>

ለወንድሜ ለይኄይስ እውነቱ፤ የየሱስና የጳውሎስን ታሪክ አትርሳ (መስፍን አረጋ)  

ለወንድሜ ለይኄይስ እውነቱ፤  የየሱስና የጳውሎስን ታሪክ አትርሳ

መስፍን አረጋ   

“ንስሐ ካማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ፣ ንሰሐ በሚገባ ባንድ ኃጢያተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል” (ሉቃስ 15፡7)

ለወንድሜ ለይኄይስ እውነቱ።  በቅድሚያ ባማራ ሕዝብ የሕልውና ተጋድሎ ላይ ለምታደርገው የበኩልህን አስተዋጽኦ ላመሰግንህ እወዳለሁ፣ አንተው ራስህ እንዳልከው ጊዜው የትግል እንጅ የመመሰጋገን ባይሆንም።  ይህችን አጭር ጦማር ልጦምርልህ የተነሳሳሁት ደግሞ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለውን በተመለከተ ላዲስ ድምፅ አዘጋጅ ለወንድማችን ለአቶ አበበ በለው በጻፍከው ጦማር መሠረት ነው።  በይፋ የጦመርኩልህ ደግሞ ጦማሩ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ሁኖ ስለታየኝ ብቻ ነው።  

በጦማርህ ይዘት ባብዛኛው እስማማለሁ።  በሌላ አንጻር ግን አቶ ዮሐንስ ቧያለው (ከልቡ ሆነም አልሆነም) “በሴራ ፖለቲካ ተበልጠናል፣ ነገ ሊገሉኝ ይችላሉ፣ አፋኝና ጨቋኝ መንግሥት እንዳለን ማወቅ አለብን፣ መከላከያ ወዳማራ ክልል የገባው በማን ፈቃድ ነው፣ መከላከያን የፈጠርነው ሊከላከለን እንጅ ሊያሳድደን አይደለም፣ ወዘተ …) በማለት ሲናገር፣ ላማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ያበረከተውን እጅግ ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳዊ ጠቀሜታ በደንብ እረዳለሁ።  በብልጽግና አባልነቱ ውስጥ አዋቂ የሆነው አቶ ዮሐንስ ቧያለው ብልጽግናን በተለይም ደግሞ ጭራቅ አሕመድን በዚህ ደረጃ ሲያጋልጥልን ከኛ የሚጠበቅብን እንዲቀጥልበት ማበርታታት ብቻ ነው።  የወንድም አበበ በለውም እሳቤ ይሄው ይመስለኛል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንዴ ወንጀለኛ ሁሌ ወንጀለኛ አይደለም።  ከወንጀላቸው ተጸጸተው በመመለስ፣ የተወነጀሉበትን በብዙ እጥፍ የሚክሱ ነበሩ፣ አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ።  ለምሳሌ ያህል የክርስትና መሠረት እየሱስ ቢሆንም፣ ክርስትናን የዓለም ሐይማኖት ያደረገው ግን እየሱስን በጽኑ ያሳድድ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።  የወያኔና የኦነግ ጃንደረባ ወይም ደንገጡር በመሆን ባማራ ሕዝብ ላይ የፈጸምነው ወንጀል ጸጽቶናል የሚሉ የብአዴን አባሎችንም መመልከት ያለብን በዚህ እይታ ነው (በውነት መጸጸት አለመጸጸታቸውን ለማወቅ ድርጊታቸውን ባይነቁራኛ እየታዘብን)።  

ከጸጸት የሚበልጥ አነሳሳሽ ስሜት የለም።  በወንጀላቸው በጽኑ የተጸጸቱ ወንጀለኞች፣ ወንጀልን እና ወንጀለኛን ከአልወንጀለኞች በላይ በጽኑ እንደሚታገሉ የታወቀ ነው።  ጭራቅ አሕመድን ጨርቅ ለማድረግ፣ የጭራቅ አሕመድ ግብራበር በመሆን ባማራ ሕዝብ ላይ በሠራው ወንጀል በጽኑ ከተጸጸተ የብአዴን አባል የሚበልጥ ጠቃሚ ሰው የለም።  ለምሳሌ ያህል ባንድ ወቅት የጭራቅ አሕመድ ቀንደኛ ደጋፊ የነበሩና በደጋፊነታቸው የተጸጸቱ የሚመስሉ የሚዲያ ሰወች፣ ባሁኑ ወቅት ለፀረጭራቅ አሕመድ ተጋድሎ እያደረጉ ያሉትን ጉልህ አስተዋጽኦ በጉልህ እያሳዩን ነው።        

ድል የሚገኘው የጠላትን ሰፈር በማዳከምና የራስን ሰፈር በማጠናከር ነው።  የጠላትን ወንጀል በማጋለጥ ከጠላት ሰፈር ወጥተናል ብለው በይፋ የሚያውጁ ሰወች (በውነት ወጡም አልወጡም)፣ በጠላት ተራ ካድሬና ተራ ወታደር ላይ ሽብር ስለሚለቁበት የጠላትን ሰፈር ያፍረከርኩታል፣ ወገንን ደግሞ ጠላትን በጽኑ እንዲታገል ይበልጥ ያነሳሱታል።  ያቶ ዮሐንስ ቧያለው ንግግር ደግሞ ያማራን ሕዝብ ለሕልውናው ትግል ይበልጥ እንዳነሳሳና፣ በጭራቅ አሕመድ ካድሬወችና ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ እንደፈጠረ አሌ ማለት አይቻልም።  ስለዚህም አቶ ዮሐንስን አይዞህ ልነለው ይገባናል።  አቶ ዮሐንስን አይዞህ ስንል ደግሞ ሌሎች ብአዴኖች ያቶ ዮሐንስን ፈለግ ለመከተል ይነሳሳሉ። 

አማራን ያሳደድ የነበረ የብአዴን አባል፣ በወንጀሉ ተጸጽቶ ያማራ ሕዝብ መድሕን የማይሆንበት ምንም ምክኒያት የለም፣ ምንም እንኳን የብአዴን አባል ያማራ መድሕን ከሚሆን፣ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብታልፍ ቢቀልም።  ኤርትሬው በረከት ስምዖን በአማራ ሕዝብ ላይ የሠራው ትልቁ ወንጀል፣ ብአዴንን የሞላው አማራ ጠል ጌቶቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ ማናቸውንም ወንጀል በአማራ ሕዝብ ላይ ለመፈጸም ቅንጣት የማያቅማሙ ታዛዥ ውሾች የሆኑትን፣ የጃግሬኔት (follower) ሰብዕና አለመጥን የተጠናወታቸውን የደመቀ መኮንንን ዓይነት መፃጉወች በማሾ እየፈለገ መሆኑ ነው፡፡  

በወንጀሉ ተጸጽቶ ያማራን ሕዝብ የሕልውና ትግል ልቀላቀል የሚል ከሺ አንድ የብአዴን አባል ሲገኝ ግን፣ ካማራ ሕዝብ የሚጠበቀው፣ በወንጀሉ የተጸጸተውን አባል እጁን ዘርግቶ በመቀበል ወንጀሉን በሺ እጥፍ እንዲክስና የወያኔንና የኦነግን ግብአተ መሬት እንዲያፋጥን ማመቻቸት ነው።  ያማራ ሕዝብ ይህን ሲያደርግ ሲያዩ ደግሞ፣ ሌሎች የብአዴን አባሎች በወንጀላቸው ተጸጽተው ትግሉን ለመቀላቀል ይበልጥ ይበረታታሉ።  ትግሉም ይበልጥ እየተቀጣጠለ፣ ወያኔንና ኦነግን ይበልጥ እያቃጠለ፣ ተንጨርጭረው /ድብን/ የሚሉበትን ቀን ይበልጥ እያቃረበ ይሄዳል።  

በመጨረሻም፣ ወያኔና ኦነግ በመካከላችን የመርፌ ቀዳዳ ካዩ ቀዳዳውን ለማንቦራቀቅ ነቅተው የሚጠባበቁ፣ መቸም የማይተኙልን፣ ዛላለማዊ ጠላቶቻችን መሆናቸውን መቸም መዘንጋት የለብንም።  ስለዚህም፣ ለነዚህ ዘላለማዊ የሕልውና ጠላቶቻችን በር ላለመክፈት ስንል፣ ስንተቻችም ሆነ ገንቢ ሐሳቦችን ስንለዋወጥ በውስጥ መስመር ሊሆን ይገባዋል፣ ገሃድ ማወጣቱ የግድ አስፈላጊ ወይም ደግሞ ሌላውን አስተማሪ ካልሆነ በስተቀር።  ስለዚህም በኔ በኩል፣ ካሁን በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ የምለው ምንም የለኝም። 

መስፍን አረጋ     

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic