>

ተሐዝቦት!?

ተሐዝቦት!?

ከይኄይስ እውነቱ

‹ተሐዝቦት› ባልሁት ርእሰ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥቂት ትዝብቶቼን ወይም የተሰማኝን ሐሳቦች ለአንባቢ ለማካፈል በማሰብ የተጻፉ ናቸው፡፡ ተሐዝቦት የሚለውን ቃል ነፍሳቸውን ይማርልንና ከማከብራቸው ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት ከአምባሳደር ብርሃኑ ዲንቄ የተዋስሁትና በእንግሊዝኛው ‹observation› የሚለውን ለመተካት የተጠቀሙበት ነው፡፡ 

1/ ‹‹ከፈተና በፊት እና ከፈተና በኋላ››፤ የሚል አንድ በቪዲዮ የተቀረፀ ዝግጅት ‹‹የኪነጥበብን በጎ ድጋፍ እያገኘ ያለው የዐምሐራ ሕዝብ የህልውና ትግል›› በሚል ርእስ እ.አ.አ. ኖቬምበር 28/2023 ኢትዮ 360 ሚዲያ ላይ በልዩ ዝግጅትነት ቀርቦ ነበር፡፡ ወንድማችን ሀብታሙ ስለ ቪዲዮው ሲናገር ‹ትንሽ ወጣ ያለ ነው› የሚል አስተያየት አስቀድሞና መርሐ ግብሩ የኪነ ጥበብ በመሆኑ ምናልባት ፈገግ የሚያስደርግ ከሆነ በማለት ለቅቆታል፡፡ ቪዲዮው በዋናነት ዒላማ ያደረገው ታሪኩን ያበላሸውና ራሱን አገራዊ ቅሌት ውስጥ የከተተው፣ በፋሺስታዊው አገዛዝ ትውልድ ገዳይ የሆነው የትምህርት ሥርዓትና ‹ፖሊሲ› አስፈጻሚ የሆነው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በእኔ ትሁት እምነት ይህ ቪዲዮ ባይቀርብ ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከፈተና በፊት በሚል የቀረበው የተማሪዎቹ ቪዲዮ ኹለት አሉታዊ መልእክት አስተላልፏል፡፡ ሀ/ ተማሪዎቹ ያቀረቡት የዝሙት ዳንስ ችግር የለውም በሚል ሌሎችንም ተማሪዎች ሊያበረታታ የሚችል መሆኑ፡፡ ለ/ ፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝና የመንፈስ አባቱ ወያኔ ሆን ብለው ትውልድ ገዳይ የትምህርት ሥርዓትና ‹ፖሊሲ› አቁመው አገርና ትውልድ ተስፋ ቢስ እንዲሆኑ አጥብቀው እየሠሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተከታታይ ዓመታት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤት እያሽቆለቆለ መጥቶ በ2015 ዓ.ም. በመላው አገራችን ከስምንት መቶ ሺሕ በላይ ተማሪዎች ተፈትነው 3 በመቶ የሚሆኑበት ብቻ ፈተናውን እንዳለፉ መነገሩ በዋናነት የአገዛዙ ብልሹነት ቢሆንም ተማሪዎቹም (ሁሉንም ባይወክል) በትጋት ከማጥናት ይልቅ ጊዜአቸውን በዋዛ ፈዛዛ በዝሙት ዳንስ በማሳለፋቸው ምክንያት ውጤት አልባ እንደሆኑ አንደምታ ይሰጣል፡፡ በነገራችን ላይ ሀብታሙም ሆነ አርቲስት ሽመልስ ይህ ቪዲዮ በሚተላለፍበት ጊዜ ሲሳቀቁ አስተውዬአለሁ፡፡ ያቺ ውብ ኢትዮጵያዊ ወጣት ገጣሚ በቀረበችበት ግሩም መርሐ ግብር የምትሳቀቁበትን መልእክት ማስተላለፉ ለምን አስፈለገ?

2/ ‹‹የተደራጁ ማኅበራት አባል ሳትሆኑ ወይም አስተዋጽኦ ሳታደርጉ መተቸት/መንቀፍ አይቻልም›› የሚለው ሐሳብ ደግሞ ቃል በቃል ባይሆንም ‹‹ወሳኝ ምዕራፍ የዐዲስ ድምጽ አበበ በለው የአድማጮች ቀጥታ ውይይት›› በሚል ርእስ በዐዲስ ድምፅ ሜዲያ እ.አ.አ. ዲሴምበር 2/2023 በተላለፈ መርሐ ግብር የተደመጠ ሐሳብ ነው፡፡ ወንድማችን አበበ የተጠቀሰውን ዓይነት አንደምታ ያለው መልእክት ያስተላለፈበት ምክንያት እረዳለሁ፡፡ በዐምሐራው የህልውና ትግል የዐምሐራ ተወላጅ የሆነ ኹሉ ችሎታውና ሙያው በፈቀደለት መጠን ተደራጅቶና አንድ ወጥ ሆኖ መታገል ያለውን ታላቅ ፋይዳና የሚከፈለውንም መሥዋዕትነት እንደሚቀንሰው ከመገንዘብ የመነጨ መሆኑ አንዱ ሲሆን፤ ባንፃሩም ከትግሉ በአፍአ ሆነው፣ ተቆርቋሪ መስለው፣ አንዳንዶችም በስም ዐምሐራ ነን (በስም የሚነግዱም ስላሉ) ብለው እንደ በድኑ ብአዴን ለጠላት በባንዳነት ተሰልፈው የሚያገለግሉ በመኖራቸውና በብዙ ጥረት የተቋቋሙ አደረጃጀቶችን/ኅብረቶችን የመበተን ተልእኮ በርጉም ዐቢይ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ስላሉ ሚናችሁን ለዩ የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ጭምር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ከተሳሳትሑ እታረማለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ሐሳቡ ትእዛዝ ነክ ከመምሰሉ በተጨማሪ አንድ የዐምሐራ ተወላጅ በየትኛውም ቦታ ይኑር የዐምሐራው የህልውና ትግልን ለማገዘ በተቋቋሙ አደረጃጀቶች ላይ ትችት ከማቅረቡ በፊት በሚተቻቸው ማኅበራት ውስጥ አባል ሆኖ ተሳታፊ በመሆን ከውስጥ ሆኖ ማስተካከል/ማረም አሊያም ለትግሉ በሚችለው ዐቅም አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የሚል አስገዳጅ አንደምታ መኖሩ ትክክል አይመስለኝም፡፡ በመሠረቱ የዐምሐራ ሕዝብ የሞት ሽረት ትግል በሚያደርግባቸው በአራቱም ክፍላተ ሀገራት አንድ ወጥ አመራር ተፈጥሮ ፋሺስታዊውን የርጉም ዐቢይ አገዛዝ በማስወገድ የነፃነትና የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት የማስቀጠል ትግል ፍጻሜ እንዲደርስ የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ከርጉም ዐቢይና ደጋፊዎቹ በስተቀር፡፡ ለዚህም ትግል እያንዳንዱ ዐምሐራ በተለይ፣ ሀገር ጠል ከሆነው ከፋሺስታዊው አገዛዝ መገላገል የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ባጠቃላይ አስተዋጽኦ ይጠይቃል፡፡ የትግሉ ተሳትፎ ድርሻ በመጀመሪያው ረድፍ በመሰለፍ ደረትን ለጦር ግንባርን ለጠጠር በመስጠት የሕይወት መሥዋትነት ከመክፈል አንሥቶ ቢያንስ ለትግሉ እንቅፋት ባለመሆን ‹ዝም ማለት› ድረስ ያጠቃልላል፡፡ ወንድማችን ደጋግመህ እንዳልኸው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለ አንድ ሰው ብቻውን ትልቅ ሥራ መሥራት ይችላል፡፡ ሳይደራጁ በዕውቀታቸው፣ በችሎታቸውና በልምዳቸው ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ያሉ የዐምሐራ ተወላጆችም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ታዲያ በድርጅት ስም ለህልውና ትግሉ እንቅፋት የሚሆኑ አፍራሽ ድርጊቶችን የሚያይ ግለሰብ ስሕተቶች እንዲታረሙ ትችት ማቅረቡ ጥፋቱ ምን ላይ ነው? ላለፉት 33 ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሕዳር ተቃዋሚ የ‹ፖለቲካ ማኅበራት› ነን ያሉ ድርጅቶች (የጐሣ ፋሺስታዊአገዛዞች ሸፍጥ እንደተጠበቀ ሆኖ) አብዛኛዎቹ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በውስጣቸው የጥቅም ልዩነት፣ የሥልጣን ፖለቲካን ላገርና ለሕዝብ የተሻለ የእኩልነት ሥርዓት መፍጠርያ መሣሪያነት ከማዋል ይልቅ ተራ መተዳደሪያ በማድረግ፣ የዓላማ አንድነት ባለመኖር፣ ሕዝብን አስተባብረው ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንኳን ባለመቻል፣ ማኅበራዊ መሠረታችን ነው የሚሉትን ሕዝብና አባላቱን በመክዳት፣ ሆዴ ይቅላ ደረቴ ይሙላ በማለት ለፋሺስታዊ አገዛዝ በማደር ወዘተ. የሕዝባችንን ሰቆቃ ሲያራዝሙ ታዝበናል፡፡ ታዲያ እነዚህን በመዝገብ ብቻ ያሉ በተግባር አድራሻቸው የማይታወቁ የስም ‹ፖለቲካ ማኅበራትን› ለመተቸት ውስጣቸው መግባትና አባል መሆን ያስፈልግ ነበር? በጭራሽ! ያገራቸውና የሕዝባቸው ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳቸው ብዙ ግለሰቦች አሉ፡፡ የግድ ማኅበራዊ አንቂ የሚል ስም አያስፈልጋቸውም፡፡ ይህ ማዕርግ ከሆነ ማን እንደሚሰጠውም አላውቅም፡፡ በተግባሩ ከሚገለጽ በቀር፡፡ ፊደል የቆጠሩም ይሁኑ ምሁራን ለአገር ለሕዝብ ይበጃል የሚሉትን ከወቅታዊ ጽሑፍ ጀምሮ እስከ ጥናታዊ ጽሑፍ የማቅረብ መብት ያላቸው ይመስለኛል፡፡ መቼም አገር ቤት ያለው ሕዝብ ውጭ ያሉ የዐምሐራ ማኅበራት አባል እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ንግግራችንም ሆነ ጽሑፋችን የህልውና ትግሉን ባገናዘበ መልኩ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል የሚለውን እኔም አምንበታለሁ ተገቢ ነው፡፡

ሆኖም ከሁሉም በላይ በልባችን ልንጽፈው የሚገባን ቁም ነገር ቢኖር አመራሮችም ሆኑ ተዋጊዎች ባገር ውስጥ  በአራቱ ክፍላተ ሀገራት ያሉ የሕዝባዊ ፋኖ መሪዎች፣ የፋኖ አርበኞችና እና ራሱ የፋኖ አርበኛ የሆነውና የገፈቱ ቀማሽ የሆነው ደጀኑ ሕዝብ ነው፡፡ ቀሪው ኃይል ባገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኘው እገዛው ቢያስፈልግም ድጋፍ ሰጭ መሆኑ ላፍታ መዘንጋት የለበትም፡፡ በነገራችን ላይ የውጩ ድጋፍ ሰጭ ኃይል መኖሩና ተስማምቶ አንድ ወጥ ሆኖ ከሠራ መልካም ነው፡፡ ይህም ባይሆን ግን ደጃፉ ድረስ የመጣው ፋሺስታዊ የጠላት ኃይል የኢትዮጵያ መንግሥትና ሠራዊት ሳይሆን ፈሪ÷ አረመኔ÷ ልክስክስና ተራ ወንበዴ በመሆኑ፣ ዐምሐራው ተገድዶ የገባበትን የህልውና ትግል የራሱን ነፃነትና የአገሩ ኢትዮጵያን አንድነት በማስከበር በድል መደምደሙ የማይቀር ነው፡፡ ለዚህም ትምክህታችን ከፍ ሲል የኢትዮጵያ አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር ሲሆን፤ ዝቅ ሲል ደግሞ የፈጣሪን ቸርነት ኃይል ያደረገው÷ እውነትና ፍትሕን የያዘው የዐምሐራ ሕዝባዊ የፋኖ ኃይል ነው፡፡ ስለሆነም በውጭ የምትገኙ አደረጃጀቶች ዓለማችሁ በቅድስት ሀገር ምድር ላይ ‹ከልቡሳነ ሥጋ አጋንንት› ጋር የሚታገለው የዐምሐራ ሕዝብ ዓላማ ከሆነ ሁሉም በየኪሱ ይዞ የሚዞረውን ‹የመሪነት፣ የግል ፍላጎት/ጥቅም እና የእኔ እበልጣለሁ ፉክክር፣ የክሬዲት ሽሚያ› ከሥሩ አስወግዶ (ዕለት ዕለት በፋሺስቶች የሚያልቀውን ንጹሐን ሕዝብ፣ በአውሬዎች የሚደፈሩትን እናቶችና እኅቶች፣ የሚያልቁትን ሕፃናት፣ ሰብሉ የሚቃጠልበትን ገበሬ፣ ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉትን እውነተኛ ካህናት፣ የሚወድሙትን አድባራትና ገዳማት፤ ዒላማ የተደረጉ መስጂዶችን እና የሙስሊሙን ማኅበረሰብ የሚያገለግሉ እውነተኛ ዑላማዎች፣ ኢማሞችና ኡስታዞች በማሰብ) ወጥነት ባለው አደረጃጀት ላንድ ዓለማ ይሰለፍ፡፡ ውስጣችሁ ንቁርያ ካለ ለትግሉ እንቅፋት በሚሆንበት ደረጃና ለጠላት መሰባሰቢያ ‹አጥንት› እንዳይሆን አደራችሁን እንላለን፡፡ የፋኖ አደረጃጀት ወጥነት እየተሠራ ያለው ፋታ ከሚነሳ ጦርነት ጋር ነው፡፡ እናንተ በነፃነት ቦታ ሆናችሁ (ቢያንስ የዐምሐራ የህልውና ትግል ከተጀመረ ወዲህ) ‹ፋና› የተባለው ሙከራ ቢኖርም ለምን 50 እና 60 ሆናችሁ እንደዘለቃችሁ መድኃኔ ዓለም ይወቀው? ለማንኛውም ለትግሉ ክፍተት የሚፈጥር ድርጊት ከፈጸማችሁ የሚያሳስበው ወገን ኹሉ ሊወቅስ÷ ሊገሥፅ÷ ሊተች ይችላል፡፡ ምክንያቱም ድሉን ሊያዘገይብን የሚችሉ ማናቸውንም እንቅፋቶች የምንታገሥበት ሁናቴ ላይ አይደለንምና፡፡ ይህንን አጋጣሚ የርጉም ዐቢይ ‹ዘመዶች› ይጠቀሙበታል? ምን ጥያቄ አለው! ጥፋቱ ግን የኛ መሆኑን አንዘንጋ፡፡

3/ ‹‹ሽምግልናና የሰላም ድርድር›› በሚል በተወዳጁና አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ ዐዲሱ በዐዲሱ ሚዲያ እ.አ.አ. ኖቬምበር 27/2023 አንድ ግሩም የሆነ መርሐ ግብር ተላልፎ ነበር፡፡ በርእሰ ጉዳዩ ላይ የተጋበዙት እንግዶች በውጩ ዓለም የሚኖሩ ኹለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች – መልአከ ብርሃን ቀሲስ ታደሰ ዶጋ ከደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን (ናሽቪል ቴነሲ) እና መጋቤ ሐዲስ ልዑለ ቃል አካሉ የደብረ ቅዱሳን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ (ሲያትል ዋሽንግቶን) – ናቸው፡፡  ሁለቱም ካህናት በውይይቱ ጊዜ ባነሷቸው አብዛኞቹ ሐሳቦች የምስማማ ቢሆንም የኔ ትዝብት የሚያተኩረው መልአከ ብርሃን ቀሲስ ታደሰ ዶጋ በማጠቃለያነት በሰጡት ሐሳብ ላይ ልዩነት ስላለኝ ያንን ባጭሩ ለመግለጽ ነው፡፡ የመልአከ ብርሃን ሐሳብ እንደሚከተለው ነው፤ 

‹‹…የሚያስኬደው መንገድ ብቸኛው ሁሉን አቀፍ የሰላም ድርድር ለዛውም ደግሞ በመንግሥት የተዘጋጀ [የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን] ከሚባለው ያለፈ … ከዚያ ከፍ ያለ÷ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ መንግሥት ያልሆነና የመንግሥት የበላይ ተጽእኖ የሌለበት ሁሉንም [በኦሮሚያም ሆነ በትግራይ] ኢትዮጵያውያንን ያካተተ የሰላም ውይይት (truth and reconciliation) የሚባለው [ሆኖ]፤ … ሲኖዶሱ በዚህ ደረጃ መፍትሄ ያገኘነው ይሄ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም አገራችንም ያለችበት ሁኔታ እዚህ ደረጃ ደርሳለች፣ ይሄ እንዲሆን ነው የምንፈልገው ብለው ለኢትዮጵያ ሕዝብም ለፖለቲካ ድርጅቶችም ለዓለም አቀፉም ለአብያተ ክርስቲያናትም ለሁሉም ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታት ሁሉ ይሄንን ካቀረቡ በጣም ጥሩ ነው፡፡›› 

ሲሉ ያመኑበትን የመፍትሄ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ይህ ሐሳብ ፋሺታዊው የጐሣ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ ፈውስ ለሚያስፈልጋት አገራችን ጠቃሚ በመሆኑና በበርካታ ኢትዮጵያንም ሲነሣ በመቆየቱ በዚህ አግባብ ቢሰነዘር ማለፊያ ይሆን ነበር፡፡

ከታላቅ አክብሮት ጋር መልአከ ብርሃን ቀሲስ ታደሰ ዶጋ በውይይቱ ሲገነቡ የመጡት ሐሳብና ድምዳሜአቸው የተለያየ ይመስላል፡፡ በመንፈሳዊው ጀምረው ድምዳሜአቸው ግን ዲፕሎማሲያዊ ወይም ፖለቲካዊ ቃና አለው፡፡ ችግሩ ለምን ዲፕሎማሲያዊ ወይም ፖለቲካዊ ሆነ አይደለም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁናቴ ከፖለቲካ (በሰፊው ብያኔው) ነፃ የሆነ አስተሳሰብ የለም፡፡ ድምዳሜው ውገናን የያዘ መምሰሉ ግን ምቾት ነስቶኛል፡፡ ላብራራው፡፡

1ኛ/ በቅድሚያ ባለመድኃኒት የሚሻ በእጅጉ የታመመ አካል ራሱ መድኃኒት ሊሆን አይችልም፡፡ ሲኖዶሱ በተግባር ሦስት ቦታ ተከፍሎ ባመዛኙ በርጉም ዐቢይ ለሚመራው ፋሺስታዊ መለካውያን በማደሩ ላለፉት አምሳ ዓመታት ያላደረገውን ዛሬ በተአምር ያደርጋል ብሎ መጠበቅ ነፋስ መጐሰም ጉም መዝገን ይሆናል፡፡ ይህ ሲኖዶስ ጸሎትና ምሕላን ከመንፈሳዊ ዓላማ ውጭ ለፋሺስታዊው አገዛዝ ፋታ ለመስጠት መሣሪያ አድርጎ መጠቀሙ ምን ያህል ከመንፈስ ቅዱስ አሠራር የተራቆተ ለመሆኑ ምስክር ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃው ለአምሳ ዓመታት ሲፈጸም የቆየውን ያለፈውን ግፍና በደል ኹሉ ትተን በማለት ከእውነትና ፍትሕ ጋር በተቃራኒ ሆኖ ከአገርና ሕዝብ ጠላቶች ጋር መሰለፉን የሚያመለክተው ዓዋጅ ነው፡፡

2ኛ/ መልአከ ብርሃን በሲኖዶሱ በኩል እንዲቀርብ የተናገሩት የመፍትሔ ሐሳብ ላለፉት 5 የግፍ ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ታይቶ በማይታወቅ ሁናቴ በገዛ ሕዝቡና አገሩ ላይ ለሰማይና ለምድር የከበደ ወንጀል ሲፈጽም የቆየና እየፈጸመ ያለ፣ አስተዳድረዋለሁ በሚለው ሕዝቡ ላይ ጦርነት በይፋ ዓውጆ በሕዝብ ሀብት ድሮን ተበድሮ ገዝቶ ንጹሐንን እየጨፈጭፍ የሚገኝ፣ እናቶቻችንና እኅቶቻችንን በ‹አውሬዎች› እያስደፈረ ያላ የወሮበሎች አገዛዝ፤ ቀደም ሲልም በትግራይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖቻችንን (ሕዝቡ ለመንፈስ አባቱ ወያኔ ያለውን ጽኑ ጥላቻ በመጠቀም) ያስጨፈጨፈ፣ እናትና እኅቶቻችንን ያስደፈረ፣ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩትን አካለ ጎዶሎ ያደረገ፣ ክፍለ ሀገሩን ያወደመ፣ የትግራይ ቤተ ክህነትን ከወያኔ ጋር በመተባበር ያስገነጠለ፣ ሕዝቡን ለከፋ ረሃብና ቸነፈር የዳረገ አረመኔያዊ አገዛዝ በሥልጣን ላይ ሆኖ ‹‹ሁሉን አቀፍ የሰላም ድርድር›› ይደረግ የሚል ነው፡፡ ‹ሁሉን አቀፍ› የሚለው ቃል ፋሺስታዊውን አገዛዝ እንደሚጨምር ግልጽ ነው፡፡ ቀሲስ ለእሳት ባሕርይ ቊረት፣ ለውኃ ባሕርይ ውእየት እንደማይስማማው ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ለ‹አጋንንትም› ባሕርይ ሰላምና ድርድር አይስማማውም፡፡ ፋሺስታዊው አገዛዝም በግብሩ የአጋንንት ማኅበር መሆኑን ከበቂ በላይ አሳይቶናልና፡፡ የቤተ ክርስቲያን መምህር የሆኑት ቀሲስ ታደሰ የሰነዘሩት የመፍትሄ ሐሳብ – እግር ተወርች የተያዘው ሲኖዶስ በተአምር ቢያቀርበው እንኳን – ፋሺስታዊው አገዛዝ ጊዜ ገዝቶ እንዲያንሰራራ ዕድል ከሚሰጥና ደም እንደጎርፍ የፈሰሰበትን የሕዝብ ትግል ከሚያዳክም በቀር በጐሣ ፋሺስታዊው አገዛዝ ተፈጥሮ ምክንያት ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ልቦናዎ ያውቃል፡፡ 

ታዲያ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን፣ ዐምሐራና ኦርቶዶክሳዊነትን በማጥፋት ሌት ተቀን እየሠራ የሚገኝ ፋሺስታዊ ቡድን፣ ኢትዮጵያን በዓለም ፊት ያዋረደ÷ መሳቂያ መሳለቂያ በማድረግ ሕዝባችን ባለበት ሁሉ አንገቱን ያስደፋ የወረበሎች ቡድን ከመንግሥት ተቆጥሮ እንዲቀጥል ሐሳብ ማቅረብ መብት ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያውያን ባጠቃላይ÷ በተለይም ላለፉት አምሳ ዓመታት ሲገፋ ለኖረው የዐምሐራ ሕዝብ ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ ለአንባቢ ትቼዋለሁ፡፡ በቤተ ክህነቱ የታየው የጐሣ ክፍፍል አትላንቲክን ተሻግሮ ሥር የሰደደ ለመሆኑ ታላቅ ምልክት ይመስላል፡፡ ቀሲስ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ ለማስወገድ ‹‹የሩቢከንን ወንዝ እንደተሻገረ›› አያውቁምን? አንተኑ ነግድ ለኢትዮጵያ?

ድል ለኢትዮጵያ!

ድል ለዐምሐራ ፋኖ!

አምላከ ኢትዮጵያ አገራችን ኢትዮጵያን እኛ ከማናውቀው እሱ ከሚያውቀው ጠላቶቿ ኹሉ በሐፁረ መስቀሉ ይጠብቅልን፡፡፡

Filed in: Amharic