የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ላይ የሚደርሰውን በደል ግፍና ግድያ በጽኑ እንደሚያወግዙና መንግስት ለተቋማቱ አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደረግ ባወጡት መግለጫ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በኦሮሚያ ክልል፣ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ስር በምትገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መነኮሳት አባቶች ላይ የተፈፀመውን የግፍ ግድያ አስመልክቶ የተሠጠ መግለጫ!
በሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ላይ የሚደርሰውን በደል ግፍና ግድያ በጽኑ እያወገዝን መንግስት ለተቋማቱ አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደረግ በአጽንኦት እንጠይቃለን!”
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን፣ በምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ስር በምትገኘው የጥንታዊዋ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መነኮሳት አባቶች ላይ የተፈፀመውን የግፍ ግድያንና በቤተ ክርስቲኒቱ ላይ የደረሰውን ጥቃት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በጽኑ እናወግዛለን፡፡ ስለደረሰው ጥቃትም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ አገልጋዮችና ምዕመናን እንዲሁም ለገዳማውያኑ በሙሉ መጽናናትን ይመኛል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት እና የሃይማኖት አባቶች ፍቅርንናሰላምን፣ አንድነትንና መከባበርን፣
ፍትህንና ሰብኣዊነትን፣ ይቅርታንና እርቅን፣ ልግስናንና ርህራሄን እንዲሁም ሕግንና ሥርዓትን በማስተማር ምዕመናንም እነዚህን መልካም ባህሪያት ገንዘቦቻቸው አድርገው እንዲይዙ ቀን ከሌት ይሠብካሉ! ያሳስባሉ፡ ይህም በውጤቱ አማኞች በግላዊ ጠባያቸውና ባሕራያቸው ትvትናን የተላበሱና ግብረ ገባዊ ሕይወት እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ ሀገር ወዳድና ወገናቸውንም አክባሪ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የሃይማኖት ተቋማት በሀገርና ትውልድ ግንባታ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ እንደኖሩና አሁንም እያደረጉ እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ተግባርም በቀጣይነት ተጠብቆ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ላይ ጥቃትና የግፍ ግድያ እየተፈፀመባቸው ይገኛል፡፡ በተቋማቱ ላይ የሚፈፀመው ጥቃት፣ የግፍ ግድያ፣ ኢሰብኣዊ አያያዝ እና መዋቅራዊ በደል ሁሉ የተወገዘ ተግባር ከመሆኑም በላይ ሕጋዊ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ኢፍትሀዊ ተግባር እንደሆነም እናስገነዝባለን፡፡ ይህ መሰሉ ድርጊት ከዚህ በፊትም በሌሎች የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ላይ መፈፀሙ የሚታወስ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ በተደጋጋሚ እየተከሠተ ያለውን ጥቃት በተመለከተ እኛ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች የግፍ ግድያውንና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ አቋማችንን እንደሚከተለው እንገልፃለን፡-
1. በቤተ ክርስቲያኒቱ መነኮሳት ላይ የተፈፀመውን የግፍ ግድያ በማጣራት የወንጀል ተግባሩን የፈፀሙትን አካላት ተከታትሎ ለፍርድ እንዲያቀርብና በቀጣይም በስጋት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም በመንግስት በኩል
አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው በአጽንኦት እናሳስባለን፡፡
2. መንግስት ይህንን የግፍ ግድያ የፈፀሙትንና ያስፈፀሙትን በማጣራት በአስቸኳይ ለፍርድ
በማቅረብ የሕግ የበላይነት የማስፈን ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን።
3. የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የሃይማኖት ተቋማትንና መዋቅራቸውን ሁሉ በሕግከተቋቋሙበት መንፈሳዊ አገልግሎት ውጪ ለሆነ ተግባር ለፖለቲካዊና ለርዕዮተ-ዓለማዊ ተልዕኮው መጠቀሚያ ባለማድረግ የሃይማኖት ተቋማት መንፈሳዊ ነፃነታቸው እንዲከበርና
እንዲያስከብር አበክረን እንጠይቃለን!
4. በየትኛውም ደረጃ በሚገኙ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባቶችና አስተማሪዎች ከመሠረታዊ የሃይማኖታቸው አስተምህሮ፣ ዶግማና
ቀኖና ውጪ የሆነና ከአስተምህሮው በሚቃረን መልኩ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሁነው የትኛውንም ፖለቲካዊ አቋም ከማራመድ እንዲቆጠቡ በአጽንኦት እናሳስባለን!
5. በመጨረሻም መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው የንፁሀን ዜጎች እገታና የደህንነት ስጋት በማስወገድ የዜጎችን
የመንቀሳቀስ ሕገ መንግስታዊ መብት የማስጠበቅ መንግስታዊና ሕጋዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
የበላይ ጠባቂ አባቶች
የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም