>

አንበሳው ተነሳ

አንበሳው ተነሳ

 

“አባቱ ውድማ የተኛውን በሬ፣ 

ነካክተው ቆስቁሰው አደረጉት አውሬ።” 

  የሕዝብ ስንኝ

____________________

ልባችሁ ተደፍኖ በትዕቢት ጮማ

አትነካኩት ስንል ብላቸሁ አልሰማ

እየነካካችሁ በሚያቃጥል ሳማ

አንገብግባችሁት ቆሽቱ እስከሚደማ፣

ሲጠናበት ጊዜ ሲበዛበት ቂያማ

በደረቀ ሌሊት በድቅድቅ ጨለማ

አንበሳው ተነሳ ከተኛበት ውርማ።

 

ብዙ ሲታገሰው መስሎት ሙት እሬሳ

እየፈነጨበት ባፍቂጡ እየፈሳ

የቀሰቀሰውን በትቢት ትንኮሳ

ጅብም ሆነ አነር፣ ተኩላም ሆነ ሰሳ

አሳዶ በመያዝ እያሳየ አበሳ፣

ዳግም ላይረበሽ ሰላም ላይነሳ

ምሎ ተገዝቶ ሦስት ጊዜ ሲያገሳ፣

አደበላለቀው አስራ አራቱን ማሳ

በአንድነት ሰማው ሰማኒያ ሶስት ጎሳ።

 

ጦሙን እንደዋለ ጡሙን ስላደረ

ጨጓራው ተቃጥሎ አንጀቱ እንዳረረ

ሆዱ ተቆራምዶ አፉ እንደከረረ፣

በገባችሁበት ገብቶ እያባረረ

በክንዱ ደቁሶ እየዘገረረ

ቁርስ ያረጋችኋል እየሰባበረ።

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com  

 

ቂያማ ማለት በላኮመልዛ አማረኛ መከራ፣ ችግር፣ አበሳ ማለት ነው “ምን ዓይነት ቂያማ ነው” እንዲሉ።

 

 

Filed in: Amharic