>

ወንጌልና ወንጀል፤ ቁራንና ቅጥፈት፤ ምን አገናኛቸው ?!

ወንጌልና ወንጀል፤ ቁራንና ቅጥፈት፤ ምን አገናኛቸው ?!

 አሥራደው ከካናዳ 

– Dear past, thanks for all the lessons; Dear future we are ready !

የአብይ አህመድ ፖለቲካ « ሳያዩ የሚያምኑ፤ ብፁዓን ናቸው » የሚል ሲሆን፤ ለእኔ ሥልጣን ስትሉ ብትሞቱ፤  « ገነትን ወይም  ጀነትን ትወርሳላችሁ ይላል » ወታደሮቹን የገዛ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን  እንዲጨፈጭፉ ልኮ፤ ለእሱ ሥልጣን ሲሉ ቢሞቱ፤ « ገነትን ወይም ጀነትን እንደሚወርሱ » ይነግራቸዋል::

በፓርማው ውስት የታጎሩት፤ አይምሮ ሰንካላዎች ሙሴ እያሉ ሲሞካሹት፤ እንደፈጣሪ አምልኩኝ ለማለት፤ ትንሽ ነው የሚቀረው ::  

ሂትለር « ጀርመናውያን፤ ሰማያዊ የዓይን ቀለም፤ ቀላ ያለ ጠጉር (ብሎንድ) ረጅም ቁመና፤ ደንደን ያለ ሰውነት፤ ያላቸው ናቸው » ቢልም፤ እራሱ ለእነዚህ መስፈርቶች ያልታደለ፤ ቁመቱ አጭር፤ ጠጉሩ ጥቁር፤ሰብዕናው በዘር ጥላቻ የጠቆረ ኮስማና ፍጡር ነበር::

አምባ ገነኖች፤ ትልቅ ሃሳብ ሳይኖራቸው፤ ትልቅ ሰው ለመምሰል እየደነፉ፤ የዘር ጥላቻቸውን በአደባባይ የሚለፍፉ፤ እብዶች ናቸው :: 

   « ሃሰትና ስንቅ እያደረ ይቀላል!! » እንዲሉ:

አብይ አህመድ በመደመር የቅዠት ፍልስፍናው፤ ሰሞኑን ደግሞ እንዲህ ሲል ተደምጧል ::

  • « ዲሞክራሲ ስለበዛ ነው ሠላም የሌለው » 
  • « አናርኪን * የሚወልደው ዲሞክራሲ ነው » (አናርኪ የሚለው ስርዓተ አልበኝነት ለማለት ነው)
  • « ዲሞክራሲና ነፃነት በዝቷል » እነ ኬኛ ባዮቹ፤ ዘረኞችና ጎሠኞች በኢትዮጵያ እንዳሻው ስለሚቦርቁ 
  • « አስር ሰው ቢገደል መቶ ሰው ዝም ይላል » በድሮን ስለሚያስጨፈጭፋቸው ወገኖቻችን ሲነግረን
  • « በኢትዮጵያ የተራበ ሰው የለም »

በትግራይ፤ በጎጃም፤ በሸዋ፤ በወሎ፤በጎንደር፤ በአፋር…..ወዘተ. እሱ በከፈተው ጦርነትና በችጋር፤ እንደቅጠል የሚረግፉት ወገኖቻችን እልቂት፤ ለአብይ ዓህመድ ምኑም አይደለም ::

አብይ አህመድ፤ እራሱ በዘረኝነት በረት ውስጥ ታጉሮ፤ የጎሠኝነት ፖለቲካውን፤ የወርቅና የብር ቀለማት ለመቀባባት፤ አንድ ጊዜ ከወንጌል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቁራን፤ ቃላትን እየቃረመ፤ ህዝብን ለማጃጃል፤ የሚያደርገውን መገለባበጥ ስንመለከት :

ወንጌልና ወንጀል፤ ቁራንና ቅጥፈት፤ ምን አገናኛቸው ?! ለማለት እንገደዳለን ::

ምንም እንኳን ወንጌሉ፤ « ሳያዩ የሚያምኑ፤ ብፁዓን ናቸው » ቢልም፤ 

እኔና መሰሎቼ ደግሞ፤ የቶማስ የልጅ፤ ልጅ….: ልጆች: በመሆናችን፤ የምናምነው በዓይኖቻችን አይተን የተረዳነውን፤ በእጆቻችን ዳብሰን ያረጋገጥነውን ብቻ በመሆኑ፤ አብይ አህመድ በዘረኝነት የታጠረና፤ በጎሠኝነት የበሰበሰ ፖለቲካውን፤ የወርቅና የብር ቀለማት ለመቀባባት፤ አንዳዴ ከወንጌል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቁራን፤ ቃላትን እየቃረመ፤ ፖለቲካና ሃይማኖትን አብሮ እያቦካ፤ ህዝብን ለማጃጃል፤ የሚያደርገውን መላላጥ ስንመለከት « ለማያውቁሽ ታጠኝ » የሚለውን አገራዊ ብሂል ያስታውሰናል:: 

ይህ ሰው ገና ከጅምሩ « ኑ ተደመሩ .. » እያለ ህዝብን ሲሸነግል፤ « 

« ይቅርታ! ከዜሮ በታች ከሆኑ ሰዎች ጋር አብረን አንደመርም !! »  በሚለው መጣጥፌ መልስ ሰጥቼው ነበር ::  አንባቢዎች ርዕሱን ጠቆም በማድረግ፤ ሙሉውን መቃኘት ይችላሉ ::

መደመር የቁጥር ክምችት እንጂ፤ የፖለቲካ ፍልስፍና ሆኖ አገር ተመርቶበት አያውቅም:: ወደፊትም መሆን አይችልም :: በመደመር የተገኘ የቁጥር ክምችት፤ በመቀነስ ስሌት ይራቆታል፤ በኢትዮጵያ እያየን ያለነውና፤ እየሆነ ያለው ይኸው ነው ::

መደመር የፖለቲካ ፍልስፍና ሆኖ፤ የአንድን አገር ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህረሰባዊ አቅጣጫዎች የሚነደፍበትን ሳይንሳዊ ትንታኔና ግንዛቤዎችን፤ ማስጨበጥ አይችልም :: 

በሳይንሳዊ ንድፈ ሃሳቦች ( Theories ) ላይ ተመስርቶ፤ ወደ ተግባር ወይም ድርጊት እንዴት ለመሸጋገር እንደሚቻል፤ ጥርት ያሉ አቅጣጫዎችን የማያመላክት፤ ወይም ማሳየት የማይችል ዳፍንታም ፖለቲካ ነው ::

ከምን ተነስቶ፤ በምን ላይ ተመስርቶ፤ ምን ይዞና ምን ትቶ፤ በየትኛው አቅጣጫ፤ ከነ ማን ጋር ሆኖ፤ መቼና እንዴት፤ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድና ቀመር የአንድ አገርን ህዝብ፤ ካለበት ኢኮኖሚያውና ማህበራዊ ቀውስ አውጥቶ፤ ህዝብን ወደተሻለ የኢኮኖሚና ማህበራዊ መደላድል እንደሚያደርስ የሚያመላክት፤ አቅጣጫና ተስፋ ( vision) የሌለው ዳፍንታም ፖለቲካ ሲሆን፤ ነጮቹ (Myopic) የሚሉት ዓይነት ነው ::  

ዳፍታም ፖለቲካ ደግሞ፤ እራሱን ብቻ ሳይሆን፤አገርና ሕዝብን ይዞ ይወድቃል:: ያለንበት ሁኔታ  የሚያሳየን ይኸንኑ ነው ::

አምባ ገነኖች፤ ከዝሆን በላይ ገዝፈው ለመታየት ሲንጠራሩ፤ ከአይጥ አንሰው ይሞታሉ!! 

ሁልጊዜ ትንንሽ ሃሳቦችን የሚኮተኩቱ ሰዎች፤ እራሳቸው አንሰው፤ ሕዝባቸውንና አገራቸውን ያሳንሳሉ ::  

ዘወትር ጉራ፤ ዝና፤ መደነቅ፤ መወደድ፤ መከበር፤ መብለጭለጭ፤ ታዋቂና አዋቂ ለመምሰል የሚደረግ ኳኳታ፤ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ባዶነትን ነው :: ነጮቹ የዚህ ዓይነቱን የአፍ ፍጆታ (Political  Marketing) ይሉታል ::

  • የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩባት ኢትዮጵያ
  • የወጣት ሥራ አጦች በብዙ ሚልዮን በሚቆጠሩባት አገር
  • የኑሮ ውድነቱ ሕዝብን እንደ እሳት በሚለበልብበት አገር
  • « ሃይማኖት የግል ነው አገር የጋራ ነው » የሚለውን የአብሮነት ድልድያችንን አፍርሰው: ፖለቲካና ሃይማኖትን አንድላይ እያቦኩ ሕዝብን ከሕዝብ እያባሉ፤  
  • በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በረሃብ እንደቅጠል እየረገፉ፤
  • በዕብሪት በከፈተው ጦርነት፤ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን እየፈጀ……ወዘተ.

« ዲሞክራሲና ነፃነት በዝቷል » ይለናል ::

ማሳረጊያ

መደመር፤ ግልጽ የሆነ ሳይንሳዊ ፍልስፍና የሌለው፤ በሳይንስና ቴኖሎጂ በመታገዝ፤ ሕዝብን ወደተሻለ፤ የኢኮኖሚና የማህረሰባዊ ዕድገት መምራት የማይችል፤ ግን በተቃራኒው ወደ ድቅድቅ ጨለማ የሚወስድ፤ የዘርና የጥላቻ መንገድ ነው ::

« የዓሣ ግማቱ ከጭንቅቅቱ » እንዲሉ፤ ብዙ ወገኖቻችን በርሃብና በዕብሪት በከፈተው ጦርነት፤ እንደቅጠል እየረገፉ፤ አብይ አህመድ፤ ከአረብ አገራት በሙስና በሚዝቀው ዶላር፤ « የጫካ ሃውስ » በሚል ወደፊት እነግሥበታለሁ የሚለውን ቤተ መንግሥት ይገነባል ::

ፍትህ ተደፍጥጣ፤ ሠላም ተረግጦ፤ ጎሠኝነት አፍጥጦ፤ ወንድማማችነት ተረስቶ፤ ዘረኝነት ነግሦ፤ ንቅዘትና ጦርነት ታውጆ፤ መፈናቀልና ረሃብ በርክቶ፤ ዕድገት አለ ቢባል እራስን ከማታለል በቀር፤ ማንን ያሳምናል ?!

 

ለአድዋ በዓል በምኒሊክ ዓደባባይ እንገነኝ!!

የፈራ ይመለስ !!

በአንድነት በመነሳት፤ ነፃ ሕዝብ እንሁን !!

በሥር ነቀል ለውጥ፤ ወደ አዲስ ተስፋ !!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነት ይለምልም !!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !! 

የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ( 12/02/2024 ) እኤአ

ከላይ የተጠቀምኩባቸው  ምስሎች፤ ከባንክሲ የመንገድ ላይ የጥበብ ሥራዎች የተዋስኳቸው ናቸው ::

 

 

 

Filed in: Amharic