>

የአዲስ አበባ ነዋሪን ለማስራብና ለማንገላታት የሚደረገው ኢ- ሰብዓዊ የቤት ፈረሳ ዘመቻን እንቃወማለን!!!

የአዲስ አበባ ነዋሪን ለማስራብና ለማንገላታት የሚደረገው ኢ- ሰብዓዊ የቤት ፈረሳ ዘመቻን እንቃወማለን!!!

በባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በኦህዴድ ብልፅግናው ቡድን የሚመራው የኦሮሙማው ሥርአት አዲስ አበባን እና አዲስ አበቤነትን ቢቻል ለማጥፋት፣ ካልሆነለት መልኳን እና ማንነቷን ለመቀየር፣ ካልሆነም ታሪካዊ ገፅታውን ለማደብዘዝ ቀን ከሌሊት እኩይ ተግባሩን እየሠራ ይገኛል።  ብዙ ገንዘብ፣ ቁሳቁስና የሰው ጉልበት የፈሰሰባቸውን የከተማዋን ነባር ቅርሶች፣ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች በጭካኔ በማፍረስና በብልጭልጭ ግንባታ በመቀየር የአዲስ አበባን ማንነት ለመለወጥ እየተጣደፈ ነው።   ለበርካታ ዘመናት በተከታታይ ትውልዶች የጋራ ጥረት ተገንብታ እዚህ የደረሰችው ከተማችን አዲስ አበባ ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚጠፋ፣ የሚለወጥ ወይም የሚደበዝዝ ታሪክ እና ማንነት የላትም።  ይህን መረዳት የማይችለው በነገድ ፖለቲካ የሚመራው የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥት ይዞት የተነሳውን የኦሮሙማ የፖለቲካ ዓላማ  ለማሳካት የአዲስ አበባን ታሪካዊ ይዘት የመቀየር  ሥራውን ተያይዞታል። ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ልዩ መለያ እና ምልክት በሆኑት፣ በፒያሳ፣ በአራት ኪሎ፣ ግንፍሌ፣ በምስማር ፋብሪካ፣ በመገናኛ፣በሜክሲኮ፣በወሎ ሠፈር መስመር እና በሌሎችም የከተማዋ ሰፈሮች አለርህራሄ ነባር ቤቶችን እና ህንፃዎችን ሳይቀር በማፈራረስ ላይ ይገኛል። በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዛፍ ችግኞች በመትከሌ ልሸለም ይገባል በማለት የሚኩራራው የኦሮሞማው መንግሥት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ሳይራራ ከነሥራቸው በዶዘር እየነቀላቸው ይገኛል፡፡
በከተማው ውስጥ እየተካሄደ ያለው የማፍረስ ዘመቻ ለነባር ነዋሪዎቿ ከፍተኛ ድባቴ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡ በቀጥታ መኖሪያ ቤታቸው፣ የንግድ ቤታቸው በአካባቢያቸው ለዘመናት የገነቡት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስራቸው ከሚፈርስባቸው ንብረት ጋር አብሮ ከሚጠፋባቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተመጫሪ፣ ለየአካባቢው የቀድሞ ትዝታ ያላቸው ነዋሪ ዜጎች በመላ ምን ታመጣላችሁ እየተባሉ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
በ2011 ዓ.ም ተሻሽሎ የፀደቀውና ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 በቀዳሚነት አንድ ይዞታ እንዲለቀቅ የሚደረገው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚሰራ ስለመሆኑ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለህዝብ ነሮ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዋፅኦ ሲኖረው፣ እንዲሁም ለአካባቢው የጎላ ማህበራዊ ፋይዳ ሲያበረክት እንደሆነ በአዋጁ ተመላክቷል፡፡ በአዋጁ መሰረት አፍራሽ ግብረ ሃይሉ ፈረሳውን ከማካሄዱ ከአንድ ዓመት በፊት ነዋሪዎችን ማወያየት ይጠበቅበታል፡፡
የሚሰራው ሥራ አስቸኳይ ነው ቢባልም እንኳን ነዋሪዎቹ ከመነሳታቸው ከስድስት ወራት በፊት ውይይት መደረግ እንዳለበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ደንብ ቁጥር 447/2012 አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀፅ 5 ይደነግጋል፡፡ በሕጉ መሠረት ማወያየት አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ነዋሪው የሚለቀው ይዞታውን ብቻ ሳይሆን፣ ሃብቱን፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ ትስስሩን ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ትዝታውን ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ የሚሄደው ወደ አዲስ ሕይወት፣ የኑሮ ትግልና በዘመናት ኑሮ የገነባው እንደ እድር ያሉ ማህበራዊ ተቋሞች ወደ ሌሉበት አዲስ ሠፈር እንደመሆኑ፣ በመፈናቀሉ ምክንያት የሚከፈለው ዋጋ ለብልጭልጭ ግንባታ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ስለመሆኑ አምኖ መቀበል ይኖርበታል፡፡ ይህ ሰብዓዊ አስተሳሰብ ለኦህዴድ/ብልፅግና የኦሮሙማው አገዛዝ ትርጉመ የማይሰጥና በባልጩት ድንጋይ ላይ ውሃ እንደማፍሰስ ቢቆጠርም፣ለሪኮርዱ ሲባል አባባሉ ተከትቦ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡
በሀሰት የታሪክ ትርክት ላይ ተመርኩዞ፣ ከተማዋ ኦሮሞን መምሰል አለባት ከሚል እሳቤ በመነሳት በአማራ   ጠልነት ላይ ብቻ በተመሰረተ  “ዕውቀት” በአዲስ አበባ ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት በየጊዜዉ እያጠናከረው ይገኛል። ወትሮም “በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ስለ አለኝና አዲስ አበባ የኔ-ብቻ አንጡራ ሀብት መሆን አለባት” በሚል የጠባብ እና ፅንፈኛ ብሔረተኛ አስተሳሰቡ በአዲስ አበቤው እና በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እተጠላ የሄደው የኦህዴድ-ብልፅግና አገዛዝ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአንዳንድ ደጋፊዎቹ ሳይቀር እየተወገዘ ይገኛል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጂ የማንም ነገድ/ብሔረሰብ የግል ንብረት እንዳልሆነች በተደጋጋሚ ሲሞግት ቆይቷል። አሁንም እየሞገተ ይገኛል። የኦህዴድ-ብልፅግናው ፓርቲ አሽንፊያለሁ በሚለዉ የ2013 ምርጫ ላይም ሳይቀር ባልደራስ  አዲስ አበባ በንጉሡ ጊዜ እንደነበረው 122,000 ሄክታር ይዞታዋ እንደተጠበቀ የ“ራስ ገዝነት መብት” እንዲኖራት የሚለውን ጥያቄውን እንደዋና የምርጫ የክርክር ርዕስ  በማድረግ በምርጫው ወቅት ታግሎበታል። ይሁንና የ2013ቱ ምርጫ በገዥው ፓርቲ አምባገነናዊ ጫና የታጀበ እና ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ሳይሆን አልፏል፡፡ በዚያም ምክንያት  ፓርቲያቸን ለአዲስ አበባ ወጥኖት የነበርው እቅድ  በወቅቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ለአዲስ አበቤው ነዋሪ እና ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ባልደራስ ከምስረታው ጀምሮ ይዞት የተነሳውን ዓላማ ከግብ የሚደርስበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ባልደራስ ያምናል።
የኦህዴድ/ብልፅግናው መንግሥት የተጣባውን ከተማን የማፈራረስ አባዜ ባልደራስ በጽናት በመቃወም የአቋም መግለጫውን እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡
1. የኗሪውን ማህበራዊ ህይወት በማናጋት ህዝባዊ አንድነቱን ለመበታተን የሚካሄደውን ኢ- ሰብዓዊነት የተላበሰውን የአዲስ አበባን ነዋሪ ከየአካበቢው የማፈናቀል እኩይ ተግባር ባልደራስ አጥብቆ ያወግዛል፤
2. መላው የአዲስ አበባ ህዝብ፣ በዘመናት ሂደት ከገነባኸው መኖሪያ እና የንግድ ቤት ሲያፈናቅልህ  አይሆንም በማለት በጋራ ሆነህ ተቃውሞህን እንዳታሰማ ይጠይቃል፤
3. የሚዲያ አካላት፣ የኦሮሙማውን አገዛዝ አዲስ አበባን የማፈራረስ ተግባር ዋና አጀንዳችሁ አድርጋችሁ እንድታስተጋቡ ያሳስባል፤
4. በመንግሥት ተቋማት የምትሠሩ፣ የኦሮሙማው መንግሥት በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው በደል በተለያየ መልኩ በናንተም ላይ እየደረሰ በመሆኑ፣ ህገ ወጥ ተግባራት በሚፈፀሙበት ጊዜ በዝምታ ከማለፍ ይልቅ በጋራ በመሆን ተቃውሟችሁን እንድታሰሙ ይመክራል፤
5. ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት፣ በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መፈናቀል ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመሆኑ፣ ይህ እኩይ ድርጊት በትክክለኛ ገፅታው በዓለም ደረጃ እንዲጋለጥ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡
6. አዲስ አበባ የተገኘባቸው በመላው ኢትዮጵያውያን ላብና ጥሪት በመሆኑ፣ ይህ በአዲስ አበባ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመ ጥቃት መሆኑን ተገንዝቦ መላው ህዝብ የተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይጠይቃል፡፡
ባልደስራ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
    መጋቢት 10/ 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic