>

ደንቃራ እያመጣችሁ ከዋናው ጉዳይ አታናጥቡን !

ደንቃራ እያመጣችሁ ከዋናው ጉዳይ አታናጥቡን!

ከይኄይስ እውነቱ

 

ዛሬ ሃይማኖታዊም ሆነ ብሔራዊ በዓላችንን እነሱ ሰፍረው ቈጥረው በሚሰጡን መለኪያ ‹የምናከብር› ከሆነ ነገ ሲከለክሉን (ዓላማቸው የኢትዮጵያ የሆነን በተለይም ነባር እምነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ዕሤት፣ ቅርስ ወዘተ. ማጥፋት ነውና) በለመድነው የባርነት መንፈስ የማንታዘዝበት ምክንያት የለም፡፡ ከምንሳቀቅ የሚያሳቅቀንን ተባብረን እናስወግደው፡፡ … በጠላት ኃይል እየተፈተሽን፣ እየታፈንን፣ እየታሠርንና እየተገደልን በዓል አከበርን ማለት ራስን መሸንገል ነው፡፡

ለመሆኑ በየትኛው ክርስቲያናዊ ዶግማ÷ ቀኖና እና ትውፊት ነው እግዚአብሔር በደሙ የዋጀውን ክርስቲያን ከሚያሳርዱና ሲታረድም ዝም ብለው ከሚመለከቱ መለካውያን ጋር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኅብረት እንዳለው የተጻፈውና የተላለፈልን? ለመሆኑ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ተላለፎ ሰለመ እግዚአብሔር አለ ወይ?

አገር እንዳይኖረን እያደረጉ ያሉትን ወያኔን እና ወራሹ ፋሺስታዊውን የኦነግ አገዛዝ ከማስወገድ ውጭ ቀዳሚና ዋና ጉዳይ የለንም፡፡

አሁን አሁን የተያዘው ፈሊጥ ኹላችን በፍጹም ልባችን በፍጹም ነፍሳችን በፍጹም ሕይወታችን ልናተኩርበት ከሚገባን አገራዊና ሀገር-አከል ከሆነው የኢኦተቤክ ጉዳይ የሚያናጥቡን ደንቃራዎች ይዘው የመጡብን ማደናገሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጀማውን የሚያፈዙ ሐሳውያን የአምልኮ መልክ ይዘው እና ጐሣ ቈጥረው የሚመጡ ደንቃራዎችን በጊዜው ካላወቅንባቸው ጊዜአችንን በአርቲ ቡርቲው እንድናጠፋ ከማድረጋቸውም በላይ መዘዛቸው በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል ልንላቸው ይገባል፡፡ ሥር መሠረታቸውን ስንመዝ ‹አቡሃ ለሐሰት› የሆነው የፋሺስቱ ቁንጮ ርጕም ዐቢይ ጋር ወይም የጐሣ አገዛዝን በኢትዮጵያችን የተከለው ወያኔ ትግሬ ጋር ያደርሰናል፡፡ እነዚህ ደንቃራ አኗሪዎች ባንድም በሌላም መንገድ÷ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የአገር አጥፊዎችን ተልእኮ አስፈጻሚዎች በመሆን እያገለገሉ ያሉ የክፋት መሣሪያዎች ናቸው፡፡

1/ ደንቃራ አንድ – ‹‹የአእላፋት ዝማሬ››፤ እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል፡፡

ጉዳዩን ከኢኦተቤክ ብንጀምር፤ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከሔድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኵላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ ዐውቃለሁ፡፡›› የሐዋ. 20÷28-30 

የሚገርመውና የሚያስደነግጠው እነዚህ ርኅራኄ አልባ የሆኑት፣ ጨካኞች፣ ተኵላዎችና ጠማማ ነገር ሠሪዎች ቤተ መንግሥቱን እንደተቆጣጠሩት ሁሉ ቤተ ክህነቱንም ዋሻቸው አድርገውታል፡፡

እግዚአብሔር ሁሌም ጥቂት ቅሪቶች ይኖሩታልና በጎላው ልናገር፡፡ ዛሬ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብለው፣ የመለካውያን ተገዢዎች በመሆን ካገራችን ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሆነውን የተዋሕዶ ምእመናን ለነጣቂ ተኵላዎች አሳልፈው በመስጠት ከፍ ብሎ በርእሰ መጻሕፍቱ የተጠቀሰውንና በ‹ባለቤቱ› የተሰጠውን አደራ ቅርጥፍ አድርገው የበሉ፣ ከመንፈሳዊነት ጋር የማይተዋዋቁ ብቻ ሳይሆን ከፊሉም ክህነቱም የሌላቸው ሐሳውያን ‹ጳጳሳት› እና ካድሬዎች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ላገር ውድቀትም አሉታዊ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ እነዚህ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ተቀምጠው፣ በተለይም በመንፈስ ቅዱስ ሊመራ ይገባው የነበረውን ሲኖዶስ የዓላውያን ተወካዮች የጐሣ ሸንጎ በማድረግ ሳይወሰኑ፣ ቅዱሳን ሐዋርያት በሲኖዶስ የሚተላለፈውን ውሳኔ ‹‹እኛና መንፈስ ቅዱስ›› ብለው በሐዲስ ኪዳን የሥርዓት መጻሕፍታቸው ከሠሩት ሕግ በማፈንገጥ መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝን ብሎም የድፍረት ኀጢአት በሆነ መልኩ የአባቶቻችን ሐዋርያት ቀኖናን በመተላለፍ የሰጡት ውሳኔ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ላይ በግልጥ ለመዋሸታቸው ምስክር ሆኗል፡፡ በዚህም መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን ለዓላውያን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በተሰጣቸው የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ቊልፍ ምእመናን ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ያስገባሉ ተብለው የሚጠበቁቱ አንዳንድ ‹ካህናት› ሆን ብለው በዕቅድ አገር ከሚያጠፉ ቤተ ክርስቲያንን ከሚያወድሙ የጐሣ ፋሺስቶች ጋር አባሪ ተባባሪ በመሆን የሲኦልን በር ብርግድ አድርገው ከፋቾች ሆነዋል፡፡ ለመሆኑ በየትኛው ክርስቲያናዊ ዶግማ÷ ቀኖና እና ትውፊት ነው እግዚአብሔር በደሙ የዋጀውን ክርስቲያን ከሚያሳርዱና ሲታረድም ዝም ብለው ከሚመለከቱ መለካውያን ጋር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኅብረት እንዳለው የተጻፈውና የተላለፈልን? ለመሆኑ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ተላለፎ ሰለመ እግዚአብሔር አለ ወይ?

በዚህም ምክንያት እረኛ አጥቶ የሚቅበዘበዘውን መንጋ እንደ ጥገት ላም ለማይነጥፍ (ለምኖም ጭምር ለሚሰጠው) ገንዘቡ ሲሉ ቤተ ክህነቱና የጥቅም ተካፋዮቻቸው የሆኑ የበግ ለምድ የለበሱ ተኵላዎች እየተናጠቁት ይገኛሉ፡፡ ደጋግሜ እንደተናገርሁት ዛሬ አብዛኛው ምእምን እግዚአብሔር የሰጠውን ሀብት/ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለዘራፊዎች አሳልፎ እየሰጠ መሆኑን የተረዳው አይመስለኝም፡፡ ጽድቅ ለመሥራት ከተፈለገ ኢትዮጵያችን የችግር ‹ሀብታም› ናት፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በረሃብና በቀጠና ተይዘው እያለቁ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በትግራይና ዐምሐምራው በዋናነት በሚኖርባቸው ክፍላተ ሀገራት፡፡ 

ወደ ቀደመ የደንቃራ ነገር ልመለስና አንዱ ‹‹የማንቂያ ደወል›› እያለ ቤተ ክርስቲያንን ሲያምስ ቆየ፤ በቅርቡ ደግሞ ‹‹አእላፋት ዝማሬ›› እያሉ ምእመኑን በአፍዝ አደንግዝ ሲያታልሉት እንደ አህያ ዦሮ እየተጎተተላቸው ለጊዜውም ቢሆን ፈቃዳቸውን እየፈጸመ ይገኛል፡፡ በሰው የሚታመን ያለ ጥርጥር ይወድቃል እንዳለ ርእሰ መጻሕፍቱ ‹ታዋቂ› ባሕታዊ፣ ሰባኬ ወንጌል፣ መምህር ወዘተ. እያለ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በአዳራሽና በዐደባባይ ለሚደረግ የአንድ ሰሞን ‹ግርግርና ጫጫታ› አዳማቂ መሆን ክርስትና አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አይከብርበትም፡፡ ጽድቅም አይሆንም፡፡ ምሥጢረ ተዋሕዶ የተፈጸመበት የጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የዐደባባይ በዓል አይደለም፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ከዋዜማው ጀምሮ በጾም፣ በጸሎት ሥርዓት፤ ከዚያም በቅደሴ፣ በማኅሌት (በያሬዳዊው ጥዑመ ዜማ) በቤተ መቅደስና በቅፅረ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ዐቢይ በዓል ነው፡፡ መስቀል ዐደባባይና ጃን ሆይ ሜዳ የሚለውን ሲጀመር ምን አመጣው? ነጭ ብቻ ለብሰን የሚለውን ምን አመጣው? የትልቋ ‹ቤተ መቅደሳችን› የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መግፋት ለምን ተፈለገ? በካህናት፣ በመዘምራን፣ በሰንበት ተማሪዎች፣ በምእመናን አልባሳት፣ በንዋያተ ቅድሳት ኹሉ (በከበሮው፣ በጸናጽሉ፣ በመቋሚያው ወዘተ.) የሚገለጠው የሰንደቅ ዓላማች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ቀለም እንዳይታይ ለምን ተፈለገ? ጉዳዩ ከሰንደቅ ዓላማችንም ያለፈ ይመስላል፡፡ ይሄ የማን ተልእኮ ነው? የጣዖት አምላኪዎቹ የነ ቀጄላና የርጕም ዐቢይ፣ ክህነታቸውን ያጡት የነ አቶ አካለ ወልድና ጓደኞቹ፣ የመለካውያኑ የነ ‹አባ› ሔኖክ አይደለምን? ለመሆኑ አንድ ሰባኬ ወንጌል ነኝ የሚል ግለሰብ በግሉ ተነሥቶ ስለ በዓላት አከባበር ሥርዓት መደንገግና ማዘዝ ይችላል ወይ? ምእመናን! መቼ ነው በመንጋነት መነዳት የምናቆመው? ከበሮ በመደለቅ በስሜት ሰክረን ራሳችንን አናታልል፡፡ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለመፈጸም መሣሪያዎች አንሁን፡፡ እንደ ባለ አእምሮ እንመላለስ፡፡ ለጽድቅ ከመጣን እንደ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንመላለስ፡፡ ኋላ ላይ ከዕብደታችን ስንመለስ፣ ከቅዠታችን ስንባንን ጩኸታችንም ሆነ ልቅሶአችን የማይጠቅም እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ‹‹የአእላፋት ዝማሬ›› በተባለ አፍራሽ እንቅስቃሴ ውስጥ የገባችሁ ወገኖች በተለይም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ተጠንቀቁ፡፡ እውነቱን ለመናገር ገዳማውያን አባቶቻችን እና በከተማም ያሉ ጥቂት መንፈሳውያን ካህናት በየአድባራቱ በሚደረጉ የሠርክ ጉባኤዎች የሚሰማውን ቅጥ ያጣ የካሴት ሕዝባዊ መዝሙሮች በመስማት ‹‹ቤተ ክርስቲያንን የ11 ሰዓት ሙዚቃ ቤት አደረጓት›› እስከ ማለት ሲያዝኑ ሰምቼአለሁ፡፡ ምእመናን የግል ጸሎታቸውን ለማድረስ እስኪረበሹ ድረስ፡፡ ይህን አንቀጽ ወንድማችን መምህር ፋንታሁን ደጋግሞ በሰጠው ማሳሰቢያ እቋጫለሁ፡፡ በቅድሚያ አገራችንን ለባርነት ከዳረጉን ‹ነፃ አውጪዎች› እናስመልስ፡፡ መለካውያኑን ከ‹ቤታችን› እናጽዳ፡፡ ያኔ አምልኮታችንን በሥርዓት እና በነፃነት እንፈጽማለን፡፡

የጐሣ ፋሽስቶችን ካገራችን አስወግደን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ከመለካውያንና የበግ ለምድ ከለበሱ ተኵላዎች እስከምናጸዳ የዐደባባይ በዓላት አንድ ሐሙስ ለቀረው አገዛዝ ህልውና ምስክር ከሚሆኑና የገጽታ ግንባታ ከሚውሉ በቀር እግዚአብሔር ይከብርባቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ ይልቁንም ትርጕም ለሌለው መሥዋዕትነት እየዳረጉን ነው፡፡ እየተሳቀቁ በዓል ማክበር የለም፡፡ በጠላት ኃይል እየተፈተሽን፣ እየታፈንን፣ እየታሠርንና እየተገደልን በዓል አከበርን ማለት ራስን መሸንገል ነው፡፡ በየጥምቀተ ባሕሩ ‹ሊቃነ ጳጳሳት› ከተባሉት ጀምሮ እስከ አድባራት ‹አለቆች› እና ካድሬ ጸሐፊዎች አገርና ሃይማኖት አጥፊዎችን ሲያወድሱ ከመስማት የበለጠ ምን የሚያም ነገር አለ?  ዛሬ ሃይማኖታዊም ሆነ ብሔራዊ በዓላችንን እነሱ ሰፍረው ቈጥረው በሚሰጡን መለኪያ ‹የምናከብር› ከሆነ ነገ ሲከለክሉን (ዓላማቸው የኢትዮጵያ የሆነን በተለይም ነባር እምነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ዕሤት፣ ቅርስ ወዘተ. ማጥፋት ነውና) በለመድነው የባርነት መንፈስ የማንታዘዝበት ምክንያት የለም፡፡ ከምንሳቀቅ የሚያሳቅቀንን ተባብረን እናስወግደው፡፡ ሁሉም በተሰጠው ጸጋ ይትጋ፡፡ አገሩን ቤተ እምነቱን የሚወድ በሙሉ ንዋየ ሐቅሉን ሸክፎ ይነሣ፡፡ ከፊሉ በነፍጡ ከፊሉ በጸሎቱ ጽሙድ ሆኖ ያገልግል፡፡ ወያኔ ሕወሓት እና ኦሕዴድ/ኦነግ ከተከሉብን የአስተሳሰብ ባርነት ነፃ ለመውጣት የመጨረሻውን ፍልሚያ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሰልፍ ውስጥ ጥግ ቆሞ የሚመለከት ሁሉ በዳተኝነቱ ወይም ከክፉዎች ጋር በመተባበር ምርጫውን ባርነት አድርጓል፡፡ አገር እንዳይኖረን እያደረጉ ያሉትን ወያኔን እና ወራሹ ፋሺስታዊውን የኦነግ አገዛዝ ከማስወገድ ውጭ ቀዳሚና ዋና ጉዳይ የለንም፡፡ ሌሎች ችግሮችና ተግዳሮቶች ሁሉ ከዚህ ዐቢይ ሳንካ የሚቀዱ በመሆናቸው ደረጃ በደረጃ የሚፈቱ ይሆናሉ፡፡ 

ጥቂት የማይባሉ ‹ሰባክያነ ወንጌል›፣ ዘማርያን እና አንዳንዶችም መጋቤ እገሌ የሚባሉ የወንጌል ገበሬዎች በመሆን ሰማያዊ ዋጋ ከመሻት ይልቅ እንደ ዓለማውያን ዘፋኞች፣ ተዋንያን፣ በፋሽን ትርኢት ወይም በፎቶግራፍ ልብስና ሌሎች ሸቀጦችን በማስተዋወቅ እንደሚሠሩ ወይም ሠዓሊዎችና ቀራጮች ፊት ሰውነታቸውን አጋልጠው እንደሚቆሙ ሴቶች ‹ስመ ጥር› (ሴሌብሪቲ) ለመሆን ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላሉ፡፡ ዝናና ታዋቂነትን ፍለጋ በዚህም የሚገኘውን ገንዘብ በማሰብ ከባለሥልጣናት፣ ‹ከሃይማኖት› መሪዎች፣ ከቱጃሮች ሥር ሥር ሱክ ሱክ ሲሉ ይገኛሉ፡፡ ‹አባቶች› ከተባሉ ጋር በመቀራረብ ተአማኒትን ያገኙ ሲመስላቸው በፈጠሩት እንግዳ ባህል አማካይነት ላልተገባ ጥቅም ካደሩ አንዳንድ ‹አርቲስቶች› ጋር በቅንጅት በመሥራት የዋህ እና ጅል ምእምናንን በማሰባሰብ ይዘው ይጠፋሉ፡፡ በመንጋ ስሜት የሚጓዝ ‹ምእመን› አንዳንዱ የደንቃራ አኗሪዎቹ ሰለባ በመሆኑ በከሃድያን የጣዖት አዳራሾች ውስጥ ቀልጦ ይቀራል፤ አንዳንዱም ባንኖ እስኪመለስ ለአጥፊዎች ሽንጡን ይዞ በመሟገት ይቆይና ከብዙ ጥፋት በኋላ ሲያለቅስና ሲያላዝን ይሰማል፡፡

2/ ደንቃራ ኹለት – ‹‹የምክክር ኮሚሽን››፤ ፋሺስታዊው አገዛዝ ተልእኮውን እንዲያስፈጽምለት ያቋቋመው ይህ ድርጅት ሌላው ሕዝብን ከዋና ጉዳይ አናጣቢ የአደንዛዦች ስብስብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ‹ምክረ አይሁድ› ፈጻሚ ሸንጎ ቢባል ተገቢ የግብር ስም ይመስለኛል፡፡ ይህ ጭንጋፍ ተቋም በብዙ መልኩ ባርነትን ገንዘቡ ካደረገው ብአዴን ከሚባል ፈውስ በሌለው ደዌ ከተያዘ ልዩ ‹ፍጥረት› ጋር ይመሳሰላል፡፡ የርጕም ዐቢይን ፋሺስታዊ አገዛዝ በፈጣሪ የተቆረጥ ዕድሜ ካልቀጠልሁ ብሎ የሚደክም ከንቱ አካልና የከንቱዎች ስብስብ ነው፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት የሌለበት ዕውቀት ከንቱ ነውና፡፡ ለሕዝብ ደኅንነት ላገር አንድነት የማይጠቅም ዕውቀት ከንቱ ነውና፡፡ በዚህ ሞቶ የተወለደ ስብስብ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን መግለጽ የሚቻለው አንድም አፍቃሬ ወያኔ ወ ኦነግ እንደሆኑ በማመን ወይም በተግባር የኢትዮጵያና የተዋሕዶ ጠላቶች መሆናቸውን በመቀበል ብቻ ይመስላል፡፡ 

3/ ደንቃራ ሦስት – ‹ድርድር› እና ‹የሽግግር ሥርዓት›፤ ፋሺታዊው የርጕም ዐቢይ አገዛዝ በጻእረ ሞት ላይም ሆኖ የተበጠሰ ገመዱን ለመቀጠል ‹ድርድር› እና ‹የሽግግር ሥርዓት› እያለ ባንድም በሌላም መንገድ የሚያላዝን ኃይል በሙሉ ከደንቃራ አኗሪዎች አንዱና ዋናው ነው፡፡ በኢትዮጵያ አምላክ ስም የተረገመ ይሁን፡፡ የጌባል መርገም ይውደቅበት፡፡ ለዚህ ዦሮውን የሚሰጥና የሚያስተጋባም ከርኵሰቱ ተባባሪ መሆኑን ይወቅ፡፡ 

4/ አጠቃላይ ትዝብት፤ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኘው በነፍስም በሥጋም ከበደለው ወያኔ ትግሬ ጋር መጣበቁ፤ በተመሳሳይ መልኩ ጥቂት የማይባሉ የኦሮሞ ወጣቶች ኦነግ/ኦሕዴድ የተባሉ አረመኔዎችን ሰይጣናው አስተሳሰብ ደግፎ ከሰብአዊነት፣ ከእውነትና ፍትሕ መለየቱ የዘመናችን ግዙፍና አገራዊ ሕማም ሆኖ ይሰማኛል፡፡ መቼ ይሆን እሊህ ወገኖቻችን ወደ ዐቅላቸው ተመልሰው ‹ሰው› የሚሆኑት? አሁንም በጎላው ለመናገር እንጂ በሌላውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረው ሕዝብ ከዘረኝነት ወይም አድርባይነት ልክፍት ነፃ ነው ለማለት አልደፍርም፡፡

በዚህ ዘመን ባገሬ በኢትዮጵያ ተቀምጬ የሚሆነውን ኹሉ በዐይኔ አይቼ በዦሮዬ አድምጬ በመታዘቤ ነፍሴ ጽንፍ በያዙ ኹለት ተቃራኒ ሐሳቦች ተሰቅዛ ተይዛለች፡፡ አንደኛው፤ በግብረ ገብ እና በሥነ ምግባር የላሸቀና የዘቀጠ በማኅበራዊ ድቀት የተመታ፣ ‹ነፃ አውጪ› ነን የሚሉ የባሪያ አሳዳሪዎችን በማምለክ፣ አእምሮውንና ሕሊናውን ለነዚህ አጋንንታዊ ቡድኖች አስረክቦ፣ በራሱም ሆነ ባገር ላይ ጥፋት ዓውጆ፣ ራሱን ለርኵሰት አሳልፍ የሰጠ ትውልድ ውስጥ መገኘት ሲሆን፤ ከዚህ በርባሮሳዊ ዐዘቅት በተቃራኒው የአያት የቅድመ  አያቶቹን የጀግንነት፣ የአገር ፍቅር፣ የፈሪሃ እግዚአብሔር መንፈስ፣ የአልበገር ባይነት፣ የሥርዓትና የጨውነት፣ ፍጹም ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ይዞ ለእምነቱ፣ ለታሪኩ፣ ለዕሤቶቹና ለቅርሶቹ ተቆርቋሪ የሆነ፣ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ለነዚህ ልዕለ ሐሳቦች ሕይወቱን ለመስጠት ዝግጁ የሆነና በተግባርም እያስመሰከረ ያለ ትንታግ ትውልድ – የዐምሐራ ፋኖን – ማየቴ ደግሞ ፈጣሪዬን እንዳመሰግን፤ ለእግዚአብሔር ሆነ ለሰው እንዳለመመቸታችን ለካስ ጨርሶ አልተወንም የሚል የተሰፋ ጭላንጭል/ብርሃን ይፈነጥቅብኛል፡፡

5/ መልእከት ለጀግኖች ፋኖቻችን፤ በመጨረሻም ባራቱም ክፍለ ሀገራት ላሉ የዐምሐራ ፋኖ ጀግኖቻችን፤ የዐምሐራ ሕዝብ ከባንዳዎች በላይ ጠላት እንደሌለው ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ፡፡ ከባለቤቱ ያወቀ…ነው እንዲሉ እየተከፈለ ካለው የሕይወት መሥዋዕትነት አኳያ ሥጋቴን ማጋራት ከቻልሁ ፈቃዳችሁን እጠይቃለሁ፡፡ ብአዴን የሚባለውን የነውረኞች ስብስብ እስከ መጨረሻው ላለማመን የቈረብሁ ነኝ፡፡ ዛሬ አይደለም ገና ከጠዋቱ ‹ባይተዋር› በሆኑ የወያኔ ቅጥረኞች ሲመራ፤ የክህደት ቁንጮው አንዳርጋቸው አለቃቸው ሆኖ ሳለ፤ ገና ስመ ተፋልሶ ሳይገጥመው ነፍሴ ትጸየፈው ነበር፡፡

በቅርቡ በሸዋ በርካታ የብአዴን የበታች ሹማምንት ተፈራርመው እጃቸውን ለጀግኖች ፋኖቻችን እንደሰጡና ከፋኖ ጋር ለመሥራት ቃል እንደገቡ ሰምተናል፡፡ እጅ መስጠታቸው መልካም ሆኖ ሳለ ለሰማይ ለምድር የከበደ ወንጀል በሕዝባችን ላይ ሲፈጽሙ የቆዩት ጉዶች ምን ያህል ቊጥጥርና ክትትል ወይም አመኔታ ኖሮን ነው በህልውና ትግሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ የምንፈቅደው? በጥንቃቄ ከተያዙ በመረጃ ደረጃ ይጠቅሙን ይሆናል፡፡ መቼም በሸዋም ሆነ በተቀሩት ሦስት ክፍላተ ሀገራት ያሉ ባንዳዎች፣ ባለፈው ሰሞን በምሥራቅ ጎጃም ዞን በጎዛምን ወረዳ በየቦቅላ ቀበሌ የዐምሐራ ሕዝባዊ ኃይል ፋኖ ዐባይ ብርጌድ በቊጥጥር ሥር ከዋለው የሚሊሻዎች አዛዥ ኮማንደር ያነሰ ነውር ፈጽመዋል ብዬ አልገምትም፡፡ ፋሺስታዊው የርጕም ዐቢይ አገዛዝ እነዚህን እጅ ሰጡ የተባሉ ነውረኞች እንደማይጠቀምባቸው ዋስትናው ምንድን ነው? ጥያቄዬ የየዋህነትና ሥጋቴም መሠረት የሌለው ከሆነ ታላቅ ዕረፍት ነው፡፡ ሳላነሣው ብቀር ግን ቅር ይለኛል በሚል ለጀግኖች ወንድሞቼ እነሆኝ ብዬአለሁ፡፡

ድል ለዐምሐራ ፋኖ!!!

ድል ለኢትዮጵያ!!!

Filed in: Amharic