>

የፋኖን ሥም ይዞ የባንዳውን ብአዴን የሎሌነት ፍልስፍና ማስፈፀም አይቻልም!

የፋኖን ሥም ይዞ የባንዳውን ብአዴን የሎሌነት ፍልስፍና ማስፈፀም አይቻልም!

 

በ ትግሉ ሠመረ 

 

ፋኖ አስረስ ማረ በቅርቡ የጎጃም አማራ ፋኖ ስር የተመረቁ  ፋኖዎችን ለማስመረቅ  ባደረገው ንግግር   በቀጥታ ሥም ባይጠራም የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት አመራሮችን የቀድሞ አጋር  ታጋይ ወንድሞቹን እነ ማስረሻ ሰጤንና  ታላቁ እስክንድር ነጋን  ለረጅም ደቂቃ  ሲያብጠለጥል ተሰምቷል። ማብጠልጠሉ ሳይበቃው ትግሉን የጎተቱ  ባላቸው በነማስረሻ ሰጤ ላይ  አዲስ የተመረቁ ፋኖዎች ቃታ ከመሳብ እንዳይመለሱ ሲያሳስብ ለሰማው ጆሮን ይሰቀጥጣል።

  ፋኖ አስረስ  ምን ለማግኘት ይኽንን ንግግር እንዳደረገ ለጊዜው ባይታወቅም ንግግሩን  ሲጨርስ  ሃሳቡ የእሱ ብቻ ሳይኾን የመሪው ዘመነ ካሴ መኾኑን  መናገሩ ደግሞ ጉዳዩን  እጅግ አስደንጋጭ ያደርገዋል።  ይኽ ሃሳብ በርግጥ እውነት የዘመነ ካሴም አስተሳሰብ  ከኾነ እጅግ አደገኛና  የአማራ ህዝብ ወገኑን የመኖር ህልውና ለማረጋገጥ ቤቱንና ንብረቱን ጥሎ የወጣውን  ፋኖ እርስ በርሱ የሚያጋድል ጥንስስ ሃሳብ  ተደግሷል ማለት ነው። ይኽ ክፉ ጥንስስ ሃሳብ  እግር አውጥቶ ከፍተኛ ቀውስ ከመፍጠሩ በፊት  በሁሉም  ፋኖ አመራሮች ጊዜ ሳይሰጥ ሊወገዝ የሚገባው ነው። ማንኛውም ነገር ሲጀመር መነሻው ሃሳብ ነው ያለው አስረስ  ‘ፋኖን ከፋኖ’ የሚያጋድል ሃሳብ ማመንጨቱ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በቅጡ ያጤነው አይመስልም።   ምንም አይነት ቅራኔ በፋኖዎች መካከል ቢነሳ ችግሮችን ለመፍታት ሳይታክቱ ጥረት ይደረጋል እንጂ፣ አንዱ ባንዱ ላይ ጠመንጃ እንዲያነሳ መቀስቀስ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።   

ፋኖ የተሰማራው የአማራን ህዝብ ህልውና ትግል  ለማቀጣጠልና ህዝቡ  እየደረሰበት ካለው የህልውና አደጋ ብሎም ኢትዮጵያን ከክፉ ዘረኛ አውሬ እጅ አላቆ ወደ ቀድሞ ክብሯና ታሪኳ ለመመለስ  እንጂ የአካባቢ ንጉሶችን ለመፈልፈል አይደለም። እርጉሙ ብአዴን የአማራውን ህዝብ ላለፉት ሠላሳ አምስት አመታት ሲያስቀጠቅጥ የኖረ የኾድ አምላኪ ዝቃጭ ስብእና ባለቤቶች ስብስብ እንደመኾኑ አሁንም ቢኾን  የበታች የአገልጋይነት አስተሳሰቡ ያልተላቀቀ መሰሪና አደገኛ ቡድን ነው።  ብአዴኖችን የሚገዛቸው ሥልጣንና ከሥልጣን ጋር ተያይዞ የሚገኝ መናኛ የኾነ የቁስ ሰቀቀን የወለደው ጥቅም ብቻ ነው። በሀገር ውስጥ ያሉትም ኾኑ በውጪ ያሉት ብአዴኖች  የአማራ ህዝብ ስቃይ የነገዱ አሁንም ፋኖ ተነቃንቆ  ከአውሬው የኦሮሙማ ቡድን ጋ ግብግብ ገጥሞ በሚፋለምበት ሰዓት ለአውሬው  ዋና መሳሪያ በመኾን  የአማራ ፋኖን ለመከፋፈልና ለማስመታት የማያደርጉት ጥረት የለም።  

አስረስ ማረ የተናገረው ‘ፋኖ ፋኖን’ እንዲመታ የሚያበረታታ ሃሳብ ከአንድ እውነተኛ ፋኖ የሚመነጭ ሳይኾን ከከርስ አምላኩ የብአዴን ስበስብ ብቻ ሊኾን እንደሚችል መገመት እንደ አስረስ (self-proclaimed intellectual) ምሁር መኾንን አይጠይቅም። በመኾኑም የአስረስ ማረ ንግግር፤ በተለያዩ ፋኖዎች እነ አስረስ የብአዴን ተስፈኞች ናቸው እየተባለ ሲነገር የነበረውን  ጥርጣሬ፣ ወደ እውነትነት የሚቀይረው ይኾናል።   እንዲኽ ያለው የነ አስረስ ሃሳብ ለአውሬው ሥልጣን መራዘም  በር መክፈት ብቻ ሳይኾን የአማራን ፋኖ ታሪክ የሚያጠፋ ከዚኽ ቀደም ያልነበረ  ባንዳዊ አስተሳሰብም ነው። ባንዳነት በኢትዮጵያ ታሪክ የነበረ ክፉ የታሪክ ገፅታ ነው። አሁንም ቢኾን ሀገሪቷን የተቆጣጠሯት   በዘር የተደራጁ ባንዶች  ናቸው።  ከነዚኽ ባንዶች ጎን በዋነኛ ሎሌነት እያገለገለ ያለው ደግሞ ባንዳው ብአዴን ነው። እነ አስረስ ማረ አካኼዳቸው ከገባቸው ባንዳዊ አካኼድ እየሄዱ ነው። 

ባንዳውን ብአዴን አማክረው አማራውን ነፃ ማውጣት እንደማይችሉ አሁኑኑ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።  በዚህ አካሄዳቸው ከቀጠሉ በባንዳነት መፈረጃቸው የማይቀር ነው። የፋኖን ሥም ይዞ የባንዳውን ብአዴን የሎሌነት ፍልስፍና ማራመድ አይቻልም።  ባንዳው ብአዴን አሁንም ቢኾን ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው የነአስረስ ማረ አስተሳሰብ ምስክር ነው። ይኽ የብአዴን ተጽእኖ ማስፈፀሚያ  ዋነኛ መሳሪያው ደግሞ ከአማራው ህዝብ በሥልጣን ላይ እያሉ የዘረፉት ገንዘብ ነው።  ብአዴኖች የቢዝነስ ኢምፓየር የዘረጉ ብራሞች ናቸው።  እንደ ሕወሀቶች መላው ሀገሪቷን መዝረፍ ባይችሉም አማራው አናት ላይ ተደላድለው አማራውን በዝምታ በያለበት ከማስጨፍጨፍ ባሻገር ሃብቱን  ዘርፈው አዘርፈውታል።  አሁን በፋኖ ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር እየጣሩ ያሉት ከህዝቡ የዘረፉትን ብር በመርጨት ነው። ብአዴን እነ ፋኖ ዘመነንና ፋኖ አስረስን በጎጃም ምድር ያላቸውን ከፍተኛ ተቀባይነት  መሳሪያ አድርጎ በመጠቀም በመላው የአማራ ጠቅላይ ግዛት  የተቀጣጠለውን የህልውና ትግል የ’አማራ ጥያቄዎች’ ይመለሱ  ወደሚል የተለሳለሰ   አውሬውን ለማዳን የሚያስችል የእርቅ ጥሪን የሚጋብዝ ፕሮፖዛል  በመቀየር ትግሉን ለመጥለፍ  የማይፈነቅለው ድንጋይና የማይረጨው ገንዘብ እንደማይኖር ሳይታለም የተፈታ ነው።  

የቢዝነስ መረቡን   እስከ ውጪ ሀገር ድረስ   የዘረጋው ብአዴን    ‘መነሻችን አማራ መዳረሻችን አማራ’ የሚል አማራዊ ኢትዮጵያዊ አርበኝነትን  የሚያጣጥል የአናሳ አስተሳሰብ (minority mindset) በአማራው ላይ እንዲሰርፅ ለማድረግ  በውጪ ሀገር በሚገኙ በአካባቢና በጎጥ የተሰባሰቡ ብአዴናውያን ቡድኖች በመጠቀም  እየተረባረበ ይገኛል። እውነተኛው ፋኖ ያነገበውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ  ብአዴንን ሊፀየፈውና እስከወዲያኛው ሊያስወግደው ይገባል እንጂ በብአዴን ሊሸነገል አይገባም። 

ከብአዴን ጋር መነካካት ትርፉ እራስን ማስበላትና ትግሉ በእርቅ ሥም በአውሬው መዳፍ ውስጥ ገብቶ እንዲከሽፍ ማመቻቸት ነው። ከዚኽ ቀደም ብአዴን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አ.ብ.ን) አመራሮችን እንዴት በገንዘብና በሥልጣን ደልሎ ለአውሬው እንዳስገበራቸው የሚዘነጋ አይደለም። ብአዴን ጀነራል አሳምነው ጽጌን የመሰለ ጀግና  አሳልፎ የሰጠ የአፍረተ ቢስ  ስብስቦች ቡድን መኾኑንም እነ ዘመነና አስረስ ማረ ሊዘነጉት አይገባም። በመኾኑም  እነ ዘመነም ከብአዴን ጋር ያላቸውን ንክኪ አቁመው  በፊት ህዝቡ ይሰጣቸው ወደነበረው የአታጋይነት  ማማ ላይ ለመቀመጥ መሥራት ይኖርባቸዋል።  ነገር ግን   አሁን እየተነገረባቸው  ያለው ከነሱ ሃሳብ ጋር ያልተስማሙ መሪ ቃላቸውን ‘መነሻችን አማራ መዳረሻችን የኢትዮጵያ አንድነት’ ያደረጉት  በጎጃም የሚንቀሳቀሱ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት ፋኖዎችን  የማሰርና የማሳደድ ድርጊት እየፈፀሙ ከኾነና ከቀጠሉበት የህዝብን አመኔታ እስከወዲያኛው የሚያጡበትና በባንዳ ብአዴንነት የሚፈረጁ ይኾናል።   ከዚኽ ጋር በተያያዘ  እነ አስረስ ማረ  ከፋኖ እስክንድር ነጋ በተፃራሪ መቆም የለየለት ባንዳነት መኾኑን ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል።  ከታላቁ እስክንድር ነጋ ጋ አጉል ፉክክር ውስጥ መግባት እራስን ትዝብት ውስጥ ከመጣል ያለፈ ጥቅም አያስገኝም። 

እንደ እስክንድር ያለ የህዝብ ከበሬታንና ተቀባይነትን (earned respect) ለማግኘት እስክንድርን ኾኖ መገኘትን ይጠይቃል።     እስክንድር ነጋ የአንድ አካባቢ ወይም የአንድ ጎጥ ዝንባሌ የሌለው የመላው አማራ ህዝብ ባህል፣ እምነት፣ አርበኝነት፣ ጨዋነት፣ ጥበብ፣ ሀቀኝነትና የጀግንነት  ታሪክ  የወለደው  ብርቅዬ የኢትዮጵያ ጀግና ነው።  ምሁራዊ አድርባይነት እንደ እውቀት ተንሰራፍቶበት በነበረበት ወያኔ ሠራሽ የፖለቲካ ምህዳር፣  እስክንድር ምሁራዊ ግዴታውን  ለ30 ዓመታት ሳያቋርጥ በከባድ መስዋዕትነት የተወጣ ጀግና ምሁር ነው። ሌላው በትግሉ ዙሪያ አጽነኦት ሊሰጠው የሚገባው  ከምንም በላይ አማራው ከወታደራዊው ድል ባሻገር ፖለቲካዊ ድልን መጎናጸፍ እንደሚጠበቅበት መገንዘብ ነው።   መላው የአማራ ፋኖ እስክንድር ነጋን  የትግሉ ማእከላዊ ምሰሶና አርማ አድርጎ በመነሳቱ   ከወታደራዊው ድል በተጨማሪ የፖለቲካውን ድል  ከወዲኹ  እየተጎናፀፈ  መኾኑን መረዳት ያስፈልጋል። አማራው ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ ጥንት አባቶቹ ጀግናውን ማክበር የመስማትና መከተል ሃላፊነት አለበት። እውነተኛ ጀግናውን ለይቶና አውቆ የማያከብር ህዝብና ትውልድ ብዙ ዋጋ እንደሚከፍል ያለፈው ግማሽ ምእተዐመት የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ነው። 

አይደለም እራሱን ሀገሩ ኢትዮጵያን የማዳን አቅምና እድል  የነበረው የአዲስ አበባ ህዝብ በተገቢው ሰዓት ቪዥነሪ ከኾነው ከታላቁ እስክንድር ነጋ ጎን ቆሞ አውሬውን ለመታገል ባለመቻሉ፤  በአሁኑ ሰዓት ሃብታም፣ደሃ፣ ነጋዴ፣የመንግሥት ሠራተኛ ሳይል  አቅሙን መጠቀም ያቃተው፤ አቅመ ቢስ  ኾኖ    የኑሮ፣ የመፈናቀል፣ የመሰደድ፣ የማንነት አሻራውን የማጣት  ውርጅብኝ  እየወረደበት ይገኛል። በሌላ በኩል የአማራ ፋኖ እስክንድር ነጋን ይዞ መነሳቱ በአዲስ አበባ ህዝብ ዘንድ ምንም ብዥታ የሌለው ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል። አሁን አዲስ አበባ ላይ ካለው ከፍተኛ የህዝብ ምሬትና በፋኖ ላይ ተስፋውን መጣል አንጻር፤ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ሠራዊት የፋኖን ሥም ይዞ የባንዳውን ብአዴን የሎሌነት ፍልስፍና ለማስፈፀም ከሚሯሯጡ ኃይሎች እራሱን አጥርቶ  የህልውና ትግሉን ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር በማስተሳሰር አውሬውን በአነስተኛ መስዋዕትነት  ከአራት ኪሎ የምንሊክ ቤተ-መንግሥት የማሰናበት  ሥራውን መጀመር ይጠበቅበታል። 

ድል ለአማራ ፋኖ፣ ለነ  እስክንድር ነጋ!

Filed in: Amharic