>

የማኦ ዜዶንግ መመሪያወች ለፋኖ (መስፍን አረጋ)

የማኦ ዜዶንግ መመሪያወች ለፋኖ

መስፍን አረጋ

ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል

 

ብአዴኑ አበባው ታደሰ ኦነጋዊ ጌታውን ጭራቅ አሕመድን ለመስደሰት በመቻኮል፣ ሺ ዓመታት ያስቆጠረውንና ቀፎው እንደተነካበት ንብ በነቂስ የተነሳውን ፋኖን በሁለት ሳምንት ውስጥ አጠፋለሁ ብሎ ተነስቷል። ይህ ችኮላው ግን ለፋኖ ትልቅ ዕድል ይከፍትለታል።  ፋኖ ማድረግ ያለበት በችኮላ እየተሯሯጠ የታጠቀውን ያበባው ታደሰን ጦር አድፍጦ ከመታ በኋላ እያሯሯጠ ትጥቁን ማስፈታት ነው።  ለዚህ ተግባር ደግሞ በተግባር የተፈተኑት የማኦ ዜዶንግ ሦስቱ ስልታዊ ትእዛዞች (The Three Tactical Commandments) ፍቱን ናቸው።

  1. ጠላት ሲበረታ አፈግፍግ
  2. ጠላት ሲዳከም አጥቃ
  3. ጠላት ሲያርፍ አውክ

እነዚህ ስልታዊ ትዕዛዞች ተተግብረው፣ ያበባው ታደሰ ጦር ተባሮ ቀበሌወችና ቀጠናወች ነጻ ሲወጡ ደግሞ፣ ፋኖን ይበልጥ በማጠናከር ትግሉን ይበልጥ ለማቀጣጠል፣ የማኦ ዜዶንግ አሥሩ ስነስርዓታዊ ትዕዛዞች (The Ten Disciplinary Commandments) የግድ መተግበር አለባቸው።

  1. ያለቃህን ትእዛዝ ቅንጣት ሳትጠራጠርና ላፍታ ሳታንገራግር ፈጽም፡፡
  2. የሕዝብን ንብረት አትንካ፣ መርፌም ብትሆን፡፡
  3. ከሕዝብ ስጦታ አትቀበል፣ ክርም ብትሆን፡፡
  4. ከሕዝብ ምንም ነገር አተዋስ፣ የግድ መዋስ ካለብህ ደግሞ የተዋስከውን ወዲያውኑ ተጠቅመህ በተዋስክበት ሁኔታ መልስ፣ ካበላሸህም ትክክለኛ ዋጋውን ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
  5. ከገበያም ሆነ ከየትም ቦታ ለምትገዛቸው ወይም ለምትሸምታቸው ነገሮች ሁሉ ተገቢ ዋጋቸውን ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
  6. በውጊያ ወቅት ላወደምከው ወይም ላጠፋኻው ወይም ለጎዳኻው የሕዝብ ሐብት፣ ንብረትና ሂወት ተገቢውን ካሳ ሙሉ በሙሉ ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
  7. የውጊያ ግርግር ለዘራፊ ያመቻልና፣ በግርገሩ የተዘረፈን፣ የተበዘበዘን ወይም የተመዘበረን የሕዝብ ሐብትና ንብረት አስመልስ፣ ማስመለስ ካልቻልክ ደግሞ ተገቢውን ካሳ እራስህ ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
  8. ሴት፣ ወንድ፣ ሕጻን፣ አረጋዊ ሳትል ማናቸውንም ሰው ስታናግር ሁልጊዜም በትሕትና አናግር፣ በተቻለህ መጠን ደግሞ እርዳ፡፡
  9. ልጃገረድ፣ ኮረዳ፣ ባለትዳር፣ ፈት፣ ጋለሞታ፣ ሴታአዳሪ ሳትል ሴትን አክብር እንጅ በጭራሽ እንዳትደፍር፡፡  ግዳጅ ላይ እስካለህ ድረስ ከሩካቤ ሥጋ ፈጽሞ ታቀብ፡፡
  10. ምርኮኛም ሆነ እስረኛ አታጎሳቁል፣ በተቻለህ መጠን ተንከባከብ፡፡

  መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic