ፀረ-ኢትዮጵያዊው በሐሳዊ ሰባኪነት ሲገለጥ
ከይኄይስ እውነቱ
እንደ ኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከአራቱ የዓመቱ ክፍላተ ዘመናት መፀው በሚባለው ነፋሻማ ወቅት የሚውለው ንኡስ ክፍለ ዘመን (ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ድረስ ያለው) ሰሙነ/ዘመነ ጽጌ በመባል ይታወቃል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመዘገበው ይህ ዘመን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ልጇን ወዳጇን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን ይዛ ከቤተልሔም ወደ ምድረ ግብጽ የተሰደደችበት ወቅት ነው፡፡ በቅዱስ ትውፊት (በቃል ቅብብሎሽ) እንደተላለፈልን ደግሞ በዚህ ዘመን ከልጇ ጋር ኢትዮጵያን ጎብኝታ አገራችንን በዐሥራትነት የተቀበለችበት ሰሞን ነው፡፡
መሠረታዊ ምክንያቱ ይለያይ እንጂ ላለፉት ግማሽ ምዕት ዓመታት ኢትዮጵያውያን በዓላውያን አገዛዞች ስደተኛና ተቅበዝባዥ ሆነው እንደ ጨው ዘር በዓለም ተበትነው ይገኛሉ፡፡ ባገር ቤት ያለውም በተለይም ዐምሐራው ገሚሱ ተገድሎ ገሚሱ በገፍ ተፈናቅሎ ረሃብና የኑሮ ውድነት እየጠበሰው በገዛ ምድሩ ስደተኛ ሆኖ አልሞትሁም ብዬ አልዋሽም እያለ የቁም ሞት የመሰለ ኑሮ እየገፋ ይገኛል፡፡ የስደቱ ዕጣ ፈንታ ከገጠማቸውና አገር ከቆመችባቸው ዐበይት ዓምዶች ዋነኛዋ የኢኦተቤክ ትገኝበታለች፡፡
ኢትዮጵያ አገራችን በኢኦተቤክ አማካይነት ‹ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠውን ሃይማኖት› ተዋሕዶ ክርስትናን በ34 ዓ.ም. በቀደምትነት ከሐዋርያት ተቀብላ፣ በሥርዓት የተደራጀ አገልግሎቱን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምራ ላለፉት ኹለት ሺሕ ዓመታት ባለማቋረጥ ወልድ ዋሕድ እያለች በማስተማር የምትገኝ፣ ብሉያትን ከሐዲሳት አስማምታና አዋሕዳ በቅዱሳን ሊቃውንት ተርጕማና አመስጥራ ቃለ እግዚአብሔርን ስትመግብ የኖረች፣ የብቻዋ በሆነውና አጥንትን በሚያለመልመው ልዩ ያሬዳዊ ዜማዋ ስትሰብክ የኖረች፣ ከፊደል እስከ ትምህርት÷ ከሕግ እስከ ሥርዓተ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሰጠችና ያስተዋወቀች፣ መሠረትና ጉልላቷ ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ በየዘመናቱ የተነሡ የውስጥና የውጭ ጠላቶች በርካታ ፈተናና መከራ ቢያጸኑባትም ተቋቁማ ያለፈች ‹ሀገር-አከል› ተቋም ናት፡፡ አንዳንዶች ኢትዮጵያ እምነትን ተቀብላ ሲባል ከእሥራኤል ተቀብላ የመጣች ይመስላቸዋል፡፡ የተቀበለችው ከራሱ ከባለቤቱ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ሐዋርያው ይሁዳ እንደተናገረው ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠውን ሃይማኖት ነው የተቀበለችው፡፡
በአምላክ ወልደ አምላክ ክርስቶስ፣ በእመ አምላክ ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከመባረኳ በተጨማሪ እንደ ደመና የከበቧት በምድራችን የበቀሉና ኢትዮጵያን መርጠውና ተልከው እንዲሁም አምባ መጠጊያ በዓት ያደረጓት አእላፍ ቅዱሳን (እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ፣ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ተስዓቱ ቅዱሳን ወዘተ.) በኪደተ እግራቸው የባረኳት፣ የቃል ኪዳኑ ታቦት፣ ግማደ መስቀሉ፣ በሌሎችም የብሉይና የሐዲስ ኪዳን አምላካዊ አሻራዎች የታተመች የቃል ኪዳን ምድር ናት፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ እንደ ሀገርም ትልቋ ቤተ መቅደሳችን ናት ብንል ስሕተት የለውም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ እምነቱን ካገሩ አንድነትና ህልውና ነጥሎ አያይም፡፡ አገሩ ስትኖር አምልኮቱን በነጻነት ይፈጽማልና፡፡
ከፍ ብሎ የተመለከተውን በመግቢያነት ያነሣሁት የጽሑፌ ዓላማ ስለ ነገረ ሃይማኖት በስፋት ለማተት ሳይሆን በተለያዩ ‹እምነቶች› ሽፋን በውስጥም በውጭም ከሚሸረቡ ሴራዎች እንድንጠነቀቅና በነፍስም በሥጋም እንዳንጎዳ ቆም ብለን እንድናስብ/እንድናሰላስል ነው፡፡
በተቀደሰችው የኢትዮጵያ ምድር ፋሺስታዊ የጐሣ ሥርዓት በሕግና በመዋቅር ተክሎ አገራችንን እና ሕዝቧን የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ ባደረገውና አሁን በቀጠለው አገዛዝ ቀደም ብሎ የወያኔው አለቃ መለስ የቤት ባሪያ በመሆን፣ ርጉሙን መለስ በእግዚአብሔር ቸርነት ስንገላገል ደግሞ በኢትዮጵያ የሥልጣን መንበር ላይ በአሻንጉሊትነት ተቀምጦ በሱ የመጨቆኛ ‹ጨፈቃነት› ሕዝብንና አገርን ሲበድል የነበረውን ነውረኛና በበርካታ አገራዊ ወንጀሎች ተጠያቂነት የሚፈለገውን ኃይለማርያም ደሳለኝን በሚመለከት አንድ ኹለት ቃላት ለመናገርና ኢትዮጵያን ያዋረደና ሕዝቡን ለመከራ የዳረገ ሁሉ በጊዜው ጊዜ በሕዝብ አስተያየት ፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን በፍትሕ አደባባይ መፋረዳችን እንደማይቀር ለማስታወስ ነው፡፡ የወጋ ቢረሳ የተወጋ መቼም አይረሳምና፡፡ አንዳንድ የዋሆች እንደዚህ ዓይነቱን አስተሳሰብ የቂም በቀለኝነት ይመስላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በባሕርይው መሐሪና ይቅር ባይ እንደሆነ ኹሉ ባንፃሩም እውነተኛ ፈራጅ ሠሪ ቀጪ ፍርድ አደላዳይ ነው፡፡ እስከ መስቀል ሞት ያደረሰው በአዳም ተገብቶ የአዳምን ጥፋት ክሶ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ እንደሆነ ክርስትናው ያስተምረናል፡፡ ያለ ሕግና ፍትሕ የሚጸናና የሚቆም አገርና ኅብረተሰብ የለምና፡፡
ወያኔና ውራጆቹ በኢትዮጵያ ምድር ያሰፈኑት ሕግ አልባነትና ልቅ የሆነ ተጠያቂነት ያለመኖር ባህል ዐምሐራው የራሱን ህልውና ቀጥሎም ያገርን አንድነትና ህልውና ካረጋገጠ በኋላ እንደሚለወጥ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እስከ መቼ ከአቧራ ላይ ተነሥተው አቧራቸውን በሕዝብና ባገር ላይ የሚያራግፉ ዱርዬዎች መጫወቻ ትሆናለች? ኢትዮጵያውያን ባንድነት ተነሥተን ከዚህ የጥፋት አዙሪት ልንወጣ ይገባል፡፡ የአገር ምልክት ሰንደቅ ዓላማ አትያዙ ዝም፤ በዓላትን አታከብሩም ዝም፤ ልጆቻችን ያለ ፍላጎታቸው ለዚያውም በባዕድ ፊደል ኦሮምኛ እንዲማሩ በፖለቲካ ውሳኔ ሲገደዱ ዝም፣ ብሔራዊ ቋንቋችን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ክፍል ሲታጠፍ ዝም÷ በኹለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችም ከ10ኛ ክፍል በላይ እንዲቆምና ከ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሲወጣ ዝም፤ ባጠቃላይ የትምህርት ሥርዓታችን ትውልድና አገር ገዳይ ሲሆን ዝም፤ ጥቂት የማይባሉ የግል ት/ቤቶች ለንግድ ዓላማ ብቻ ተቋቁመው ሲዘርፉን ዝም፤ ለመሆኑ ምን ዓይነት ትውልድ ነን ባርነትን ገንዘባችን ያደረግን፡፡ ይሄ ትዕግሥት አይደለም፡፡ ፍጹም ፍርሀትና አላፊነት መጉደል ነው፡፡ በተለይም በዐዲስ አበባ ከተማ የምንኖር ኅብረት ያልፈጠረብን ወላጆች (ገሚሱ ከአገዛዙ ጋር በዝርፊያ የተሳሰረ፤ ገሚሱ በወላጅ ኮሚቴነት ተሰይሞ ከዘራፊዎች ጋር ተባባሪ፤ ገሚሱ ጥቂት ጥሪት ዘርፎም ይሁን ሠርቶ ስለያዘ የትምህርትንም ጉዳይ በገንዘብ ብቻ የሚፈታ የሚመስለው፤ ገሚሱ ተበድሮ ተለቅቶ ልጆቹን ት/ቤት ቢልክም በቸልተኝነትና ያለ ዕውቀት ልጆቹን የማይከታተል፤ ዓይነቱ ብዙ ነው)፡፡ ልጅ ማሳደግ ሆዱን መሙላትና ት/ቤት መስደድ ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን፡፡
ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና በቅርቡ ወንድማችን መምህር ፋንታሁን ዋቄ በወንድማችን አበበ በለው
ኢሕአዴግ የሚባለው አጋንንታዊ ቡድን በኢትዮጵያ በሠለጠነበት ባለፉት ከሠላሳ በላይ በሆኑ ዓመታት የእምነት ተቋማት የወንበዴዎች ዋሻ መሆናቸው በእጅጉ ያሳዝነኛል፤ ይገርመኛልም፡፡ ጭንጋፉ ኃይለማርያም (አይገርማችሁም ይሄ ፀረ-ማርያም ታላቁን የእመቤታችንን ስም ተሸክሟል) አስቀድሞ የደቡቡ ኢትዮጵያ ክፍል ፕሬዚዳንት ሆኖ፣ ኋላም የላንቲካ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብሎ ባገርና በሕዝብ ላይ ብዙ ወንጀሎችን – ከግድያ እስከ ግዙፍ ዝርፊያ – ፈጽሟል፡፡ ይሄ የአገርና የሕዝብ ማፈሪያ የሆነ ርጉም ግለሰብ የትኛውንም እምነት መከተሉና አልፎም ‹ሰባኪ› መሆኑ መብቱ ቢሆንም ይሉኝታና ኃፍረትን ጥሶ ብጤዎቹን ሰብስቦ በአጋንንታዊ ዝላይ ሲያጓራ መስማት እንደ ሰው የደረስንበትን ዝቅጠት ያሳያል፡፡ ማንም በኢትዮጵያውያዊነቱ የሚያምን ሰው በዚህ ወንጀለኛ ሰው ጩኸት ታድሞ የወንጀሉ ተባባሪ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ ነውረኛ ሕሊና ቢኖረው ኖሮ ኮሽታ ሳያሰማ ንስሓ ገብቶ ለፈጸማቸው ወንጀሎች ፍርዱን በትዕግሥት መጠባበቅ ይገባው ነበር፡፡ አስቀድሞ የሌለውን ሥልጣን ለርጉም ዐቢይ ካስረከበም በኋላ በለመደው የቤት ባርያነቱ ተልእኮ ተሰጥቶት ለኦሮሙማው ኃይል ሲላላክ እንደነበረ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አሁን ደግሞ ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥሮ፣ ራሱን በ‹ሰባኪነት/ፓስተርነት› ሰይሞ፣ በ‹እምነት ዋሻ› ውስጥ ወሽቆ ሲዘል ማየት የነውረኛነት ጥግ ነው፡፡ ይህ የሌጌዎን ማደሪያ የሆነ ሰው ከራስ ጠጕሩ እስከ እግር ጥፍሩ የዘር ፖለቲካ ውስጥ ሲቡካካ ከርሞ፣ በሐሳዊ ሰባኪነት ሲገለጥ ማየት ታላቅ ፌዝና ስላቅ ነው፡፡ ጉድ በል ሸዋ! የሚያሰኝ ነው፡፡
አሁንም ደግሜ እላለሁ፡፡ ማንም ሰው የሌላውን መብትና ነጻነት እስካልተጋፋ ድረስ እንጨት ጠርቦ ድንጋይ አለዝቦ ያሻውን ስያሜ ሰጥቶ ‹አምላኬ› ነው ብሎ የማምለክ ነፃነት አለው፡፡ አምልኮት በጋራ ቢፈጸምም እምነት የግል ጉዳይ መሆኑንም በሚገባ እረዳለሁ፡፡ በዚህም አንድ ግለሰብ የሚከተለው አምልኮ በሥጋም በነፍስም የሚያመጣውን ውጤትም ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የአምልኮ ነጻነቱ ግዑዝ ለሆኑ እንጨትና ደንጊያ በመገዛቱ በሌሎች ዘንድ የጣዖት አምላኪ መባሉን አያስቀረውም፡፡ ዋቄ ፈታውን የባዕድ አምልኮ ተከታይ እንደሚያሰኘው ሁሉ፡፡ ለባህል ጠቃሚና ጎጂ እንዳለው ሁሉ ለ‹እምነትም› እንዲሁ ዘላለማዊ መንግሥት የሚያስወርስ ጠቃሚ እና በነፍስና በሥጋም ጎድቶ ወደ ጥልቁ ገሃነም የሚሰድ ጎጂም አለ፡፡
የክርስትና እምነት ምድራዊና ሰማያዊ ሕይወትን ይመለከታል፡፡ አገራዊ ልዩ ጠባይ እንዳለው ኹሉ ድንበር ዘለል ዓለም አቀፋዊም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጋር ስንመጣ የኢኦተቤ ከእኅት አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በክርስትና ስም ከሚጠሩ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በእጅጉ ትለያለች፡፡ ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ያልተቋረጠ የ5ሺህ ዓመታት ታሪክ አላት፡፡ በብሉያቱም ሆነ በሐዲሳቱ ከአርባ ጊዜ በላይ መነሣቷ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገር ለመሆኗ ሌላ ማስረጃ ነው፡፡ በሦስቱም ሕግጋት (በሕገ ልቦና ወይም ሕሊና/በሕገ ኦሪት/በሕገ ወንጌል) በአምልኮተ እግዚአብሔር ለመኖሯ ርእሰ መጽሐፉና ሕያው አሻራዎች (ርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን፣ ርእሰ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም፣ ጣና ቂርቆስ፣ መርጡለ ማርያም እና ብርብር ገዳማት) አሁንም ምስክር ሆነው ይገኛሉ፡፡ የቅዳሴው፣ የማኅሌቱ፣ የበዓላት አከባበር፤ ባጠቃላይ ከልደት እስከ ሞት ያላት መንፈሳዊ ሥርዓት በእጅጉ የተለየ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይም የቅዱስ ትውፊት መሠረት ያለው ነው፡፡ እዚህ ጋር ስስ ተደርጎ የሚቆጠር፣ እንደ አይነኬ የሚታይና አንዳንዶችን ደስ የማያሰኝ እውነታ ለመናገር እፈልጋለሁ፡፡ በእምነት ጉዳይ ላይ የዘመኑ የፖለቲካ ትክክለኛነት የሚባል ሐሳብ ቦታ የለውም፡፡ ባንፃሩም በምዕራባውያኑ መሪነት በዓለም ላይ ነግሦ የሚታየው ለዘብተኝነት (liberalism) የሚባለው አስተሳሰብ በእምነትም ቦታ ካገኘ ውሎ አድሮአል፡፡ ይሄ በተዋሕዶ ቦታ የለውም፡፡ በመሆኑም ማስታመም ትክክል አይሆንም፡፡ አጠር ባለ አገላለጽ እምነት በእግዚአብሔር የተገለጠውን እውነት (ሃይማኖት) ሳይጠራጠሩ መቀበል ነው፡፡ ያም ሃይማኖት አንድ መሆኑና ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠ ስለመሆኑ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ይሁዳ ጽፈውልናል፡፡ የነፍስ ዕረፍት የምናገኝባትና በእርስዋም እንድንመላለስ የታዘዝነው መልካሚቱ መንገድ (ሃይማኖት) የቀደመችዋ እንደሆነች ደግሞ ከማሕፀን ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ የተባለው ነቢዩ ኤርምያስ በትንቢት መጽሐፉ መዝግቦታል፡፡ ክርስትናውን እንከተላለን የምትሉ ወገኖች ራሳችሁን በዚህ ሚዛን ውስጥ አስገብታችሁ ብታዩ መልካም ይመስለኛል፡፡
በኢትዮጵያ ዐውድ ስለ ተለያዩ እምነቶች ስናነሣ በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ብለን ልንጠራ የምንችለው የኢትዮጵያ ርትዕት (ኦርቶዶክስ) ተዋሕዶ ሃይማኖት እና የኢትዮጵያ ነባሩ የእስልምና ሃይማኖትን ብቻ ነው፡፡ ካቶሊክ ብሎ የኢትዮጵያ፣ ፕሮቴስታንት (አእላፍ የሆኑትን ክፍፍሎች ጨምሮ) ብሎ የኢትዮጵያ የሚባል የለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ ሰዎች ግን ይከተሉታል፡፡ ማንም የማይሰጣቸውና የማይነሣቸው መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ እምነቶች የኢትዮጵያ ካልሆኑ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እሤቶች ይገዳቸዋል ለማለት በእጅጉ እቸገራለሁ፡፡ እነዚህ እምነቶች ሥሪታቸው መለካዊ (የአገዛዞችን ፈቃድ ለመፈጸም የተቋቋመ) ነው፡፡ ዶግማና ቀኖናቸው ሳይቀር፣ ባህሉም ይዘቱም ዛሬ የእጅ ሥራቸውን/ፍልስምናቸውን የሚያመልኩቱ፣ የሰው ልጅ የተገኘው ከዝንጀሮ ነው የሚሉቱ፣ ዓለም አቀፋዊውን ሥርዓት ጉልበት/ጡንቻ ትክክል ነው (might is right) በሚለው አጋንንታዊ አስተምሕሮ የሚመሩቱ የአውሮጳና የአሜሪካኖቹ ነው፡፡ በተለይም ናዚያዊ የሆነው የጀመርን እና ፋሺስታዊ የሆነው የጥልያን ዓላማ ማራመጃ እንዲሆኑ ታስበው የተዘጋጁ ‹ካልእ (ልዩ እንግዳ) ክርስትና› ናቸው፡፡ በመሆኑም ብዙዎች በዕውቀትም ሆነ ያለ ዕውቀት የነጮቹ ተልእኮ ተሸካሚዎች ናቸው፡፡ ዛሬ እንደ ‹ብልጽግና ወንጌል› መንግሥታዊ የ‹ፖለቲካ ሃይማኖት› የተደረገው ዋቄ ፈታ/‹እሬቻ› ባዕድ አምልኮ ስለሆነ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚታይ አይደለም፡፡ ‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?›› የሚለውን በነቢዩ ኤርምያስ የተነገረውን የእግዚአብሔር ቃል እናስተውል፡፡ በየዋህነት እውነት መስሎን፣ ባለማወቅ ተታለን ወይም በድፍረት ለሥጋዊ ጥቅም ስንል ያጠለቅነውን የነጮች ‹ድሪቶ› አውልቀን እንጣለው፡፡ ይህን የምለው ከእገሌ እምነት የእገሌ ይበልጣል ወይም ትክክል ነው በሚል የውድድር መንፈስ ሳይሆን በሥጋም በነፍስም ስለምንጎዳበትና የእግዚአብሔር ባርያ እንሆናለን ብለን ሳናስበው የፍጡራን የነጮች ባርያ ሆነን በመገኘታችን ነው፡፡ ለሰማያዊው አልመን ምድራዊ ሆነን እንዳንቀር ሥጋት ስላለኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያና የኢኦተቤ በነጮቹ ጥርስ ውስጥ የገባን በሥላሴ አርዓያና መልክ የተፈጠረ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው የሚለውን መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት ይዘን በመገኘታችንና ይህንኑ በተግባር በዓድዋ በማሳየታችን ነው፡፡
ዛሬ መነሻቸውም መዳረሻቸውም ይሄ ጠፊ አላፊ ክፉ ዓለም የሆነ፣ ‹እምነት መሳይ› ማታለያዎችን (ከባዕድ አምልኮ እስከ ሐሰተኛ ክርስቶሳውያን) በቅልውጥ/በተውሶ የያዙ በውስጣቸው ግን የጀርመን ናዚዝም እና የጥልያን ፋሺዝም ፍልስምናዎችን ዓላማ አስፈጻሚዎች በየዘመናቱ ወዳገራችን ገብተው ንጹሕ የ‹ስንዴ› ማሳ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ አረም ክህደትና ጥርጥር በመዝራትና በእንክርዳድነት በማብቀል የተቀደሰችውን ምድር ከማርከስ እስከ ማጥፋት እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ ርጕም ዐቢይና ኦነጋዊ ግብረ አበሮቹ÷ አሽከሩ ኃይለማርያምን ጨምሮ ዓለም አቀፉን አጋንንታዊ ተልእኮ ለማስፈጸም የሚያገለግሉና አገልግሎታቸው ሲያበቃ የሚጣሉ ተራ ‹መሣሪያዎች› (‘mere disposable item’) ናቸው፡፡ በተቀደሰው ስፍራ ርኵሰትን የምታይ አንባቢ ሆይ አስተውል!!! ኢትዮጵያውያን እናስተውል!!! ማንም እንደ አህያ ዦሮ አይጎትተን፡፡
ድል ለዐምሐራ ፋኖ!!! ድል ለኢትዮጵያ!!! አምላከ ኢትዮጵያ አገራችንን ከኃይለ አጋንንት ይታደግልን፡፡ ማስተዋሉን ይስጠን፡፡