መነሻችን እና መድረሻችን
ከፕሮፌሰር ዘላለም ይግዛው
”ታሪክ እና ሴተኛ አዳሪ ለከፈላት ታድራለች” ነውና ቢሂሉ ደጋፊዎች ለበሉበት መጮሀቸው የሚገርም አይደለም፡፡ ዘመነ ካሴ በብአዴን ታዛ ስላደገ ልቡን በደስታ ዳንኪራ የሚያስረግጠውና ስሜቱን የሚያላወሰው የብአዴኖችን አይነት ወንበር ላይ በመቀመጥ መሪ መሆንን እንጅ የአማራ ጥያቄዎች መመለሳቸው ለእርሱ ሁለተኛ አጀንዳ ነው፡፡ በ2013 በነበረው የይስሙላ ምርጫ ብርሀኑ ነጋ(ሳይነጋለት ይቅርና) ከኢዜማ ደጋፊዎች ጋር ባህር ዳር ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ሊያደርግ ወደ ባህር ዳር ባቀናበት ጊዜ ዘመነ ካሴ ብርሀኑ ቅስቀሳ እንዳያደርግ አድርጎ መልሶታል፡፡ ይህ ክስተት ያለ ብአዴን ድጋፍ ይሳካል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ አሽቃባጩ ብርሀኑም እሳት ውስጥ እንደገባች ጅማት ኩምትር ብላ ተመለሰች፡፡ (ሁኔታውን ባልደግፈውም አሁን ላይ ብርሀኑ ለሚያሳየው ባህሪ ግን ይገባዋል)፡፡ ዘመነ ካሴ ከእስር ለመፈታቱም እና ባህር ዳር ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የብአዴን ሙሉ ድጋፍ ነበረው፡፡
የአማራ ቀንደኛ ጠላት ብአዴን ነው፡፡ አማራው በዘመናት መካከል ለደረሰበት መሪር ሰቆቃ የመጀመሪያ ተጠያቂው ብአዴን ነው፡፡ ብአዴን ደግሞ በአማራ ህዝብ ዘንድ እንደተጠላ ተረድቷል፡፡ ስለዚህ የህዝቡን ትግል በነ ዘመነ ካሴ ዛሬም መጥለፍ ይፈልጋል፡፡ የብአዴን አባላት በአማራ ክልል እና በኢትዮጵያ ላይ ያከማቹትን ኢኮኖሚ ማስጠበቅ የሚችሉት ያሳደጉት ልጅ ስልጣን ሲረከብ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ብአዴናውያን ያከማቹትን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉት የብአዴናውያንን ድውይ ሀሳብ ያነገበ እንቅስቃሴ ድል ሲያደርግ ብቻ እንጅ ስር ነቀል ለውጥ ከመጣ ያከማቱትን ኢኮኖሚ ማስጠበቅ ይቅርና በሰሩት ጥፋት ተጠያቂነትንም የሚያስከትል ስለሆነ ስር ነቀል ለውጥን አይፈልጉም፡፡ ስለሆነም የብአዴን የበኀር ልጅ የሆነው ዘመነ ካሴ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን መነሻችን አማራ መድረሻችን አማራ የሚል መፈክር ይዞ ብቅ አለ፡፡ ዘመነ ብአዴንን ለመተካት እንጅ ከአማራ ክልል ውጭ ላለው ኢትዮጵያዊ ጉዳዩ አይደለም፡፡ አብዛኛዎቹ የብዓዴን ርዝራዦች እና የእነ ዘመነ ደጋፊዎች (እነ አስረስ ማረ፣ እነ ጌታቸው በየነ፣ እነ አቻምየለህ ታምሩ፣ እነ ሀብታሙ ተገኝ፣ እነ አበበ ፈንታው) በጥቅም ስለተሳሰሩ የስርዓቱ ወይም የብዓዴን ስር ነቀል ለውጥ አይመቻቸውም፡፡
ከ1983ዓ.ም በኃላ በአርባ ጉጉ፣ በሀረር እና በተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት አማራዎች በግፍ ሲታረዱ መለስ ዜናዊ ለታምራት ላይኔ እና ለአዲሱ ለገሰ ከአማራ ክልል ውጭ ለሚገኘው አማራ ደህንነት አይመለከታችሁም እንዳላቸው ዘመነም ከአማራ ክልል ውጭ ላለው አማራ እና ኢትዮጵያዊ አይመለከተውም፤ መፈክሩ የሚያመለክተው ይሄው ነው፡፡ ከእስክንድር ነጋ ጋርም ለልዩነታቸው አንዱ ምክንያት ይኀው ነው፡፡ ‘ደሮ ብታልም ጥሬዋን’ እንዲሉ ዓላማቸው የአማራ ክልል አስተዳዳሪ መሆን እንጅ ፍትህ እና ነፃነት ሁለተኛ አጀንዳቸው ነው፡፡
ህወሓት እና ብልፅግና ባለፉት ሠላሣ ሶስት ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ፣ በሀገረ ኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈፀሙት በደል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በተለይ በአማራ ህዝብ ላይ የተፈፀመው በደል በሁሉም ኢትዮጵያውያን የልብ ፅላት ላይ ተቀርፆ የሚኖር መሪር ትውስታ ነው፡፡ ስለሆነም የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የትግል መርህ መነሻ የአማራ ብሶት የወለደው ስለሆነ መነሻችን አማራ የሚለው የትግል አርማ ሀረግም አመክንዮ ይሄው ሲሆን መድረሻችን ኢትዮጵያ የሚለው አገላለፅ ትግሉ በአማራ ክልል እና ህዝብ ላይ ተወስኖ እንደማቀር አመላካች ሀሳብ ነው፡፡
የብልፅግና ካድሬዎች መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ የሚለውን የድርጅቱን መሪ ቃል ባልተገባ አረዳድ በመተርጎም የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት በሌሎች ብሄሮች ላይ ጫና እንደሚያደርስ እና ፋኖ ለሌሎች ብሄሮች መብት ግድ እንደማይለው ተደርጎ መታሰቡ ብልፅግና ህዝባችንን ለማደናገር የሚጠቀምበት ተንኮል መሆኑን ከወዲሁ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮች ለፋኖ ትግል አጋር እንዳይሆኑ ብልፅግና የሸረበው የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሆነ እንድትረዱ ማሳወቅ እንፈልጋለን፡፡ ብልፅግና ኃላ ቀር በሆነ በብሄር/በጎሳ ፖለቲካ የተቸነከረ፣ ፀረ-አንድነት፣ በእኩልነት የመልማት መብትን የሚያጨናግፍ፣ አምባገነናዊ አገዛዝ ስለሆነ ሌሎች ብሄሮች ከፋኖ ጎን እንዳይቆሙ ለማድረግ የሚጠቀምበት ስልት ስለሆነ ለብልፅግና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ቀልባችሁን ሳታስገዙ በብሄር ማንነታችን ጠፍንጎ የለያየንን ስርዓት ለማስወገድ በሚከፈለው መስዋእትነት ዲሞክራሲን ስርዓትን ለማስፈን በምናደርገው ህዝባዊ ትግል ቀና ትብብራችሁን እንድትቸሩን ስንጠይቅ በከፍተኛ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ነው፡፡
ህወኃት እና ብልፅግና በአማራ ህዝብ ላይ ከሚያሰራጩት መሰረተ ቢስ የሀሰት ትርክት ውጭ የአማራ ህዝብ በታሪኩ የትኛውንም ብሄር ጨቁኖ፣ ደፍጥጦ አያውቅም፡፡ የአፄዎቹ ስርዓት(ዲሞክራሲያዊ ባይሆንም) የአማራ ህዝብ ከሌሎች ህዝብ ለይተው የጠቀሙበት ጊዜ የለም፡፡ የብሄር እሳቤም በጊዜው አይታወቅም ነበር፡፡ ቀደምት የአማራ ስርዓት ሌሎች ብሄሮችን ደፍጣጭ ቢሆን ንሮ በአማራ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ብሄሮች (አገው፣ ቅማንት፣ አርጎባ፣ ኦሮሞ፣ ቤተ-እስራኤል) ባልኖሩ ነበር፡፡ የአማራ ህዝባዊ ኃይል ፋኖም የሚያደርገው ትግል የነፃነት፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲ እና ግፍን አራግፎ ለመጣል እንጅ በሌሎች ላይ ጫናን ለመፍጠር እንዳልሆነ በመረዳት የኢትዮጵያ ብሄሮች የአማራ ፋኖ ለሚያደርገው ሀገር አቀፍ ትግል ቀና አመለካከት እንዲኖራችሁ እና ይህንን ዘረኛ ስርዓት ከስሩ መንግለን ለመጣል ለምናደርገው መሪር ትንቅንቅ አውንታዊ እይታ እንዲኖራችሁ በታላቅ አክብሮት ደጋግመን እንጠይቃለን፡፡
ቸር እንሰንብት፡፡
በትግሉ ለተሰው ታጋዬቻችን ዘላለማዊ እረፍትን ፈጣሪ ይስጥልን፡፡