የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቀዳሚው የቦይንግ ባለቤት ያደረጉት የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ትዝታን በጨረፍታ
ተረፈ ወርቁ ደስታ
-
እንደ መንደርደሪያ፤
ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የ98ኛ ዓመት ልደታቸውን ከማክበራቸው ጥቂት ሳምንታት በፊት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመስብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው፤ ‹የአፍሪካ ወጣቶች የሰላም ኮንፈረንስ› ላይ በመገኘት ያስተላለፉት መልእክት ብዙዎችን የስብሰባውን ተሳታፊዎችን ያሰደነቀ ነበር።
በኮንፈረንሱ ላይ ልዑልነታቸውን ያገኟቸውና ኑሮአቸውን በመዲናችን አዲስ አበባ ያደረጉ ሁለት አፍሪካውያን ወዳጆቼ፤ በልዑልነታቸው ታላቅ ሰብእና፣ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ባበረከቷቸው ሥራዎች እጅግ በመደነቃቸው ልዑል ራስ መንገሻን በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተው ሊጎበኟቸው እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፡፡
እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ ከሳምንት በኋላ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የ 98ኛ ዓመት ልደታቸውን ያከብሩ ነበርና ልደታቸውን ምክንያት በማድረግ ‹እንኳን አደረስዎ!› ለማለት ከአፍሪካውያን ወዳጆቻችን ጋር በመሆን በመኖሪያ ቤታቸው ተገኘን፡፡ ልዑልነታቸው በ98 ዓመታቸውም እንደ 50 እና 60 ዓመት ጎልማሳ ብርቱ፣ ጠንካራ፣ ወግ አዋቂ፣ በዕድሜ ዘመናቸው ያለፉበትን ትዝታዎቻቸውንና እያንዳንዱን ነገር የሚያስታውሱ ናቸው፡፡ ሕያው የታሪክ ምስክር!!
-
የመጀመሪያው ቦይንግና የልዑል ራስ መንገሻ ትዝታ፤
ራስ መንገሻ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሥራና የመገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ እናም ከልዑልነታቸው ጋር በነበረን ቆይታ ከነገሩን ታሪክ መካከልም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ አየር መንገዶች ቀድሞ የቦይንግ አይሮፕላን ባለቤት ያደረጉበት ታሪክ አንዱ ነው፡፡ ልዑልነታቸው ትዝታቸውን እንዲህ አወጉን፤
‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ የሺሕ ዘመናት ታሪክና የገናና ሥልጣኔ ባለቤት፤ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ኩራት ትእምርት/ሲምቦል የሆነች ሀገር ናት፡፡ ስለሆነም አየር መንገዳችን በዓለም ከሚገኙ አየር መንገዶች ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን ከተፈለገ የቦይንግ አውሮፕላን ባለቤት ሊሆን ይገባዋል!›› በማለት ይህን ሐሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቀረቡ፡፡ ይህን ሐሳባቸውን የሰሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ይልማ ደሬሳና ጠቅላይ ሚ ር ልጅ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ለልዑል ራስ መንገሻ እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤
‹‹ሐሳቡ ግሩም ነው፤ ግና የቦይንግ አውሮፕላን ለመግዛት የሚያስፈልገውን 45 ሚሊዮን ዶላር ሀገራችን የላትም፡፡ ብድርም ማግኘት የሚቻል አይደለም። ስለዚህ ልዑልነትዎ የሚኒስትሮች ም/ቤት ይህን የቦይንግ ግዢ ሐሳብዎትን ለጊዜውም ቢሆን ውድቅ ለማድረግ ይገደዳል፤››
ራስ መንገሻ በሚኒስትሮቹ ሐሳብ አልተስማሙም ‹‹አገራችን፣ አየር መንገዳችን ቦይንግ አውሮፕላን ያስፈልገዋል፤ እናም ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ይግባኝ እላለሁ!›› በማለት ለአቤቱታ ወደ ጃንሆይ ገቡ፡፡ ነገሩን ለጃንሆይ አስረዷቸው፡ ግርማዊነታቸውም፤ ‹‹ይህን ያህል ገንዘብ የሚገኝበት መላ ካለህ ወዲህ በል፤›› በል ሲሉ ልዑልነታቸውን ይጠይቋቸዋል፡፡
ልዑል ራስ መንገሻም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ ‹‹የአሜሪካ ቦይንግ ካምፓኒ በብድር እንድንገዛ እንዲፈቅድልን የአሜሪካን መንግሥት እንጠይቃለን፤ ለዚህም እኔ ሙሉ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ፤›› አሉ፡ሁለት ቦይንግ አውሮፕላን በብድር እንዲገዛ ከጃንሆይ ፈቃድ ያገኙት ራስ መንገሻ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከአሜሪካ ባልሥልጣናት ጋር ንግግር ጀመሩ፤ ይሁን እንጂ ለቦይንግ አውሮፕላን መግዣ የሚሆነውን የ45 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘት የገጠማቸው ውጣ ውረድ ቀላል አልነበረም፡፡ ብድሩን ለማግኘት በነበረው ድርድር ወቅት አሉን ራስ መንገሻ- አንድ የአሜሪካ የኮንግረስ አባል፤ ‹‹ንጉሥዎ በቅርቡ ወደ ሩሲያ ጉዞ አድርገው ነበር፤ እና ለምን የሩሲያ መንግሥት አያበድራችሁም?!›› በማለት የሀገራቸውን የገለልተኝነት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ ጥያቄ አነሳባቸው፡፡
ልዑልነታቸው ሀገራቸው ከሩሲያም ሆነ ከአሜሪካና ከተቀረው ዓለም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያ ግንኙነት የገለልተኝነት መርሕን የተከተለ መሆኑን በመግለጽ የአሜሪካ መንግሥት ብድሩን እንዲፈቅድላቸው ድርድሩን አስቀጠሉ፡፡በመጨረሻም ከእልህ አስጨራሽ ድርድር በኋላ ብድሩ ተፈቅዶላቸው ኢትዮጵያ የሁለት ቦይንግ አውሮፕላን ባለቤት ለመሆን በቃች፡፡
-
እንደ መውጫ፤
ባለፈው ሰሞን ደግሞ የቦይንግ ካምፓኒ በአፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያ ጽ/ቤቱን በኢትዮጵያ ለመክፈት ስምምነት ላይ የመድረሱን መልካም ዜና ሰማን፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በጽኑ የዐለት መሠረት ላይ እንዲቆም ያደረጉት የእነ ራስ መንገሻና ከእርሳቸውም በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በኃላፊነት የመሩ ኢትዮጵያውያን በሳልና አመራርና በሥራቸው ያስመዘገቡት ስኬት ውጤት ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ስኬቱን፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱንና ተመራጭነቱን በማስቀጠል በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደጋጋሚ ምርጥና ተሸላሚ አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከመሩት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን መካከል የሆኑት አቶ ግርማ ዋቄ- ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ላበረከቱት ታላቅ አስተዋፅዖና ሥራቸው ከጥቂት ወራት በፊት በቤታቸው ተገኝተው ስጦታ አበርከተውላቸው ነበር፤ ከስጦታቸውም መካከልም የቦይንግ አውሮፕላን ቅርፅ ይገኝበታል፡፡ በዚህ ቤተሰባዊ ጉብኝትና ባለውለታዎቻችንን የማክበር ዝግጅት ላይ ተገኝቼ ነበር፤ እናም በስልኬ የወስደኳቸውን ፎቶዎቹን ከዚህ ጽሑፍ አባሪ አድርጌያለሁ፡፡
ፓንአፍሪካዊውንና የኢትዮጵያውያንና የመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ትእምርት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበለጠ የስኬት መንገድ ይጓዝ ዘንድ ምኞቴ ነው!!