>

ያማራ የሕልውና ትግል መሪወች ሆይ፣ ከወያኔ ትሮይ ፈረስ ተጠንቀቁ (መስፍን አረጋ) 

ያማራ የሕልውና ትግል መሪወች ሆይ፣ ከወያኔ ትሮይ ፈረስ ተጠንቀቁ

“ላማራ ሕዝብ ከኔ በላይ የታገለ የለም!” (የድል አጠቢያ አርበኛ)

አታላይ ማታለል ነውና ፍጥረቱ

አንዴ ቢያታልለን ለሱ ነው ሀለቱ

ሁለቴ ቢደግም የኛ ነው ጥፋቱ።

መስፍን አረጋ 

 

እውነተኛ ያማራ ልጆችና አመራሮቻቸው ዳዋ እየለበሱ፣ ጤዛ እየላሱ፣ ዲንጋ እየተንተራሱ፣ ደማቸውን እያፈሰሱዐጥንታቸውን እየከሰከሱያማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ፍሬ ማፍራት በጀመረበት ባሁኑ ወሳኝ ወቅት፣ አሜሪቃ የተቀመጠው አቶ ልደቱ አያሌው፣ ደረቱን በትቢት ነፍቶ በሙሉ ኩራት፣ ዓይኑን በጨው አጥቦ በሙሉ ድፍረት “ላማራ ሕዝብ ከኔ በላይ የታገለ የለም’” ሲል ተደምጧል።  ለምን?  

የዚህ ጦማር ዓላማ ይህን ጥያቄ መመለስ ነው።  ጥያቄውን መመለስ ያስፈለገበት ምክኒያት ደግሞ አቶ ልደቱ አያሌው የወያኔ ትሮይ ፈረስ (Trojan horse) መሆኑን በማሳየት፣ ላማራ ሕዝብ ታግያለሁ በሚል ማታለያ በእውነተኛ ያማራ ታጋዮች መኻል ገብቶ፣ የቅንጅትን ዐብዮት ባከሸፈበት መንገድ ያሁኑን የአማራን ሕዝብ ዐብዮት ለማክሸፍ እድል እንዳያገኝ ያብዮቱን ዋና መሪወች ከወዲሁ ለማስጠንቀቅ ነው። 

የቅንጅት አብዮት ዋና ግብ የጦቢያና የጦቢያውያን ዋና ጠላት የሆነውን ወያኔን ከናስተሳሰቡ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጦቢያ ምድር ላይ መንቀል ነበር።  ስለዚህም አቶ ልደቱ አያሌው ባንደበቱ እንደሚሰብከው በልቡ ለጦቢያና ለጦቢያውያን የሚያስብ ቢሆን ኖሮ፣ ሙሉ ትኩረቱን በቅንጅት ዐብዮት ዋና ግብ ላይ አድርጎ፣ የነ ዲባቶ (doctor) ብርሃኑን ሸፍጥ ለጊዜው ችላ ብሎ፣ ወያኔን ለመንቀል ማድረግ የነበረበትን ሁሉ ማድረግ፣ መፈረም የነበረበትን ሁሉ መፈረም ነበረበት።  ወያኔን ከነቀለ በኋላ ደግሞ እነ ዲባቶ ብርሃኑን ቀስ በቀስ በማራገፍ ቅንጅትን ከኢሕአፓ ሸፍጠኞች ሙሉ በሙሉ አጽድቶ፣ በራሱ እጅ አስገብቶ፣ በራሱ መንገድ ሊቀርጸው ይችል ነበር።  ይህን ማድረግ ባይችልም እንኳን፣ ወያኔን ለመንቀል ያንበሳውን ሚና በመጫወቱ ብቻ የጦቢያና የጦቢያውያን ዘላለማዊ ጀግና ይሆን ነበር።  

አቶ ልደቱ ግን ባንድም በሌላም ምክኒያት ተነሳስቶ፣ የቅንጅትን አብዮት ለማክሸፍ ቁልፉን ሚና ተጫውቶ ወያኔን ከሞት በማትረፍ፣ የጦቢያና የጦቢያውያን መከራ እንዲቀጥል ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በጣም እንዲከፋ አደረገ።  የጦቢያ ሕዝብ ደግሞ ውጉዝ ከመ አርዮስ ብሎ ዓይንህን ላፈር አለው።   

ወያኔ የሚባለው በላዔ አማራ የቀን ጅብ ባማራ ሕዝብ ላይ እጅግ እየከፋ የመጣው፣ በቅንጅት ዐብዮት ክፉኛ ከቆሰለ በኋላ ነበር።  በተጨማሪ ደግሞ ኦፒዲኦ (OPDO) የተባለው ከወያኔ እጅግ የባሰው በላዔ አማራ የቀትር ጅብ እያደገ መጥቶ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወያኔን ለመተካት የቻለው የቅንጅት ዐብዮት ወያኔን አቁስሎ ካዳከመው በኋላ ነበር።  ስለዚህም አሁን ላይ ቁመን ስናየው፣ ላማራ ሕዝብ ይሻለው የነበረው የቅንጅት ዐብዮት ተጀምሮ ከሚከሽፍ ይልቅ ባይጀመር ነበር ማለት ነው።  ስለዚህም ያማራ ሕዝብ በወያኔና በኦነግ ለደረሰበትና ለሚደርስበት የዘር ጭፍጨፋ ዋና ተጠያቂ መሆን ካለባቸው ሰወች ውስጥ አንዱ፣ የቅንጅት አብዮትን ለማክሸፍ ቁልፉን ሚና የተጫወተው አቶ ልደቱ ነው።  

ያሁኑ ያማራ ሕዝብ ዐብዮት ደግሞ የጭራቅ አሕመድን ኦነጋዊ መንግሥት የመገርሰስና ወያኔንና ኦነግን የማጥፋት ግቡን ሳይመታ በመሸማገልም ሆነ በመገላገል ሰበብ ባጭሩ ተቀጭቶ ከከሸፈ፣ ያማራን ሕዝብ መከራ ይበልጥ የሚያከፋ ስለሆነ ባይጀመር ይሻል ነበር።  ያማራ ሕዝብ ዐብዮት ከሽፎ ያማራን ሕዝብ መከራ እንዳያከፋ ደግሞ አቶ ልደቱ አያሌውን ከመሰሉ ያማራ ለምድ ከለበሱ የወያኔ ተኩላወች መጠንቀቅ ያስፈልጋል።  ስለዚህም አቶ ልደቱ አያሌው ያሁኑን የአማራን ሕዝብ ዐብዮት ለማክሸፍ ሊጫወት የሚችለው ሚና ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ የግድ ነው። 

ያቶ ልደቱ የጊዜው ሥራ በወያኔና በኦነግ ሚዲያወች ላይ እየቀረበ እሳቤውቹን መተንተን ነው።  ላስተዋለ ሰው ደግሞ  አቶ ልደቱ አድፍጦ ከተደበቀበት እየወጣ በየሚዲያወቹ በመሯሯጥ ሐሳቦቹን የሚያቀርበው ያማራ ሕዝባዊ ትግል በተግባራዊ መንገድ ተቀጣጥሎ ወያኔንና ኦነግን ሊያቃጥላቸው ሲል ሥራየ ብሎ እየጠበቀ ነው።  የሚያቀርባቸው ሐሳቦቸ ደግሞ ለሰሚው የሚያስደሰቱ ቢሆኑም፣ ነባራዊ ሁኔታወችን ያላገናዘቡ በመሆናቸው ሳቢያ ወደ ምድር ወርደው ሕዝብን በነቂስ ማነሳሳት የማይችሉ ባዶ ሐሳቦቸ ናቸው። 

ስለዚህም ያቶ ልደቱ ዋና አላማ፣ ያማራ ሕዝብ ሙሉ ትኩረቱን ባቶ ልደቱ ሊተገበሩ የማይቸሉ ፍሬከርስኪ ሐሳቦች አድርጎ፣ ከተግባራዊ ትግል ራሱን አግልሎሙሉ በሙሉ በወሬ ላይ ብቻ እንዲጠመድ ማድረግ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም።  በሌላ አባባል ያቶ ልደቱ ሙሉ ጥረት የአማራን ሕዝብ ውጤታማ ትግል አቅጣጫ በማስቀየር፣ ምንም ውጤት ወደሌለው ወደ ወሬ ትግል መለወጥ ነው።  በዚህ ረገድ ሲታይ፣ አቶ ልደቱ አያሌው ያማራ ሕዝብ የሕልውና ጠላቶች የሆኑትን ወያኔንና ኦነግን በቀጥታም ባይሆን በተዛዋሪ መንገድ በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ ያማራ ሕዝብ ዋና የሕልውና ጠላት ነው።     

በኔ በመስፍን አረጋ እይታ ደግሞ አቶ ልደቱ እነ ጃዋርንና ደብረጽዮንን ለመሰሉት ፀራማራ ጽንፈኞች የሚሰጠውን ከፍተኛ ክብር፣ እነ ፕሮፌሰር አሥራትን ጨምሮ ያማራ ብሔርተኞች ናቸው ለሚላቸው ሰወች የሚያሳየውን ግልጽ ንቀትና ጥላቻ ሳስተውል፣ የግለሰቡን ማንነት በተመለከተ ወደማልፈልገው ድምዳሜ ሳልወድ በግዴ አመራለሁ።  ያማራ የሕልውና ጠላቶች የሆኑትን ወያኔንና ኦነግን በበጎ ዓይን እየተመለከተ፣ በእከክልኝ ልከክልህ መንፈስ ያማራን የሕልውና ትግል ሊያግዝ የሚችለውን የኤርትራን መንግሥት ነክሶ መያዙ ደግሞ ድምዳሜየን ያጠናክርልኛል።  ባጠቃላይ ደግሞ ግለሰቡ ከወያኔና ከኦነግ በላይ አማራን የሚጠላ፣ ስምንቱን አስቀምጦ አንዱን የሚያጫውት ዘጠኝ ልበኛ ጽንፈኛ ይሆን እንዴ የሚለው ጥርጣሬ አለቅጥ ይከነክነኛል።  

ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ አቶ ልደቱ ማለት ያማራ ሕዝብ ወያኔንና ኦነግን ዐመድ ለማድረግ በትግሉ በሚያቅጣጥለው እሳት ላይ ውሃ እየጨመረ ለወያኔና ለኦነግ ቤዛ የሚሆን፣ በሐሳቡም ባይሆን በምግባሩ ፀራማራ የሆነ ግለሰብ ነው።  ስለዚህም ያማራ ሕዝብ ሕልውናውን መታደግ የሚችለው ላቶ ልደቱ ኢተግባራዊ እንቶ ፍንቶ ጆሮውን ባለመስጠት ወያኔንና ኦነግን አሁን እያናገራቸው ባለው ተግባራዊ ቋንቋ ማናገሩን ሲቀጥል ብቻ ነው። 

ላማራ ሕዝብ ሕልውና እንታገላለን የሚሉ ሚዲያወች ደግሞ ሙሉ ትኩረታቸውን ያማራ ሕዝብ በሚያደርጋቸውና ሊያደርጋቸው በሚገባ ተግባራዊ የትግል ፈርጆች ላይ ብቻ ማዋል አለባቸው።  ስለዚህም አቶ ልደቱን በየጊዜው እየጋበዙ ያማራን ሕዝብ ከውጤታማ ትግሉ እንዲያናጥብ መድረክ መስጠት፣ የትግላቸውን ዓላማ በፅኑ የሚፃረር መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል። ባሁኑ የሞት ሽረት ወቅት ያማራ ሕዝብ ማድመጥ ያለበት በወሬ ሳይሆን በተግባር እየተዋደቁለት ያሉትን የሕዝባዊ ትግሉን መሪወች ብቻ መሆን አለበት።  እየየም ሲደላ ነውና፣ በነጻነት ነጻ አስተሳሰብ ማራመድ የሚቻለው ሕልውናን ካስጠበቁ በኋላ ነው። 

ለማጠቃለል ያህል፣ አቶ ልደቱን በተግባሩ ስንመዝነው፣ ላይ ላዩን የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ነኝ የሚል፣ ውስጥ ውስጡን ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ ቀንደኛ ጠላቶች ለሆኑት ለወያኔና ለኦነግ ስስ ልብ ያለው፣ የጦቢያዊነት ካባ የለበሰ የለየለት ፀራማራ ሁኖ እናገኘዋለን።  ስለዚህም፣ ይህ የለየለት ፀራማራ ዛሬ በድንገት ተነስቶ የድል አጥቢያ አርበኛ በመሆን “ላማራ ሕዝብ ከኔ በላይ የታገለ የለም” በማለት በሙሉ ድፍረት የተናገረው፣ ባማራ የሕልውና ትግል አመራር ውስጥ ገብቶ፣ የቅንጅትን አብዮት ባከሸፈበት መልክ ያማራን ሕዝብ አብዮት ለማክሸፍ የበኩሉን ሚና ለመጫወት ነው ብሎ መጠርጠር ያስፈልጋል፣ ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነውና። 

መስፍን አረጋ      

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic