>
5:26 pm - Saturday September 15, 9945

‹‹እነ አባ ለከርሡ››

‹‹እነ አባ ለከርሡ››

ከይኄይስ እውነቱ

በአገር ውስጥም ይሁን በዝርወት ለምትገኙ ለኢትዮጵያ ርትዕት (ኦርቶዶክስ) ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ፤

አሁን አሁን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የቤተ ክህነቱ ጉዳይ አልቆለታል ብለውና ተስፋ ቆርጠው እጅና እግራቸውን አጣምረው የተቀመጡ ይመስላል፡፡ ለፍቶ ያገኘውም ሆነ በዝርፊያ ጥሪት የያዘው ምእመን  ለቀማኞች ገንዘቡን ከመስጠት ግን አልተቆጠበም፡፡ ከሞት ከስደት የተረፉት ሊቃውንትም ‹ጎመን በጤና› ብለው የተቀመጡ ይመስላል፡፡ ለማን ትተው? በተኩላ ላስጨረሱት ምንደኞች፣ ከቤልሖር ጋር ኅብረት ፈጥረው ላደነዘዙት ለእነ ‹አባ ለከርሡ› እና ለርጉም ዐቢይ ቅጥረኛ ካድሬዎች ትተው፡፡ ልክ የዐዲስ አበባ ሕዝብ ተወልዶ ያደገባትን፣ በዕድሩና በዕቁቡ÷ በጽዋና በሻይ ማኅበራቱ ተሳስሮና ተጋምዶ÷ ተባብሮና ተሳስቦ ማኅበራዊ ሕይወት የኖረባትን፣ ተምሮ ለቁም ነገር የደረሰባትን፣ ሠርቶ የሚተዳደርባትን፣ ተኩሎ የተዳረባትን፣ ልጅ ወልዶ ያሳደገባትን፣ አርጅቶ የሚጦርባትን፣ ሙቶ በማዕርግ የሚቀበርባትን፣  ከየክፍላተ ሀገሩ ተሰባስቦ መኖሪያ ቤቱ ካደረጋት ወገኑ ጋር ወጥቶ ወርዶ በጋራ ያቀናትን መናገሻ ከተማውን ለማጅራት መቺዎች ትቶ ለባርነት ተመቻችቶ እንደተቀመጠ ሁሉ ማለት ነው፡፡ 

ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ የሚል የርእሰ መጻሕፍቱ ቃል እንዳለ እናውቃለን፡፡ አገር ከሚያጠፉ፣ ሕዝብን በእምነቱና ማንነቱ ለይተው የዘር ማጥፋትና ጅምላ እልቂት ከሚፈጽሙ አረመኔ ዓላውያን ጋር እጅና ጓንት ሆነው ከሚሠሩ፣ በተለይም በራሱ በሕይወት ባለቤት እንዲጠብቁት ሰማይ ሩቅ አደራ ጥብቅ ተብለው የተሰጣቸውን ምእመን ለግማሽ ምእት ዓመት በተኩላዎች ሲያስብሉና አሳልፈው ሲሰጡ የኖሩ፣ ቤተ ክርስቲያንን የቀማኞችና የወንበዶች ዋሻ ያደረጉ ሐሳውያን መነኮሳት እና ሳይገባቸው በልዩ ልዩ ማዕርጋት ለሚጠሩ ‹‹የቤተ ክህነት ሰዎች›› እምነትና ሥርዓት በመጠበቅ ሽፋን የምትሰጡት ያልተገባ ክብር አገርና የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንን ሊያሳጣን (አሁንም አሉ ብለን የምናምን ከሆነ) ተቃርቧል፡፡ ይህቺ አገራችን ኢትዮጵያ ከቆመችባቸው ዋነኛ አዕማድ ዋናዋ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ነን የምንል እስከ መቼ ነው ደንዝዘን አጥፊዎቿን ስናደልብና ስናሰባ የምንኖረው? ማኅበረ ሊቃውንቱ፣ ማኅበረ ካህናቱና ማኅበረ ምእመናኑ ጨርሶ ከሕሊናችን ተለያይተናል እንዴ? በተለይም ምእመናን እስከ መቼ ‹የበዓል ክርስቲያኖች› ሆነን ሲከፋን እያማንና ከንፈር እየመጠጥን፣ ጮሌ ‹ካድሬዎች› (በሽንገላ ‹ክቡር› በሚባባሉ አለቃና ጸሐፊ ተብዬዎች)  በሚያደርጉት  የጥፋት ንግግርና ‹ተውኔት› ሁሉ እልል እያለንና እያጨበጨብን የገዛ ቤታችንን ለወንበዴዎች አሳልፈን የምንሰጥ? መቼ ይሆን እንደ ባለ አእምሮ አስበን እውነተኛ አገልጋዮችን ከምንደኞች ለይተን ሀብት ንብረታችንን ለጥፋት ማዋል የምናቆመው? ለሌቦች ለቀማኞች ‹ትዳራችንን› ጭምር የምንሰጥ ስንቶች ነን? ጽድቅ እየሠራን ይመስላችኋል?

  ሊቁ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹አባ ለከርሡ›› የሚለውን ቃል ሥጋዊ ዓለማዊ መነኵሴ፤ ‹‹አባ አይረባ›› ርባና ቢስ፣ ፈሎ ቢስ፤ ዓለመኛ መነኵሴ በማለት ፍቺ ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ የደገኛ መነኮሳትንና ባሕታውያንን ስም ተሸክመው በተግባር ያራከሱ የዘመናችን ‹አባ ለከርሡ›ዎች ለዓለም ሕያው ለነፍስ ምውት የሆኑ አንዳንዶቹም ክህነታቸውን ያልጠበቁ የቤተ ክርስቲያን ጠንቆች ናቸው፡፡ እነዚህ በረዥም ቀሚስና አስኬማ ተደብቀው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለከርሣቸው፣ ሥልጣናቸውና ለግል ጥቅማቸው የሚጠቅሱ ግብዞች ‹ፈሪሳውያን› ከለየላቸው ከሀዲዎችና መናፍቃን የባሱ የጭቃ ውስጥ እሾኾች ሆነው ሊቃውንትና ምእመናን አገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዳይጠብቁ እግር ተወርች አስረውና አፋቸውን ለጉመው ይገኛሉ፡፡ ‹አባ ለከርሡ› በምንላቸው መነኮሳትና አውደልዳይ የቤተ ክህነት (ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤክ ያሉትን ያጠቃልላል) ሰዎች ውስጥ ዶግማና ቀኖና ጥሰው ጵጵስናን መቀለጃ ያደረጉ፣ ተወግዘው የተለዩና ቤተ መንግሥቱን ጥግ አድርገው ሰብረው የገቡ ‹ወንበዴዎች› ክህነት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ ከክርስቲያን ማኅበርም የተለዩ ግለሰቦች በመሆናቸው እነሱን አይመለከትም፡፡ እነዚህ የምዕራባውያን ቅጥረኛ ከሆነው ከርጉም ዐቢይ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የገቡ የአገዛዙ ሎሌዎች ናቸው፡፡ አባ ለከርሡዎቹ ግን ‹ብፁዕ› እየተባሉ የሚኩነሰነሱ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት አንስቶ በየአኅጉረ ስብከቱ፣ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ የነሱ ተወራጆችና ጉዳይ አስፈጻሚዎች ሆነው በልዩ ልዩ የማዕርጋት ስሞች እየተጠሩ የምእምናኑን ደም የሚመጡና ምእመናንና ሊቃውንቱን ስለ ቤተ ክርስቲያን አያገባችሁም በማለት ቤተ ክርስቲያናችንን የግል ኩባንያቸው ያደረጉ ኀፍረተ ቢስ ጉዶች ናቸው፡፡ በሚፈጸመው ጥፋት ከሊቀ ጳጳስ እስከ አናጕንስጢስ ተሳታፊ ሲሆኑ በዘመነ ወያኔ ቤተ ክህነቱን የወረሩት የወያኔ ካድሬዎች አሁንም ዋና ተዋናዮች መሆናቸው የቤተ ክህነቱን መዋቅር የሚያውቅ ሰው ይገነዘባል፡፡

ምእመኑ ምን ያህል ያውቅ እንደሆነ ርግጠኛ ባልሆነም ‹አባ ለከርሡ› ዎች ባሉበት ቦታ ያለ አገልግሎት ከሚያገኙት ጠቀም ያለ ‹ክፍያ›ና በቅጥርና በዝውወር ስም ከሚያደርጉት ቅጥ ያጣ ዝርፊያ በተጨማሪ በዐዲስ አበባ የሚገኙ አድባራትና ገዳማትን እንደ ግል ንብረታቸው ተከፋፍለው ‹የበላይ ጠባቂ› በሚል የሌብነት ሹመት በየአድባራቱና ገዳማቱ ካሉ የውስጥ ሰዎቻቸው (በተለይም ጸሐፊዎች፣ አለቆችና ሳይገባቸው በኃላፊነት ከተቀመጡ አውደልዳዮች) ጋር በመመሳጠር የቤተ ክርስቲያንን ቦታ በመሸጥ፣ በመለወጥ በማከራየት ከሌሎችም ‹የልማት ሥራ› ከሚባሉ ገቢዎች ቋሚ ድርሻ በማግኘት ቤተ ክርስቲያናችንን ‹በባለአክሲዮንነት› እየተቀራመቷት ይገኛሉ፡፡ በክብረ በዓላትም ሆነ በልማት ስም በዓውደ ምሕረቶችና በአዳራሾች የማይነጥፍ ጥገት ከሆነው ምእመን የሚሰበሰው ሀብት በአመዛኙ ለነ አባ ለከርሡዎች ሲሳይ እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህ ወያኔ ከተቆጣጠረው ቤተ ክህነት ጀምሮ አሁንም ባሉት አረማውያን አገዛዞች የቀጠለ ጥፋት ነው፡፡ ይህን የሀብት ዝርፊያ የማነሣው ክርስቶስ በደሙ የዋጀውን በሚሊዮን የሚቆጠር ክርስቲያን በተኩላ አስበልተው ከበረት ቤተ ክርስቲያን ወጥቶ እንዲባዝንና እንዲቅበዘበዝ ማድረጋቸው ሳይዘነጋ ነው፡፡ በዚህ ተግባር ውስጥ የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከቶቹ እነ የማነ ብርሃን (በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን የትግሬኛ ፕሮግራም ዜና አንባቢ የነበረው)፣ እነ ‹‹ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ›› ወዘተ. ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ለአብነት ጠቀስሁ እንጂ ንቅዘቱ የተወሰነ ነገድ/ጐሣ ወይም ዕድሜና ጾታ አይመለከትም፡፡ ኆልቈ መሣፍርት ናቸው፡፡ 

ምእመናንና ማኅበረ ሊቃውንት! እነ አባ ለከርሡ ስለ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ታሪክ፣ ቅርስና ፍትሐዊ አስተዳደር የሚጨነቁ ይመስላችኋል? ርእሰ መጻሕፍቱ ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም እንዳለ እነ አባ ለከርሡ ገንዘብን ‹አምላካቸው› አድርገው መርጠዋል፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንትና የቤተ ክርስቲያናችን ማኅበራት ተሰባስበው ጥናት በማድረግ በመንፈሳዊው አገልግሎትም ሆነ በአስተዳደር ረገድ ለዘመናት የተንከባለሉትን ሥር የሰደዱ ችግሮች ነቅሰው በማውጣት ከነ መፍትሔዎቻቸው ያቀረቡትን ሰነዶች የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ በጓጕንቸር ቊልፍ ከርችመውባቸው የቀን ብርሃን እንዳያዩ ያደረጓቸው፡፡ በተቃራኒው አገርና ቤተ ክርስቲያንን ፈጽሞ ለማጥፋት ሌተ ተቀን እየሠራ ካላ ሰይጣናዊ አገዛዝ ጋር ‹ምክረ አይሁድ› ሲፈጽሙ ይገኛሉ፡፡ አልፎ ተርፎም በሌለ መንፈሳዊና ሞራል ልዕልና ቀናእያን ምእመናንን፣ መምህራንና ሊቃውንትን በሚያሳፍር ሁናቴ መዝለፍና ማስፈራራት ተግባራቸው አድርገው ይገኛሉ፡፡ ሰው ውሎውን አይደል የሚመስለው?! ለመሆኑ እነዚህ ማን ሆነው ነው ምእመኑን ከዋናው አጀንዳ ለማናጠብ በማሰብ ምሕላ የሚያውጁት? ለአገርህ አንድነትና ሰላም አትዋደቅ፣ በእምነትና በነገድ ማንነትህ ሲያጠፉህ፣ ሲያፈናቅሉህ፣ ሲያዋርዱህና አገር አልባ ሲያደርጉህ ዝም ብለህ በባርነት ኑር የሚሉ፤ ቤተ ክርስቲያንህን አትጠብቅ፣ ለሰማዕትነት አትዘጋጅ፣ ካህናት ምእመናን ሲታረዱ፣ የአብነት ትምህርት ደቀ መዛሙርት በግፍ ሲገደሉ፣ አድባራትና ገዳማት ከነቅርሳቸው ሲቃጠሉ ሲወድሙ ዝም ብለህ ተመልከት የሚሉ፤ በዓላውያኑ ለተገደሉት ጸሎተ ፍትሐት የማያደርጉ፤ በሐዘን፣ በመፈናቀል፣ በጦርነት የተጎዳውን ምእመንና ባጠቃላይ በመከራና በስቃይ የሚገኘውን ሕዝብ የማይረዱና የማያጽናኑ ሆዳሞች ‹ቤታችን› ምን ይሠራሉ? በእነዚህ ላይ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በታላቁ መጽሐፍ እንደተመዘገበው ቤተ መቅደሴን የሻጮችና የለዋጮች÷ 

የወንበዴዎችና የቀማኞች ዋሻ አድርጋችሁታል በማለት ‹ያን ጅራፉን› የማያነሣ ይመስላችኋል?

በዐምሐራ ፋኖ በሚመራው የሕዝብ ትግልም ውስጥ ‹ሊቀ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ሊቃውንት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና ምእመናን አሉ› ፡፡ ለህልውና ለነፃነት ብሎም የአገርን አንድነት ለመታደግ የሚደረግ ትግል ባለቤት ሕዝቡ (ምእመኑ) ነው፡፡ በዚህም ረገድ በውስጥ በአፍኣ ያላችሁ ‹አባ ለከርሡዎች› (ባንዳዎች፣ ወጡ ሳይወጠወጥ የሥልጣን ፍትወት ያሰከራችሁ፣ ለልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም ለመገዛት ራሳችሁን ያመቻቻችሁ ካላችሁ) መወራጨታችሁ ከማዘግየት በስተቀር የትግሉን ዓላማና ግብ አያስቀረውምና ቢቻል ወደ ልቦናችሁ በቶሎ ብትመለሱ እና ዓፄ ምንይልክ ቤተመንግሥት የመሸገውን አጽራረ ኢትዮጵያና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ኃይል በቶሎ አስወግደን ለሕዝባችን እፎይታ እንድንሰጥ ወንድማዊ ጥሪዬ ይድረሳችሁ፡፡ አሻፈረኝ ካላችሁ ግን በአእላፋት (ሚልዮን) የሚቆጠር ሕዝብ ላለመጥፋት ቤት ንብረቱን ትዳር ልጆቹን ሳይል ፈንኖ ውጥቷልና፣ ‹አባ ለከርሡ›ዎችን አንጓልሎ/ትቶ ከግቡ መድረሱ ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው፡፡

አምላከ ኢትዮጵያ ለዐምሐራ ፋኖ አንድነት እና ኅብረትን ይስጥልን፡፡

ጠላቶቿን ደግሞ ከእግሯ በታች ፈጥኖ ያስገዛልን፡፡

Filed in: Amharic