>

የአማራን ሕዝብ የህልውና ትግል የሚያቀናጅ ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ! (ከአሕግ የተሠጠ አስቸኳይ መግለጫ)

የአማራን ሕዝብ የህልውና ትግል የሚያቀናጅ ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ!

ከአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተሠጠ አስቸኳይ መግለጫ

የአማራ ሕዝብ ላለፉት ረጅም ዓመታት እንደ ሕዝብ ሲደርስበት የነበረውን መስፈሪያ-የለሽ መከራ፣ አገርና ሕዝብን ለማቆየት ሲል ስቃዩን ችሎ ሰላማዊ የለውጥ ሁኔታ ይፈጠራል በሚል ሲታገስ ቆይቷል። ትዕግሥቱን ፍርሃት፣ ዝምታውን የተሸናፊነት፣ መንግሥት ማክበሩን እንደ አላዋቂነት ተወስዶ በመከራ ላይ መከራ ሲደራረብበት ቆይቷል። ይህ ሁሉ የአማራው ታጋሽነት የአገርን ሕልውና ከአደጋ ለመጠበቅ፣ የንጹሃን እልቂትን ለማስቀረትና በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መፍትሄ ይገኛል ከሚል ፍጹም ስልጡንነት ነበር። ሆኖም የአብይ አህመድ የኦሮሙማ የፓለቲካ አይድዮሎጂን ተከትሎ፣ የአማራውን ሕህዝብ፣ ከክርስትናና ከሙስሊም እምነት ተከታዮች ጋራ አጥፍቶ፣ በምስራቅ አፍሪካ የኩሽ ግዛት ለመፍጠር የጀመረው የፋሺዝም የዘር ማፅዳትና የመስፋፋት ፓሊሲ ከኢትዮጵያም አልፎ በመላው አፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ ታላቅ የፀጥታ ችግር ፈጥሮ፣ ቀጠናውን የኃያላን ጦር አውድማ ሳያደርገው ኢንተርናሽናል ኮሚኒቲው አስፈላጊውን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ይህ የጉግማንጉግ ሰው-በላ የአራዊት አገዛዝ ለሠላም የተዘረጋውን የሕዝባችንን እጅ ለመቁረጥ ምሳሩን መዞ እልቂትን አውጇል። ዐማራው ህልውናውን ለመከላከል ያለው ብቸኛ አማራጭ ኃይል ብቻ በመሆኑ ሳይወድ በግድ በጠላቶቹ ጋባዥነት ወደ ለየለት ጦርነት ውስጥ ገብቷል። የአማራ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት የአብይ አህመድ የኦሮሙማ-ኦህዴድ-ኦነግ አገዛዝን ወረራ ለመመከት በበርካታ ግንባሮች እየተፋለመ ይገኛል። ሕዝባችን እየተፈጸመበት ያለውን መረን-የለሽ ጭፍጨፉ፣ አፈናና ግድያ ዝም ብሎ ከመመልከት ወደ ሁለገብ የተከላካይነት ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የተጋድሎው ግለትና የጦር ግንባሩ ስፋት አማራው የሚያደርገውን ትግል በበለጠ ውጤታማና አሸናፊ እንዲሆን የተቀናጀ አመራር የሚሰጥ አካል ማዋቀር አስፈልጓል።
ይህንንም የሚያቀናጅ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል።
የአማራው የተለያዩ ክፍላተ አገሮች፣ በሥራቸው የፋኖ ብርጌዶች ያሏቸው ኮማንድ ፖስቶች ሲኖሯቸው፣ እነዚህንም በበላይነት የሚያስተባብረው ጀግናው አርበኛ ሉቴናንት ኮረኔል ፉንታሁን ሙሃባ ነው።
የኮማንድ ፖስቱ ዓላማዎች፡-
* ክልሉን ሙሉ በሙሉ ከጠላት ለማፅዳት የተባበረና የተቀነባበረ ትግል እንዲካሄድ ማድረግ፤
* ነፃ የወጡ ከተሞችን ጥበቃ እንዲኖራቸውና ሕዝባዊ አስተዳደር በማዋቀር የአገልግሎት ተቋማት ስራቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ፤
* ትግሉን ለመቀላቀል የሚፈልጉ ኃይሎችን ማሰልጠን፣ ማስታጠቅና ለትግል ማሰማራት፤
* የሎጅስቲክስ አቅርቦትን ለማሳለጥና፣ ጉዳት የደረሰባቸውን በመንከባከብ እርዳታ እንዲያገኙ ማመቻቸት፤
* የጠላት ምርኮኞችንም ዓለም ዓቀፍ ህግ በሚፈቅደው መሠረት መጠብቅ፣ ተጸጽትውና ይቅርታ ጠይቀው ከወገን ጦር እንዲቀላቀሉ መሞከር፣ ወይም ወደፊት ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ።
ይህንንም ሕዝባዊ ዓላማ ለማሳካት የተቋቋሙት ኮማንድ ፖስቶችና ብርጌዶች የሚከተሉት ናቸው፡
ኮረኔል ፉንታሁን ሙሃባ አጠቃላይ የኮማንድ ፖስቶቹ የበላይ አስተባባሪ ከመሆኑም በተጨማሪ የወሎን ብርጌዶች ኮማንድ ፖስት ይመራል፡፡ ብርጌዶቹ:-
* አንደኛ ብርጌድ
* ሁለተኛ ብርጌድ
* አሳምነው ብርጌድ-ላሊበላ
እንዲሁም ይህ ኮማንድ ፖስት ከምስራቅ አማራ ፋኖ ዋና አዛዥ አርበኛ ምሬ ወዳጆ ጋር በመመካከር ተናቦ እንዲታገል ተዋቅሯል፤
በጎንደር ያሉ ብርጌዶች ኮማንድ ፖስት በጊዜያዊነት በሻለቃ አንተነህ ይመራል፡፡ ብርጌዶቹ፦
* ምኒልክ ብርጌድ
* ቆስቁስ ብርጌድ
* ደቡብ በጌምድር ብርጌድ
* ቋረኛው ብርጌድ
የሽዋ ኮማንድ ፖስትን የሚመራው በሻለቃ መከታው ሲሆን በእዙ ሥር አራት ብርጌዶች ይኖራሉ፡፡
የጎጃም ኮማንድ ፖስት፦
* ብርጌዶቹ
* የበረኸኛ ብርጌድ
ኮማንድ ፖስቶቹ የዓማራ ሕዝባዊ ኃይሎች ባሉበት ቦታ ሁሉ ተናበውና ተባብረው ይሠራሉ። ሌሎችም ብርጌዶች በሂደት ወደፊት ይካተቱበታል።
እንዲሁም በውይይት ላይ ያሉ በተለያየ የፋኖ አደረጃጀት የተዋቀሩ የቁርጥ ቀን ልጆች በሚያደርጉት ትግል፣ ሁሉም ተቀናጅቶ በአንድ ሠፊ ግንባር እንዲዋቀሩ መሬት የረገጠ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ለጊዜው ከተፈጠረው አጣዳፊ ሁኔታ አኳያ ከላይ የተዘረዘሩት የፋኖ ብርጌዶች በአንድ ዕዝ ሥር ተናበውና ተደጋግፈው ለመታገል የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለሕዝብ ስናሳውቅ በታላቅ ኩራት ነው። በዚህ ኮማንድ ፖስት የተካተቱትንም ሆነ በየአካባቢው ከጠላት ጋር የሚፋለሙትን ሁሉ፣ ወገናችን በሚችለውና ባለው አቅሙ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው አደራ እንላለን።
በመጨረሻም በአገር መከላከያ ሥር ተሰልፈህ አገር ለመጠበቅ አደራ የተቀበልክ ሠራዊት፣ ጦርነቱ በሕዝብና በጥቂት አንባገነንና ጨፍጫፊ የብልጽግና ፋሽስታዊና ዘረኛ መሪዎች መካከል መሆኑን አውቀህ ከሕዝባዊ ፋኖዎች ጋራ እንድትቀላቀል፣ ወይም በብልጽግና መሪዎች ላይ አፈሙዝህን እንድታዞር ታሪካዊ ጥሪ ቀርቦልሃል።
በዚህ ጦርነት ግፉና መስዋዕትነቱ የከፋ ቢሆንም፣ የአብይ አህመድ ፋሺስታዊው የኦሮሙማ ሰው-በላ አገዛዝ ፈጽሞ አገር የመምራት እድል ከእንግዲህ ወዲያ አይኖረውም። ከግብረ-አበሮቹም ጋራ ለፍርድ የሚቅርብበት ጊዜ ሩቅ አደለም። ስለሆነም በተለያየ የመንግሥት ሃላፊነት  ላይ ያላችሁ ባለስልጣናት፣ በውጭ የዲፕሎማሲ ስራ የተሰማራችሁ፣ አገዛዙን በተለያየ መንገድ የምታገለግሉ፣ ከዚህ ሕዝብ ጨፍጫፊ ሥርዐት እራሳችሁን በጊዜ እንድታገሉ ሞራላዊና ሕሊናዊ ግዴታ አለባችሁ። ለለውጥ የተነሳው ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን መከራ ችላ ብላችሁ ከአራጁ አገዛዝ ጋር ከቀጠላችሁ ሕዝባችን በእናንተ ላይ ሊያደርሰው የሚችለውን የበቀል እርምጃ ማስቆም የሚችል ኃይል አይኖርም።
ለሃያ ሰባት ዓመታት የሕወሃት/ኢህአዴግን፣ እንደዚሁም ላለፉት አምስት ዓመታት የኦህዴድ ኦነግ/ብልጽግናን የግፍ ጽዋ የቀመሳችሁ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሆይ! የአማራ ሕዝብ ለህልውናው ብሎም ኢትዮጵያ እንደአገር እንድትቀጥል ለሚከፍለው ከፍተኛ መስዋእትነት የድርሻችሁን እንድትወጡ ወገናዊ ጥሪ ቀርቦላችኋል።
የአማራ ሕዝብ በልጆቹ መስዋዕትነት ያሸንፋል!

መነሻችን የአማራ ሕልውና፣ 

መዳረሻችን የኢትዮጵያ አንድነት!

የአማራ ሕዝባዊ ግንባር!
ሐምሌ 30/2015 ዓ.ም. (August 6, 2023)
Filed in: Amharic