>

ጦርነት የሚቋጨው በድርድር ሳይሆን ባንደኛው ወገን አሸናፊነት ብቻ ነው!

ጦርነት የሚቋጨው በድርድር ሳይሆን ባንደኛው ወገን አሸናፊነት ብቻ ነው!

ከይኄይስ እውነቱ

እውነትና ፍትሕን ይዞ የሚደረግ ህልውናን የማስጠበቅ እና አገርን ከአጥፊዎቿ ለመታደግ የሚደረግ ጦርነት በየትኛውም መመዘኛ ፍትሐዊ ጦርነት ነው፡፡ እየተነጋገርን ያለነው የዐምሐራ ሕዝብ ባጠቃላይ፣ በልጆቹ የዐምሐራ ፋኖ በተለይ ላለፈው አንድ ዓመት እየተደረገ ስላለው ተጋድሎ ነው፡፡  ይህ ጦርነት አንዳንዶች እንደሚናገሩት በወንድማማቾች መካከል እየተካሔደ ያለ የርስ በርስ ግጭት አይደለም፡፡ የዐምሐራን ሕዝብና ባጠቃላይ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ቆርጦ ከተነሣ ፋሺስታዊ የጠላት ኃይል ጋር የሚደረግ ፍልሚያ ነው፡፡ ውጊያው ሕዝብና አገርን ለመታደግ ከተነሡ የተቀደሱ ኃይላት እና የባዕዳን ቅጥረኞች ሆነው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የቅዠት አገር ለመገንባት ከተነሡ ዲያቢሎሳዊ የርኵሰት ኃይላት ጋር ነው፡፡ ይህ ጦርነት የሚደረገው የጀግንነትን ጥግ ከሚያሳይ ከፍተኛ ሥነ ሥርዓትና የሞራል ልዕልና ባለው የዐምሐራ ፋኖ እና የፈሪነትና ጭካኔ ጥግ ከሚያሳይ ሞራል አልባ ዘራፊና አውዳሚ የርጉም ዐቢይ ሠራዊት ጋር ነው፡፡ 

ይህ ጦርነት ያለ ጥርጥር እውነትንና ፍትሕን በያዙት የዐምሐራ ፋኖዎች አሸናፊነት ይደመደማል፡፡ ሆኖም በተራዘመ ቊጥር በሕዝባችን ላይ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋቱ እየጨመረ ስለሚሔድ እና በሕዝቡም ሆነ በተዋጊው ኃይል ላይ አሉታዊ የሥነ ልቦና ጫና ስለሚያሳድር ባጭሩ የመቋጨቱን ግብ ለማሳካት ጥንቃቄ የተሞላበት ዐዲስ ዕቅድና ስልት መንደፍ የሚጠይቅ ይመስላል፡፡ ጀግኖቻችን ደግሞ ለዚህ ብቃቱ ስላላችሁ በአራቱም ክፍላተ ሀገራት (ጠቅላይ ግዛቶች) ያላችሁ የፋኖ አመራሮች ባስቸኳይ ምከሩበት፡፡ ከዐቅማችሁ በላይ የሆነውን ጉዳይ ደግሞ ከምታምኗቸው ወገኖች ምክርን ጠይቁ፡፡ ‹‹አባትህን ጠይቅ ያስታውቅህማል፤ ሊቃውንትህን ጠይቅ ይነግሩህማል፡፡›› እንደተባለ፡፡ ውጊያው ምሕረት ከሌላቸው ሥጋ ከለበሱ ሠራዊተ አጋንንት ጋር መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ የዐምሐራ ሳይንቱና የመርዓዊው ፍጅት በሌላ ቦታ እየተደገመ እንዲቀጥል መፍቀድ የለብንም፡፡ 

ይህ ጦርነት ዕድሜ ያገኘው የዐምሐራ ሕዝብ ነቀርሳ በሆነ፣ የዓለሙ ሁሉ ማፈሪያ የሆነ ‹ታሕተ ሰብአ ጉድፎች› የተሰባሰቡበት ብአዴን የተሰኘ ባንዳ ቡድን ለጠላት በሚሰጠው እገዛ ነው፡፡ ስለሆነም እስካሁን በጀግኖቻችን የተገኘውን ታላቅ ድል ለማስጠበቅና ጦርነቱ ተጓትቶ የዐምሐራ ሕዝባችን ካሁኑም የከፋ እልቂት እንዳይደርስበት እውነተኛ ፋኖዎቻችን በዚህ ከሃዲ ቡድን ላይ የተለየ ጥብዐት ልታሳዩ ይገባል፡፡ ጥብዐት እና ተራ ጭካኔ ለየቅል ናቸው፡፡ የኋለኛው ከሰብአዊነት የወረደ አራዊት የማይፈጽሙት የምናምንቴዎች አረመኔአዊ ተግባር ነው፡፡ በተቃራኒው ጥብዐት ለበጎ ወይም ለመልካም ተግባር የሚደረግ ድፍረት ወይም በራስ ላይ ሁሉ የሚደረግ ቆራጥነት ነው፡፡ በመሆኑም ሰማዕትነት አንዱ መገለጫው ነው፡፡ በዚህ ጦርነት ጥቂት የማይባሉ ጀግኖች ወንድሞቻችን በጠላት እጅ ላለመግባትና ሌሎች ጓዶቻቸውን ለማዳን ሲሉ በራሳቸው ላይ የወሰዱት ‹ቴዎድሮሳዊ› ርምጃ ጥብዐትን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለሆነም ከእንግዲህ ወዲህ ለብአዴን ምክር መስጠትና ርኅራኄ ማሳየት ከአሁኑም በላይ የሚያስከፍል ስለሚሆን መረር ያለ ጥብዓት የተሞላበት ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ በታገሣችሁ ቊጥር ጠላት ጊዜ ያገኛል ንጹሐንም ያልቃሉ፡፡ 

ሌላው የጠላት ህልውና በዋነኛነት በብአዴን እገዛ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ስለሚታወቅ ከጠላት ወገን በገዛ ፈቃዱም ሆነ ተማርኮ የሚመጣ ሚሊሻም ሆነ ሌላ ኃይል ላይ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ጀግኖቻችንን ለጥቃት ሊያጋልጥ ይችላልና፡፡ እኔ ወንድማችሁ ለጦር ጉዳይ ‹ጨዋ› ብሆንም ከፋሺስታዊው አገዛዝ መሠሪያዊ ባሕርይ በመነሣት የሚከተለውን ለማለት እደፍራለሁ፡፡ በክዳት ወይም በምርኮ የሚቀላቀል የጠላት ኃይል የለበሰውን የደንብ ልብስም/ዩኒፎርምም ይሁን ተራ ልብስ ወዲያው ማስወገድ፤ ስንቅና ትጥቁንም በጥንቃቄ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ርጉም ዐቢይ እና ጠጃሙ መጋቢ ዐሥር አለቃ ብርሃኑ ለቦታ ጠቋሚነት ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ መጠርጠር ክፋት የለውም፡፡ ከዚሁ ከብአዴን ሴራ ጋር በተያያዘ በአራቱም ክፍላተ ሀገራት የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባመዛኙ ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ አይመስሉኝም፡፡ እነዚህ ተቋማት ለፋሺስታዊው አገዛዝ ሠራዊት ማሰልጠኛ፣ ስንቅና ትጥቅ ማከመቻ ሆነው የሚያገለግሉ እንዳሉ ይሰማል፡፡ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ጥቂቶችም ካሉ አገዛዙ በዐምሐራው ግዛት ህልው መሆኑን ለማረጋገጥ ለፕሮፓጋንዳ ዓላማ ለመጠቀም እንጂ ስለ ትምህርት ተጨንቆ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ይልቁንም ተማሪው መያዣ ሊሆን ስለሚችል ጥበብ በተሞላበት ሁናቴ አሰናብቶ ጦርነቱ እስኪጠናቀቅ መዝጋቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ወላጆችም በዚህ ረገድ ልጆቻችሁን መምከር ይኖርባችኋል፡፡ ከትምህርቱ በሕይወት መቆየት ይቀድማልና፡፡ 

በማጠቃለያነት የማነሣው ሐሳብ ኅብረትና አንድነታችሁን አጠንክሩ!!! ኅብረትና አንድነታችሁን አጠንክሩ!!! ኅብረትና አንድነታችሁን አጠንክሩ!!! ምን ጊዜም የተነሣችሁበትንና የቆማችሁለትን የጋራ ዓላማና ግባችሁን እንዳትዘነጉ፡፡ በችሎታቸው÷ በብቃታቸውና በጸና የመርህ ሰውነታቸው የምታምኑባቸውን ጓዶቻችሁን በየደረጃው አመራር አድርጋችሁ ሰይሙ፡፡ ከእኔ ወንድሜ ይሻላል በሉ፡፡ ሁሉንም በጊዜው ጊዜ እንደርስበታለን፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን መሥዋዕትነታችንን ከንቱ እናደርጋለን፡፡ ከጠላቶቻችንም ከምንጸየፈውም ፋሺስታዊ አገዛዝ አስተሳሰብ የተለየን አንሆንም፡፡ በትግል ሜዳው ያሳያችሁትን ወደር የሌለው ጀግንነት፤ በአመራር ጥበብም ደግማችሁ ልታሳዩን ይገባል፡፡ ትችላላችሁ ብለን ደግሞ እምነት ጥለንባችኋል፡፡ ሆኖ መገኘት የናንተ ፈንታ ነው፡፡  ሰው ናችሁና የሐሳብ ልዩነት መኖሩ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ሳይገባ÷ አደባባይ ሳትወጡ እዛው ተመካከሩ፣ ተወያዩ፣ በሙቀት ተከራከሩ፣ ተገሣሠፁ ግን አነስተኛው ድምፅ ለብዙኀኑ ድምፅ ይገዛ፡፡ ቢቻል እንደ አንድ ልብ መካሪ÷ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ÷ እንደ አንድ ሕይወት ኗሪ በመሆን ለመወሰን ሞክሩ፡፡ ከአብራኩ የተከፈላችሁት ሕዝባችሁ እና በአገርና በውጭ የሚገኙ የትግላችሁ ደጋፊ ኢትዮጵያውያን በሙሉ አንድ የዐምሐራ ፋኖ ጠቅላይ ዕዝ እወጃ ዜናን ለመስማት በእጅጉ ጓጉቷል፡፡ ይህን የምሥራች አሰሙንና ጠላት ይፈር እርሙን ያውጣ፡፡ ወዳጅም በሙሉ ኃይሉ፣ በሙሉ ልቦናው፣ በሙሉ መንፈሱ እንዲረዳችሁ ይሁን፡፡

በመጨረሻም ከማሸነፍ ውጭ ሌላ ምርጫ የለንም፡፡ ውጊያችን ከማን ጋር እንደሆነ በመግቢያዬ ላይ የተናገርሁትን ቃል አስተውሉ፡፡ አጋድሞ ከሚያርዳችሁ የአጋንንት ኃይል ጋር ድርድር የሚባል ነገር በጭራሽ እንዳታስቡ፡፡ ድርድር ለእኛ መቼም የማይተኙት ምዕራባውያኑ እጃቸውን በማስገባት ተረኛ ቅጥረኛ ለማስቀመጥ የሚጠቀሙበት የረቀቀ ሰይጣናዊ መንገድ ነው፡፡ ድርድር ባጭሩ ትግሉን መክዳት ነው፡፡ የሰበሰባችሁትን መበተን ነው፡፡ የተጨፈጨፈ ሕዝባችሁን እና የወደቁ ጓዶቻችሁን እርም መብላት ነው፡፡ አሁንም ደግሜ እላለሁ የጦርነት ሁሉ መቋጫ ድርድር አይደለም፡፡ ጦርነት የሚያበቃው (በተለይም የዐምሐራ ሕዝብ ሳይወድ በግድ የገባበት ጦርነት) በድርድር ሳይሆን ባንዱ ወገን አሸናፊነት ብቻ ነው፡፡ በዐምሐራ ፋኖ አሸናፊነት፡፡ ይሄንን በልቦናችሁ አኑሩ፡፡ ይህን ካደረግን ህልውናችንን እናስጠብቃለን፤ አገራችንን እንታደጋለን፤ ሃይማኖታችንን እናስከብራለን፤ የጋራ ታሪካችንን፣ ባህላችንን፣ ቅርሶቻችንን፣ ምልክት የሆኑ ብሔራዊ ተቋሞቻችንን ወደቀደመ ክብራቸው እንመልሳለን፤ ባጠቃላይ መልካም እሤቶቻችንን እንጠብቃለን፡፡ የደፈረሰውን እናጠራለን፤ የፈረሰውን እንጠግናለን፤ የተጣመመውን እናቃናለን፤ የጎደለውን እንሞላለን፡፡ ከ‹ሰዶምና ከገሞራ ምድር› የሚመጡብን ምዕራባውያን ጣልቃ ሳይገቡብን ኢትዮጵያዊ መንግሥት በራሳችን ከራሳችንና ለራሳችን ማቆም እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን ይርዳችሁ፡፡ 

Filed in: Amharic