ድርድርና ሽግግር ከፋሺስታዊው አገዛዝ ስንብት በኋላ
(አቋምን የበለጠ ለማጽናት)
ከይኄይስ እውነቱ
የዐምሐራ ሕዝብ ጀግናም ዐዋቂም ሞልቶታል፡፡ ጨዋነት፣ ሰብአዊነት፣ ሕግና ሥርዓትን መጠንቀቅ ተፈጥሮአዊ ገንዘቦቹ ናቸው፡፡ እነዚህ የእምነት የባህል መሠረት ያላቸው ጠባያት በሩቁ ትውልድ ብቻ የሚነገሩ የታሪኩ ክፍሎች ሳይሆኑ በትውፊት ሲተላለፉ ቆይተው የአሁኑም ትውልድ በዐይኑ አይቶ በዦሮው አድምጦ የመሰከረላቸው እውነታዎች ናቸው፡፡ መገለጫው ባይሆኑም እንደማንኛውም ማኅበረሰብ ደግሞ ከውስጡ የበቀሉ እንክርዳዶች አሉ፡፡ የምድር ሐሠሮች የሆኑት ብአዴንና አብን ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
የዐምሐራው ሕዝብ ሳይወድ በግዱ ህልውናውን ለማስከበር ሲል በገባበት ጦርነት የፋሽስቱን አገዛዝ ሠራዊት አይቀጡ ቅጣት እየቀጣውና ከፍተኛ መሥዋዕትነትም እየከፈለ በአራቱም ክፍላተ ሀገራት ትግሉ ከፍተኛ እመርታ ላይ ይገኛል፡፡ ግቡ ግን እነዚህን ክፍላተ ሀገራት ነጻ አውጥቶ መቀመጥ ወይም ወያኔ የትግራይ ሕዝባችንን እንዳዋረደው በእነዚህ ቦታዎች በርጉም ዐቢይ ፈቃድ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞለት መኖር አይደለም፡፡ ይልቁንም ህልውናው ተረጋግጦ፣ ሰብአዊ መብቱና ነጻነቱ ተከብሮ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት ተንቀሳቅሶና ኑሮውን መሥርቶ፣ በአራቱም ማዕዝናት ካለው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ዜግነትን መሠረት አድርጎ፣ ባንድነትና በእኩልነት የሚኖርባት፣ የወደፊት መንግሥታችንም ከምዕራባውያን ቅጥሮች አመራር ነጻ የምትሆን ኢትዮጵያን ማረጋገጥ ነው፡፡
ነገደ ብዙነታችን እንዳለ ሆኖ፣ እምነታችን÷ባህላችን÷ ቋንቋችን÷ወግና ልማዳችን÷ ታሪካችን በእኩልነት ተከብሮ፣ ግለሰብ ዜጋ በጐሣና በነገዱ ሳይዋጥ፣ አንዱ ማኅበረሰብ በማን አለብኝነት ተነሥቶ በወርድና በቁመቴ ልክ ዝኆን ነኝ እውጣለሁ እጨፈልቃለሁ ሳይል፣ ባንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ÷ ባንድ ብሔራዊ መዝሙር÷ በወል በሚያስተሳስረን ባህል÷ እሤት፣ ታሪክና ሥነ ልቦና ተያይዘን እንደ አንድ ሕዝብ መኖር ነው፡፡ ‹‹ሕዝቦች›› የሚለው ቃል ተደጋግሞ በተነገረ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ አማካይነት ተለምዶ ምሁሩም፣ ፊደል የቈጠረውም ሆነ ማይሙ አእምሮው ታጥቦ የሚናገረው ቢሆንም፣ መሠረቱ ወያኔ ከሠላሳ ኹለት ዓመት በፊት በ‹ሕግ› እና በመዋቅር የዘረጋው የጐሣ ፋሺስታዊ የአገዛዝ ሥርዓት ሲሆን፣ ዓላማውም ከሰማንያ በላይ የሚሆነው የአገራችን ማኅበረሰብ የተለያየ ሕዝብ ነው፤ የጋራ የሆነ የእሤት ሥርዓቶች የሉትም፤ በማለት ልዩነትና መከፋፈልን ለማሥረፅ፣ በጥላቻ ላይ ተመሥርቶ ሰውነትንና ዜግነትን ለማጥፋት ፋሺስታውያኑ አገዛዞች በኢትዮጵያ ምድር ከረጯቸውና ትርጕም አልባ ከሆኑት ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች›› ከሚባሉት መርዞች አንዱ ነው፡፡
ከፍ ብሎ የተመለከተውን በመንደርደሪያነት በመያዝ፣ የዛሬው ጽሑፍ መልእክቴ አጭር ነው፡፡ ከዐምሐራው ህልውና እስከ አገራችን ኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና የሚዘልቀው ትግላችን ኹላችን በተሰጠን ጸጋ መጠን በአርበኝነት ተጋድሎ፣ ስንቅ በማቅረብ (ትጥቁን ርጉም ዐቢይ እያቀረበልን መሆኑን ታሳቢ አድርጌ)፣ እውነተኛ መረጃ በመስጠት፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ርዳታ በማድረግ፣ የሐሳብ መዋጮ በማድረግ ወዘተ. አስተዋጾአችን ሊገለጽ ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ እኔም ወንድማችሁ በየጊዜው እንደማደርገው ትግሉን የሚመሩት ወገኖቼ – መነሻና መድረሻውን፣ ተልእኮውን፣ ዓላማውንና ግቡን ዐቅደው እየመሩት እንደሆነ በመረዳት – ፋሺስታዊው አገዛዝን በሚመለከት የያዙትን ጽኑ አቋም ትክክለኛነት የሚያጠናክር ሐሳብ እነሆ ለማለት ነው፡፡ ይኸውም የዐምሐራው ግዛት ወያኔና ኦነግ ሠፍረው ቈጥረው የሰጡት ‹ክልል› የተባለ ጋጣ ሳይሆን መላዋ ኢትዮጵያ የብሱም÷ የውኃ አካሏና የአየር ክልሏ ጭምር ነው፡፡
ለጊዜው ትግሉ እየተካሔደባቸው ያሉ ክፍላተ ሀገራትን ነጻ ማውጣት፣ ማስተዳደርና ሕዝቡ ሰላማዊ ሕይወት መምራቱን ማረጋገጥ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ አካባቢዎቹ ነጻ የሚወጡት በብላሽ ሳይሆን ጀግኖች ወገኖቻችን የሕይወት መሥዋዕትነት እየከፈሉ፣ አካላቸውን እያጡ፣ ደጀን የሆነው የዐምሐራ ሕዝብም በቀጥታ ከሚያደርገው ተሳትፎ ባለፈ በፋሺስታዊው አገዛዝ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመበትና ተቋማት÷ መሠረተ ልማቶችና ንብረት እየወደመ ጭምር ነው፡፡ በዚህ መልኩ ነጻ ያደረግናቸውን አራቱን ክፍላተ ሀገራት ለማስተዳደር ደመኛ ጠላታችን የሆነውን ፋሺስታዊ አገዛዝ ቡራኬ በጭራሽ አያስፈልገንም፡፡
ትግሉ ዳር የሚደርሰው በዐዲስ አበባ እና ወያኔ ኦሮሚያ ባለው የኢትዮጵያ ግዛት ላይ ተወስኖ አልሞትኹም የሚለውን ፋሺስታዊ አገዛዝ በማስወገድ ኢትዮጵያን ከጥፋት ማዳን ሲቻል ነው፡፡ ድርድር ሽምግልና የሚሉ ወሬዎች የሚሰሙት የመጨረሻ እስትንፋሱን ለማራዘም እየቃተተ ካለው ፋሺስታዊ አገዛዝ፣ ደጋፊዎቹና ሊለወጡ ፈቃደኛ ካልሆኑና ስሌታቸው ሆዳቸው/ጥቅማቸው ከሆኑ አድር ባዮች ነው፡፡ ባገርና ሕዝብ ላይ የማይጠገን ጥፋት ካደረሰና የፈጸማቸው ወንጀሎች ለምድርም ሆነ ለሰማዩ ከከበደ ፋሺስታዊና አጋንንታዊ ኃይል ጋር መነጋገር አገርና ሕዝብን ማጥፊያ ሸምቀቆ ባንገት ማስገባት ነው፡፡ ይህን ደግሞ በአእምሮው ያለ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊያደርገው አይፈቅድም፡፡ የርጉም ዐቢይ አገዛዝን በሽምግልና ወይም በድርድር ስም ላንድ ቀን ዕድሜውን ማራዘም አገራችንን እስከማጣት ሊያደረሰን የሚችል ግዙፍ ታሪካዊ ስሕተት መፈጸም ይሆናል፡፡ ይህን ከፈጸምን በኋላ የሚደረግ ጸጸት፣ ልቅሶም ሆነ ጩኸት እንደ ርእሰ መጻሕፍቱ አባባል የማይጠቅም ከንቱ ነው፡፡
ስለሆነም ዐምሐራው ኢትዮጵያዊ የትግሉን ምዕራፍ አንድ እያጠናቀቀ የቀረውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን በማስተባበር መላ ኢትዮጵያን ከጐሣ ፋሺስታዊው አገዛዝ አላቅቆ የኢትዮጵያን ህልውናና አንድነት ወደሚያስከብርበት ኹለተኛው ምዕራፍ መሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ይገኛል፡፡ ከፋሺስታዊ አገዛዝ፣ በውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ ደጋፊዎቹ፣ ምውታን ከሆኑ ‹ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራት› ከንቱ መግለጫ (ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ እየደረሰበት ሳለለው ወገናችን ያሳዩት ኀዘኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ) እንዲሁም ኃያላን ነን ከሚሉ ከባዕዳን መንግሥታት የሚሠነዘሩ አደናጋሪ ሐሳቦች ሳያዘናጋን መነሻችን የሆነውን የዐምሐራ ሕዝብ ህልውና እና መድረሻችን የሆነውን የኢትዮጵያ ህልውናና አንድነት ወደ ማረጋገጥ የሚደረገው ግስገሳችን መቀጠል ይገባል፡፡ ውድ ጀግኖቻችንና አመራሮቹ ሰማዩ ከእኛ ጋር ነውና ሳትጠራጠሩ በያዛችሁት አቋም ጸንታችሁ ቀጥሉ፡፡
ድል ለዐምሐራው÷ ድል ለኢትዮጵያ÷ ድል ለእውነትና ለፍትሕ!!!