ዶክተር አክሎግ ቢራራ፣ ያባይ ግድብ ካማራ ሕዝብ ሕልውና ይብልጣልን?
መስፍን አረጋ
ዶክተር አክሎግ ቢራራ የኢትዮ 360ውን አቶ ሐብታሙ አያሌውን ለመውቀስ ሲል “ያልተገታ ምላስ አማራውን ይጎዳዋል” በሚል ጋጠወጣዊ ርዕስ በከታተበው ጽሑፍ ላይ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፏል። መልዕክቱም ያባይ ግድብን በተመለከት ያማራን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለማጥፋት ቆርጦ ከተነሳው ከጭራቅ አሕመድ ጋርም ሆነ ከሌላ ከማናቸውም ቡድን ጋር እወያያለሁ የሚል ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ ዶክተር አክሎግ ቢራራ “አራተኛው የግድብ ሙሌት ስኬታማ እንዲሆን ዐብይ አሕመድ ገንቢ ሚና ተጫውቷል” በማለት በላዔ አማራውን ጭራቅ አሕመድን ያመሰግነዋል።
ስለዚህም ዶክተር አክሎግ ቢራራን “ያባይ ግድብ ካማራ ሕዝብ ሕልውና ይበልጣልን?” ብሎ መጠየቅ ግድ ነው። ዶክተር አክሎግ ቢራራ በጽሑፉ የነገረን ደግሞ ያባይ ግድብ ሙሌት ካማራ ሕዝብ ሕልውና እንደሚበልጥበት ነው። አለያማ ያማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሙቶ ከተቀበረ በኋላ ዐባይ ተገደበ አልተገደበ ላማራ ሕዝብ ምን ይተክርለታል?
ዶክተር አክሎግ ቢራራ ላማራ ሕዝብ ሕልውና ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ያለውን ፋኖውን አቶ ሐብታሙ አያሌውን “አለማወቁን አያውቅም” በማለት ሊያንኳስሰው ሞክሯል። ስለዚህም አዋቂውን ዶክተር አክሎግ ቢራራን “ያባይ ግድብ የሚገኝበትን ቤንሻንጉል ጉሙዝን ሙሉ በሙሉ ካማራ ሕዝብ ለማፅዳት የጭራቅ አሕመድ ጭራቃዊ መንግስት ጠንክሮ እየሰራና አመርቂ ውጤት እያገኘበት እንደሆነ ሽመልስ አብዲሳ በግልፅ መናገሩን አታውቅምን?” ብሎ መጠየቅ የግድ ነው።
ዶክተር አክሎግ ቢራራ “አለማወቅን ማወቅ ራሱ እውቀት ነው” የሚባለውን ሶቅራጥስ ከኑብያውያን የሰረቀውን ብሂል የፈረንጅ ብሎ ጠቅሷል። ይህን ሲጠቅስ ግን “ሌባ ጣትህን ወደሌላው ስትቀስር፣ ዐራቱ ጣቶችህ ወደራስህ ይቀሰራሉ” የሚለውን ተመሳሳይ ብሂል የዘነጋው ወይም የማያውቀው ይስመስልበታል።
ዶክተር አክሎግ ቢራራ “ለ50 ዓምታት ለኢትዮጵያ ተሟሙቻለሁ” በማለት ራሱን በራሱ ከፍ እያደረገ፣ በወያኔ መንግሥት ከፍተኛ በደል የደረሰበትን፣ ባሁኑ የሞት ሽረት ወቅት ላማራ ሕዝብ ሕልውና በከፍተኛ ደረጃ እየተሟሟተ ያለውን ፋኖውን አቶ ሐብታሙ አያሌውን “የቀደመውን የህውሃት ሴራውን ስኬታማ ለማድረግ” በማለት በወያኔ ተላላኪነት ሊፈርጀው ሞክሯል። ይህ ፍረጃ የሚጠቅመው ደግሞ ጀግናው ሐብታሙ አያሌው በፅኑ እየታገላቸው ያለውን፣ ያማራ ሕዝብ የሕልውና ጠላቶች የሆኑትን ወያኔና ኦነግን እንደሆነ ለዶክተር አክሎግ መንገር አያስፈልግም።
ስለዚህም ዋናው ጥያቄ ዶክተር አክሎግ ቢራራ ለምን ተተቸሁ በሚል ሰበብ ለጀግናው ለሐብታሙ አያሌው ያለ ስሙ ስም መስጠት ለምን አስፈለገው የሚለው ነው፣ በተለይም ደግሞ ላማራ ሕዝብ ወሳኝ በሆነው ባሁኑ የሞት ሽረት ወቅት።
ያልተገራ ምላስ የሚያስብለው ዶክተር አክሎግ ቢራራ አቶ ሐብታሙ አያሌውን በወያኔነት ለመፈረጅ መሞከሩ እንጅ፣ አቶ ሐብታሙ አያሌው ከጭራቅ አሕመድ ጋር መዋጋት እንጅ መወያየት አያስፈልግም በማለት ዶክተር አክሎግን መተቸቱ አይደለም። ያማራን ሕዝብ የሕልውና ትግል እጅጉን የሚጎዳው እንደ ሐብታሙ ያሉትን ያማራ ሕዝብ ጀግኖች ስም ለማጥፋት መሞከር እንጅ፣ እነ ዶክተር አክሎግ ቢራራን መተቸት አይደለም። ዶክተር አክሎግ ቢራራ ግን “አትንኩኝ የሹም ዶሮ ነኝ” እያለን ነው። የየትኛው ሹም?
መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com