>
5:21 pm - Wednesday July 21, 9520

በርግጥም “የኢትዮጵያ ተጠሪ ማነው”? (አሰፋ ታረቀኝ)

በርግጥም “የኢትዮጵያ ተጠሪ ማነው”?

አሰፋ ታረቀኝ

የትህነግ ጸሐይ ከአድማስ እስከ አድማስ ባሸበረቀችበት ዘመን፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማራከስና በጦር ሜዳው፣ በድፕሎማሲውና በሃገር ግንባታው የተሳተፉትን የሃገር ባለውለታዎች በነጋ በጠባ መዝለፍና ማዋረድ እንደ ሙያ ተይዞ ነበር፡፡ የትህነግ አገልጋይ የነበረ የነጭ ቅጥረኛ ሁሉ ቤተ-መንግሥቱንም ቤተ-ክህነቱንም ሲርመሰመሱበት የተመለከተው አንጋፋው የብዕር ሰው ሙሉጌታ ሉሌ በዝነኛዋ ጦቢያ መጽሄት ላይ “ በማን እጅ ነን?” የሚል ጥያቄ አንስቶ በወቅቱ የነበረውን የቁምጣ ለባሽ ዘራፊ ቡድን ራቁቱን አስቀርቶ ነበር፡፡ፕሮፌሰር ጌታቸው ሐይሌም ከሌሎች ጋር ተባብረው ያዘጋጁትና በ 2012 የታተመው መጽሐፋቸው ርእስ “የኢትዮጵያ ተጠሪ ማነው?” የሚል ነበር፡፡ እትዮጵያን በታሪኳ ልክ የሚመጥናት ሰው አግኝታ ዕፎይ ሳይሉ ሁለቱንም ሞት ቀደማቸው፡፡ ኢትዮጵያ በማን እጅ እንደሆነች አሁን ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ መልስ ያላገኘው ተጠረዋ ከየት ይምጣ የሚለው ነው፡፡አንደበተ ርዕቱውና “ትሁቱ” ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/አብይ አህመድ ሥልጣን ላይ መደላደላቸውን ካረጋገጡ በኋላ፣ የኦነግርንና የትህነግን የድርጊት መመሪያ /manual/ አንድ በአንድ ተግባራዊ እያደረጉ ናቸው፡፡ 

የኦነግና የትህነግ የፖለቲካ ግብ አንድን ህዝብ/አማራን/ በኢትዮጵያ ውስጥ ተሠሩ ለተባሉ “ወንጀሎች” ሁሉ ተጠያቂ ማድረግ ሲሆን፣ ከ50 ዐመት በላይ የዘለቀ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ አካሄደውበታል፡፡

  • ነፍጠኛ
  • ትምክህተኝ
  • ወራሪ
  • ተስፋፊ የሚሉና አዲስ የተጨመረለት የ “ማዕረግ ስም” ደግሞ፣
  • የቀድሞው ሥርአት ናፋቂ የሚል ነው፡፡

ሕብረተሰቡን አንቆ ይዞት የነበረውን የባላባት ሥርአት ለመቀየር ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ አሁኗ ሰአት ድረስ ያላቋረጠው  የአማራ ልጆች ደም መፍሰስ፣ ለትህነግና ለኦነግ ካድሬዎች ጉዳያቸው አይደለም፡፡ መድረሻቸው ጎሳን ተገን አድርጎ ሥልጣን ላይ መቆናጠጥና ሚስኪኑን ድሀ ገበሬ እየዘረፉ ራሳቸውንና የቅርብ ዘመዶቻቸውን ማበልጸግ ነው፡፡ ትህነግ የሠራውን ተረኛው ኦነግ “ብልጽግና” ተብሎ በተሰየመው ድርጅት አማካይነት እየፈጸመ የገኛል፡፡ ለትህነግና ለኦነግ ጭፍን ተከታዮችና አማኞች፣ አማራ ከዲያብሎስም በላይ የከፋ ነው፡፡ የሁለቱም ድርጅቶች የ“ርዕዮተ-አለም” አባት የሆነው ሮማን ፕሮ ቻዝካ  Abyssinia: The Powder Barrel( አቢሲኒያ፡ የባሩድ በርሜል) በተሰኘውና በ1935 (እ.ኤ.አ) አሳትሞ ባሰራጨው መጽሄት “………… Moreover, the opponents of Imperialism should bear in mind that the numerous non-Amharic native tribes in Ethiopia,and these constitute by far the greater part of the total population of the empire,are themselves the victim of Abyssinian imperialism. “…በተጨማሪም የኢምፔሪያሊዝም ተቀናቃኞች ሊገነዘቡት የሚገባው እውነታ፣ አማርኛ ተናጋሪ ያልሆኑትና አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሌሎች የሀገሪቱ ዜጎች፣ የኢትዮጵያ ኢምፔሪያሊዝም ተጠቂዎች መሆናቸውን ነው፡፡  ይላል፡

ይህንን የቅኝ ገዥወች ትንተና ሳያላምጥ የዋጠው የኦነጉ ዋና ሰው አቶ ለንጮ ለታ በ80ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአድስ አበባ ይታተም ለነበረው ሳሌም መጽሄት በሰጠው ቃለ-መጠይቅ “ We are Abyssinian subjects” እኛ በአቢሲኒያኖች ቁጥጥር ሥር ነን፡፡” ነበር ያለው፣ ባጭሩ የኢትዮጵያ ዜጎች አልነበርንም ነው፡፡ ትህነጎች ጉዳዩን ከአቢሲኒያኖች አወጡና/ምክንያቱም አቢሲኒያ አማራና ትግሬን ስለሚጠቀልል/ አጼ ምኒልክን መገለጫ አድርገው አማራውን የክፍለ-ዘመናቱ ሁሉ ችግር ተጠያቂ በማድረግ ያለመታክት ቀሰቀሱበት፤ ከትህነግ የጎደለውን ኦነግ እያሟላ ያለ ርህራሄ የጥላቻ ዘመቻቸውን አወረዱበት፤ ከዚያ ወደ ጭፍጨፋው ተረማመዱ፡

 የበደኖውን ጭፍጨፋ ኦነግ በትህነግ ትህነግ በኦነግ አመካኙ፤ አማራው ደመ-ከልብ ሆኖ ቀረ፡፡ እኔስ ከማን አንሼ ያለው ኦሆድድ፣ ዲማ ጉርሜሳ በተባለው ካድሬው አማካይነት አርባ ጉጉና አቦምሳ ላይ አማራውን እንደ ቅጠል አረገፈው፡፡ ይኸ ሁሉ ግፍ አማአራና ኦሮሞ ተጫረሰ ለማሰኘት ነበር፡፡ የተገላቢጦሽ ሆነና ሁለቱ አንድ ድምጽ በማሰማትና በጋራ በመቆም ትህነግን ወደመጣችበት ሸኟት፡ ፈገግተኛውና ቅልስልሱ ዶ/ር አብይ አሕመድ ብቅ ብለው “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ” ሲሉን፣ በውጭም በውስጥም ያለው ኢትዮጵያዊ “ ከአብይ ጋር ወደፊት እስከ ሞት” የማለት ያክል አብሮ ተሰለፈ፡፡ ሰላምና ነጻንት የተጠማው ሕዝብ ባለበት ላይ ሆኖ ሲጠብቃቸው፣ ጠቅላይ ሚንስትሩን ማማው አልተመቻቸውም፤ በወጡበት ርቀት ልክ ተምዘግዝገው ወረዱ፡፡ መቸም ቢሆን፣ አንድን ፖልቲከኛ የህዝብን ፍቅር ከማጣት የበለጠ የሚጎዳው ነገር የለም፡፡ ለወደፊቱ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም ይተካል ተብሎ በሚጠበቀው “ኦሮሚያ” የግዛት ክልል ውስጥ የሚኖረው የአማራ ተወላጅ በወለጋና በሻሸመኔ እንደ አውሬ እየታደነ ሲታረድ አንድት የማጽናኛ ቃል አልተናገሩም፡፡ ምናልባትም ኦሮሞውም እየሞተ ስለሆነ፣ ወገነ እንዳይባሉ ነው የሚል ግምት ተወስዶ ነበር፡ ትህነግ ደብረ ብርሃን ጥግ ድረስ መጥቶ አማራ ክልልን ሲያወድም፣ ከፌደራል መንግሥቱ አቅም ማነስ ጋር አያይዘነው ነበር፤አሁን አሁን እየሆነ ያለውን ስናይ፣ ለካ ነገሩ ወድህ ኖሯል፡፡ አንድኛው የ“አቢሲኒያ ኢምፔሪያሊዝም” ክንፍ፣ ማለትም ትግሬው፣ በማያንሰራራበት ሁኔታ ተመትቷል፡፡ የቀረው ከላይ በተጠቀሱት አምስት አይነት ወንጀሎች የሚከሰሰው አማራው ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ለመተካት በታጨችው “ኦሮሚያ” ውስጥ እንዳይኖር የተፈረደበት አማራ፣

  • ገደሉት፣ የሞተው ሞቶ የተረፈው ሸሸ፣ 
  • እንደ ሰማዕቱ እስጢፋኖስ ዘቅዝቅው ሰቀሉት
  • በህይወት የተረፈው አልቅሶ  ወደ በቱ ገባ፡፡
  • አድስ አበባ አትገባም ተባለ፣ ስንቁን እንደቋጠረ፣ ወደመጣበት ተመለሰ፤ 
  • ህግን መሰረት አድርገው በሸጡለት መሬት ላይ የሠራውን ቤት “ሸገር የሚባል ከተማ እንመሰርታለን” ብለው አፈረሱበት፤ ልጆቹን ይዞ ሜዳ ላይ ወደቀ፤

 ይኸ ሁሉ እየሆነ ያለው በጠቅላይ ሚንስትሩ ዐይን ሥር ነው፡፡እንኳን ክቡሩ የሰው ልጅ ይቅርና፣ እንሰሳም ሲሞት መፈራገጡ ተፈጥሮዊ ነውና፣ ከእንግደህ መሸሻ የለኝም፣ እጥጉ ደርሻለሁ ብሎ ነፍሱን ለማትረፍ ሲነሳ፣ የኖቬል ተሽላሚው ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/አብይ አህመድ በአማራ ሕዝብ ላይ፣ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለዋል፡፡ ከአድስ አበባ ጭምር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲዘረፍ፣ ሸኔ ተብሎ የተሰየመው አሰማሪው ማን እንደሆነ የማይታወቀው”ጦር” ወለጋን ተቆጣጥሮ የመንግሥትን መዋቅር ሲያፈራርስና የብልጽግናን አባሎች ሲገድል፣ በ‘እናት ኦሮሚያ’ ካህናት ሲገደሉ፣ ቤተክርስቲያን ስትዘረፍ፣ ድምጻቸውን ያጠፉት ጠቅላይ ሚንስትር፣ ራሱን ከመከላከል በስተቀር የገበሬ እሸት ቆርጦ ያልበላውን የአማራ ታጣቂ ለማጥፋት እንቅልፍ አጥተው እየሠሩ ናቸው፡፡ የቅርብ አማካሪዎቻቸው ጉምቱ የኦነግ ሰዎችና የትህነጉ ታማኝ ካድሬ ረድዋን ሁሴን፣ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣አሜሪካኖቹ ራብጣ እያሳዩ እያማለሏቸው ነው፡፡  አማራ ከተቻለ፣ መጥፋት፣ካልሆነ በማያንሰራራብት ሁኔታ መመታት አለበት፤ የተሻል ምክር ሊሰጡ?? አይሞከርም!

እንዳለመታደል ሆኖ ደግሞ የነጩም፣ የኦነግም፣ የአድዋ ባንዳዎችም ኢላማ የሆነው አማራው ነው፡፡ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እንድል ያገሬ ሰው፣ አፍሪካ ቀንድን አንድ አደርጋለሁ እያሉ ይደስኩሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር፣ ኢትዮጵያ ከእጃቸው እያመለጠች ነው፡፡ ይህ ጦርነት የአማራና የኦሮሞ፣ የትግሬና የአማራ፣ ወይም የሌላው አከባቢ ኢትዮጵያዊ ጦርነት አይደለም፤ ሲጀመር፣ የኦነግ፣ የትህነግና የኦሆድድ ጦርነት ነው፡፡ ይህንን በየተራ እንድናልቅ የተደገሰልንን ጦርነት አንድ ላይ ሆነን ካላስቆምነው፣ በጥቂት አመታት ውስጥ ትውልድም ሐገርም አልባ መሆናችን የማይቀር ነው፡፡ 

አማራው የ30 አመቱን እልቂት ተቋቁም ቢቆይም፣ በወረፋ እየተገደለ ስለሆነ፣ ተጋድየ ልሙት ብሎ ተነስቷል፤ ማቆሚያ የሌለው የደም አላባ  ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለመጭው ትውልድም እዳ ነው፡፡ ተሳትፎ ባላጸደቀው ህገ መንግሥት አንቅጽ ተጠቅሶ በአንድ ህዝብ ላይ ጦርነት ሲታወጅ፣ እንደ ህዝብ አማራ፣ እንደ መንግሥት ኦሆድድ-ኦነግ  የመጀመሪያ መሆናቸው ነው፡፡ የኢሃደግ አስኳሉ ትህነግ እንደነበረው ሁሉ፣ የብልጽና አስኳሉ፣ ኦሆድድና ኦነግ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

ኢትዮጵያ ተጠሪ ያስፈልጋታል፡፡ በጎሳ ጭቃ የተለወሰው የዶ/አብይ መንግሥት፣ ታጥቦ ከመላቀቅ ይልቅ ወደውስጥ እየሰመጠ ነው፤  “ እሪ በይ ሀገሬ” Cry, the Beloved Country ነበር ያለው የደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ Alan Paton ከዛሬ 75 አመት በፊት። በተያዘው አካሄ ከቀጠለ፣ አማራ ምናልባት ከእስካሁኑ የበለጠ ዋጋ ላይከፍል ይችል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ተመልሳ እንደ ወትሮው ትሆናለች ብሎ መጠበቅ ግን በእጅጉ ቂልነት ነው፡፡ ከላይ የተጠቅሰው ደራሲ እንዳለው፣ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክሉ ጥጋበኛ ጎረምሶች አገር ከማውደማቸው በፊት እሪ ብለን ልናስቆማቸው ይገባል፡፡ ወደድንም ጠላንም፣ታሪክ ይመዘገባል፣ ዶ/ር አብይ አህመድ ከአማራዋ ሚስቱ የወለዳቸውን ልጆቹን አሁን በሸዋ፣በወሎ፣ በጎንደርና በጎጃም እየተፈጸመ ስላለው እልቂት ምን ብሎ እንደሚያስረዳቸው እግዚያብሔር ይወቀው፡፡

ለኦሆድድ-ኦነግ መሸፈኛ የተዋቀረው ‘ብልጽግና’ ጭራሹን ወደ ብ..ና (ሁለት ፊደሎች ጨምሩበት) ተምዘግዝጎ ወርዶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉን አቶ ክርስቲያን ታደለን በታጠቁ ኅሎች እያስደበደበ አፍኖ እሥር ቤት ዘግቶበታል፡፡ በ19ኛው ማብቂያና በ 20ኛው ክፍለዘመን መግቢያ ላይ በራሺያና በምስራቅ አውሮጳ አይሁዶች በዘራቸው ምክንያ እየተለቀሙ ይታሠሩ፣ ይገደሉ ነበር፡ ጎረቤቶቻቸው ሁሉ ጨከኑባቸው፣ ተገደሉ፣ ተዘረፉ፣ የተረፉት አገር ጥለው ሄዱ፤ የደረሰባቸውን ግፍ ለመግለጽ የተጠቀሙበትን ቃል Pogrom ይሉታል፤ እንግሊዝኛው ወስዶ  የራሱ አድጎታል:: ፖግረም ማለት በአንድ የተወሰነ የህብረተስብ ክፍል ላይ  ዘርን ወይም ጎሳን መሰረት ያደረገ ዝርፊያን፣ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ማካሄድንና የዚያን ሕብረተሰብ የሞራል መሠረት እስክመሰባበር የሚዘልቅን ግፍ ያጠቃልላል፡፡ አማራው ወደዚያ ክልል ውስጥ ከገባ የቆየ ቢሆንም፣ የወደፊቱ የሚከፋ ይመስላል፡፡ “ከቀይ ሽብር የከፋ ይሆናል” አይደል ጠቅላይ ሚንስትሩ ያሉን? ኦነግና ኦሆድድ በብልጽግና  ካባ ሥር ተሸፍነው ለሚያደርሱት ዕልቂት፣ከሌላው  የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ ኢትዮጵያን እዚህ ያደረሳት ታላቁ የኦሮሞ ህዝብ ተጠያቂ አይደልም፡፡ በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ሰአት ከአማራ ሕዝብ ጎን መቆም፣ ለራስም ለኢትዮጵያም የመቆም ያኽል ነው፡፡               

 ኢትዮጵያ በእርግጥም ተጠሪ ያስፈልጋታል፤ መንገላታቱ በዛባት!

Filed in: Amharic