>

በደልን መላመድ ባርነት ነው!!!

በደልን መላመድ ባርነት ነው !!!

 አሥራደው ( ከካናዳ )

ሕሊና ሃቅ ነው፤ ሕሊና እምነት ነው፤ ሕሊና ፍቅር ነው፤ ሕሊና ማንነት ነው፤ ሕሊና ባህል ነው፤ ሕሊና ቋንቋ ነው፤ ሕሊና ለሕዝብ ዘብ በመቆም: ለአገርና ለራስ ክብር ሲሉ በአንድ ላይ አብሮ  በመነሳት ነፃ ሕዝብ መሆን ነው!!!   

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ፤ የሰብዕና ዋልታዎችን፤ አምባ ገነኖች በምፅዋት አይሰጡንም :: ጥቂቶች  ለሚጣልላቸው  ፍርፋሪ ሲሉ ፤ ሰብዕናቸውን አርክሰው ሆዳቸውን የሚያመልኩ ድኩማንን ፈጣሪ በእጅጉ ይጠየፋቸዋል::  በአምሳሉ የተፈጠሩበትን ክብር አርክሰዋልና !!   ከጽሁፉ ውስጥ የተቀነጨበ::

መንደርደርያ

 1. « A l’ instant où l’esclave décide qu’il ne sera plus esclave, ses chaînes tombent. »  Mahatma Gandhi

    ” ባርያ፤  ባርያ ላለመሆን በወሰነበት ቅጽበት፤ የባርነት ሰንሰለቱ ይበጠሳል”  መሃተማ  ጋንዲ

 1. ” un patrie sans justice est un prison”  Georges Clemenceau 

 ” ፍትህ የሌለበት አገር እንደ እስር ቤት ይቆጠራል ” ጆርጅ  ክሊመንሶ

 1. ” Le problème de notre temps n’est pas la bombe atomique, mais le cœur de l’homme.”  Albert Einstein 

” የዘመናችን ትልቁ  ችግር የአቶሚክ ቦንብ ሳይሆን፤  የሰው ልጆች ጨካኝ ልብ ነው ” :: 

አልበርት አነስታይን 

 1. ” Ne craignez jamais de vous faire des ennemis; si vous n’en avez pas, c’est que vous n’avez rien fait.”  Georges Clemenceau 

” ጠላት አፈራን ብላችሁ በጭራሽ አትፍሩ (አትጨነቁ)፤ ጠላት ከሌላችሁማ፤ ምንም የረባ ሥራ አልሠራችሁም ማለት ነው!! ”  ጆርጅ  ክሊመንሶ

መግቢያ :

 የማሰብ ነፃነት ማጣት ባርነት ነው፤ ያሰቡትን አለመናገር ባርነት ነው፤ ያሰቡትን አለመጻፍ ባርነት ነው፤ ፍትህ ማጣት ባርነት ነው፤ ከገዛ አገሩ መሰደድ ባርነት ነው፤ ተማሪው “መሬት ለአራሹ” ብሎ በደሙ የዋጀውን የመሬት ባለቤትነት መብት: ከገበሬው ነጥቆ በማፈናቀል: ለድንበር ዘለል ከበርቴዎች መቸብቸብ፤ የባርነት ቀንበርን መልሶ መጫን ነው :: ሠራተኛውን በዓለም አቀፍ ዘራፊ ኢንዱስትሪዎች፤ በገዛ አገሩ ጉልበቱን ማስበዝበዝ: ባርነትን ማስፈን ነው፤ ምሁራንን በአገራቸው ጉዳይ፤ ምሁራዊ  ተሳትፎ እንዳይኖራቸው በየምክንያቱ ማግለል: ባርነትን እንዲነግሥ ማድረግ ነው፤ ወጣቱን ለሥራ አጥነትና ለስደት መዳረግ አገርን መግደል ነው :: 

ዝምታ ባርነትን አሜን ብሎ መቀበል ነው፤ አድር ባይ መሆን ባርያ መሆን  ነው፤  ሕዝብን በገዛ አገሩ የበይ ተመልካች እንዲሆን ማድረግ: የባርነት ሥርዓትን ማስፈን ነው፤………….ወዘተ :: 

በተለይ ከአያት፤ ከቅድም አያቶቹ ነፃነትን የወረሰ ትውልድ: ባርነትን መላመድ ከጀመረ:  ሰብዕናው ይዋረዳል፤ ዕምነቱ ይጠፋል፤ ሃብቱ ይዘረፋል፤ ትውልድ ይበከላል፤ ፍቅር ይጠፋል፤ አንድነት ይፈርሳል አገር ይናዳል:: 

በየቤቱ ተወሽቀን: በፍርሃት የበረዶ ግግር ሆነን  ከመንቀጥቀጥ፤ በተናጠል እየተወራጨን ተነጥለን  ከመመታት፤ በየጎሣው እንደረጋ ውሃ ተከትረን: እያቆርን ከመሽተት፤ በአንድላይ እንደ ዓባይ ውሃ ሞልተን ገንፍለን በመውጣት፤ ግሳንድሱን ጠራርገን በማስወገድ፤ ንጹህ አየር መተንፈስና በአንድነት ወጥተን የነፃነት ፀሐይን በመሞቅ የነፃነት ሕብስት አብረን መቋደስና አዲስ ተስፋን መፈንጠቂያ ጊዜው አሁን ነው!!

ያ ካልሆነ ባርነት ይነግሣል፤ ሰብዕና ይገሰሳል፤ አገር ይሞታል፤ በወቅቱ በአገራችን ኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ይኸው ነው::

ባርያ ቆዳው ጠቆር፤ ጠጉሩ ከርደድ፤ አፍንጫው ጠፍጠፍ፤ ዓይኑ ደፍረስ፤ ሰውነቱ ደንደን፤ ……… ያለ ነው፤  ብሎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል:: 

ነፃነት በሌለበት አገር: ቆንጆዋ ውብ ኮረዳ፤ መልከመልካሙ ጎረምሳ፤ ለግላጋው ወጣት፤ እድሜ ጠገቡ አዛውንት፤ የተማረ፤ ያልተማረ፤ ወንዱ ሴቱ፤ እኔም፤ አንተም፤ አንቺም፤ እሱም፤ ገና በማህጸን ውስጥ ያለ ሕፃን እንኳን ሳይቀር፤ ሁላችንም ባርያዎች እንሆናለን:: 

ቀደም ብሎ ህወሃት ለ27 ዓመታት፤ አሁን ደግሞ የህወሃት የቀድሞ አሽከሮች (የኦህዴድና/ኦነግ) ጥምር ብልጽግና በሚል የዳቦ ስም፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያሰፈኑት ዘረኝነትና ጎሠኝነት፤ አመድ እያቦነነ አመድ የሚያለብስ ባርነት ሲሆን፤ አብሮነታችን ስለሚያስፈራቸው፤ ልዩነቶቻችንን በማራገብ: የዘረኝነት እሳት በኢትዮጵያ ውስጥ አንድደው፤ እግሮቻቸውን አንፈራጠው ፍሙን ሲሞቁ ይኸው 5 ዓመታት ሊሞላቸው ነው:: 

(የኦህዴድና/ኦነግ) ጥምር: ብልጽግና ተብዬው፤ የአዘራፊና የዘራፊዎች፤ የሙሰኞችና የሌቦች ጥርቅም፤የሸንበቆ ከዘራ ተደግፎ የቆመ አፅም በመሆኑ፤ ዜጎች ተባብረው በአንድነት ገፋ ቢያደርጉት፤ ወዲያውኑ ወድቆ የሚንኮታኮት፤ ውስጠ ነቀዘ እንጨት ነው ::  

 የባርነት አይነቶች

– የአካል ባርነት 

– የአይምሮ ባርነት

– የምቾት (የቅንጦት) ባርነት፤ 

– በውጪ አገር በስደት ያለነው፤ እራሴን ጨምሮ (ዲያስፖራ ተብሎ የሚጠራው ባርነት)

–  ቀደም ብሎ ህወሃት፤ አሁን ደግሞ (የኦህዴድና/ኦነግ) ጥምር: ብልጽግና ባርያ ያደረጋቸው ናቸው :: 

ቀደም ብሎ ህወሃት፤ አሁን ደግሞ ብልጽግና ባርያ ያደረጋቸው፤ዓይነታቸው ብዙ ነው ::  እነሱም: 

  • የስልጣን ባርያዎች፤  ከካድሬዎች ጀምሮ በጦር ሃይሉ፤ በፖሊስ፤ በሲቪል ሥራ በስልጣን ላይ ያሉ አገልጋዮች፤
  • የጎሣ ባሪያዎች፤  ቀደም ብሎ ለህወሃት፤ አሁን ደግሞ ለብልጽግና ባርያ የሆኑ የትግራይ፤ የአማራ፤ የኦሮሞ፤ የሲዳማ፤ የሃዲያ፤ የአደሬ፤ የወላይታ: የጉራጌ፤ የሱማሌ…….ወዘተ.  ወግኖቻችን ፤
  • አዲስ ደጅ ጠኚ ባርያዎች፤  ለብልጽግና  ጧት ማታ ደጅ በመጥናት ለሚቀጥለው ዝርፊያ የተዘጋጁ፤ ሕሊና ቢስ ሆዳም ባሪያዎች::
 • የምሑራን ተብዬ  ባርያዎች፤

ምሑራን ተብለው: በንዋይ ፍቅር የታወሩ፤ ድሃ ወገኖቻቸውን በመካድ፤ ቀደም ብሎ የህወሃት፤ አሁን ደግሞ፤ የብልጽግና ባርነትን የመረጡ፤ ከተለያዩ ጎሳዎች ያሉ ሲሆን፤ ከተራው ገበሬና ሠራተኛ  አፍ እየተነጠቀ በተሰበሰበ ግብር ተምረው ፤ ሳይማር ያስተማራቸውን ሕዝብ ውለታ በመዘንጋት፤ ከራሳቸው አልፈው ሌላውን ሕዝብ በማስተማርና በማደራጀት፤ ለመብቱና ለነፃነቱ በአንድነት እንዲቆም በማድረግ ፤ ለድል እንዲበቃ በማድረግ ፈንታ፤ እራሳቸው ባርነትን አሜን ብለው በመቀበል: ባርያ መሆንን የመረጡ::

ምሑራን ለሆዳቸው ሲሉ ባርያ መሆንን ሲመርጡ፤ እጅግ አሳዛኝና አጠያፊ ከመሆኑም በላይ፤ በእጅጉ አደገኛና አገር ገዳይ ነው::  

 • በውጪ አገር በስደት ያለነው (የዲያስፖራው) ባርነት፤

በፈረንጅ አገር ሠርተን በምናገኘው ገንዘብ፤ ሆዳችንን እንዳይርበው: በቂጣ ብንደልለውም እንኳን፤ የሕሊና ረሃብተኝነታችንን: በምንም ነገር ልንደልለው አንችልም::  ጧት ማታ፤ ስንሄድ ስንተኛ፤ብቻችንን ወይም ከሰው ጋር ስንሆን፤ ያሳብቅብናል፤ ሠላም እየነሳ ያስጨንቀናል፤ (ሕሊናውን ከታደልን ማለቴ ነው)::

ሕሊና አገር ነው፤ ሕሊና ነፃነት ነው፤ ሕሊና ፍቅር ነው፤  ሕሊና እምነት ነው፤ ሕሊና ማንነት ነው፤ ሕሊና ባህል ነው፤ ሕሊና ቋንቋ ነው፤ ሕሊና ሃቅ ነው፤ ሕሊና ለወገን ዘብ በመቆም ለአገር፤ ለሕዝብና ለራስ ክብር ሲሉ በአንድ ላይ አብሮ በመነሳት ነፃ ሕዝብ መሆን ነው!!!  ታዲያ እነዚህን ሁሉ የፈረንጅ አገር ቂጣ አይተካቸውም::

 • እጅግ የሚያሳስበው፤ ለ’ኛም ለልጆቻችንም የማትሆን ኢትዮጵያ፤ በዘረኝነት ሃረግ ስትጎነጎን፤ በጎሳ መጥረቢያ ስትሸነሸን፤ በድንበር ዘለል ከበርቴዎች ስትቦጠቦጥ፤ ማዕድኖቻችን ሲዛቁ፤ ደኖቻችን ሲጨፈጨፉ፤ መሬታችን ሲቸበቸብ፤ በየአቅጣጫው የአገራችን ድንበር ሲሸራረፍ፤ ኢትዮጵያዊነት እየተገዘገዘ ለጥፋት ሲቃረብ፤ ዘረኝነት ሲነግሥ፤ ጎሰኝነት ሲያብብ፤ እያየን እንዳላየ በዝምታ ማለፋችን ሲሆን፤ በፈረንጅ አገር ባርነት ላይ የምቾት ባርነት፤ ጨምረንበት፤ ድርብ ባርያዎች ሆነናል::

በስደቱ ዓለም፤ ምንም አይነት ዕውቀትና ችሎታ ኖሮን ብንሠራ: የምናበለጽገውና የምንገነባው የሰው አገር እንጂ የገዛ አገራችንን አይደለም::

 • የሰፊው ሕዝብ ባርነት፤ 

ይህ የህባችን ክፍል ቀደም ብሎ ህወሃት፤ አሁን ደግሞ (የኦህዴድና/ኦነግ) ጥምር ብልጽግና በጫነበት የባርነት በትር: ዘወትር እየተቀጠቀጠ፤ ለራሱም ሆነ ለልጆቹ ዋስትና በማጣት፤ የዕለት ተዕለት ጉርሱን ለማግኘት ሲባዝን የሚውል ሲሆን፤ የኑሮ ክብደት አጉብጦት ዛሬን ከመኖር ባሻገር: ነገን ለመኖሩ ዋስትና ያጣ ነው::  

በተማረው ወገኑ ላይ ከፍተኛ ዕምነት ያለውና የነበረው ሲሆን፤ የተማሩ ልጆቹ: ከባርነት፤ ከድህነት፤ ከችግርና ከመከራ ነፃ ያወጡኛል እያለ ሲጠብቅ፤ ብሎም ሲናፈቅ: እንዳልነበር፤  ባልጠበቀው መንገድ: የባርነት ጉድጓድ ሲምሱለት በማየቱ፤ ግራ ገብቶትና ተስፋ ቆርጦ: ዓይኖቹን ወደ ፈጣሪው እያማተረ፤ እጆቹን ዘርግቶ ሻል ያለ ቀን እንዲያመጣለት ፈጣሪውን ይማጠናል::    

ማሳረጊያ 

ባርያ ፈንጋይ: ለባርያዎቹ በፈቃዱ ነፃነት የሰጠበት ጊዜ የለም፤ ባርነት የተጫነበት ህዝብ፤ በተናጠል ሳይሆን፤ በአንድነት፤ እደግመዋለሁ: በአንድላይ ሆነው በማመጽ ብዙ ጊዜ ነፃነታቸውን ማግኘት እንደቻሉ ግን ታሪክ ይነግረናል:: የአያትና የቅድም አያቶቻችን ለወራሪ ሃይል የአልበገር ባይነት ገድልም የሚነግረን ይኸንኑ ነው ::  

ታዲያ ባርያ ፈንጋዮቹ ህወሃትና፤ (የኦህዴድና/ኦነግ) ጥምር ብልጽግና ተብዬዎች፤ ነፃነታችንን እንዲሰጡን የምንለምነው እስከመቼ ነው?! 

ህወሃትና (የኦህዴድና/ኦነግ) ጥምር ብልጽግና: ተክለው እየኮተኮቱ ውሃ የሚያጠጡት፤ የዘረኝነትና የጎሣ ቁልቋል ሲያድግ፤ ነገ ሁላችንንም እየወጋ ማድማቱ አይቀሬ ነው፤ በዛሬ ዝምታ ለሁል ጊዜ መድማቱ ይሻላል፤ ወይስ ዛሬ በአንድነት ለዘላቂ ነፃነት መነሳት?! 

እስከመቼ በየመንደሩ ትንንሽ ጉልቻዎች ሆነን ፤ ህወሃትና (የኦህዴድና/ኦነግ) ጥምር ብልጽግና የባርነት ድስቶቻቸውን ጥደው፤ እያንተከተኩ በእሳት ይለብልቡን ?!  

ሁል ጊዜ እጃችንን አጣምረን የእኛን ሥራ ፈጣሪ  እንዲሠራልን መለመኑን እናቁም :: ሁላችንም በአንድነት በመነሳት፤ ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነታችንን የምናስከብርበት ጊዜው አሁን ነው !!  

ሁላችንም በአንድነት፤ የዘረኝነትና የጎሠኝነት ሥርዓቱን ፤እምቢ በምንልበት ቅጽበት፤ የአምባ ገነኖቹ የህወሃትና (የኦህዴድና/ኦነግ) ብልጽግና: የባርነት ሰንሰለት ይበጠሳል !!

እስቲ ከህወሃትና፤ ከብልጽግና፤ እንዲሁም ከስደት ባርነት፤ ነፃ ለመውጣት የወሰንን ስንቶቻችን ነን ??!! 

 ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!   

ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነት ይለምልም !!   

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !!         

 

Filed in: Amharic