>

ስለቀድሞው አባ መላኩ ጌታነህ (‹‹አባ ፋኑኤል››) በጥቂቱ (ከይኄይስ እውነቱ)

ስለቀድሞው አባ መላኩ ጌታነህ (‹‹አባ ፋኑኤል››) በጥቂቱ

ከይኄይስ እውነቱ

‹‹የምናውቀን እንናገራለን ÷ በአየነው እንመሰክራለን፡፡›› ዮሐ. 3÷11

የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እና አገራችን ኢትዮጵያን ለዐላውያን እና ለአረመኔዎች አሳልፈው የሰጡ÷ ሳይገባቸውና ሳይገባቸው በስመ ጳጳሳት ነን የሚሉ ጉዶች (የርጉም ዐቢይ ምልምሎች የሆኑት እነ አቶ አካለ ወልድ እና ከወያኔ ጋር አብረው ቤተ ክርስቲያንን እና አገርን የከዱትን የትግራይ አኅጉረ ስብከት ‹ጳጳሳት› ተብዬዎችንና የውሸት ተሿሚዎችን ጨምሮ) የዘመናችን ‹ጸሐፍት ፈሪሳውያን› መሆናቸውን የሚገልጽ ጽሑፍ በቅርቡ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ በተጠቀሰው ጽሑፌ መጨረሻው የተቃረበው የጐሣ ፋሺስታዊ አገዛዝ እስኪወገድ ድረስ በየትኛውም መመዘኛ እነዚህ ሆዴ ይሙሉ ደረቴ ይቅላ ብለው የተነሡ የስም ‹ጳጳሳት› እና ሐሳውያን ኤጲሲ ቆጶሳት› (ገሚሶቹም መናፍቃን) በውግዘት መለየታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የቤተ ክርስቲያናችን ‹አባቶች› አለመሆናቸው ታውቆ ማናቸውንም የመንፈሳዊ አባትነት ክብር እንዳይሰጣቸው ለምእመኑ ተማፅኖ ማቅረቤ ይታወቃል፡፡

ከነዚህ ነውረኞች አንዱ በወያኔው ተሿሚ በአባ ጳውሎስ ርእሰ ሊቀ ጳጳስነት ዘመን የአሜሪካን ዶላር ይዞ በመመላለስና ደጋግሞ ደጅ በመጥናት ‹አባ› ፋኑኤል ተብሎ የተሾመው አባ መላኩ ጌታነህ አንዱ ነው፡፡ ይህን ግለሰብ ከወጣትነት ዘመኑ ጀምሮ የማውቀው የዐዲስ አበባ ልጅ ሲሆን፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ባለፈ በየትኛውም የአብነት ትምህርት ውስጥ ያላለፈ፣ ማናቸውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት በወንበር ያልተማረ፣ ቅዳሴውንም በድምጫ የሚፈጽም፣ ለስብከት የሚሆን ኮርስ በዝዋይ ሐመረ ኖኅ ቅዱስ ገብርኤል ማሰልጠኛና በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ከመከታተሉ ሌላ በአፈ ጮሌነት ምእመናን መሸንገልና ማስተባበር የተካነ፣ በተደጋጋሚ በመናፍቅነት ስሙ የተበላሸ፣ አልፎ ተርፎም (ወደ ውጭ ከመውጣቱ በፊት) ልጅ እንዳለው ከሐሜት በላይ በስፋት የተነገረበትና በመሐላ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ የቅርብ ወዳጆቹ የነበሩ ካህናት አሁንም አሉ፤ በማማለጃ በተሾመበትም ጊዜ ዕድሜው÷ ዕውቀቱም ሆነ መንፈሳዊ ብቃቱ ለማዕርገ ጵጵስና የማያበቃው ግለሰብ ነው፡፡ 

አባ መላኩ ዕድገቱም ሆነ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱ በዐዲስ አበባ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከሰንበት ትምህርት ጀምሮ የስብከተ ወንጌል ኃላፊነት ከዛም እስከ ደብሩ ምክትል አስተዳዳሪነት ከደረሰ በኋላ አሁን ወደሚገኝበት አሜሪካ ወጥቷል፡፡ በወጩ ዓለም የተከታተለው ትምህርት ስለመኖሩ መረጃ የለኝም፡፡ 

ይህ ግለሰብ ዓለምን ንቄ መንኩሻለሁ ቢልም ለሥልጣንና ነዋይ ያለው ፍትወት እንዲሁም ለአድርባይነቱ ለከተ የሌለው ነው፡፡ ቆቡና ቀሚሱም ሳይከለክለው በሽቱ ተኩነስናሽና አጥብቆ ተርእዮ (እዩኝ ባይነት) ወዳጅ ነው፡፡  ከዛሬ ሰባት ወራት በፊት ርጉም ዐቢይና አገዛዙ እና የነዚህን መለካውያን ፈቃድ ለመፈጸም በውግዘት የተለዩት ‹ጳጳሳት› እና ከቤተ ክርስቲያኗ መሠረተ እምነት፣ ቀኖና ሥርዓት ውጭ ራሳቸውን  በሾሙት ሐሳውያን ‹ኤጲስ ቆጶሳት› አማካይነት መፈንቅለ ሲኖዶስ በማድረግ፣ ሲኖዶሱን የጐሣ  ሸንጎ በማድረግና በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት በይፋ እንቅስቃሴ በጀመሩበት ሰሞን፤ በተፈጠረውም ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት በርካታ ምእመናንና ካህናት ሰማዕትነት በከፈሉበት፣ ካህናት በዐደባባይ በጥፊ እየተመቱ በተዋረዱበት እና በሺዎች የሚቈጠሩ ምእመናንና ካህናት ለእስርና እንግልት በተዳረጉበት፣ ምእመናን ከሥራቸው በተባረሩበት፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት በተደፈሩበት፣ በወደሙበትና ቅርሶች በጠፉበት ወቅት፣ አገዛዙ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የወጠነው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ባደረገው ኤምባሲ ተገኝቶ የበዓል አዳማቂ የነበረ ግለሰብ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

አሁን ደግሞ የ2016 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓል ወቅት ቤተኛ በሆነበትና በውጩ ዓለም የርጉም ዐቢይ ኦሮሙማ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ጽ/ቤት በሆነው ‹ኤምበሲ› (ዋሽንግቶን ዲሲ) ተገኝቶ የድግስ፣ ዳንኪራና አስረሽ ምቺው ተካፋይ መሆኑ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ግን የኢኦተቤክ. ‹ጳጳስ› ነኝ ብሎ ዐምሐራው ኢትዮጵያዊ የዘር ማጥፋት በዓዋጅ ታውጆበት ንጹሐን እንደ ቅጠል እየረገፉ ባለበት፣ በመቶ ሺዎች የሚቈጠሩት ደግሞ በዐምሐራነታቸው እንደ አይሁድ በማጎሪያ ካምፖች ተከማችተው የሚዘገንን ግፍ፣ ስቃይና ውርደት እየተፈጸመባቸው÷ በረሃብና በበሽታ በሚሰቃዩበትና በሚያልቁበት ወቅት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስድስቱ የጳጕሜን ዕለታት የሐዘን ጊዜ እንዲሆን ጾምና ምሕላ ማወጇ እየታወቀ፣ እግዚአብሔርን ሳይፈራ ሰውን ሳያፍር የሕዝብ ደም መጣጮችና አገር አፍራሾች ከሆኑ የአጋንንት ማኅበር ጋር ኅብረት ፈጥሮ የጽዋቸው ተካፋይ መሆኑ እንኳን የሃይማኖት አባት ተብሎ ሊያስከብረው በምድርም በወንጀለኛነት÷ በሰማይ ደግሞ በኀጢአት የሚያስጠይቀው ነው፡፡ ምንኵስናን ያህል ታላቅ ማዕርግ ይዘው ለዓለም ምውት ነን ያሉ ሰዎቸ ‹መቃብር ፈንቅለው ተነሥተው› ለጽድቅ ምውት ለኀጢአት ሕያው ሆነው መገኘታቸው በእጅጉ ይገርመኛል፤ ያሳዝነኛልም፡፡ የእነ አባ እንጦንስና መቃርስ የተከበረ ምንኵስና ለዓለማዊ ሕይወት ምቾትና ድሎት የፈቃድ ወረቀት የሆነበት ዘመን ላይ መድረሳችን በእውነቱ መረገም ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ ግለሰብ ምንድን ነው የሚፈልገው? በምንኵስናው ተስፋ ቆርጦ ከሆነ ለምን ለማኅበረ ክርስቲያኑ እንቅፋትና መሰናክል ይሆናል? ያጠለቀውን ቆብና ቀሚሰ አውልቆ፣ ክርስትናውን የሚፈልግ ከሆነ ንስሓ ገብቶ ተራ ምእመን ሆኖ እኮ መኖር ይቻላል፡፡ ነዋሪነታችሁን በምድረ አሜሪካ ያደረጋችሁና በቅርብ የምታውቁት ሰዎች የሚሰማችሁ ከሆነ ምከሩት፡፡

ይህ ሕይወቱ በነውረኛነት የተሞላ ሰው ንስሓ ገብቶ ከፈጣሪው ጋር መታረቅ ሲገባው፣ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም እንዲሉ በነውር ላይ ነውር መፈጸሙን ቀጥሏል፡፡ ይህን ማንነቱን እያወቁ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በአገር ላይ እየፈጸመ ያለው ክህደትና ግፍ ዝም ማለት ከነውሩ ተባባሪ ስለሚያደርግ ለቤተ ክርስቲያኔ፣ ላገርና እልቂት ስለታወጀበት ወገኔ ስል ይህንን ምስክርነት ለመስጠት ተገድጄአለሁ፡፡

በመጨረሻም ዐባይ ከመፍሰሱ ጊዜ ከመመላለሱ አያቆምምና የዘመናት ጌታ ለርእሰ ዓውደ ዓመቱ በጤናና በሕይወት ጠብቆ ያደረሳችሁ ኹሉ የጊዜያት ባለቤትን ማመሰገን ይገባልና በሐዘን ውስጥም ብንሆን ኢትዮጵያውያን በያላችሁበት እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ የአገራቸውን አንድነት የሕዝባቸውን ህልውናና ነፃነት ለማስከበር ውድ ሕይወታቸውን እየከፈሉ ላሉት ጀግኖቻችን ታላቅ አክብሮትና ድል፤ በጀግንነት ለተሠዉት ነፍሳቸውን በቅዱሳን መካነ ዕረፍት እንዲያሳርፍልን፤ በመከራና ስቃይ ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንዲሰጥልን ጽኑ ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡ ከምኞቱና ጸሎቱ ባለፈ ደግሞ ኹላችን በተሰጠን ጸጋ የሕዝባችንን የመከራ ጊዜ ለማሳጠር አጥብቀን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

በሌላ በኩል ዘመኑ ዐዲስ እንዲሆንና ለውጥ እንድናይ ከፈለግን ዘመን በመጣ ቊጥር ብልየት (እርጅና) የሚያገኘው ሰውነታችንን ሳይሆን ልብና አእምሮአችንን አድሰን አገራችንን ምድራዊ ሲኦል ካደረጉብን ሠራዊተ አጋንንት አፅድተን በማይነገር ስቃይ ውስጥ የሚገኝ ሕዝባችንን የሚከፈለውን ከፍለን መታደግ ይኖርብናል፡፡ የተፈጠርነው በነፃነት ለነፃነት እንጂ የማንም ባርያ ልንሆን አይደለምና፡፡

Filed in: Amharic