>
5:26 pm - Saturday September 15, 8621

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት ጎጃም ዕዝ ምስረታን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት ጎጃም ዕዝ ምስረታን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲከ መቀንቀን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እኛ አማሮች በሀሰት በጨቋኝነት ስንወነጀል ቆይተናል። ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ ባለፉት 50 አመታት ደግሞ ከውንጀላም በዘለለ በፖለቲካው መድረክ ሲገላበጥ የቆየው ዶሴ የፖለቲካ ፍርድ አግኝቷል። ይኸውም አማራ ከሌሎች ነባር ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በመሰረታት ሀገሩ ባይተዋር ብሎም ተሳዳጅ እንዲሆን ማድረግ ነው። በዚህም ፊውዳል እየተባለ የፖለቲካ ሥልጣን ተካፋይ፣ የምጣኔ ኃብት ተጠቃሚ እንዳይሆን ተደርጓል። ከዚህም በዘለለ በዓለማዊም ሆነ መንፈሳዊ የተራቀቁ ሊቃውንቱ እየተመረጡ በነሲብ ተገድለውብናል። ሃይማኖቱ በግላጭ፣ ባህሉና ታሪኩ ደግሞ በስውር እንዲጠፉ ተሠርቶበታል። የ17 ዓመቱ እንቅስቃሴ በቀጣዩ ስርዓትም ተባብሶ አማራ ትህምክተኛ እየተባለ በነፃ አውጭዎች በይፋ በጅምላ ይጨፈጨፍ ጀመር። ጭፍጨፋውን ለማስቆም እንቁ የአማራ ልጆች ሰማዕት ሆነዋል። አሁንም የባሰው መጣ! 

ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ ነፍጠኛ እየተባለ በጅምላ ተጨፍጭፎ እስላም ክርስቲያን ሳይባል በአንድ ጉድጓድ በጅምላ መቀበሩ ቀጥሏል። አማራ በኦሮሙማው ስርዓት የመንግሥት መዋቅርን በመጠቀም የዘር ፍጅት እየተፈፀመበት ይገኛል። በዚህም ባለፉት አራት አመታት ብቻ  በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አማሮች በብሄራቸው ብቻ ተነጥለው በጅምላ ተጨፍጭፈዋል። ከወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ ብቻ ሚሊዮን አማሮች ተፈናቅለዋል። በመሆኑም በትጥቅ ትግል ራስን ከመከላከል የዘለለ አማራጭ ባለመገኘቱ የአማራ ፋኖ ከጨፍጫፊው ስርዓት ጋር እየተዋጋ ይገኛል። ካፕቴን መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ እኛ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት ጎጃም ዕዝ መስራች ፋኖዎችም ትግሉ ወደ ሽምቅ ውጊያ ብሎም መስመራዊ ውጊያ እንዲያድግ በማድረግ ስንታገል ቆይተናል። ከሀምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ከሰራዊታችን ጋር በመሆን ጠላትን እየተዋጋን እንገኛለን። 

በመሆኑም ትግላችን የያዘውን መደበኛ ድርጅታዊ አካሄድ አሳድጎ መጓዝ ያለበት በመሆኑ ቀደም ብለው የተደራጁ ብርጌዶቻችንን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ዕዙን መስርተናል። ዕዙ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በታላቁ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት አካል ሲሆን በጎንደር፣ በወሎ – ቤተ አማራ እና በሸዋ እየተዋጉ ካሉ ጓዶቻችን ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በሕብረት ይሠራል። በሁሉም የአማራ ጠቅላይ ግዛቶች የምንገኝ ፋኖዎች ፊታችንን በሕብረት ወደ አዲስ አበባ እንድናዞር ብሎም ቤተ መንግሥቱን እንድንቆጣጠር የአማራ ፋኖ ጎጃም ዕዝ አበክሮ ይሠራል። 

ርዕያችን የአማራን በሕይዎት የመኖር መብት ማረጋገጥ ብሎም ሕዝባችን እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከቁጥሩ ተመጣጣኝ የፖለቲካ ውክልና እንዲያገኝ፣ ከሀገሪቱ ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ እና ማህበራዊ መገለል እንዳይፈፀምበት ማስቻል ነው። የኢትዮጵያን አንድነትና የግዛት ኢ-ተነጣጣይነት ማረጋገጥ ነው።  

ተልዕኳችን የአገዛዙን ሰራዊት ድል አድርጎ አራት ኪሎ እምዬ ምኒልክ ቤተ መንግሥትን መቆጣጠር ነው። ይህንን ለማሳካት ከብአዴን እና የጥቅም ተጋሪዎቹ በስተቀር ሁሉም አማራ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ትብብሮችን ማድረግ ይገባዋል። በመሆኑም ከዚህ ቀደም በየአውደ ውጊያው ስናደርጋቸው የባጁ ቀጣናዊ ትስስሮችን አጠናክረን በአንድነት ወደ ጋራ ቤታችን እንገሰግሳለን። 

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት ጎጃም ዕዝ ይህንን ያሳካሉ ያላቸውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመራሮችን ሰይሟል። በዚህ መሰረት፦ 

 ✓ ፋኖ መቶ አለቃ ካፕቴን ማስረሻ ሰጤ፤ ሰብሳቢ

 ✓ ፋኖ ዶ/ር እንዳላማው ጤናው፤ ም/ሰብሳቢና የአስተዳድር ጉዳዮች ሓላፊ

 ✓ ፋኖ ይታያል ጌታቸው፤ በም/ሰብሳቢ ማዕረግ የመገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ሓላፊ

 ✓ ፋኖ ኢንጂነር አሻግሬ ባዬ፤ የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊ

 ✓ ፋኖ ደስታ ይበልጤ፤ ም/የዘመቻ አዛዥ

 ✓ ፋኖ ኢንጂነር ከፋለ አለሙ፤ የገንዘብ አስተዳድር ሓላፊ

ሆነው ተሰይመዋል። 

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት ጎጃም ዕዝ

ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. 

መነሻችን አማራ፤ መድረሻችን የኢትዮጵያ አንድነት!

Filed in: Amharic