>

ፍጹም ተጠያቂነት የሌለበትን ሥር የሰደደ ባህል ማቆም ከህልውና ትግሉ ፍሬዎች አንዱ ሊሆን ይገባዋል

ፍጹም ተጠያቂነት የሌለበትን ሥር የሰደደ ባህል ማቆም ከህልውና ትግሉ ፍሬዎች አንዱ ሊሆን ይገባዋል

 

ከይኄይስ እውነቱ

ኢትዮጵያኖች ባጠቃላይ በተለይም የዐምሐራው ሕዝብ ህልውናውን ለማስጠበቅ እና አገሩን ለማጥፋት ምለው ከተነሡት ፋሺስቶች እጅ ለማስመለስ የመጨረሻው ትንቅንቅ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ትግሉ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተቃረበ ይገኛል፡፡ ለፖለቲካ፣ ወታደራዊና አስተዳደራዊ አመራር አንድ ወጥ ማዕከላዊ አደረጃጀት ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ጀግኖች የዐምሐራ ፋኖዎች በዚህ ረገድ የቀሩ ተግባራትን በቅርቡ እንደሚያገባድዱ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ የእንቅፋት ደንጊያ የሚያኖር በሙሉ የአገርና ሕዝብ ጠላት ነው፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ እንደሚለው የወፍጮ ደንጊያ በአንገቱ አጥልቆ ወደ ጥልቁ ቢወረወር ይቀለው ነበር፡፡ ባንፃሩም ፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝ ዕርቃኑን ቀርቶ፣ በሙቱ ብአዴን እና በንጹሐን ላይ በሚፈጽመው ግፍ ብቻ ህልው መስሎ የመጨረሻ ሕቅታውን ለማሰማት በሞት አልጋ ላይ ይገኛል፡፡ 

ይህ የህልውናና አገርን የመታደግ ትግል ያለ ጥርጥር በድል ይጠናቀቃል፡፡ ከዚያስ… ስለ ቀጣዩ መነጋገር ጊዜው አይደለም ወይ? ከጦርነቱ የማይተናነሱ ብዙ ግዙፍ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ለምሳሌ መሠረታዊ የሆኑ አገራዊ አጀንዳዎችን በመለየት ብሔራዊ መግባባት ማድረግ፤ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ቊርሾዎችን በዕርቅ የማድረቅ፤ አገርና ሕዝብ የበደሉ አጥፊዎችን ሕግ ፊት አቅርቦ ፍትሕ ማግኘት፤ ወያኔ የተከለወን የጐሣ ሥርዓት ከነ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ› እና መዋቅሩ ማገድ፤ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚሳተፍበት ዜግነትን መሠረት ያደረገ ዐዲስ ሕገ መንግሥት ማቆም፤ ለኢትዮጵያውያን ዜጎች የመሬት ሥሪት ለውጥ ማድረግ፤ እነዚህና ሌሎች አንኳር አገራዊ ተግባራትን ለመፈጸም የሽግግር ዘመን አስፈላጊነት ወዘተ፡፡ ይህ ጽሑፍ አንዱን ብቻ መዝዞ ለማስታወስ ይሞክራል፡፡

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በኢትዮጵያችን ባገርም በሕዝብም፣ በማኅበረሰብም በግለሰብም ላይ ከወንጀልም ግዙፍ ወንጀሎች ፈጽሞ በሕግ አለመጠየቅ (culture of absolute impunity) ሥር የሰደደ ባህል መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ግዙፎቹን ወንጀሎች በዋናነት ፈጻሚዎቹ በተጠቀሰው ግማሽ ምእት ዓመት በኢትዮጵያችን ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ የሠለጠኑ ጨካኝና ፋሺስታዊ አገዛዞች ሲሆኑ፤ የተቀሩትም አገዛዞቹ ባደራጇቸው የሽብር ቡድኖች፣ ገዳይ ቡድኖችና ግለሰቦች የተፈጸሙ ናቸው፡፡ የሚገርመው እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ከነ ነውራቸው ባደባባይ ሲፎክሩ፣ ሲሸልሉ፣ ሲንጎማለሉ፣ ካንዱ ሥልጣን ወደ ሌላው እየተሸጋገሩ፣ በነውር ላይ ነውር ሲፈጽሙ፣ አልፎ ተርፎም ካገር ወጥተው ምንም እንዳልፈጸሙ ቆጥረው ሲኖሩ ታዝበናል፡፡ በአገዛዞች ስንል ማናቸውንም የመንግሥትና የፓርቲ (በአገዛዞች ዘንድ ልዩነት ባይኖራቸውም) መዋቅሮችን ከቀበሌ አንሥቶ እስከ መጨረሻው የሥልጣን አካላት ይመለከታል፡፡ ወንጀላቸውን ለማራመድ በእነዚህ ነውረኞች የተቋቋሙ የኢኮኖሚና የሲቪክ ተቋማትንም ይመለከታል፡፡ ተጠያቂነቱም ከግለሰብ አመራሮች የተናጥል ኃላፊነት እስከ ድርጅታዊ/ቡድናዊ የጋራ ኃላፊነት ይዘልቃል፡፡ ግዙፋኑ ወንጀሎችም ለአብነት ያህል ዘር ማጥፋት በየዓይነቱ፣ የአገር ክዳት፣ የጦር ወንጀሎች በየዓይነቱ፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች በየዓይነቱ፣ የዘር ማጽዳት፣ ግዙፍ ንቅዘት በየዓይነቱ (ባገር ኢኮኖሚ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች፣ የአገር ሀብትን ወደ ውጭ ማሸሽ ጨምሮ) ይጠቀሳሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ወንጀሎች በዐደባባይ የተፈጸሙና ግዙፍ ማስረጃዎች (የሰነድ፣ ኤሌክትሮኒክስ/ዲጂታል፣ የድምፅ፣ የተንቀሳቃሽ ምስል፣ወዘተ) ያሏቸው ሲሆኑ፣ በሕይወት ያሉ የዓይን ምስክሮችም አሉ፡፡

የቅርቡን ትተን ደርግ የሚባል የወታደራዊ ቡድን አገዛዝ አልቦ እግዚአብሔር የሚል የጭካኔ አገዛዝ አቁሞ ንጹሐንን ያለ ፍርድ መግደልን በኢትዮጵያ በይፋ አስታዋወቀ፡፡ ‹አብዮት› እያለ የስድሳዎቹን የዓፄ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ደም በማፍሰስ አሟሽቶ፣ የኢትዮጵያ ቤክ በትርያርክን እና ንጉሠ ነገሥቱን አንቆ በመግደል፤ የዐዋቆችን ምክር አልሰማ በማለት አገርን በማያባራ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ከቶ የቊልቊለቱን መንገድ ከጀመረው በኋላ በመጨረሻም ኢትዮጵያ በምእት ዓመት የማታገኛቸውን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በመፍጀትና ሰሜናዊ ጫፍ ግዛታችንን (መረብ ምላሽ) እና ሕዝባችንን በማስገንጠል ተደመደመ፡፡ ዜጎች በላባቸው ያፈሩትን ንብረት ሁሉ ቀምቶ፣ የግል ንብረት እንዳያፈሩም ከልክሎ ሕዝቡን አስተካክሎ መናጢ ደሀ አደረገው፡፡ መሬት ላራሹ ብሎ የጀመረው ለውጥ በተግባር ገበሬውን የካድሬዎች ጭሰኛ በማድረግ መንገዱን ሳተ፡፡ በዚህ አገራዊ ጥፋት ውስጥ ሁሉ አገራቸውን በቅጡ ያልተረዱ የ‹ያ ትውልድ› በተለይም ኢሕአፓ በሚባለው ሰይጣናዊ ድርጅት ሳይገባቸው የተሰባሰቡ ወጣቶች ባመጡት የተውሶ ርእዮተ ዓለም አማካይነት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ከሥር መሠረቱ የጥላቻ፣ የሴራና የመጠላለፍ በማድረግ ምስቅልቅሉን አወጡት፡፡ አገራችን በደም አበላ ለመታጠቧ ከደርግ የማይተናነስ ጥፋት ፈጽመው፣ ከትግሉ ሜዳ ተሸንፈው ቢወጡም ለጐሣ አገዛዝ ትርክቱን እና መደላድሉን ፈጥረው ኢትዮጵያን ለጐሠኞች ካስረከቡ በኋላ ‹አልሞትሁም ብዬ አልዋሽሞቹ› በወረቀት ነብርነት አለሁ ሲሉን አያፍሩም፡፡ በፋሺስቱ የርጕም ዐቢይ አገዛዝ እንኳን ኢሕአፓ፣ በተግባር የፖለቲካ ማኅበር የሚባል የለም፡፡ የብርቱካንን ‹መዝገብ› ማስረጃ የምታደርጉ ከሆነ እሷም የሚገርማት ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ የዚያን ዘመን ጎረምሳ÷ አሁንም በ‹እንጨት ሽበት› ውስጥ የተደበቀ  ሌንጮ ለታ የተባለ ‹ጎረምሳ› በሽተኛ ትልቁ ስኬታችን የፖለቲካ ማኅበራትን ማጥፋታችን ነው ሲል ኢሕአፓ ዎች ካሉ አልሰሙ ይሆን? ታሪካዊና ፖለቲካዊ ዓውዱን ግምት ውስጥ በማስገባት ላገርና ለወገን ለማይበጅ ዓላማ የተከፈለ ‹መሥዋዕትነት› እና ‹የዓላማ ጽናት› የሚወደስበት ምን ዓይነት ምድራዊ ምክንያት አለ? በነገራችን ላይ ንስሐ ገብተው በቀሪ ዕድሜአቸው አገራቸውን ዐቅማቸው በፈቀደው መጠን ለመካሥ የሚጥሩ መኖራቸው ቢታወቅም፣ አንዳንዶቹ በሽምግልና ውስጥ የተደበቁ ‹ጎረምሶች› አሁንም ከክፉዎች ጋር ሆነው አገር በማመስ ተግባር ላይ የሚገኙ አሉ፡፡ እባካችሁ የራሳችሁን ጊዜ ማባከናችሁ ሳያንስ የሌላውን ትውልድ ሕይወት ባትሰርቁ መልካም ነው፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና ኢትዮጵያ በታሪኳ ተወዳዳሪ የሌለውን የጨለማ ዘመን በተለይም ያለፉትን 33 የግፍ፣ የሰቆቃ፣ የድንቊርናና ዕብደት ዓመታት የምትዘጋው ፍትሕን በማደላደል ብቻ ነው፡፡ ይኸውም በአገርና በሕዝብ ላይ የማይጠገን ጉዳት ያደረሱትን በሙሉ (በተለይም ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ በየደረጃው ያሉ የመንግሥትና ፓርቲ አመራሮችን እንዲሁም የነዚህ አካላትና አመራሮች ወንጀል አባሪ ተባባሪ በመሆን የተደራጁ የሽብር ኃይሎችንና ግለሰቦችን) ሕግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በጐሣ የተደራጁ የፖለቲካ ማኅበራትን ሙሉ በሙሉ ማገድ፤ በተለይም በድርጅትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የሚኖረው የወንጀል ተጠያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ ብአዴን (በተለያየ ስያሜ ቢታወቅም) ÷ ወያኔ ሕወሓት÷ ኦነግ÷ ኦሕዴድ/‹ብልጽግና›÷ ከነዚህ የወንጀል ድርጅቶች ጋር ኅብረት የነበራቸው ሌሎች የፖለቲካ ማኅበራት÷ባጠቃላይ ቀድሞ ኢሕአዴግ ተብሎ በሚታወቀው የወንጀል ስብስብ ውስጥ የተደራጁ የፖለቲካ ማኅበራት ሙሉ ለሙሉ መታገድ ይኖርባቸዋል፤ በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ አባላት በሙሉ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ለተወሰኑ ዓመታት ማናቸውም የፖለቲካ ማኅበራት ውስጥ እንዳይሳተፉ በሕግ ማገድ ተገቢ ይሆናል፡፡ ባንፃሩም የዕርቅ ሥርዓት ለብሔራዊ መግባባት አስፈላጊ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ በደንብ መተላለፍ ደረጃ የሚታዩ አነስተኛ ወንጀሎችን ብቻ የሚመለከት ይሆናል፡፡

አንዳንዶች በተጠቀሱት ዓመታት በኢትዮጵያችን የተፈጸሙ ለምድር ለሰማይ የከበዱ ወንጀሎችን ለ ‹ሰላምና ለወደፊት አብሮነት› ሲባል በዕርቅ ብናልፈው የሚል ከነውርም የከፋ ነውር ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ የሚነፃፀሩ ጉዳዮች ባይሆኑም ቀኖና የተላለፍነው ለ‹ሰላም› ስንል ነው ከሚለው ጋር ይመሳሰል ይሆን? ለማንኛውም በማንነታቸውና በእምነታቸው በጅምላ ባለቁና የዘር ፍጅት በተፈጸመባቸው ማኅበረሰብ እና ግለሰቦች ተገብቶ የትኛው ደፋር ይሆን ይቅር እንበል/አንበል የሚል የሞራል ብቃት ያለው? ይሄ ነውር አረመኔዎቹ ከፈጸሙት ጭካኔ የማይተናነስ ሆኖ ይሰማኛል፡፡

በወያኔ ትግሬም ሆነ የኦነግ/ኦሕዴድ ፋሺስታዊ አገዛዞች ግፍ ያልተነካ የኢትዮጵያ ክፍልና ማኅበረሰብ ባይኖርም የዐምሐራ ሕዝብ ከደርግ ዘመን ጀምሮ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት እልቂት ታውጆበት ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ አለ የሚባል የግፍና መከራ ዓይነት ንቅስ ተደርጎ የተፈጸመበት በመሆኑ በዳዮችን በሙሉ ለፍርድ የማያቀርብ የህልውና ትግል በድል ቢጠናቀቅም የተሟላ አይሆንም፡፡ በዚህ ረገድ ባገር ውስጥም ይሁን በውጭ የምትገኙ ለዚህ የግፍ ኹሉ ማረፊያ ለሆነ ሕዝብ ቆመናል የምትሉ አደረጃጀቶች በሙሉ አንዱና ዋናው ሥራችሁ መረጃዎችን በማጠናቀር፣ ማስረጃዎችን በማሰባሰብና በመሰነድ ወንጀለኞችን እንደ ወንጀሉ ዓይነት በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የፍትሕ መድረኮች ለማቅረብ በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጅምሮች ቢኖሩም ሰፋ ባለ መልኩ አጠናክሮ ከወዲሁ ዝግጅት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ እነ ልዑል ዶ/ር ዐሥራተ ካሣ፣ ጋሼ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስና የሥራ አጋሮቻችሁ ይህንን ተግባር በጥልቀት ልታስቡበት ይገባል፡፡ በተጨማሪም ይህ በምዕራባውያን የበላይነት የሚመራው የተዛባ ዓለም አቀፍ ሥርዓት በአፍሪቃና በቀረው አዳጊ ዓለም ሁሌም የእነሱን ጥቅም የሚያስጠብቅ የአገር መሪ መኖሩን ማረጋገጥ ዋና ተግባራቸው መሆኑን በሚገባ ስለምታውቁ፣ የዐምሐራ ሕዝብ ለዓመታት የደረሰበትንና አሁንም ያልተቋረጠውን ግፍና መከራ ጠንቅቃችሁ ስለምትረዱ፣ ከሁሉም በላይ ጀግኖች ፋኖቻችን በሕይወት እየከፈሉ ያሉትን መሥዋዕትነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከዚህ ኹሉ አገራዊ ምስቅልቅል በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ የእኩልነት፣ የፍትሕና የነፃነት ሥርዓት ይገባዋል፡፡ በቅጥረኞች ሳይሆን አገርና ሕዝብን በሚወዱ የገዛ ልጆቹ መመራትን ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ከእንግዲህ ወዲህ ኢትዮጵያ የምዕራባውያን እጅ ያለበት ሥርዓትና መሪ እንዳይተከልባቸው እናንተ በዕውቀት፣ በሕይወት ልምድና በሙያ በቂ ተሞክሮ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ፈጣሪን ጥግ አድርጋችሁ የሚቻላችሁን ኹሉ እንድታደርጉ በታናሽ ወንድምነት አሳስባችኋለሁ፡፡

ወገኖቼ! ከፈረሱ ጋሪውን እያስቀደምሁ አይደለም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው የህልውና ትግሉን መቋጨት ዘንግቼው አይደለም፡፡ ከፍ ብሎ የጠቀስኋቸውን እና ሌሎችንም ድኅረ ጦርነት መከናወን ያሉባቸውን አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ ማዋጣት የኹላችን ድርሻ በመሆኑ፣ ከአንዳንድ የትግሉ ደጋፊ ነን ከሚሉ ወገኖች የፍትሕን እና በቀልን ድንበር ባለመለየት አላዋቂ ንግግር በመስማቴ ሥጋቴን ለመግለጽ ያሰፈርሁት ጽሑፍ ነው፡፡ ያጠፋን የበደለን (ያውም አገርን እና ሕዝብን) ለፍርድ ማቅረብ በሥጋዊ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊም ሕይወት የፍትሕ አካሔድ ነው፡፡ ለበቀልማ ሕግ ፊት ማቅረብም አያስፈልግም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰለባዎች እስከነ ሕማማቸው ደም እምባ እያነቡ ይገኛሉ፡፡

ፋሺስታዊዎቹ የወያኔና ኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዞች ተጠያቂነት ያለመኖር ባህልን ሥር እንዲሰድ ያደረጉት የማናቸውም መንግሥት ምሰሶ የሆነውን የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት በማጥፋትና የሕግ የበላይነት እንዳይኖር በማድረግ ነው፡፡ ትክክለኛ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ማቆም ከተቻለ ግን ተበዳዩ ብቻ ሳይሆን በዳዩም ትክክለኛ ዳኝነት/ፍትሕ ያገኛል፡፡ አገርም በሕግ የበላይነት እንዲተዳደር መሠረት ይጥላል፡፡ በዚህም ዜጎች ለሕይወታቸው፣ ለነፃነታቸውና ለንብረታቸው ዋስትና የሚሰጥ ሥርዓት እንዲያገኙ ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic