>
5:26 pm - Monday September 15, 6577

ከአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የተሰጠ መግለጫ !

እስካሁን ባሳለፍነው የነፃነት ትግል ከጠላት ጋር ከወታደራዊ የነፍጥ ትግል ባሻገር የጠላትን የፖለቲካና የሚዲያ ዘመቻዎችን ተቋቁመን በአሸናፊነት ትግላችንን በድል እየቀጠልን መሆኑ ይታወቃል ። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ላይ በመደበኛ ጠላቶቻችን የመንግስት ስርዓት እና ተልዕኮ ተሸካሚዎች አንዳንድ የጠላት አጀንዳ አራጋቢ ቅጥረኛ ሚዲያዎች የሚራገበውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ ለህዝባችንና ለመላው ደጋፊዎቻችንና የትግሉ ባለቤት ህዝብ ግልፀኝነትን ለመፍጠር ሲባል ባለ 5 ነጥብ ዝርዝር የአቋም መግለጫ አስቀምጠናል ።
 1ኛ. የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ራሱን ችሎ ከበረሃ ጀምሮ በፖለቲካዊ የትጥቅ ትግል ራሱን በማደራጀት ጠንካራ ዕዝ የገነባ ሲሆን አሁን በትግል ከሚገኙት የአማራ ፋኖ ዕዝ የአንበሳውን ድርሻ ከሚወስዱት መካከል ነው ። ስለዚህ የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ራሱን ችሎ የቆመ ጠንካራ ክፍለ ጦሮችና ብርጌዶችን ያቀፈ በአለት ላይ የተመሠረተ በዓለም ህዝብ የሚታወቅና በጠላት የሚፈራ የጦር አደረጃጀት በመያዝ በአርበኛ መከታው ማሞ ጦር መሪነት እየተመራ የመጣና ያለ እንዲሁም ተቋማዊ አሰራርን የሚከተል መሆኑን እያሳወቅን ከዚህ ውጪ ጠላት የሚያራግበው ማንኛውንም በተቋሙ እና በተቋሙ አመራሮች ላይ የሚሰነዘሩ የጠላት አጀንዳዎችን ተቋሙ የማይቀበላቸውና የማይገልፁት ከመሆኑም ባሻገር  የአማራን ህዝብ ትግል ለማጓተት ሆን ተብሎ ትግሉን ለመጥለፍና ለማስጠለፍ የተቀነባበረ የጠላት ሴራ መሆኑን እንገልፃለን ።
 2ኛ. የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ከአማራ ፋኖ ህዝባዊ ሠራዊት ጋር እንደማንኛውም የአማራ ፋኖ ታጋይ አጋር ድርጅት እንጂ የህዝባዊ ሠራዊቱ አካል ያልሆነና ህዝባዊ ሠራዊቱም በራሱ አደረጃጀት የሚመራ ተቋም መሆኑን እንገልፃለን ።
 በመሆኑም የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ከሌሎች ዕዞች በተለየ መንገድ ከህዝባዊ ሠራዊቱ የገንዘብም ሆነ ማንኛውም ድጋፍ በልዩነት የተደረገለት የሚደረግለት አለመሆኑን እናሳውቃለን ።
 3ኛ. የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ከሌሎች መስራች ድርጅቶች ጋር በመሆን በአማራ ህዝብ ሲጠበቅና ሲጓጓለት የነበረውን አንድ መሪ የሆነውን አማራዊ ድርጅት መስርተናል ። በመሆኑም ቀሪ የሃሳብ ልዩነት አለን የሚሉ የፋኖ አደረጃጀቶች ጋር ልዩነታችንን በማጥበብ በአንድ የአማራ ድርጅት ውስጥ ሆነን ለመታገልና ለማታገል እንዲሁም የአማራን ህዝብ የህልውና አደጋ በአጭር ለመቋጨት ተቋሙ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል ።
 4ኛ. እንደሚታወቀው ትግሉ ውጫዊ ፈተናዎች እንዳሉት ሁሉ ውስጣዊ ፈተናዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መጥተዋል ። በእኛ በኩል እስካሁን በመጣንበት መንገድ ዘርፈ ብዙ የስም ማጥፋት ዘለፋዎች ሲደርሱብን ፤ ለህዝባችን ክብር ስንልና ትግሉ ሊኖረው የሚገባ የራሱ ምስጢር በመኖሩ ብዙ መሠረታዊ ክፍተቶችን እያየን እንኳን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከመሻት ባለፈ ታሪክ የሚዘግበው ሁነት እንደሆነ ተረድተን የአማራን ህዝብ ክብር ላለማሳነስ “የፋኖን ስም ፋኖ አያጠፋውም ” በሚል ቀናኢነት በተሞላበት ሁኔታ በብዙ ትዕግስት ታግሰን አልፈናል ። ነገር ግን “ዝንጀሮ ቂጧ አይታያትም ” እንዲል ብሂሉ ከሚያወሩት በላይ የምናወራው ነውርና ጥፋት በመረጃና በማስረጃ ይዘን ሳለ ከጠላት ብልፅግና የማንጠብቀው መግለጫና እንደመስሳለን የሚሉ የዘወትር ፉከራዎች እንኳን እየሰማን አደባባይ መውጣት ያልፈለግነው ለአባቶቻችን የቃል አደራ ለህዝባችን ክብር ስንል ብቻ እንደሆነ ማሳወቅ እንወዳለን ።
 “ከአማራ ህዝብ ክብር የሚበልጥ ክብር የለንም” ። የምንሰራውን እኛ እናውቃለን ፤ የምንሰራውንም መሬት ላይ ያለው ህዝባችን ያውቃል ። ወንድሞቻችንን እንዲሰድቡ ብለን የምንቀጥረው (lobbyist) የለንም ። ቀጣሪዎች የሚፈልጉት ትግሉን ሳይሆን ስልጣን ነው ያንን መሠል ሂደቶች ደግሞ በዚህ አይነት መንገድ አይሳኩም  ።
 5ኛ. በውጭ ሃገር የምትገኙ የአማራን የህልውና ትግል የምትደግፉ ወንድም እህቶቻችን የምታደርጉትን የትግል ተሳትፎ በእጅጉ እናበረታታለን ። እንዲሁም ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረብን አሁንም ለሚደረገውና እየተደረገ ላለው የህልውና ትግል ከአማራ ህዝብ ጎን እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን ።
 ድል ለተገፋው የአማራ ህዝብ ክብር ለትግሉ ሰማዕታትና አርበኞች አማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ሃምሌ 25/2016 ዓ.ም
Filed in: Amharic