንታዋ ዕድል ተርታዋ ላይ ዓይነተኛ አንድምታ ያለው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ በመሆኑም ለአንድ የጋራ ዓላማ በተሰለፉ ወገኖች መካከል የጎንዮሽ አተካራ የምንገጥምበት ሰዓት አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህም መልእክት በዚህ መንፈስ የተጻፈ በዕድሜ በምንቀራረብ ሰዎች መካከል የሚደረግ ወንድማዊ ምክር ነው፡፡ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ሚዲያ ከሐዲዱ እንዳይወጣ በጽኑ በመመኘት የቀረበ ነው፡፡ 

ለአንድ ዓላማ በቆሙ ወገኖች መካከል አንዱ ወንድም ሲደክም ሌላው ሊያበረታው፤ አንዱ ሲሳሳት ሌላው በትህትና ሊያርመው ይገባል፡፡ በዚህ የትግል አጋርነት መንፈስ ወንድማችን አበበ በለው ዐዲስ ድምፅ በሚባልና ከኢትዮጵያ ውጭ በሚተላለፍ መገናኛ ብዙኃን (ራዲዮና ማኅበራዊ ሚዲያ) አማካይነት ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያንና እሴቶቿን ማዕከል አድርጎ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የግፍ ማዕበል እየወረደበት ያለውንና ህልውናው በቋፍ የሚገኘውን የዐምሐራ ሕዝብ የሞት ሽረት ትግል በሚመለከት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ የሆነውን ሁሉ ለማጥፋት፣ በተለይም ዐምሐራውን ሕዝብ ከምድረ ገጽ ለማጥፈት ዐቅደው በዓላማ እየሠሩ ያሉትን የወንጀል አገዛዞችን – ወያኔ/ሕወሓት እና ኦነግ/ኦሕዴድን – ሴራ በማጋለጥና በመፋለም ሕዝብን በማንቃት፣ በመቀስቀስ፣ እውነተኛ የሆኑ ወሳኝ መረጃዎችን በማቅረብ የማይተካ ሕይወቱን እየሰጠ ካለው ፋኖ/የዐምሓራ ሕዝባዊ ኃይል ጋር የተካከለ ታላቅ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኝ ወንድም መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ጊዜው የምንሞጋገስበት ባለመሆኑ እንጂ ክብር ለሚገባው ተገቢውን ክብር መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ባንፃሩም በዚህ ትግል ውስጥ ስማቸው በዐደባባይ የማይነሣ እልፍ አእላፋት ያልተዘመረላቸው ጀግኖች እንዳሉ እኔም ሆንኹ ወንድማችን አበበ እናውቃለን፡፡ 

ይህ አጠቃላይ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሚሠራ ሰው ይሳሳታል፡፡ አንዳንዴም ለቆመበት ዓላማ የሚጠቅም የሚመስለውን ነገር ሲሰማ እጅግ ስሜታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ያሉ አጋጣሚዎች እገሌ ከእገሌ ሳይባል በማናችንም ሊከሠት ይችላል፡፡ 

በወንድማችን አበበ ደጋግሜ ከታዘብኹት ጉዳዮች አንዱ ለጥቂት የብአዴን እና የአብን (ኹለቱን ረብ የለሽ ድርጅቶች ስጠራ በእጅጉን ይቀፈኛል) አመራሮች ያለው ስሱነት ነው፡፡ በስም ለመጥቀስ አሁን ንግግሩ እንደ ቫይረስ የተሠራጨው የአቶ ዮሐንስ ቧ ያለው፣ የአብኖቹ ክርስቲያን፣ ደሳለኝ ጫኔ(ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡ በተጠቀሱት ‹ገረድ÷ ደንገጡር› ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች አማካይነት በክፍለ ሀገርም ሆነ በማዕከል ባሉ የሕዝብ ባልሆኑ የወንጀለኛ አገዛዙ ‹ሸንጎዎች› ውስጥ በዐደባባይ የሚደረጉ እንደ አበባ ያሸበረቁ ንግግሮች ሊያዘናጉንም ሆነ ሊያታልሉን አይገባም፡፡ ወንድማችን ግን በነዚህ የአንድ ሰሞን ዜና ማሟሟቂያ ንግግር ሲማረክና ስሜቱንም በአድማጮችና ተመልካቾች ለማጋባት ሲጥር አስተውዬአለሁ፡፡ በፕሮፓጋንዳ መልክ የጠላትንና ደጋፊዎቹን መንፈስ ለመስበር ከሆነ መልካም ብዬ የማልፈው ይሆናል፡፡ ግን ከዛ ያለፈ ስለመሰለኝ አካሔዱ ፍጹም የተሳሳተ ነው፡፡ ለቆመለት ዓላማና የዐምሐራ ሕዝብ ለሚያደርገው የህልውና ትግል ቢጎዳ እንጂ አይጠቅምም፡፡ በቀደም ዮሐንስ ቧ ያለው የተባለው ግለሰብ ወያኔ ‹የዐምሐራ› ‹ም/ቤት› ብሎ ባቋቋመው (ቀድሞ የወያኔ አሁን ደግሞ የኦነጎች ተልእኮ አስፈጻሚ በሆነው) ‹ም/ቤት› ተናገረ የተባለው ንግግር ባብዛኛው ፀሐይ የሞቀው ሕዝብ የሚያውቀው ነው፡፡ በውስጡም መርዞች እንዳሉበት ማስተዋል ይገባል፡፡ ወንድም አበበ እንዳልኸው የወገናችን የዐምሐራን ጉዳይ ስናስብ፣ ለ32 ዓመታት የተፈጸመበትንና አሁንም እየተፈጸመበት ያለውን ለዦሮም ለዓይንም የሚሰቀጥጥ ግፍና በደል በውስጣችን ይዘን ስሜታችን ሳይገነፍል መነጋገር አይቻልም፡፡ እኔም በዚህ ዓይነቱ ስሜት ከሚታመሙ ወገኖች አንዱ ነኝ፡፡ ዮሐንስና ጓደኞቹ ሰብእናቸውንና እግዚአብሔር የሰጣቸውን አእምሮ ለአሳዳሪዎቻቸው አስረክበው ለሦስት ዐሥርታት ሕዝባችንን በጅምላ ሲያስፈጁ፣ በሚሊዮን እንዲፈናቀል ሲያደርጉና ሲያስደርጉ፣ በረሃብ አለንጋ እንዲጠበስና ከማናቸውም ማኅበራዊ ልማት እንዲለያይ ያደረጉ፣ ለሕዝባቸው የሚቆረቆሩ ዐምሐራዎችን በማጎሪያ ስፍራ ያኖሩ፣ ለሞቱት የክብር ቀብር የነፈጉ፣ ምክረ አይሁድ በሚፈጽሙበት ሸንጓቸው ለሞቱት የሕሊና ጸሎት የነፈጉ፣ አረመኔዎች ናቸው፡፡ ዛሬም ዮሐንስም ሆነ እነ ክርስቲያን ተለውጠው አይደለም፡፡ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብለው ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ፣ በተለይ የዐምሐራው ሕዝብ አጥፊዎች ከሆኑ የአጋንንት ማኅበር የተቀላቀሉ ሰዓት የነዚህ ‹ሰዎች› ጭንጋፍ ማንነት ፍንትው ብሎ ወጥቷል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በተፈጥሮ (በእግዚአብሔር ፍጡርነታቸው) ወንድም ቢሆኑም፣ ከማኅበረ እኩያን ጋር ኅብረት ከፈጠሩ በኋላ ወንድም እያሉ መጥራቱ በደል የደረሰበትን ሕዝብ መዘንጋት ይሆናል፡፡

 ለመሆኑ እነዚህ ጉዶች የዐምሐራው ሕዝብ ላይ ይቅርታ የማያሰጥ በደል ፈጽመናል፤ ይቅርታ አድርጉልን ብለው ተንበርክከው ሲጠይቁ በየትኛው መድረክ ተሰምቷል? እነዚህ ግለሰቦች ረብ በሌለው ድርጅቶቻቸው ውስጥ ሆነው ዐምሐራውን አሳልፎ ከመስጠትና ከማስጠቃት ባለፈ ለሕዝቡ ምን አደረጉ? ዐምሐራው ተገፍቶ ተገፍቶ ጠርዝ ላይ ሲደርስና እምቢኝ ብሎ ሲነሣ ትግል ለማኮላሸትና ለማዘናጋት ቃላት በማሽሞንሞን ብቅ የሚሉ የጽጌረዳ እሾኾች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ርጉም ዐቢይ፣ ደሳለኝ ጫኔንም ሆነ ክርስቲያንን ሥልጣን ልቀቅ ሲሉ ዝም ያላቸው በንግግር ነፃነት ስለሚያምን ነው? ሕግ የሚሠራ ሆኖ ያለመከሰስ መብት ስላላቸው ነው? ከገዳይ ስኳዱ ዒላማ ውጭ ስለሆኑ ነው? በጭራሽ! የነሱ ባዶ ጩኸት ለጥፋት ተልእኮው ስለሚጠቅመውና በተወሰነ ደረጃ ሕዝብንም ስለሚያዘናጋለት/ስለሚያደነዝዝለት ነው፡፡ አንድም በተወሰነው የሕዝብ ክፍልም ተሰሚነት አግኝተው እነዚህን ቅጥረኞች ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ስለሚያስችለው ነው፡፡ ባጭሩ ርጉም ዐቢይና አገዛዙ በሥልጣን ለመቆየትና ዐምሐራውን ለማጥፋት እየቧጠጠ ካላቸው የመጨረሻ መንገዶች መካከል እንደ አንዱ የሚታዩ ስለሆነ ነው፡፡ ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ እንደሚባለው ‹ውይይት›፣ ‹ዕርቅ/ሽምግልና› ወዘተ. እያሉ ከጋለው ትግል ሕዝቡን ሊያናጥቡ የተነሡ መሠሪ ባንዳና ከሃዲዎች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ከወንድማችን አበበ ጋር የተያያዘ ባይሆንም አሁን ከጠቀስናቸው ከሃዲ ግለሰቦች ጋር ባንድነት የማየው ልደቱ አያሌው የተባለ አጭበርባሪ ፖለቲከኛ ነው፡፡ አማራው ከነገዱ በወጡ ድውያን መጠቃቱ ሁሌም እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ ይሄ ግለሰብ የዐምሐራው ጉዳይ ሲነሳ በንግግሩ ውስጥ መውሸልሸልና መሸሽ ከሚታይ በቀር አንዴም በፊት ለፊት ለዚህ ለተገፋ ሕዝብ ጥብቅና ሲቆም አይቼው አላውቅም፡፡ አፍቃሬ ሕወሐት/ኢሕአዴግና አድርባይነትን በውስጡ ታቅፎ የሚንከላወስ ሰው ነው፡፡ ሌሎቻችንን ሲተናነቀን እንደቆየው የኢትዮጵያዊነት መንፈስና ስሜት ይዞትም አይደለም፡፡ በአሳሳች ንግግሮቹና ጽሑፉ ትኩረት ፈላጊ፤ የፖለቲካ ሕይወቱ ዋና መግፍኤ አገርና ሕዝብን መታደግ ሳይሆን ሥልጣን ብቻ እንደሆነ ንግግሩም ድርጊቱም የሚያሳብቅበት ሰብእና ያለው አስመሳይ ግለሰብ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለሰ፡፡ 

ወንድም አበበ፤ ዮሐንስ የዐምሐራውን ግፍ ተረጋግቶ የተናገረው (በመሐል ከሰነቀራቸው መርዛማ ሐሳቦች ስረዳ) አስቦበት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ብአዴኖች (በ11ኛው ሰዓት ላይ ተጸጽተው ከሕዝቡ ትግል ጋር ከተቀላቀሉት ጥቂት የበታች ሹማምንቶች በስተቀር) ልባቸው በጭካኔ የደነደነ ጉዶች ናቸው፡፡ አንተ እንደገመትኸው የብስለት ወይም የአርቆ አስተዋይነት ምልክት ግን አይደለም፡፡ ‹ስወጣ ሊገሉኝ ይችላሉ› ያለው ደፋርነት ሳይሆን እንደማይነኩት ስለሚያውቅ ነው፡፡ ርጉም ዐቢይ ጀግኞቹ እነ ጄኔራል አሳምነውን ሕይወት ሲነጥቅ ይህን ግለሰብ ጨምሮ ሌሎችም ምንም ድርሻ አልነበራቸውም? ዐምሐራውን አስጨርሶ ካበቃ በኋላ ሕዝቡ በህልውና የመቀጠል ወይም ጨርሶ የመጥፋት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ የሞት ሽረት ትግል ሲጀምር ‹ውይይት/ዕርቅ› ማለት የንቀትና ለጌታው ግዳይ ለመጣል የሚደረግ የመጨረሻ ሙከራ አድርጌ ነው የማየው፡፡  የዮሐንስ ጌታ ርጉም ዐቢይ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት የጅምላ ጭፍጨፋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ንግግሮችን፡- ለምሳሌ በአ.አ. ሕዝብ ላይ ‹ኦሮሞ ጠል› እያለ ሲናገር፤ በኢኦተቤክ የውስጥ ጉዳይ ቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ሲፈተፍትና ምእምናንን ሊከፋፍል የሚችል ‹ የትግራይ ቤክ ሲገነጠል ትንፍሽ አላላችሁም› ወዘተ. የሚሉ ንግግሮችን ተረጋግቶ ሲናገር አድምጠናል፡፡ ከማስተዋል/ከብስለት ነው? ዮሐንስም ከጌታው የተማረው ይመስለኛል፡፡ ብአዴኖች የኦነግ አጋሰሶች ሆነው ዐምሐራውና ኢትዮጵያ የሚጠፉበትን መርዛማ አተላ ሲጫኑ የኖሩ፣ የተጫኑትንም በዐምሐራው ላይ ሲደፉ የኖሩና አሁንም በዚህ ነውረኛ ተግባራቸው የቀጠሉ ከእንስሳትም የወረዱ በሽተኛ ፍጡሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ‹ካልአን› (እንዲህ ናቸው ብሎ ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ‹ልዩ›) ፍጥረታት ማኅደራተ ዲያቢሎስ ከሆኑት ጌቶቻቸው ወያኔና ኦነግ ጋር ከኢትዮጵያ ምድር ሊወገዱ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ከኵርንችት በለስን ባንጠብቅ መልካም ይመስለኛል፡፡ 

ማንም ጤነኛ ሰው የወገኑን ሞት አይፈልግም፡፡ ሆኖም ጦርነት ተከፍቶብን ስንከላከልም ሆነ ፈጣሪ ረድቶን ወደ ማጥቃት ስንሸጋገር ከወገን በኩል የሚያሸልቡ መኖራቸው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ መሥዋዕትነታቸው ግን ለቤተሰባቸው፣ ለወገን፣ ብሎም ላገር ታላቅ ክብርና ኩራት ነው፡፡ 

በእኔ ትሁት እምነት የዐምሐራውን ሕዝብ ወይም ኢትዮጵያን ባጠቃላይ የገጠማቸው ፈተና በደም መሥዋዕትነት የምንገላገለው እንጂ ሌላ አማራጭ ያለው አይመስለኝም፡፡ ድርድር/ንግግር ከማን ጋር? መቼም ከአጋንንት ኃይላት (ከብአዴን፣ ከወያኔ እና ኦነግ) ጋር አትሉኝም፡፡ ወይም የርኵሰት ኃይላት ከሆኑት አንዳንድ የምዕራብ መንግሥታት/ባለሥልጣናት ጋር አትሉኝም፡፡ ኢትዮጵያ ሰው አጥታ ከብአዴን፣ ከወያኔ እና ደናቊርት ኦነጎች መካከል ፍለጋ የምትባዝን ከሆነ ታማሚዎቹ እኛ ነን፡፡

ወንድሜ የተሰለፍህበትን መልካም ሥራ/የፋኖነት ድርሻህን አጠናክረህ ቀጥልበት፡፡ እግዚአብሔር ይርዳህ፡፡

Filed in: Amharic