መዝሙረ ዳዊት እና መስቀሉ ለከሀዲነት መሸሸጊያ አይደሉም
ከይኄይስ እውነቱ
የዓፄ ምንይልክን ቤተ መንግሥት እጅ ሳያደርግ የሚቆም የዐምሐራ ፋኖ ትግል አልተጀመረምም፤ አይኖርምም፡፡
ልበ አምላክ ተብሎ የተመሠከረለት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመታት ገደማ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ያዘጋጀው (ሌሎችም ነቢያት ተሳትፈውበታል) መጽሐፍ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ኃላፍያትንና መጻእያትን የያዘ ቀዳሚና ታላቅ የጸሎት መጽሐፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንድ ክርስቲያን ዳዊት ደጋሚ ነው ማለት ጸሎተኛ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ባንፃሩም መድኅን ዓለም ክርስቶስ ዓለሙን በሙሉ ያዳነበት ቅዱስ መስቀልም የክርስትና ዋና ምልክትና የድኅነት መሣሪያ መሆኑም እንደዚሁ፡፡ ዳዊቱንም ማንገትም ሆነ ቅዱስ መስቀሉን ማሰር መልካም ነው፡፡ ጠንካራ እምነት ያለው ሠራዊት ለዓላማው እስከ ሞት የታመነ፣ ከፍተኛ የግብረ ገብና የሥነ ምግባር ልዕልና ያለው፣ ጨካኝ ሳይሆን እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጀግንነት (ጥብዐት) ያለው ነው፡፡ የዐምሐራ ፋኖም ይህንን በተግባር አስመስክሯል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ዳዊቱንና መስቀሉን አንጠልጥሎ የዞረ ሁሉ ግን እውነተኛ ክርስቲያን ነው ማለት አይደለም፡፡ ያለንበት ዘመን አለመታደል ሆኖ ዳዊቱም፣ መስቀሉም፣ ቀሚሱም፣ ካባውም፣ ጥምጣሙም፣ ቆቡም፣ አስኬማውም ወዘተ. ለሸፍጥና ማጭበርበሪያነት ሽፋን ሲውሉ ታዝበናል፡፡ ሰውን ለጊዜው ማታለል ቢቻልም ማእምረ ኵሉ (ሁሉን ዐወቂ) እግዚአብሔርን ግን ማታለል አይቻልም፡፡
ርእሰ መጻሕፍቱ እውነቱን ከሐሰት፣ ስንዴውን ከእንክርዳዱ የሚለይበት መንሽ ከፍሬአቸው ታውቃችዋላችሁ የሚለው ቅዱስ ቃል ሲሆን ይህም በሕይወት የሚታይ ፍሬ ምግባር ነው፡፡ ወንጌሉ መለያየትና ክህደትን ኀጢአት ብሎ ከሚዘረዝራቸው የሥጋ ሥራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ መለየትን የሚወድ ሰው ከንቱ ምኞቱን እንደሚከተልም ይናገራል፡፡ መለያየትንና ክህደትን ገንዘቡ ያደረገ ሰው የአምላክን እናት ስም በከንቱ ቢያነሣ፣ ዳዊት ቢሸከም፣ መስቀል ቢያንጠለጥል የዋሆችን ለጊዜው ሊያታልል ይችላል፡፡ አንድም አሳቡ በንግግሩ መካከል በሚሰነቅራቸው መርዛም ቃላቶች ሲለሚጋለጥ፤ አንድም ከወገኖቹ መከራ ይልቅ የንግሥና ፍትወቱ ልቡናውን ሰውሮት ስለሚያቅበዘብዘው፣ በሌላም መልኩ ተንኰሉና ክፉ ሥራው እየቀደመ ስለሚታይ ቁምጣውም፣ መስቀሉም ሆነ መጽሐፉ መደበቂያ ሊሆኑት አይችሉም፡፡ አንዳንዶቹም በፋኖ ስም ተሠማርተው ለትግል የወጡ ወንድሞቻቸውን እነ እገሌን አስፈላጊ ከሆነ ርምጃ ውሰዱባቸው በማለት ለፋኖዎች ክፉ ምክር በዐደባባይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ስለ እነ ማን እንደምንነጋገር ግልጽ ይመስለኛል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ‹ብረት› የሚያነሣ ኃይል ሁሉ ሕዝቡን እንደ ሰም አቅልጬ እንደ ገል ቀጥቅጬ፣ በእጄ ጭብጥ በእግሬ ርግጥ አድርጌ እገዛለሁ የሚለው ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብ አንድ ቦታ ላይ ሊገታ የግድ ነው፡፡ ከዚህ አዙሪት መውጣት ካልቻልን ከቀደሙት የሚያስንቁን ውሉደ አጋንንት መፈልፈላቸው የማይቀር ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዐምሐራ ሕዝባዊ ትግል ጥቂት አመራሮች ውስጥ ስንጥቃት መታየቱ ያደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ እንደ ድንገተኛ ደራሽ የመጣ ግን አይደለም፡፡ ስንጥቃቱ ግን የዐምሐራ ፋኖን ትግል ግፋ ቢል የሚያረዝም ሳንካ ቢሆን እንጂ የተነሣበትን ዓላማና ግብ ከፍጻሜ መድረሱን የሚገታ አይደለም፡፡ የዐምሐራ የህልውና ትግል ጥርት ያለ ዓላማና ግብ ይዞ የተነሣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከመነሻው ወያኔ ትግሬ እና ኦነግ/ኦሕዴድ እንዲሁም የሁለቱም ዘላለማዊ አሽከር ብአዴን ‹‹ክልል›› ብለው ከሰየሙት የአትድረሱብኝ አጥር ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የለውም፡፡ ቀዳሚ ትግሉ የህልውና (ከፈጣሪ በተሰጠው ጸጋ በሕይወት የመኖር መብት ማስከበር) ሲሆን እንቅስቃሴውም በአራቱ የዐምሐራ ክፍለ ሀገሮች (ጠ/ግዛቶች) ጀምሮ ዐምሐራው ሕዝብ የሚኖርበትን የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉ ይሸፍናል፡፡ የዐምሐራ ትግል ለአፍታ እንኳን ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ዝንፍ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ በመሆኑም ሁለተኛውና መዳረሻ ምዕራፉ የኢትዮጵያ አገራዊ ህልውና ወይም አንድነት ነው፡፡ በዚህኛው ምዕራፍ ውስጥ ከምድረ ገጽ ሊያጠፉት የተነሡትን እና ቅድመ አያቶቹና አያቶቹ ከሌላው ወገኑ ጋር በጋራ የገነቡአትን አገሩን ከዘረኛ ፋሺስታዊ ኃይሎች (አገዛዙን ከነመዋቅሩና አስወግዶ) ታድጎ፣ ማንም ስድ አደግ ተነሥቶ ለህልውና ሥጋት የማይሆንበትን፣ ለሁሉም ኢትዮጵያ እኩል የምትሆን፣ ዜጋው ሁሉ በፈቀደው ቦታ ተንቀሳቅሶ የሚኖርበትን÷ የሚሠራበትንና ሀብት የሚያፈራበትን፣ ዐምሐራው ሕዝብ ባገሩ ጉዳይ ባይተዋር ሳይሆን ተገቢውን ድርሻ የሚይዝባትን ኢትዮጵያ ማምጣት ነው፡፡
በመሆኑም ‹መነሻችን ዐምሐራ መዳረሻችንም ዐምሐራ› የሚል ግለሰብ ፋኖም ሆነ ቡድን ከዐምሐራ ሕዝባዊ ትግል ዓላማና ግብ ውጭ ነው፡፡ መነሻውም ሆነ መድረሻው ዐምሐራ የሚል አስተሳሰብ ብአዴናዊ ብቻ ሳይሆን የወያኔና ኦነግ/ኦሕዴድ የዘረኝነት ክልል መዋቅርን ያፀደቀ የአሽከርነት ጠባይ ነው፡፡ የዐምሐራን ሕዝብ ባጠቃላይ የዐምሐራን ፋኖ በተለይ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያማው ማንም ኃይል የለም፡፡ ዐምሐራነትና ኢትዮጵያዊነት ተለዋዋጭ ስሞች ናቸውና፡፡ በዚህ የልዕልና መንፈስ የሚመራ የዐምሐራ ሕዝብ ወያኔና ርጉም ዐቢይ እንደሚመኙት ጎንደር፣ ጐዣም፣ ቤተ ዐምሐራ ወሎ እና ሺዋ ብሎ በጎጥ የሚከፋፈል ሕዝብ አይደለም፡፡ ይህንን አሳብ የሚያራምዱ ካሉ ከጠላት ወገን የሚመደቡ ናቸው፡፡ የተከበራችሁ የዐምሐራ ፋኖዎች በሙሉ! ሁሌም በትግላችሁ ውስጥ ትልቁን ሥዕል – በየትኛውም አካባቢ የሚገኘውን የዐምሐራ ሕዝብ አንድነትና እንደ ደም ጅማትና አጥንት ሆኖ የሚያስተሳስረንን ኢትዮጵያዊነት – አንዘንጋ፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ የሚኖረው የዐምሐራ ሕዝብ አካባቢያዊ መገለጫዎች ቢኖሩትም አንድ ነው፡፡ ከሀዲ ባንዳነት የምንለው የከፋ ነውር በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ይኖራል፡፡ ለተለየ ነገድ/ጐሣ፣ ጾታ ወይም የትምህርት ደረጃ ተለይቶ የሚሰጥ አይደለም፡፡
እንደሚታወቀው የዐምሐራ ሕዝብ ጠላቶች በርካታ ቢሆኑም ዋናው ግን ብአዴን የተባለ በማይድን ነቀርሳ የተለከፈ ቡድን ነው፡፡ ደጋግሜ እንደምለው በዚህ የሙታን ስብስብ ውስጥ የሚገኙ በሙሉ ከሰውነት የጎደሉ ፍጥረታት ናቸው፡፡ ከዚህ ርጉም ስብስብ ተጸጽተን ተመልሰናል የሚሉ ግለሰቦች ቢኖሩ እንኳን ከዐምሐራ ትግል ጋር አንዳች ግንኙነት እንዳይኖራቸው አድርጎ ቀሳ አውጥቶ (quarantine አድርጎ) ማስቀመጥ የትግሉ ሀሁ ሊሆን ይገባል፡፡ በቃ ዘረ መላቸው (ዲ ኤን ኤ) ለዐምሐራ ጠላት የሚያደርጋቸው ሆነው እንደተሠሩ ማሰብ ወደ አጠገባችን እንዳይደርሱብን በሩቅ ማጠሪያ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዐዲስ መንግሥት ከመቆሙ በፊት በሚኖረው የሽግግር ዘመን በፈጸሙት ይቅርታ የማይደረግለት ነውር ልክ ፍርዳቸውን ሊያገኙ የሚገባቸው በመሆኑ፣ ‹ተመልሰናል› ያሉትን እምነት ሳይጥሉባቸው በዓይነ ቊራኛ እየተከታተሉ ከትግሉ በአፍኣ በሚኖሩበት ቦታ ማሰናበት ነው፡፡ እነዚህ ደናቊርት ብቅ ብለው በቀባጠሩ ቊጥር ዦሮ ሰጥተን ለምን እንደምናዳምጣቸው ሊገባኝ አይችልም፡፡ ለምን ደግመን ደጋግመን ባገዛዙ ወጥመድ ውስጥ እንገባለን?
ሌላው ጥንቃቄ የሚያሻው ሁሉም ፋኖዎች ለእኔ እኩል ናቸው በሚል የሚራመደው አስተሳሰብ ነው፡፡ ጠለቅ ብለን ሳናስብበት እንዳለ (at face value) በቅንንት ብንቀበለው አባባሉ ትክክል ይመስላል፡፡ አዎ! የማይተካ ሕይወታቸውን ለመስጠት ሁሉን ትተው የወጡ ወገኖቻችን በመሆናቸው፡፡ ከአመራሮችም ሆነ ከተራው ፋኖ ለትግሉ ጠንቅ የሆነ ካለ ወይም ከመነሻውም አድብቶ ጊዜ የሚጠብቅ ካለስ ወይም ከተፈጠረስ? በአንድ ዓይን ነው የምናየው ብለን እንቀጥል? በጭራሽ! ይህ ዓይነቱ እምነት የዐምሐራን ትግል ርጉም ዐቢይና ጀሌዎቹ እንዲሁም ወያኔና ጀሌዎቹ ብቻ ሲፈታተኑት ዘራፍ እንላለን፤ የውስጥ አፍራሽ ኃይሎችን ግን እንታገሣቸዋለን ወደሚል አደገኛ አስተሳሰብ ይወስደናል፡፡ እናስተውል! ጠላት ከውጭም ሆነ ከውስጥ ይነሣ ያው ጠላት ነው፡፡ እንደውም የበለጠ የሚከፋው ውስጥ ዐዋቂ ጠላት ነው፡፡ ገና ለገና የልዩነት ክፍተት ለፋሺስታዊው አገዛዝ ሠርግና ምላሽ ይሆናል በሚል አስተሳሰብ ብቻ የውስጥ ‹በሽታው› ነቀርሳ ሆኖ እስከሚያጠፋን እንጠብቅ ካልን የወገኖቻችንን ደም ከንቱ እናደርጋለን፡፡ ስለሆነም ሳይቃጠል በቅጠል ልንል ይገባል፡፡
የዓፄ ምንይልክን ቤተ መንግሥት እጅ ሳያደርግ የሚቆም የዐምሐራ ፋኖ ትግል አልተጀመረም፤ አይኖርምም፡፡ የዠመርነው የተቀደሰ ዓላማና ግብ ያለው ፍትሐዊ ጦርነት ነው፡፡ ልዑል እግዚአብሔርም እውነትን ከያዙ ጋር በመሆኑ፣ የእስካሁኑም ድልና ግስጋሴ የዚሁ እውነት ምስክር በመሆኑ፣ ድል ያለ ጥርጥር ከተገፋውና ከተበደለው የዐምሐራ ሕዝብ ጋር ነው፡፡