ፍቃዱ ላይ ወንጀል ከተገኘ “ከምላሴ ፀጉር ይነቀል!”
ወንድሙ ትርፌ
ፍቃዱ ማ/ወርቅን “የራሴን ያህል አውቀዋለሁ”። ጓደኝነታችንም 35 ዓመታትን የሚሻገር ነው። ትውውቃችን በጣም ልጆች በነበርንበት (የ11 ዓመት ታዳጊ ህፃናት) ከነበርንበት ጊዜ (ማለትም ከዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት 3ኛ ክፍል) የሚጀምር ሲሆን፣ ጓደኝነታችን ለራሳችንም በሚገርመን መልኩ በሙያ አጋርነት ጭምር የታጀበ ሆኖ ዛሬም ድረስ በሁለንተናዊ መልኩ አብረን አለን።
እኔና ፍቃዱ በዚህ ሁሉ አመታት ለአንድም ጊዜ ተለያይተን አናውቅም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ግዮን መጽሔትን አብረን እንሰራ ነበር። የመጽሔቱን ህትመት ለማስቀጠል (በመንግስት እየተደረጉ ባሉ በተደራራቢ ተፅዕኖዎች ከህትመት ውጪ እንዳይሆን ለማድረግ) እንዴት አይነት መስዋዕትነት ሲከፍል እንደቆየ በቅርብ አውቃለሁ። ይሄን ፅናቱን ባደንቅለትም አንዳንዴ ግን ራሱን ማየት እስካይችል ድረስ ተጨናንቆ ሳየው “ይሄ ሁሉ ለምን?” ያስብለኛል። ከጥቂት ጊዜያት በፊትም “ለምን አታቆመውም? ይህን ሁሉ ዋጋ እየከፈልክ ያለኸው ነገ አንድ ነገር ብትሆን ‘የት ነህ? እንዴት ነህ?’ ለማይል ህዝብ ነው። እና እባክህ ተወውና ለራስህና ለቤተሰብህ ትንሽ ጊዜ ስጥ” ብዬው ነበር። እርሱ ግን ተቆጣኝ። የእውነት ተናደደ። በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖም “ስለምን እያወራህ ነው? አንድ የቀረችው ግዮንም ትዘጋና በቃ የነፃ ፕሬስ ጉዟችን ታሪክ በዚሁ ያብቃ?…ግን እኔ አንተን ያስቸከርኩህ ነገር አለ?…እና ይሄ የእኔ ጉዳይ ስለሆነ ለእኔ ተውልኝ!” አለኝ። ንዴቱን ከፊቱ ላይ ባላይ ኖሮ በሙግቴ እቀጥል ነበር። ግን ተውኩት።
በርግጥ፣ ፍቃዱ ልጅነታችንን (የአፍላነት ዘመናችንን) ቀርጥፎ ከበላው “ነፃ ፕሬስ” ውጪ ህይወት ሊኖረው እንደማይችል እረዳለሁ። የፕሬስ (ጋዜጠኝነት) ሙያ አንዴ ከያዘ የማይለቅ “አንዳች ልክፍት እንደሆነ” በራሴ አውቀዋለሁ። ዛሬም ድረስ ከባድ ዋጋ እየከፈለ የሚገኘው ለዚሁ ነው። ለወትሮው “ምን ይሉኝ/ይሉኝታ” የሚያጠቃው የነበረው ጓደኛዬ፣ የግዮን መጽሔትን ህትመት ለማስቀጠል አደባባይ ወጥቶ በ”go fund me” የአገርና የፕሬስ ወዳዶችን ድጋፍ እስከ መጠየቅ የደረሰውም ጽኑ የሙያና የአገር ፍቅር ስላለው ብቻ ነው።
የአሁኑ መንግስት ከ3 ዓመት በፊትም ፍቃዱን አስሮት ነበር። አደባባይ ወጥቶ የደገፈውና በመጽሔት ርዕሰ አንቀጽ ጭምር “ይበል” ያለው ለውጥ “ጠላት አድርጎ ሊውጠው” መፈለጉን ያሳየን ከያኔ ጀምሮ ነው። ለውጡ እንደመጣ “በመጽሔት ርዕሰ አንቀጽ ለውጡን የደገፈበት ጽሁፍ ቀለሙ ባልደረቀበት” ለእስር ተዳርጎ፣ 6 ወራትን (ሊያውም ከለውጡ በኋላ እንዲመክን በተደረገ/expired ባደረገ ክስ ሳቢያ) በቃሊቲ ወህኒ ቤት አሳልፏል። የኮቪድ ወረርሽኝ ሰበብ ሆኖ የ7 ዓመት ፍርዱ ተሽሮ የተለቀቀ ቢሆንም፣ መፈታቱ ግን የማይቀር እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን። ምክንያቱም ለእስር የሚያበቃ ወንጀል ውስጥ የለበትም።
ይህ የአገር ባለውለታና የነፃ ፕሬሳችን የብዕር አርበኛ ዛሬም ለእስር ተዳርጓል። “ጥርስ ነክሰው ሲያደቡበት የከረሙ ተረኞች” በማታ አፍነው እስር ቤት ከተውታል። ጉዳዩ ነገ ከነገ ወዲያ በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም እኔ ግን በፍቃዱ ንጹህነት ላይ አንዳች ጥርጥር የለኝም።
“ወረቀት ሲበትን…ምናምን” እየተባለ ያለው ክስ የእውነት አስቂኝ ነው። ጓደኛዬ እንዲህ አይነት ተራ ወንጀል ውስጥ የሚገኝ “ሞኝ ሰው” ስላልሆነ ይሄ የትም የሚያደርስ አይደለም። ምናልባት ሌላ ወንጀል “ካላመረቱበት” በስተቀር በቀናት ውስጥ ነፃ እንደሚወጣ ጥርጥር የለኝም። ደግሞም የቱንም ያክል በሀሰተኛ ወንጀል ሊኮንኑት ቢሞክሩ አይሳካላቸውም። ዘወትር ማልዶ ጀጇ ላይ የሚንበረከክላት እመብርሃንም አሳልፋ አትሰጠውም።… ስለዚህ ይፈታል። የራሴን ያክል ጠንቅቄ የማውቀው ጓደኛዬ (ፍቄ ባሪያው) ይፈታል።