>

‹‹አልሞትኹም ብዬ አልዋሽም››

‹‹አልሞትኹም ብዬ አልዋሽም››

ከይኄይስ እውነቱ

የዛሬውን ርእስ የተዋስሁት ‹‹አርሙኝ›› ከሚለው የራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው መጽሐፍ ውስጥ ካለ አንድ ጽሑፍ ነው፡፡ እናንተዬ! አመዛኙ የዐዲስ አበባ ሰው ምን ነካው? እነዚህ ሥጋ የለበሱ አጋንንት በሚገርም ሁናቴ መተንፈስ እስከሚከለክሉት ድረስ ራሱን ለባርነት አመቻችቷል፡፡ በሚያሳፍር ደረጃ ቦቅቧቃ ያደረገው ምን እንደሆነ ለማወቅ ተቸግሬአለሁ፡፡ ኅብረት የሚለው ቃል ከአብዛኛው ዐዲሳቤ መዝገበ ቃላት የተወገደ ይመስላል፡፡ በፋሺስቶቹ ሥርዓቶች ላለፉት 50 ዓመታት የተሠራውን ወኔ የመስለብ፣ የማደንዘዝ፣ ግዴለሽ፣ ብሎም አድርባይ የማድረግ ተከታታይ ትውልድን የማምከን ድርጊቶች መፈጸማቸው ይታወቃል፡፡ ችግሩ ግን የምንደረድራቸው ምክንያቶች ሁሉ ነፃ አያወጡንም፣ አይጠቅሙንም፣ አያድኑንም፡፡  

በትናንትናው ዕለት (ግንቦት 2 ቀን 2016 ዓ.ም.) አንድ የቅርብ ወዳጄ በጉርብትና የሚያውቃቸው ሰዎች አያት ያርፉና አስከሬናቸውን ወደ ቀደሞ ሺዋ ክ/ሃገር ጉራጌ አውራጃ ለመሸኘት መገናኛ ከሚገኘው እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አስከሬን አውጥተው እዛው አካባቢ ያለ የሐዘንተኞቹ ቤት ይወስዳሉ፡፡ ሥርዓቱ የሽኝት ነውና ሊያስተዛዝን የመጣውን ወዳጅ ዘመድ እህል ውኃ ለማለት ዝግጅት አድርገው ነበርና አስተናጋጆች የጣት ውኃ ሲያቀርቡ ኹለት ፖሊሶች ወደ ሐዘንተኞች ቤት ቀርበው እጅ ማስታጠቡም ሆነ ለሐዘን ጉዳይ መሰባሰብ በሕግ ተከልክሏልና ባስቸኳይ አቁማችሁ እንድትበቱኑ፤ አሻፈረኝ የምትሉ ከሆነ ደግሞ ሠላሳ ሺህ ብር ትቀጣላችሁ ብለው ይነግሩአቸዋል፡፡ ጉድ በል ሺዋ!!! አትሉም፡፡ አንድም የተቃወመ ወይም የምን ሕግ ብሎ የጠየቀ ወይም ከፈለጋችሁ ክሰሱን የሚል ሰው አልተገኘም፡፡ ሰዉ እንደተለመደው ዞር ብሎ እያጉረመረመ ወደ መጣበት ተመለሰ፡፡ 

ጎበዝ! እኔን ያስገረመኝና ያሳዘነኝ እንዲሁም የበሰጨኝ የፋሺስታዊው አገዛዝ ድርጊት አይደለም፡፡ ሐዘንተኞቹ እና አስከሬን ለመሸኘት የተሰባሰበው የዐዲስ አበባ ነዋሪ ነው፡፡ የአገዛዙ ሰዎች ከፍጹም ፍርኀት የተነሣ በቁማቸው በሚጸዳዱበት ወቅት ነዋሪውም በቁም መቅዘኑ ምን የሚሉት ነው? በሕግ ከተከለከለ ምን ይደረጋል ያሉም አሉ፡፡ ኧረ የውርደት ጥግ! ኧረ ከሰውነት መውጣት? ምን ቀረን ታዲያ? ጠላትህ ሲቀዝን አንተም አብረህ የምትቀዝን አለሁ ትላለህ? ሞተው የተቀበሩት አይሻሉም?

ለመሆኑ የአገዛዙ ተላላኪዎች (ደናቊርት ‹ፖሊሶች›) ይህን የማስፈራሪያ መልእክት በሕግ ሽፋን እንዲያስተላልፉ ለምን ተፈለገ? ግምታችንን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡

1ኛ/ እንደተለመደው የሰዉን ልብ/ወኔ ለመፈተሽና በቀጣይም ያቀዱትንና የተዘጋጁበትን ፕሮጀክት ለመፈጸም፤

2ኛ/ በሌላ ወገን የአገዛዙ ሰዎች አለቀልን ብለው እየተደናበሩ በመሆናቸው ጥላቸውን እንኳን እየፈሩ (እየሸሹ) መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

አስከሬን ለመሸኘት የመጣው ሕዝብስ? በድፍረት ለመናገር የሚሸኘው ፈላጊ ‹አስከሬን› ሆኗል፡፡ ጨከንሁ ወይስ አነሰ? እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሲፈጥር በነፃነትና ባለ አእምሮ አድርጎ ነው፡፡ በደማዊት ነፍስ ብቻ ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት የለየን ዋናው ቁም ነገር ከእግዚአብሔር የተገኘች (ዐዋቂ፣ የምትናገርና ሕያዊት) ዘላለማዊት ነፍስ ገንዘብ ማድረጋችን ነው፡፡ ማሰብ፣ ማመዛዘን፤ መምረጥና መወሰን፣ ለውሳኔአችንም ኃላፊነት መውሰድ ነው፡፡ ይሄ አባባል ከሕፃናት (ሕፃናት አያውቁም ለማለት አይደለም፤ የብስለት ደረጃቸውን ለመናገር እንጂ) እና የአእምሮ ጤና እክል ካለባቸው በስተቀር በሁሉም ሰው ላይ ተፈጻሚነት አለው፡፡ 

ሰው ከዚህ ዓለም ድካም ሲያርፍ የሚፈጸመው የስንብት ሥርዓት ከአገር አገር፣ ከባህል ባህል፣ ከሃይማኖት ሃይማኖት ልዩነት ቢኖረውም በዋናነት በማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ሕግጋት የሚገዛ ጉዳይ እንጂ መንግሥት የተባለ ተቋም ሕግ የሚያወጣበት፣ ቅጣት የሚጥልበት አይደለም፡፡ በተለይም አሁን ያነሳነው ጉዳይ ከዓለማዊው ሕግ ጋር አንዳች ግንኙነት የለውም፡፡ ሕግ ሊወጣበትም አይችልም፡፡ ዛሬ ‹መንግሥት›፣ ሕግና ሥርዓት በሌለባት ኢትዮጵያ በፋሺስቱ አገዛዝ ባለሥልጣን ነን የሚሉ ‹በሽተኞች› በቃዡና ፍርኀታቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸው የሚጽፉት ቀላጤ ደብዳቤ ሁሉ ከላይ እስከ ታች ባሉ የፖለቲካና አስተዳደራዊ መዋቅሮች እንደ ሕግ እየተቆጠሩ ነው፡፡ 

እግረ መንገዴን አንድ ተመሳሳይ ሁናቴ ላንሳ፡፡ በቅርቡ ባንድ ወረዳ ውስጥ የሚሠራ ‹በሽተኛ› የብአዴን ካድሬ፣ ወዳጄ የሆነ ግለሰብ ከቤተሰቡ ጋር ኃላፊ ሆኖ በሚኖርበት ግቢ ያለው የቀበሌ መኖሪያ ቤት ውስጥ የገጠመውን ሕገ ወጥ አሠራር አጫውቶኛል፡፡ ካድሬው፣ ወዳጄና ቤተ ሰቡ ተከራይተው (ከ40 ዓመታት በላይ የኖሩበት ቤት ነው) ከሚኖሩበት ግቢ ገብቶ መንግሥት የቤት ችግርን ለማቃለል በሚያስተዳድራቸው ቤቶች ውስጥ ግቢ/ቦታ ካለ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን በመመዝገብ ግቢ ባለበት ሁሉ ቤት እየሠራ ለማስገባት በወሰነው መሠረት ይህም የመንግሥት ቤት ስለሆነ ግቢው ውስጥ ቤት ሠርተን ሌላ ሰው እናስገባለን ይላል፡፡ የቤተሰቡ ኃላፊም በሕግ እንደማይቻል አስረድቶ አስፈላጊ ከሆነና የቤት እጦትን ችግር እንደሚያቃልል ከታመነበት (ግለሰቡ ባያምንበትም) ባንድ ቤተ ሰብ የተያዙና ግቢ ያላቸው የመንግሥት መኖሪያ ቤቶችን ኪራይ ቤቶች የሚያስተዳድራቸውን ጨምሮ ዓዋጅ በማውጣት ካሬ ሜትሩን ወስኖ ከነባር ይዞታው ላይ መቀነስ እንጂ በነባር ነዋሪ ሰላምና ጸጥታ ላይ ሁከት መፍጠር ተገቢ አይደለም፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የቤት ችግርን የአንድ ግለሰብ ዜጋ መብትን በመግፈፍ ሊፈታ አይቻልም ብሎ እንደመለሰለት፤ ከዚህ ውጭ ያለው አሠራር ጉልበት መሆኑን እንደነገረው አሳውቆኛል፡፡ ጉዳዩ በዚህ አልቋል ማለት ግን አይደለም፡፡ ካድሬውም እኛ በቀላጤ ትእዛዝ ከተሰጠን በቂ ነው፡፡ በዚህ ላይ በመንግሥት ቤት እንደፈለግን ማዘዝ እንችላለን እንዳለው ማለት ነው፡፡ የቤቱ ባለይዞታዎች ኋላ ላይ ጉዳዩን ሲያጣሩ ግቢያቸው ውስጥ ቤት ሊሠራ ያሰበው ይህ አገር አጥፊ የብአዴን ካድሬ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ 

በእኔ እምነት በተጠቀሰው ጉዳይ (ልቅሶ ቤት አትስብሰብሰቡ፣ ለማስተዛዘንም ማዕድ አትቀመጡ የሚለው ነውረኛ ትእዛዝ) ላይ ሕግም ሆነ ቀላጤ ደብዳቤ የለም፡፡ አገር የሚገዙት ምናምንቴዎች በመሆናቸው ሕግ ወጥቷል ብለን ብናስብ እንኳን የሐዘንተኞቹም ሆነ አስከሬን ሊሸኝ የመጣው ሰው ከፖሊሶቹ ጋር ሳይጋጭ ሊያደርግ የሚችለውን ዝቅተኛ ርምጃ መውሰድ አልቻለም፡፡ ይኸውም አሁን የበሰለ ምግብና ውኃ አዘጋጅተናል፡፡ ሰዉን በተለመደው ሥርዓት እንሸኛለን፡፡ እንደተባለው ሕግ ካለ በሕጉ መሠረት የሚጣልብንን ክፍያ በፍርድ ቤት ሲወሰንብን የምንከፍል ይሆናል ብሎ ፖሊሶቹን ማሰናበት ይቻል ነበር፡፡ መቼም ሠላሳ ሺህ ብር ያሉትን (ያልተረጋገጠውን) አሁኑኑ ለኛ አስረክቡ የሚሉ ከሆነ መለዮ ያደረጉ ዘራፊዎች በመሆናቸው ቤሳ መስጠትም አይገባም፡፡ 

ለማጠቃለል ከእንስሳት በታች ሆነን ወራዳ ሕይወት ከምንመራና ራሳችንን ከነውረኛው ብአዴን ጋር ከምናመሳስል ዐዲስ አበቤዎች ሆይ ‹ሰው› ሁናችሁ የክብር ሞት መሞት ይሻላችኋል፡፡ ‹አልሞትሁም ብዬ አልዋሽምም› ኑሮ ሆኖ!!! ይልቁንም ይህን የከረፋ ፋሺስታዊ አገዛዝ ለማስወገድ ትንሽ ድፍረት እና ኅብረት ብንፈጥር የእኛንም መከራ፣ የወንበዴውን አገዛዝ ዕድሜም በማሳጠር ነፃነታችንን ማቅረብ እንችላለን፡፡ በቤተሰብህ የምታሳብብ የዐዲስ አበባም ሆነ የቀረኸው ኢትዮጵያዊ ነፃ አውጪ ሳትጠብቅ ልጆችህ በሰላምና ነፃነት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ከፍለህም ቢሆን እንድታዘግጅላቸው ታሪክ አደራ ጥሎብሃል፡፡ ያለ መከራ ጸጋም ሆነ ነጻነት የለምና፡፡

Filed in: Amharic