>
5:30 pm - Sunday November 2, 3851

የጐሣ ፋሺስቶች የተቆጣጠሩት ቤተ መንግሥት እና ቤተ ክህነት! 

የጐሣ ፋሺስቶች የተቆጣጠሩት ቤተ መንግሥት እና ቤተ ክህነት 

ከይኄይስ እውነቱ

የጐሣ ፋሺስቶቹን ከቤተ መንግሥቱ በዐምሐራ ሕዝባዊ ፋኖ ማስወገድ፤ 

የጐሣ ቤተ ክህነቱን (ሲኖዶሱን) በመድኃኔ ዓለም ‹‹ጅራፍ›› ማጽዳት ይኖርብናል፡፡

የእምየ ምን ይልክን ቤተ መንግሥት ልቡሰ ሥጋ አጋንንት እየተፈራረቁበት ካረከሱት ግማሽ ምእት ዓመት አለፈ፡፡ በጐሣ፣ በንዋይ፣ በሐሰት፣ በቅጥፈት፣ በብልግና፣ በምድራዊ ነውሮች በሙሉ ተመስሎ ባገራችን የተንሠራፋው አጋንንት ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያልነካው የለም፡፡ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ኢትዮጵያችን ያለ ደም ግብር ውላ ያደረችበት ጊዜ የለም፡፡ 

1/ በተቀደሰችው ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አልቦ እግዚአብሔር ማለትን፤ ያለ ፍርድ ደም ማፍሰስን (የሰው ሕይወት መቅጠፍን)፤ መንግሥታዊ ሽብርን እና በወንጀሉም በዐደባባይ የሚፎክርና ፍጹም ተጠየቂነት የሌለበት የነውር ባህል ደርግ የተባለ የደናቁርት ወታደሮች አገዛዝ ጀመረው፡፡ ከጠላት ጥልያን በማይተናነስ መልኩ ኢትዮጵያ የምትኮራባቸውንና ለዓለም የሚተርፉ፣ በምእት ዓመት አንዴ የሚገኙ የሲቪልና የወታደር መሪዎችን፣ በትርያርክን ጨምሮ የቤተ ክህነት ሊቃውንትን እምሽክ አድርጎ በማጥፋት፤ በሥጋም በነፍስም አራቁቶ፤ ሕዝቡን ኹሉ አስተካክሎ የደሀ ደሀ በማድረግ፤ ላገራችን ሰሜናዊ ጫፍ (መረብ ምላሽ) መገንጠል ምክንያት በመሆን እና ከሱም በእጅጉ ለከፉ አውሬዎች አሳልፎ በመስጠት ዘመነ ደርግ ተደመደመ፡፡ በዚህ የ17 ዓመታት የጥፋት ዘመን ውስጥ ከደርግ ጋር እኩል ተጠያቂ በመሆን ላገር ውድቀትና ለሕዝብ ጕስቁልና ተጠያቂ የሆነው በጥራዝ ነጠቅ መልኩ የኮሚኒስት ድርሳን አነብናቢ የነበረው እና ጎራ ለይቶ ሲጨራረስ የነበረው፣ የጥላቻና የመጠላለፍ ፖለቲካ ተክሎ አሁንም ድረስ አገራችንን የሚያምሰው ‹‹ያ›› የሚባለው ነውረኛ ትውልድ ነው፡፡ አረመኔያዊው የደርግ አገዛዝ በቀጥታ የጐሣ ሥርዓት ተብሎ ባይፈረጅም ወያኔና ኦነግ በሕግና በመዋቅር በተከሉት የጐሣ አገዛዝ መሥፈርት እንለካው ቢባል የኦሮሞዎች አገዛዝ ነው፡፡ በተለይም አመራሮቹና አንድ ዓይነት ርእዮተ ዓለም እንከተላለን የሚሉት የፖለቲካ ድርጅቶቹ አመራሮችና አመዛኙ አባላት ኦሮሞዎች በመሆናቸው፡፡

2/ መቼም ሽግግራችን ካንዱ አጋንንታዊ ኃይል ወደ ከፋው ሌላ አጋንንታዊ ኃይል በመሆኑ የደርግን ውድቀት ተከትሎ በኢትዮጵያችን ምድራዊ የሲኦል በርን ብርግድ አድርጎ የከፈተ የትግሬ ወያኔ የጐሣ አገዛዝ ተተካ፡፡ ነባር ከሚባለው የአገራችን ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሥነ ልቦና፣ ባጠቃላይ የእሤት ሥርዓቶች ጋር ሁሉ በመፋታት፣ ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት ወዲህ የተመሠረተች አድርጎ በሁሉም መስክ ዐዲስ የፈጠራ ትርክት በመጻፍ፣ በተለይም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን እና የዐምሐራውን ሕዝብ ላገሪቱ ኹሉ ችግሮች ተጠያቂ በማድረግ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ለማጣላትና ለመለያየት በእጅጉ የሠራና ተግባራዊ ያደረገ የባለጌዎች አገዛዝ ነው፡፡ እነዚህ ወያኔ የሚባሉ ነውረኞች ሥልጣናቸውን ያሟሹት ደርግ በተበላሸ አስተዳደሩና ምክር አልሰማ በማለቱ ምክንያት በሻእቢያ ለመገንጠል የተመቻቸችውን አባቶቻችን መረብ ምላሽ (ጠላት ጥልያን ኤርትራ ያላትን) ብለው የሚጠሩት ግዛታችንን ለማስገንጠል ወታደራዊ እገዛ ከማድረግ ጀምሮ በዓለም ታሪክ ውስጥ ባልተመዘገበ ሁናቴ ኤርትራን ነፃ አገር እንደሆነች ዕውቅና ስጡልኝ ብሎ ለተ.መ.ድ. አመልክቶ ከኢትዮጵያ መለየቷን ያረጋገጡ የከሀዲዎች ስብስብ ነው፡፡

በደርግ የተጀመረው ፍጅት ተጠናክሮና ጐሣዊ መሠረት ይዞ ዐምሐራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በበደኖ እና አርባ ጉጉ የተጀመረው እልቂት እስካሁነ ሰዓት ቀጥሏል፡፡ ሥር በሰደደ ጥላቻ ላይ ተመሥርቶ የማስመሰያ የዘር ‹ሕገ መንግሥት› እና የዘር መዋቅር በመትከል ለልዩነት፣ ለመከፋፈል ብሎም ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሠረቱን የጣለ ቆሻሻ አገዛዝ ነው፡፡ ለዘመናት የዘለቀውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት አፈረሰ፤ ማኅበራዊ ትስስርን በጣጠሰ፡፡ በጐሣ፣ በእምነትና በኢኖሚያዊ ጥቅሞች ላይ የተመሠረቱ ጊዜ ጠብቀው የሚፈነዱ አደገኛ ቦንቦችን በየቦታው ቀበረ፡፡ የትግራይ ሪፐብሊክን እመሠርታለሁ ብሎ የተነሣው የወንበዴዎች ቡድን በታሪክ አጋጣሚ ታላቋ ኢትዮጵያ እጁ ላይ ስትወድቅ ለሃጩን እያዝረበረበ ለከት ለሌለው ዝርፊያና ስግብግብነት ግሪሳዎቹን አሰማርቶ አገራችንን ግጠው ግጠው ዐጽሟን እንዲቀር አደረጉ፡፡ የዘረፉት የሀገር ሀብት ባሕር ማዶ ተሻግሮ ለኢትዮጵያ የማይተኙ ፈረንጆችን ጭምር ለመግዣ ዋለ፡፡ 

እርስ በርሳቸው ተደጋግፈው ወይም አንዱ ለሌላው አለኝታ ሆነው የቆዩቱን ክፍለ ሀገራቱን ወይም የአስተዳደር ግዛቶቹን አጥፍቶ ‹ክልል› የተባለ የከብቶች ጋጣ የመሰለ የአትድረሱብኝ አጥር በገረ፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተለይም ዐምሐራው በገዛ ሀገሩ ባዕድና ባይተዋር ሆነ፡፡ ይሄ ‹ክልል› የእነ እገሌ ብቻ ስለሆነ ውጣልን ተብሎ ተሳዳጅ ተቅበዝባዥ ሆነ፡፡ አልፎ ተርፎም ለእስር፣ ለእንግልትና ለሞት ተዳረገ፡፡ በፈለገው የኢትዮጵያ ግዛት እንኳን መርጦና ተመርጦ የአስተዳደር ጉዳይ ውስጥ ተካፋይ ለመሆን ይቅርና ትዳር መመሥረት፣ ወልዶ መሳም፣ ዘርቶ መቃም፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ባጠቃላይ ሠርቶ መኖር ተከለከለ፡፡ መላ አገሪቱ የዜጎች ወህኒ ቤት ሆነች፡፡ በተለያየ መንገድ ያጠፉት በሚሊዮን የሚቆጠር ዐምሐራ ኢትዮጵያዊ የደረሰበት አይታወቅም ተብሎ ባደባባይ ባገዛዙ ሰዎች ተነገረ፡፡ ባልተደራጀ ተቃውሞ ብዙዎች የአገዛዙ ሰለባ ሆኑ፡፡ ሕዝብ ግብር የሚከፍልባቸው መደበኛ የሚዲያ ተቋማት ላገዛዙ ፕሮፓጋንዳና ኹለተኛ ተፈጥሮው ለሆነው ቅጥፈት መሣሪያ ሆኑ፡፡ ማኅበራዊ የዲጂታል ሚዲያዎች ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት እየፈሰሰባቸው ካገር ውስጥ እስከ ውጭ አገርን የሚያፈርሱ ቅጥረኞች መናኸሪያ ሆነ፡፡ ፍትሕ ርትዕ ሙሉጭ ብለው ጠፉ፡፡ ሕግ የጐሠኞቹ ገረድ ደንገጥር ሆነች፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ነገሠ፡፡ በሰው ጭንቅላት የሚታሰብላቸው ደናቁርት ካድሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ፊደል ቈጥረናል÷ አንዳንዶችም ‹ምሁራን› ነን የሚሉ ቊጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ግለሰቦች የአድር ባይነትን የመጨረሻ ጥግ አሳዩን፡፡ በውስጥም በውጭም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያኖች ተዋረዱ፡፡ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ ብሔራዊ መለያዎቿን ማንሣትና ለነዚህም ጥብቅና መቆም ነውር ብቻ ሳይሆን ባልተጻፈ ሕግ የሚያስወነጅል፣ የሚያሳስርና የሚያስገድል ሆነ፡፡ መንግሥት ብለን የምናውቀውና አክብሮት የምንሰጠው አካል የተራ ዱርዬዎች፣ ወሮበሎችና ማጅራት መቺዎች መሰባሰቢያ ቡድን ሆነ፡፡  ትግሬ ወያኔ የተከለው እጅግ ኋላ ቀር ሥርዓት ኢትዮጵያን የዓለሙ ኹሉ መሳቂያን መሳለቂያ አድርጎ፤ የትግራይ ሕዝብን ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጥሎ÷ ኢትዮጵያዊነትን እስከነ መልካም እሤቶቹ አስጥሎ÷ ራሱ በፈጠረው ኦሕዴድ በተባለ የለየለት ጭራቅ (ሞንስተር) እና ኮትኩቶ ባሳደገው ውላጅ ባርያ (አጋንንት) አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ትግራዮችን በተለይም ወጣቶችን ዓላማ በሌለው ጦርነት ማግዶ፣ ቅርስ አውድሞና አስወድሞ፣ የዐምሐራና የአፋርን ሕዝብ በጭካኔ ፈጅቶ÷ ግምቱ ይህ ነው ለማለት የሚያስቸግር ንብረትና ተቋማት አውድሞ፣ በሥጋም በመንፈስም ወንድሙ ከሆነው የዐምሐራ ሕዝብ ጋር አቃቅርተው፣ በመጨረሻም ወያኔ ራሱ ለፈጠረው ጭራቅ (ሞንስተር) ለውላጅ ባርያው ተገዝቶና ተምበርክኮ ሳይቀበር በድኑን ይገኛል፡፡ ይሄ በድኑን የሚከላወስ ጥራጊ ስብስብ በፈጠረው ጭራቅ አማካይነት ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ምእመን የነበረውን የትግራይ ሕዝብ ከእናት ቤተ ክርስቲያኑ ነጥሎ፣ የጐሣ ቤተ ክህነት አደራጅቶ የመለካውያንን ፈቃድ በሚፈጽሙ ከሀድያንና መናፍቃን÷ አልፎ ተርፎም ኢትዮጵያን ‹ኤልዛቤል› እያሉ በባለጌ አንደበታቸው የሚናገሩ ሐሰተኞች ‹መነኮሳትና ካህናት› አሳልፈው በመስጠት የመጨረሻ መሸሸጊያውን ሃይማኖቱን አስጥለውታል፡፡ ዛሬ የትግራይ ሕዝብ በሥጋም በነፍስም ባዶ ሆኖ ቀጠና/ጠኔን፣ በሽታንና ሰቆቃን ገንዘቡ አድርጎ ከሞቱት የማይሻል ሕይወት እየመራ ይገኛል፡፡ በእኔ እምነት የፈለገውንም ያህል ፕሮፓጋንዳ ይሠራበት፣ የፈለገውን ያህል ማስፈራሪያና መከራ ይድረስበት ዛሬ ላይ ከዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላ ወያኔን የሚደግፍ የትግራይ ተወላጅ (ከድርጅቱ አመራርና አባላቱ በስተቀር) ካለ በማይድን የአእምሮ ሕማም የተያዘ መሆን አለበት፡፡ መቼም መላው የትግራይ ሕዝብ የዚህ ቆሻሻ ድርጅት አባል ነው ለማለት አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ደመኛ ጠላቱ የሆነውን ወያኔ ሕወሓት የተባለ አጋንንታዊ ቡድን ከዛሬ 5 ዓመታት በፊት ባደረገው መራራ ትግል ያስወገደው ቢመስልም እንደ እፉኝት ልጅ ኦሕዴድ በተባለው ውላጅ ባርያው አማካይነት ድምጥማጡ ጠፍቶ የተከለው አገር አጥፊ የማስመሰያ የጐሣ ‹ሕገ መንግሥት› እና መዋቅር አንድም ሳይነካ እጅግ በከፋ ጭካኔና ጥላቻ ተጠናክሮ ‹ብል/ጽ/ግና› የሚል ከሰይጣናዊ አምልኮ የተቀዳ ስም ይዞ በኦሕዴድ/ኦነግ ፊታውራሪነት እንዲቀጥል ሆኗል፡፡

3/ ሦስተኛውና ባለፉት አምስት የግፍ ዓመታት ኢትዮጵያን የሰው ‹ቄራ› ያደረገው የወያኔ ውላጅ ኦሕዴድ ሰይጣናዊ አገዛዝ ነው፡፡ ሁሉም የኔ ነው (ኬኛ) በሚለው የአልጠግብ ባይነት የመስፋፋት ‹ፖሊሲው› በጉልበት ይገባኛል ያለለው የኢትዮጵያ ግዛት የለም፡፡ ይህም ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ ኢትዮጵያ በተለይም ዐምሐራው ቅኝ ገዝቶኛል የሚል ስሁት ትርክት ፈጥሮ በዐምሐራውና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ ሥር የሰደደ ጥላቻ ይዞ የተነሣና የኢትዮጵያዊነት መዓዛ አላቸው የሚላቸውን እምነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ቅርስና እሤቶች ያለምንም ማመንታት ጨርሶ በማጥፋት በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ወያኔ የፈጠረለትን ‹ኦሮሚያ› የሚባል ግዛት አገር ለማድረግ የሚያልም/የሚቃዥ የወራሪዎች ቡድን ነው፡፡ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ይህ ፈጽሞ የመንግሥትነት ጠባይ የሌለው ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ አሳዳጊው ወያኔ በጣለለት መሠረት ላይ ቆሞ አንዳች የእምነት፣ የተፈጥሮ ሕግ፣ ሰው ሠራሽ ሕግ፣ የሞራል ሕግ፣ ሰብአዊነት የሚባሉ ልጓሞች ሳይዘው ኢትዮጵያን ጨርሶ ለማጥፋት ቀን ከሌት እየሠራ ይገኛል፡፡ የዚህ ጥፋት ቡድን አባላት ናዚ ጀርመን በፈጠረው ልዩ የሆነ የፕሮቴስታንት ዓይነት ግርፎች የሆኑ የኦነግ መሥራቾችን እና ‹ብል/ጽ/ግና› የሚባል የሰይጣን አምላኪዎች የሆኑ ኦሕዴድ የሚባሉ ገርባና ገበሮ የሆኑ ጥቂት በሽተኛ ‹ዲቃላዎች› ሲሆኑ፣ በወረራ ገርባና ገበሮ በተደረገው አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ስም በመነገድና ሕዝቡን ለጥፋት ተልእኮአቸው መያዣ በማድረግ፣ እንደ ወያኔ ትግሬ የኦሮሞን ማኅበረሰብ ከቀሪው ኢትዮጵያ እየነጠሉት ይገኛሉ፡፡ ይህ ጭራቅ ቡድን ዓይነተኛ መለያው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በአፍም በመጣፍም እንዲሁም በተግባር ማዋረድ ሲሆን፣ በተለይም አገር አሉኝ የምትላቸውን ኢትዮጵያውያን (ዜግነት የቀየሩትን ጨምሮ) የሃይማኖት ሰዎችን ሳይቀር ማምከንና አልከስክሶ ዳግም እንዳይንሠራሩና በሕዝብ እንዲተፉ ማድረግ ነው፡፡ የዚህ እኩይ ቡድን መሪ ርጉምና ዕቡይ ዐቢይ ከስሙ በተቃራኒ ሥር በሰደደ የትንሽነት በሽታ ተጠቂ የሆነ፣ በከፋ የአእምሮ ደዌ የተያዘ፣ መመለክ የሚፈልግ፣ ፍጹም ከሰብአዊነት የተራቆተ ማኅደረ ሰይጣን ሲሆን፣ ያለ ደም ግብር የማያድር፣ የዕውቀትና የልምድ ጦመኛ ሆኖ በብልጭልጭና ጊዜያዊ ነገሮች የተጠመደ ምናምንቴ ነው፡፡ ይህንን በሽተኛና ብልሹ አገዛዙን የማያስወግድ ኅብረተሰብ ራሱ ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡ 

ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ከሰው በታች ያደረጉንን፣ የዓለሙ ሁሉ መሳቂያ መሳለቂያ ያደረጉንን፣ ተዋርደው ያዋረዱንን እነዚህን ሰይጣናዊ አገዛዞች ተሸክመን፣ ባርነትን ገንዘባችን አድርገን የኖርን ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንደ ሕዝብ የከሸፍንና ከታሪክ ተጠያቂነትም የማናመልጥ ትውልዶች መሆናችንን ልናምን ይገባል፡፡ 

የቤተ መንግሥቱን ጉዳይ በዚህ ልግታና ወደ ቤተ ክህነቱ ስንመጣ የአገዛዞቹ አቋምና ዓላማ ለድቀቱ አንድ ዐቢይ ምክንያት ቢሆንም፣ እኔም ሆንሁ ሌሎች በቅርቡ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን ማኅበራትና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች እንዲሁም ግለሰቦች ዳጎስ ባለ ጥናትና በመግለጫም መልክ ደጋግመን ለማሳሰብ እንደሞከርነው ዋናው ጥፋቱ ያለው ባጠቃላይ በቤተ ክህነቱ በተለይም በሲኖዶስ አመራሮች ሲሆን፣ ችግሩና ተግዳሮቱ በእያንዳንዱ አድባራትና ገዳማት አብዛኛዎቹ አገልጋዮች ሥር በሰደደ መልኩ የተንሠራፋ ነው፡፡ 

አ/ በሺዎች እና ሚሊዮኖች መማለጃ ሰጥቶና ተቀብሎ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነኝ ከሚል ሰው መንፈሳዊነትን መጠበቅ ጅልነት ነው፡፡ ክህነቱን አፍርሶ ቤተ መቅደስ በድፍረት ከሚገባ ሐሰተኛ ካህን መንፈሳዊነት መጠበቅ ላም ካልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናል፡፡ ከምእመናን በልመና ጭምር የሚገኝ ገንዘብ ዘርፎ እና በንቅዘት ተጨማልቆ በተገኘ ሀብት የላመ የጣመ ከሚበላ÷ የሞቀ የደመቀ ከሚለብስ፣ በሊሞዚን ከሚንፈላሰስ፣ በልዩ ልዩ ሽቱዎች ከሚኩነሰነስ፣ በዘመናዊ አፓርትመንት ውስጥ ከሚኖር፣ ለዓለም ምውት መሆኑን ረስቶ በንቅዘት በተገኘው ገንዘብ የዘመናዊ ሕንፃዎች÷ የዘመናዊ መኪኖች፣ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ከሆነ፣ ዘመድ አዝማዶቹን ባገር ውስጥና በውጭ በቤተ ክህነቱ መዋቅር ውስጥ በኃላፊነት ሰግስጎ ጳጳስ ሊቀ ጳጳስ ነኝ፣ ቆሞስና ባለ ልዩ ልዩ መዓርግ ነኝ ከሚል ሐሳዊ መነኩሴ መንፈሳዊነት ወይም የእረኛነት ተልእኮውን እንዲወጣ መጠበቅ ከኵርንችት የበለስ ፍሬን መጠበቀ ይሆናል፡፡

በ/ አሁን ባሉት በትርያርክ ሲነገር እንዳዳመጥነው፤ ከሁለተኛው የኢኦተቤክ በትርያርክ ጀምሮ የተደረገው ሲመት ችግር ስላለበት አሁን ላይ ተነሥቶ ማስተካከል አይቻልም የሚል አንደምታ ያለው አቋም እጅግ አደገኛ ከመሆኑም በላይ በጥፋቱ ላይ ጥፋት እየቀጠለ እንዲሔድ መንገድ የከፈተ ነው፡፡ በዚህም ንግግር ራሳቸውን ጨምሮ አሁን ድረስ ያለው የኤጲስ ቆጶሳት ሲመት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ መሆኑን እየመሰከሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አሁን የሚገኙበትን መንፈሳዊ አቋም ልብና ኩልያትን ለሚፈትን ልዑል እግዚአብሔር ትተን በሲመታቸው የመጀመሪያ ዓመታት የአባ ጳውሎስን የዘረኝነት ፈለግ በመከተል ለወያኔ አድረው ቤተ ክህነቱን (እስከ ገጠር አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን) እንደ ቤተ መንግሥቱ ካንድ አካባቢ በመጡ መንፈሳዊነቱም ሆነ ዕውቀቱ/ሙያው በሌላቸው ‹ካድሬዎች› መሙላታቸው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ዘረኝነቱ ቀደም ብሎ የሚታይ ቢሆንም አፍጦ አግጦ የታየው፣ ዝርፊያና ንቅዘቱ ተራራ አኽሎ የገዘፈው፣ መንፈሳዊነቱ ሙልጭ ብሎ የጠፋው አሁን ባሉትና በአባ ጳውሎስ በትርያርክነት ዘመን መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ገ/ ባለፉት ሠላሳ ሦስት ዓመታት ዓላውያን አገዛዞች ካደረሱባት ግዙፍ ጥፋቶች በተጨማሪ የኢኦተቤክ እውነተኛ አገልጋይ በማጣት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናና እምነታቸውን ለቀው ፈልሰዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጠባቂ እረኛ በማጣት ተቅበዝባዥ ሆነዋል፤ በርካታ መንፈሳውያን ቅርሶቿን በዝርፊያ አጥታለች፡፡

ደ/ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ቤተ ክርስቲያን የተባሉ ምእመናን የክርስቶስ አካሉ÷  የቤተ ክርስቲያን ‹አልባሳት› ናቸው፡፡ ፈርጦቿ ወይም ጌጦቿ ከሆኑት ምእመናን ውጭ ቤተ ክርስቲያንን ማሰብ አይቻልም፡፡ ዛሬ ቤተ ክህነቱን በሚመሩ ‹አባቶች› እና ምእመናን መካከል የአባትና የልጅ ግንኙነት የለም፡፡ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በተግባር አያገባችሁም ተብለናል፡፡ ቤተ ክህነቱ ምእምናንን ወተቷ ከማይነጥፍ ጥገት ላም ነጥሎ አያይም፡፡ ምእመናንን የሚያስታውሰው ‹ሙዳየ ምጽዋት› ሲጎድልበት ብቻ ነው፡፡ የኢኦተቤክ ለአንድ ሺሕ ሰባት መቶ ዓመታት በልመና የዘለቀችው ለምንድን ነው? ራሷን ችላ ለምን ለሌሎች ለመትረፍ አልቻለችም? በርግጥ ምስካየ ኅዙናን ሆናለች? ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለተፈናቀሉት/ለተሰደዱት ደራሽ ሆናለች? በቂ ሀብት ስለሌላት ነው? ብዙ ጥያቄዎችን ማንሣት ይቻላል፡፡ ይዘቱን ለማየት ዕድል ባላገኝም ከትናንት እስከ ዛሬ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች (መንፈሳዊ/ቀኖናዊ፣ አስተዳደራዊ/ዘመናዊ የሥራ አመራርና የፋይናንስ ሥርዓት፣ መዋቅራዊ ወዘተ.) ዘመኑን በዋጀ መልኩ በጥልቀት ተጠንተውና ተሰንደው እስከነ መፍትሔ ሐሳቦቻቸው ሊቃውንትን በያዙት የቤተ ክርስቲያን ማኅበራት ለቤተ ክህነቱ ከቀረቡ ውለው አድረዋል፡፡ የጎደለውን ሞልቶ የጠመመውን አቅንቶ ተግባራዊ ለማድረግ ግን አልተፈለገም፡፡ ለምን? በቀደሙት ዘመናትም ማኅበረ ቅዱሳን መንፈሳዊውን ከሥጋዊው ዕውቀት አጣምረው በያዙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች አማካይነት በዘመናዊ አሠራሮች ረገድ ድጋፍ ለመስጠት ያደረጉት ሙከራ ባብዛኛው ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ለምን? ለንቅዘት/ለብልሹ አሠራር በሩን ያጠብባቸው ይሆን?

ሀ/ ላለፉት ሠላሳ ሦስት ዓመታት ክርስቲያኖች (ካህናትና መነኮሳትን ጨምሮ) ሌሎችም ዜጎች በተለይም ዐምሐራው በወለጋ፣ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በጠራው የኢትዮጵያ ክፍል፣ በጎጃሙ መተከል፣ በሻሸመኔ፣ በሲዳሞ አዋሳ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በእምነታቸውና በነገድ ማንነታቸው ሲታረዱ፣ አድባራትና ገዳማት ከነ ቅረሶቻቸው ሲወድሙ ምን አደረገ? ቤተ ክህነቱ ደሀ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል ድምፁን አስምቷል? የጥምቀት ልጆች በዐላውያን ሠራዊት ሲጨፈጨፉ የት ነው ያለው? ዜጎች ‹መንግሥት› ነኝ በሚል አካል እንደ ጠላት ጦርነት ታውጆባቸው በአየር በምድር በጭካኔ ግፍ ሲፈጸምባቸው ምን አለ? ሰሞኑን ለጉድ የጎለተው ቤተ ክህነት የጐሣ ሲኖዶስ አባል በሆኑ አንድ ካድሬ ሊቀ ጳጳስ አንደበት ክርስቲያኑን እና እስላሙን ዜጋ አንድ አድርጎ የጨፈጨፈውን ሠራዊት ለመገሠፅ ድፍረት አጥተው ሲቀባጥሩ አስተውለናል፡፡ ሕዝቤን አትግደሉ ብሎ የህልውና ትግል የሚያደርገውን ሕዝባዊ ፋኖ ሲወቅሱ ተደምጠዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ኢትዮጵያን ለማጥፋት ቀን ከሌት የሚተጋውን አረማዊ አገዛዝ እንዲቆይልን እንጸልያለን ሲሉ ተስምተዋል፡፡ የፍርሃታቸውና አድርባይነታቸው ልክ ለከትም የለው፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ‹መነኩሴ› ለዓለም ምውት ናቸው? እውነቱን ለመናገር ሀብት ንብረቱ ነው ያሳሳቸው? ወይስ ሲመነኩሱ በፈጣሪ ፊት ቃል የገቡትን መከራ መስቀሉን መሸከም ሰቀቃቸው? ጉድ በል ሸዋ! ደግነቱ ይህ ከንቱ ጸሎት ከደመና በታች ቀሪ ነው፡፡ 

ወ/ ዛሬ የኢኦተቤክ መንፈሳዊ ሲኖዶስ የላትም፡፡ እንደ ቤተ መንግሥቱ የጐሣ ሸንጎ እንጂ፡፡ ሲኖዶሱ ባመዛኙ የመለካውያንን ፈቃድ ፈጻሚዎች የሆኑ ካድሬ ጳጳሳት ስብስብ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በፈጸሙት ተግባር ከክርስቲያን ማኅበር አንድነት ተወግዘው/ተለይተው ክህነታቸውን ያጡ፤ አንዳንዶቹ ነውራቸውን ደብቀው ክህነታቸው ጥያቄ ውስጥ ያለ፤ አንዳንዶቹ ለሀብት ለንብረት ባርያ ሆነው አገልግሎታቸውን ጨርሰው የዘነጉና ‹መቃብር ፈንቅለው ለሥጋዊ ምቾት የተነሡ›፤ አንዳንዶቹ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ቀይረው እንደ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ስደተኞች የኃያላን መንግሥታትን ጥበቃና ዋስትና ፈላጊዎች፤ አንዳንዶቹ በሃይማኖት የማይመስሉን የተሐድሶ ፕሮቴስታንት እምነት አራማጆች፤ ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ እነዚህን ጉዶች ይዘን ‹አባቶች›፣ ‹ቅዱስ ሲኖዶስ› እያልን ራሳችንን ማታለል የለብንም፡፡

የፋሺስቶችና የናዚስቶች ዓላማ አራማጅ የሆኑ ዐላውያን አገዛዞችን ተሸክመን አገር ልናጣ እንደተቃረብን ሁሉ፣ ይህንን ቤተ ክህነትና የዘር ሲኖዶስ ተሸክመን ኢትዮጵያ ከቆመችባቸው አዕማዶች ዋነኛ የሆነችውን የኢኦተቤክንን እናዳናጣ ሥጋት አለኝ፡፡ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ቤተ መቅደሱን መሸጫ መለወጫ ያደረጉትን አይሁድ፡- የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የሌቦች፣ የወንበዶችና የቀማኞች ዋሻ አደረጋችኋት በማለት ጅራፍ አበጅቶ ከመቅደስ እንዳስወጣቸውና ቤተ መቅደሱን እንዳጸዳ ሁሉ፤ ዛሬም የቅድስናውን ስፍራ የጐሣ ፖለቲካ ሸቀጥ መሸጫ መለወጫ፣ የንቅዘት መናኸሪያ፣ የርኵሰት መፈጸሚያ ያደረጉትን ጠራርገን የምናወጣበት ‹ጅራፍ› ያስፈልገናል፡፡ ይህ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዐምሐራ ፋኖ ጋር ሲቆምና የበኩልን ሲወጣ፤ በቤተ ክህነቱ በኩል ደግሞ ምእመኑና እውነተኛ ካህናትና ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ያገባናል ብለን በሙሉ ኃይል የድርሻችንን ስንወጣ ብቻ ነው፡፡

የጐሣ ፋሺስቶችን ከቤተ መንግሥቱ የማስወገዱ ተግባር የተሟላ የሚሆነው ቤተ ክህነቱንም ከዘመኑ ‹ጸሐፍት ፈሪሳውያን› በክርስቶስ ‹ጅራፍ› ጠርገን ስናባርር ይሆናል፡፡ በመሆኑም የጐሣ ፋሺስቶቹን ከቤተ መንግሥቱ በሕዝባዊ ፋኖ በማስወገድ፤ የጐሣ ቤተ ክህነቱን (ሲኖዶሱን) በመድኃኔ ዓለም ‹‹ጅራፍ›› በማጽዳት ለኢትዮጵያችን ዐዲስ ምዕራፍ መክፈት ያስፈልጋል፡፡

ድል ለኢትዮጵያ!

ድል ለዐምሐራ ሕዝባዊ ፋኖ!

መድኃኒት ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የኢትዮጵያን ምጧን ያሳጥርልን፡፡

Filed in: Amharic