ኢትዮ ሪፈረንስ በጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ወንድሙ ማረፍ የተሰማንን ሐዘን እየገለጽን ፤ ለቤተሰቡ መጽናናትንና የእርሱንም ነፍስ ፈጣሪ ከደጋጎቹ ጋር በ አፀደ ገነት ያኖርልን ዘንድ ምኞታችን ነው።
ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ወንድሙ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር አባል፣በነጻ ፕሬስ ውስጥ በልዩ ልዩ ጋዜጦች በመስራት በሙያው ሳቢያ ከእስር አልፎ ለስደት የተዳረገው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ወንድሙ ትላንት ምሽት በሚኖርበት ሳውዝ ዳኮታ በአቬራ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ጋዜጠኛ ዳንኤል ለረጅም ጊዜ ሁለት ኩላሊቱን በማጣት በህክምና ክትትል ላይ የቆየ ሲሆን አዲስ ምትክ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ቀዶ ጥገናው ተጠናቆ ኩላሊቱ መስራት ከጀመረ በኋላ ሊሻለው ባለመቻሉ ትላንት ምሽት በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 8 ሰዓት ላይ ሕይወቱ ማለፉን ሰምተን አዝነናል።’
ዳንኤል ቀደም ሲል ከየመን ስደት መልስ በአትላንታ በሙያው በሬዲዮ ላይ ጥቂት ጊዜ ተሳትፎ አድርጎ ትልቅ ሥራ ሰርቷል።
የመጨረሻ ሕይወቱ ማብቂያ በሆነው ሳውዝ ዳኮታ ሲፎልስ ከተማ ማዕዶት 90 የሚል ሚዲያ አቋቁሞ ከአገራዊ ጉዳይ በተጨማሪ ማህበረሰቡን ለማቀራረብ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት የከተማው ባለሥልጣናት ከኮሚኒቲው ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋጽዎ ማድረጉን በተደጋጋሚ ያወጣቸው በነበሩ መረጃዎች አይተናል። በወንድማችን ጋዜጠኛ ዳንኤል ወንድሙ ሞት የተሰማንን ሐዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቹ ፣ለወዳጅ ዘመዶቹ፣ለሙያ ባልደረቦቹና በሳውዝ ዳኮታ ሲፎልስ ላገለገለው ማህበረሰብና በሙያው ለታገለለት ወገኑ ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን ። ነፍስ ይማር የዳንኤልን አስቸጋሪ የተባለውንና ከሞት ጋር የተጋፈጠበትን የየመን ባህር ጉዞ ጨምሮ የቀደሙ ሥራዎቹን በጨረፍታ ባልደረባችን ታምሩ ገዳ ከአራት ዓመት በፊት በዚሁ ገጽ ያወጣውን አጭር ጽሑፍ የሙያ አስተዋጽዎውንና ከሞት ጋር የተፋጠጠበትን የስደት ጉዞ ጭምር ያስቃኛል።
ዳንኤል ገዛኸኝ:- ሞትን የተጋፈጠ ጋዜጠኛ…
ስደት ሲባል ስሙ አንድ አይነት ነው። በአውሮፕላን የተጓዘውም፣በእግሩ የኳተነውም፣በግመል ጀርባ ላይ ተፈናጦ በረሃ ያቆራረጠውም ፣ከተሰባበረ እንጨት በተሰራ ጀልባ አማካኝነት የባህር አውሬዎችን እና ማዕበለን ተቋቁሞ ካሰበው ስፍራ የደረሰው፣ ሁሉም ስደተኛ ነው።
ዳንኤል ገዛኸኝ ወንድሙ በአስቸጋሪው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ሙያቸውን በመተግበራቸው ፣ህገመንግስታዊ እና ሰብአዊ መብታቸው የሆነው ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን እውን ለማድረግ ሲሉ ከአገዛዙ ብርቱ መከራ እና እስራት ከገጠማቸው ፣ በስተመጨረሻም ለስደት ከተዳረጉ በርካታ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው።
በህወሐት /ኢህአዲግ አገዛዝ ለስድስት ጊዜያት ወደ እስር ቤት የተወረወረው፣በዋስትና እጦት እና በተንዛዛ ቀጠሮ ለእንግልት የተዳረገው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ምርጫ ግንቦት 97ዓም( 2005 እኤአ) ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጠሮ በነበረው እስራት፣ወከባ እና ሞት የተነሳ በሶማሊላንድ (ቦሳሶ ) በኩል ወደ የመን ተስዷል።
በ እርስ በርስ ጦርነት ከምትታመሰው የባህረሰላጤዋ አገር የመን ለአራት አመታት ከስድስት ወራት በችግር አረንቋ ውስጥ ቆይቶ የአትላንቲክ ውቅያኖስን በመሻገር ወደ አሜሪካ ያቀናው ጋዜጠኛ ዳንኤል እነዚያ አሳዛኝ ገጠመኞቹን የግንቦቱን ምርጫ ሰማእታቶችን እና ከእናት አገሩ የተሰደደበት ወረሃ ግንቦትን ለማስታወስ ሲል እኤአ 2012 ሲዋን/ሲቫን በተሰኝ ባለ 279 ገጽ፣ በአማሪኛ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፉ አማካኝነት ከልጅነት እስከ ስደቱ የገጠመው ውጣ ውረድን ለአንባቢዎቹ አቅርቧል።
ገመና፣ሞገድ በተባሉ እና መሰል የፕሬስ ውጤቶች ላይ በዋና አዘጋጅነት የሰራው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ አስቸጋሪ እና አስገራሚው የህይወት ጉዞው በዚህ ብቻ አላበቃም ። በ ሁለቱ ኩላሊቶቹ ላይ በደረሰበት ከባድ የኩላሊት ህመም ጋር እየታገለ የሚገኘው ጋዜጠኛ ዳንኤል ባለፈው የካቲት/ፌበርዋሪ 10,2020 እኤአ ወደ ሞት ጉዞ(Journey to Death) የተሰኘ 248 ገጾች ያሉት መጽሐፉን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለእንባቢዎች አቅርቧል።ለብዙዎች አስተማሪ ሊሆን የሚችለው አዲሱ መጽሐፉ በአሁኑ ወቅት በአማዞን፣ ራአኩተን ኬቦ ፣ባርናስ እና ኖብል በተባሉት ዘመናዊዬቹ የኤሌክትሮኒክስ መጽሐፍት አከፋፋዬች እና ሻጮዎች አማካኝነት በማዳረስ ላይ ይገኛል።
ታሪካችንን በሲኒማ ብናቀርበውስ?:-
ሙያውን በተመለከተ በተለይ ወደ ሞት ጉዞ/Journey to Death መጽሐፉን እንደ ሆቴል ሩዋንዳ፣ ሊሚቴሽን ጌም ፣ ኢን ቱ ዘ ዋይልድ፣ ላዋረንስ ኦፍ አረቢያ፣ አሜሪካን ስናይፐር የመሳሰሉት በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዙ ሲኒማዎች ወደ ስኒማነት ለመቀየር ጽነ ምኞት እንዳለው ገልጾ በእርሱ እና በብዙ ጓደኞቹ ላይ ከደርሰው ችግር ፣ መከራ እና እሸናፊነት ትውልድን ለማስተማር ካለው ጉጉት አኳያ ፣ ህልሙንም እውን ለማድረግ በሲኒማ ሙያ የተካኑ ወይም ለሆሊውድ እና መሰል የሲኒማ ኢንዱስትሪዎች ቀረቤታ ያላቸው ኢትዮጵያኖች በጋራ እንዴት መስራት እንደሚቻል፣ የምክር አገልግሎታቸውን እንዲለግሱት ተማጽኗል።
(ሐብታሙ አሰፋና ታምሩ ገዳ )