>
5:16 pm - Saturday May 24, 9597

የአማራ ሕዝብ ደመኛ ጠላቶቹን አምርሮ በመታገል ዘላቂ ነጻነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል!

የአማራ ሕዝብ ደመኛ ጠላቶቹን አምርሮ በመታገል ዘላቂ ነጻነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል!

(ከምስራቅ አማራ ፋኖ ዕዝ የተሰጠ መግለጫ)
ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አማራን የመስበር ፖለቲካ በሰፊው ተሰርቶበታል፡፡ በዚህም አማራን በሕዝብ ብዛት ቁመቱን መቀነስ፣ በግዛት ወሰን ግዛቱን መቀማት፣ በኢኮኖሚያዊ አቅም ጥሪቱን በውረስና በመዝረፍ፣ በአገር ግንባታ ተሳትፎ ሂደት ከማግለል አልፎ አጠቃላይ ሕዝባዊ አቅሙን በመምታት አማራ ለማጥፋት ከሁለት ትውልዶች በላይ ተሰርቶበታል፡፡ ይህን ለዘመናት የቀጠለ የጥፋት ፕሮጀክ ለሰላሳ ሦስት ዓመታት በውክልና ያስቀጠለው ብአዴን፣ አማራን ለመስበር በተደረጉ ጥረቶች ሁሉ ቀዳሚው ተዋናይ ሆኖ የሕዝባችን ደመኛ ጠላት መሆኑን ደጋግሞ አሳይቶናል፡፡
ትላንት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) አገልጋይ፤ ዛሬ ደግሞ የኦሕዴድ ብልጽግና አሽከር ሆኖ አማራን የመስበር የጥፋት ፕሮጀክት አስፈጻሚ ሆኖ የቀጠለው ብአዴን፣ የአማራ ሕዝብ በከፈለው መስዋዕትነት ያስመለሳቸው ግዛቶቹን ከጠላቶቹ ጋር በዓይን ጥቅሻ በመግባባት ለዳግም ባርነት አሳልፎ እየሰጠው ይገኛል፡፡
ለሰላሳ ዓመታት በትሕነግ ወረራ ስር የነበሩት ራያ፣ ኦፍላ ኮረም፣ ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ነጻ የወጡ ታሪካዊ የአማራ ርስቶች ቢሆኑም በኦሕዴድ ብልጽግና ፍላጎት፣ ለቅኝ ገዥው ትሕነግ ዳግም አሳልፎ እየሰጠ ያለው የአማራ ሕዝብ የምንግዜም ጠላት የሆነው ብአዴን-ብልጽግና ነው፡፡ ይህን ለማስፈጸም በሰሜኑ ጦርነት ባለውለታ የነበሩ አደረጃጀቶችና ተቋማትን የመበተንና የማፈራረስ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
መቼውንም ቢሆን ታሪክ የማይዘነጋው ጀብዱ የፈጸመውን የአማራ ልዩ ኃይል በከንቱ ያፈረሰው፣ የአማራ ሕዝብ መዳኛ መስመር የሆነው የአማራ ፋኖ ላይ የብልጽግና ጦር ያዘመተው፣ የአማራ ተቆርቋሪዎችን በአካል፣ በሥነ-ልቦናና በኢኮኖሚ የማድቀቅ ዘመቻ፣ ወዘተ የተከፈተው አማራን ለመስበር ጊዜው አሁን ነው በሚል እምነት ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ የገጠመውን የህልውና አደጋ በመቀልበስ ህልውናውን ለማስከበር ቆራጥ ተጋድሎ ማድረጉን ተክትሎ፣ አገዛዙ ተፍረክርኮ ሊወድቅ ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡
አማራ በተጋድሎው ሊሰብሩት ያሰቡትን እንደጎመን እየቀነጠሰ፣ እንደአረም እየነቀለ፣ እንደቆሻሻ ከመንገዱ እያጸዳ ወደማይቀረው የድሉ ጫፍ በሚገሰግስበት በዚህ የታሪክ መታጠፊያ ምዕራፍ ላይ ከኋላው ለማስወጋት ራያና አካባቢው በትሕነግ ወራሪ ዳግም እንዲወረር ተደርጓል፡፡ ባለፈው መጋቢት 19/2016 በአበርገሌ ፃታ፣ ኮረም እና በራያ አላማጣ ቀበሌዎች ጨጓራ ኮሲም፣ ማሮ፣ዓዲ እደጋ የሚገኘው ህዝባችን የዐቢይ አሕመድ ሠራዊት ድጋፍ ባለው መልኩ በትሕነግ ታጣቂዎች ዘረፋ፣ ግድያና ወረራ ሲፈጸም መንግሥት ተብየው ያደረገው አንዳች ነገር አልነበረም፡፡
በመቀጠል መጋቢት 20/2016 በአዲስ መልክ ራያ ባላ ወረዳ ቀበሌዎች ውስጥ ዶዶታ፣ ማሩ፣ ዳርአይታ፣ ባሶ፣ ጦርነት ሲከፍት በመተሳሳይ ሁኔታ የብልጽግና ሠራዊት የሽፋን ድጋፍ ሰጥቶታል፡፡ ይህ ቅንጅታቸው እያደገ መጥቶ ሚያዚያ 6 እና 7 የራያ አላማጣ አማራ ግዛት ላይ ዳግም ወረራ ፈጽሟል፡፡ ትሕነግ ይህን ወረራ የፈጸመው በዐቢይ አሕመድ ፍቃድ፣ በብአዴን ታዛዥነት እንደሆነ የምስራቅ አማራ ፋኖ ያምናል፡፡ የምስራቅ አማራ ፋኖ ከዚህ ቀደም ከትሕነግ ጋር በተደረገው ጦርነት ከፊት ተሰልፎ በከፈለው መስዋዕትነት ዕዙ በተሰማራበት ቀጠና ያለው ራያ እና ኮረም ቀጠና ነጻ እንዲወጡ የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል፡፡
ዛሬም የአማራን ሕዝብ ለማጥፋት ኦህዴድ ብልጽግና በከፈተው ጦርነት ከሌሎች ወንድም የፋኖ አደረጃጀቶች ጋር በመናበብ የህልውና ትግሉን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጅ የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል የማይቀለበስ ደረጃ መድረሱን ተከትሎ ከጀርባችን እንድንወጋ ከታሪክ የማይማረውን ትሕነግ ለዳግም ወረራ ራያና አካባቢውን እንዲወር ተደርጓል፡፡
እንደ ምስራቅ አማራ ፋኖ በአማራ እና በትግራይ ሕዝብ መካከል ዳግም ወደግጭት ላለመግባት ከፍተኛ ጥንቃቄ ስናደርግ ቆይተናል፤ አሁንም ጥንቃቄ ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡ ይሁን እንጅ በትሕነግ ተደጋጋሚ የስሌት ስህተት የራያ አማራ ሕዝባችን ለዳግም ባርነት ተላልፎ እንዲሰጥ አንፈቅድም፡፡ በመሆኑም፡- የራያ አማራ ህዝብ የመጥፋት አደጋ ውስጥ መሆኑን እንድትረዱ እያሳሰብን ታሪካዊ የትግል ጥሪያችንን እንደሚከተለው እናስተላለፋለን፡-
1) የአማራ ሕዝብ በብአዴን መሪነት የሚመጣ ውርደት እንጅ ነጻነት የሌለ መሆኑን ካወቀ ውሎ አድሯል፡፡ ይሁን እንጅ በዋና ዋና ከተሞች የሚታየው መዘናጋት ዋጋ የሚያስከፍለን በመሆኑ ዘላቂ ነጻነቱን ለማረጋገጥ ፍጹም መራራ ትግል በማድረግ ትግሉን ማቀጣጠል አለበት፡፡ የአማራ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ ወደእናት ግዛቶቹ የመለሳቸውን እነ ራያ ወልቃይትን አሳልፎ እየሰጠ ያለውን ብአዴን፣ ገጠር ከተማ ሳይል የፈራረሰ መዋቅሩን ጨርሶ ግብዓተ መሬት ለማስገባት ሁሉም በያለበት እንዲፈንን (ፋኖ እንዲሆን) የትግል ጥሪያችንን እናቀርባለን!
 2) የትግራይ ሕዝብ ከአማራ ሕዝብ ጋር እስከመጨረሻው ድረስ ደም ከመቃባት ይልቅ ሁኔታዎችን ቆም ብሎ እንዲመለከት ጥሪያችንን እያቀረብን፣ ሁልግዜም ቢሆን መሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎችን የመገምገም ችግር ያለበት፣ በዚህ የስሌት ስህተት የተከበረውን የትግራይን ሕዝብ ዋጋ እያስከፈለ ያለው ትሕነግ የጀመረው የወረራ እንቅስቃሴ በጊዜ ካልተገታ ውሎ አድሮ የትግራይን ሕዝብ የበዛ ዋጋ እንደሚያስከፍለው አውቆ ድርጅቱ ከዚህ ራስን የማጥፋት ተግባር እንዲታቀብ እያሳሰብን የተከበረው የትግራይ ሕዝብ ከፍትሐዊው የአማራ ሕዝብ ትግል ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን!
በዚህ አጋጣሚ በቀደመው ጦርነት የተፈጠረውን ሁለተናዊ ቀውስ መፍታት የሚያስችል፣ የሕዝብ ለሕዝብ መተማመኖችን የሚያሳድር ነገን አሻግሮ የሚመለከት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የመፍትሄ ሀሳቦችን መጠቆም ከአማራ እና ከትግራይ ልሂቃን እንደሚጠበቅ ማሳሰብ እንወዳለን፤
3) የአማራ ሕዝብ የገባበት የህልውና ጦርነት ተገዶ ስለመሆኑ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰወረ አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብ የጅምላ ግድያና መፈናቀል የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ህልውናን አደጋ ውስጥ የሚከት ብሔራዊ የደህንነት አደጋ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተግባር እያየው ነው፡፡ ይህን ብሔራዊ አደጋ ለመቀልበስ የምናደርገውን ፍትሐዊ ትግል በመደገፍ መላው ኢትዮጵያዊያን ከጎናችን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን!
4) በአገዛዙ መዋቅር በተለይም በጸጥታና ደህንነት ውስጥ ያላችሁ የአማራ ተወላጆችና የአማራ ትግል አጋር የሆናችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ ከዚህ የደም ግብር ከለመደ፣ ጦርነትን የሥልጣኑ ማስቀጠያ ካደረገ አገዛዝ ነጻ ወጥታችሁ ሕዝባዊ ትግላችንን እንድትቀላቀሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን! ከትላንት ምሽት ጀምሮ ዘጠኝ መቶ ሰባ የሚሆን የራያና አካባቢው ሚሊሻዎች የምስራቅ አማራ ፋኖ ዕዝን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ ይህን አርዓያ በመከተል በፌዴራል፣ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ የጸጥታና ደህንነት አካላት በሕዝብ ትግል እየተቀበረ ያለውን አገዛዝ ጥላችሁ ሕዝባዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን!!
5) በሁሉም ቀጠና የምትገኙ ወንድም የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች እና አባላት የጀመርነው የህልውና ተጋድሎ በአጭር ግዜ ፍሬማ ሆኗል፡፡ በዚህ ትርጉም በሚሰጥ መስዋዕትነታችን የአገዛዙን መዋቅር በመናድ ነጻ መሬት መፍጠር ተችሏል፤ ሆኖም ግን ትግሉ ከዚህ በመረረ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በመሆኑም ከበባ ውስጥ የገባው የአማራ ሕዝብ ከበባውን በመስበር ዘላቂ ነጻነቱን ለማስከበር ከየአቅጣጫ የተከፈተውን አማራዊ ጥቃት በአንድነት ለመመከት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም ለበለጠ ግዳጅ ዝግጁ እንድትሆኑ ጥሪ እናቀርባልን!
6) ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የትህነግን ወረራ በማውገዝ አካባቢው ወደማያባራ ቀውስ እንዳይገባ አስፈላጊውን ክትትል እንዲታደርጉ ይህንንም የአማራ ዲያስፖራ እንደተለመደው የትግሉ አካል አድርጎ ሁኔታዎችን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እንዲያስረዳ የትግል ጥሪያችንን እናቀርባለን!! ሕጋዊና ፍትሐዊ የማንነት ትግል የትም ቦታ ተሸንፎ አያውቅም!
የምስራቅ አማራ ፋኖ ዕዝ ምስራቅ-አማራ
ሚያዚያ 08 ቀን 2016 ዓ.ም.
Filed in: Amharic