የአዲስ አበባ ህዝብ የብልፅግና መንግስት የቤት ፈረሳ ይበቃል ሊል ይገባል!
ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
የኦህዴድ ብልፅግና የጎጥ ፖለቲካ ወላጅ አባቱን ተክቶ አራት ኪሎን ከተቆጣጠረ ስድስት አመታትን አስቆጥሯል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ከሀሰት ትርክት የተወለደ የጥላቻ ፓለቲካን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች፣ በከፋ መጠንና በተለያየ ስልት ሳያቋርጥ ሲያራምድ ቆይቷል። እንደ ኦሀዴድ/ብልፅግና ያሉ ጥንፈኛ የነገድ ፖለቲከኞች ፖለቲካቸውን የተቃኜው የዛሬ 40 እና 50 ዓመታት በፊት በፈጠሩት የሃስት ትርክት ላይ ነው፡፡ የኦህዴድ/ብልፅግና ይዞት ከተነሳው የሀሰት ትርክት መካከል 1ኛው የአማራ ጥላቻ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የአዲሰ አበባን ነዋሪ የስነ ህዝብ (ዲሞግራፊ) ሰብጥር የመቀየር ግቡ ደግሞ ሁለተኛው ነው፡፡ በእርግጥ የህዝብ ስብጥር ለውጥ ፖሊሲው በሁሉም ማህበረሰቦች ላይ እየተተገበረ ቢሆንም፤ በተለይ ግን የአማራውን ህዝብ ዋነኛ ኢላማው ማድረጉ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ወንበሩ የተደላደለ እንደመሰለው በቀጥታ የተሸጋገረው የአዲስ አበባ ታሪክ ናቸው ያላቸውን ቅርሶችና ስፍራዎች ወደ ማውደምና በአዲስ አበባ ዳርቻ የሚኖሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ቤት ወደማፍረስ ነው። የአዲስ አበባን ዙሪያ ነዋሪ ቤት በማፍረስ የጀመረው በነገድ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተውን ተግባር ወደ መሀል ከተማ በማምጣት ነባር የአዲስ አበባ ሰፈሮችን ወደማጥፋት/erase/ ተሸጋግሯል። በዚህ ሂደትም የነዋሪዎች ህይወት ጠፍቷል፣ አባወራዎች/እማወራዎች ከእነልጆቻቸው ጎዳና ላይ ወድቀዋል፣ ህፃናት ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል፣ ማህበራዊ መስተጋብር ፈርሷል፣ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል እየተፈፀመበት ይገኛል።
ይህ በህዝብ ዝምታ ምክንያት እዚህ የደረሰው መኻል ፒያሳን ነፍስ አልባ ያደረገው የብልጭልጭ መብራትና የኮሪዶር ልማት ከመገናኛ እስከ መሪ ፣ ከፒያሳ እስከ ለግሐር፣ ቄራን እና የተለያዩ የአዲስ አበባን አካባቢዎች አዳርሶ አሁን ደግሞ ካዛንችስን፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮንን እና ሽሮሜዳን ነፍስ አልባና፣ ታሪክ አልባ፣ ባለቤት አልባ አድርጎ ለማፈራረስ ቀጠሮ ይዟል። ከሰሞኑ የአገዛዙ ካድሬዎች በካዛንችስ፣ በፈረንሳይ እና ሽሮሜዳ የሚገኙ ነዋሪዎችን በመሰብሰብ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከሀብት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉና መንደራቸውም እንደሚፈርስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። በስብሰባው ላይ ማናቸዉም መገናኛ ብዙሃን እንዳይገኙ እና ድምፅ ሊቀርፁ ይችላሉ የተባሉ መሳሪያዎች እንዳይገቡ በተደረገባቸው በእነዚህ ስብሰባዎች፣ ነዋሪዎች ተወልደው ካደጉባቸው፣ ለአመታት ከኖሩባቸው ሰፈሮቻቸው አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ እንደሚፈናቀሉ መርዶው ተነግሯቸዋል።
አንድ ዜጋ ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ይቅርና በፈለገው የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ፣ ሀብት ንብረት አፍርቶ የመኖር ህገመንግስታዊ መብቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ ብልጽግና ሲፈለግ ብቻ የሚያከብረዉ ህገመንገስት ይደነገጋል። አገዛዙ እሞትለታለሁ በሚለው በህገመንግስት አንቀጽ 43 ተራ ቁጥር 4 ላይ “የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ የዜጎችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ይሆናል” ይላል። የብልጽግና አገዛዝ አዲስ አበባ ላይ እያካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ተብዬው በርግጥ የከተማውን ህዝብ መሠረታዊ ፍላጎትቶች ለማሟላት እየተከናወነ ያለ ነው ወይ? ብለን ስንጠይቅ መልሱ አይደለም ነው። የህዝብ ጥያቄ የሚመልስ የልማት ሥራ የሚጀምረው መሠረታዊ የሆኑ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄዎችን በመመለስ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቃቸው ከኖሩ ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው፣ “የአዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝ መሆንና በጎጥ ኮታ የሚመደቡ ካድሬዎች ሊያስተዳድሩት አይገባም፤ አዲስ አበባ በራሷ ልጆች ትመራ” የሚለው ዋነኛው ሲሆን፣ በቀበሌ ቤት የሚኖሩ ነዋሪዎች በሚኖሩበት አካባቢ የመኖሪያ ቤት ችግርን የሚያቃላልሉ በቂ የኮንዶሚኒየም ህንፃዎች እንዲገነቡ፣ የግል ይዞታ ያላቸው በግል ይዞታቸው ላይ የማልማት እድል እንዲሰጣቸው፣ የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ፣ የመብራት አቅርቦት እንዲሻሻል፣ በቂ የንፁህ ውሃ አቅርቦት እንዲኖር፣ የትራንስፖርት ችግርን የሚፈቱ መፍትሄዎች እንዲቀየሱ፣ ለወጣቱ ትውልድ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እንዲነደፉ የሚሉ ጥያቄዎችም ይገኙበታል። የብልፅግናው አገዛዝ ግን በተቃራኒው እራሱ ቃል የገባውን “ከእንግዲህ ማንም ከቀዬው አይፈናቀልም” የሚለውን የማዘናጊያ መሃላውን ሙሉ በሙሉ አጥፎታል። በህገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 43 ተራቁጥር 2 ላይ “ዜጎች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ በተለይም አባል የሆኑበትን ማህበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ፕሮጀክቶች ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው” የሚለውን አንቀፅ በመተላለፍና የህዝብን ጥያቄ ወደጎን በመተው፤ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ያለው የአዲስ አበባ ህዝብ ማህበራዊ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴቶቹን በመጠቀም በጉርብትና አንዱ ከሌላው ጋር እየተረዳዳ ችግሩን ለመቋቋም በሚጣጣርበት ወቅት፤ ጭራሽ በኮሪደር ልማት ስም የከተማውን ህዝብ ቤትና ንብረት አፍርሶ ፣ ነባሩን የከተማ ማህበረስብ ከቤተ እምነቶቹ አርቆ፣ የደሃ ደሃ ለማድረግና ከተማውን አስለቅቆ ምንም አይነት የመሠረተ ልማት ባልተዘረጋባቸው ስፍራዎች ለመወርወር እየተጣደፈ ይገኛል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፣ ከዚኽ በፊት የብልጽግናን መንግሥት ከመነሻው በጎጥ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ አላማውን አውቆና ለይቶ አመራሩ እና አባላቱ ከባድ መስዋእትነቶችን እየከፈሉ ሲታገሉት መቆየቱ የሚታወስ ነው። ባልደራስ አሁንም በመሃል ከተማ የድሃው ቤትና ንብረት ፈርሶ ልማት ተብሎ እየተሠራ ያለው የሳርና ዛፍ ተከላ እንዲሁም የብልጭልጭ መብራት ጋጋታና መናፈሻ የከተማውን ህዝብ መሠረታዊ ችግር እንዲፈታ የታለመ ሳይሆን ነዋሪዎችን በማፈናቀል የብልጽግና መንግስትን የገጽታ ግንባታ ለማድረግ መሆኑን ፓርቲያችን ያምናል። ይህን አይነት በህዝብ ጥቅምና መብት ላይ እየተረማመዱ የመሪዎችን ግለሰባዊ ገጽታ የመገንባት ሂደት ፓርቲያችን አጥብቆ ይቃወማል። አብዛኛውን ደሃውንና፣ መካከለኛ ኑሮ ያለውን ማህበረሰብ ተሳትፎና የጥቅም ተጋሪነት ያላረጋገጠ ልማት ፣ ልማት ሊባል አይችልም። በመኾኑም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከአዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ በልማት ሰበብ የመፈናቀል አደጋ የብልፅግና መንግሥት የጋረጠባቸው የሽሮ ሜዳ፣የካሳንቸስና፣ የፈረንሳይ ነዋሪዎች በህገመንግሥቱ የተሠጣቸውን መብት ተጠቅመው በአገዛዙ ከታቀደው የመፍረስ አደጋ እራሳቸውን በህጋዊ መንገድ አንዲከላከሉ እያሳሰበ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫ ለማስተላለፍ ይገደዳል።
ሀ. ለብልጽግና መራሹ አገዛዝ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀረበ ጥሪ፦
1. መንግሥት በማናለብኝነት አካሄድ የአዲስ አበባን ነዋሪ ሰፈሮች በአጠቃላይ በተለየም ከአዲሱ አመት ወዲህ ደግሞ የሽሮሜዳ፣ የፈረንሳይና፣ የካሳንችስ ማህበረሰብ መኖሪያ ቤቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አፈርሳለሁ በማለት ህዝብን ከማሸበር ተግባሩ በአስቸኳይ እንዲቆጠብና ከህዝብ ጋር ነፃ ውይይት እንዲጀምር፣
2. ከዚህ በፊት የብልፅግና መንግሥት “ከእንግዲህ አንድም የሚፈናቀል ሰው አይኖርም” ሲል ለህዝብ የገባውን ቃል እንዲያከብርና፣ “እገዛለታለሁ” በሚለው ህገ-መንግሥት አንቀጽ 43 ላይ የተደነገጉትን የህዝብ መብቶች እንዲያከብር፣
3. በህገመግሥቱ አንቀጽ 43 ተራ ቁጥር 4 ላይ እንደተደነገገው የልማት እንቅስቃሴ ዋና አላማ የዜጎችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት በመኾኑ፤ ህዝብ መንግሥት የሚያቅዳቸውን የልማት ፕሮጀክቶች የማወቅ፣ አስተያየት የመስጠት፣ የመሳተፍ እና የመወያየት መብቱ እንዲጠበቅለት፣
4. ህዝብን ያላማከለ፣ የህዝብን ይሁንታ ያላገኘና በህዝብ መብት ላይ እየተረማመደ የሚከናወን ፕሮጀክት መጨረሻው ውድቀት፣ የንብረት ውደመት እና የገንዘብ ብክነት እንደሆነ አገዛዙ እንዲገነዘብ እናሳስባለን።
ለ. ከቤት ንብረቱ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚፈናቀል ለተነገረው የሽሮሜዳ ፣ የካዛንችስና የፈረንሳይ ነዋሪ የቀረበ ጥሪ፦
1. ማንኛውም የልማት ፕሮጀክት ህዝብን ያማከለና የህዝብን አመኔታና ተቀባይነት ሳያገኝ መከናወን እንደማይችል ህገ-መንግስቱ ስለሚደነግግ፤ ህገመንግሥታዊ መብትህን ተጠቅመህ በየአካባቢህ በመነጋገርና ኮሚቴዎችን በማቋቋም ህጋዊ ጥያቄዎችህን ፔቲሽን በመፈራረም በጽሑፍ ለሚመለከተው የከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት እንድታመለክት፣
2. አገዛዙ የምታቀርበውን ትያቄ አልቀበልም ብሎ ለውይይት የማይጋብዝህ ከሆነ፣ ጥቄዎችህን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በህጋዊ ትግሉ እንዲገፋበት እናሳስባለን፡፡
3. የሚመለከታችሁ አካላት ሁሉ ከአዲስ አበባ ህዝብ ጎን በመቆም ሙያዊ ትብብር እንድታደርጉ ፓርቲያችን ባልደራስ ይጠይቃል፡፡
በጨረሻም መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ በኮሪዶር ልማት ስም በርካታ የከተማዉን አካባቢ፤ ሰው አልባ፣ባለቤት አልባ ያደረገው የብልፅግና መንግሥት አሁን ደግሞ ነባር ሰፈሮችኽን አንድ በአንድ በልማት ስም ለማፍረስ እየተጣደፈ ይገኛል። በመኾኑም፤ አሁን የመፍረስ አደጋ ከተጋረጠባቸው የፈረንሳይ፣ የካሳንችስ እንዲኹም የሽሮሜዳ ነዋሪዎች ጎን በመቆም፣ በስልጡን አካኼድ ድምፅህን እንድታሰማ። እንደ ማህበራዊ ሚዲያ ያሉ የህዝብ ድምጽ የሚሰማባቸውን ዘዴዎች በመጠቀም ከተማህን ከመፍረስ አደጋ አንድታደግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የባልደስራ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
መስከረም 07/ 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ