እስክንድር ነጋ የዘመናችን የጽናት ተምሳሌትና ምልክት ነው።
በሰላሙ ትግል ድልን ተቀዳጅቷል። ጋዜጠኝነትን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነትንና ፖለቲከኛነትን ያለማወላወል ነው የተወጣቸው። ዝንፍ ሳይል። እንደ ሻማ እየቀለጡ ብርሃን መሆን የቻለ ምጡቅ፣ ትሁት፣ ታታሪ፣ፅኑ፣ ጎበዝና ጀግና ነው። በሃገራችን ውስጥ ባለፉት ሰላሳ ሶስት ዓመታት እነዚህን ሁሉ መስፈርቶች ያሟላው አንድ ሰው ብቻ ነው። ያም እስክንድር ነጋ ነው።
ግርማ እንድሪያስ ሙላት
እስክንድር ባሳየው ጽናት፣ ትግል፣ በከፈለው መስዋዕትነት ብዙዎችን አነሳስቷል። ‘‘በሰነፎች መካከል ከሚገኝ የገዥዎች ጩኽት ይልቅ የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች” እንዳለው መጽሐፉ :- እስክንድር በብዕሩም፣ በጸጥታውም ባለፉት ጊዜያቶች ሃገራችን ኢትዮጵያን ተፈራርቀው የገዟትን አምባገነኖች ጩኽታቸውን ሲያስጨንቅ፣ ውሸታቸውን ሲያጋልጥ፣ ቱልቱላቸውን ሲከልልና ሲጋርድባቸው አሳይቶናል። በዚህም ብዙዎችን አነቃቅቷል።
ይሄንን እየጻፍኩ የነጻው ፕሬስ አባላት የነበሩት የእስክንድርን ወዳጆች ጓደኞችና የስራ ባልደረቦችን በዓይነ-ህሊናዬ ለመቃኘት ሞከርኩ። ”የት ነው ያሉት?… ምን እያደረጉ ነው?… ወዘተ” አልኩኝ። እስክንድርን የማይወድ፣ የማያከብር፣ አንድም የነጻ – ፕሬስ ሰው እንዳልነበረ አውቃለሁ። የተወሰኑትን ለማነጋገር ሞክሬ ነበር። ስለ እስክንድር ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ።
ብዙዎቹ አመለካከታቸውን አለወጡም። ”በአንዳንድ ሓሳቡ ባልስማማም ጽናቱን ድፍረቱን አደንቃለሁ” ብለውኛል። ከፊሎቹ ደግሞ ከነሐሳቡ። አገዛዙን የሚደግፍ ሁሉ የእስክንድርን ሐሳብ ይደግፋል ማለት አይቻልም። ሊሆንም አይችልም። በአንጻሩም የቀድሞው የስራ ባልደረቦቹ ወይም የነጻው ፕሬስ አባላት ከነበሩት ውስጥ ሁለት ሰዎች በተቃራኒው ሚዲያ ይዘው፤ ሲሳይ አጌና ቀስ እያለ ሲጎነትለው፤ የሕብሩ ሃብታሙ አሰፋ ደግሞ፤ ከ”ነጻው ፕሬስ” የወጣ ሰው አልመስል እስኪል፤ ትላንት እንደመጣ ”ዩቱበርና” ባልቴት ”ቲክቶከር” ወዳጁን እስኬውን ” ልነጠፍልህ” ሲለው የነበረውን ጀግናውን ሲዠልጠው ይውላል። ¨አህያ ወደ ቤት ውሻ ወደ ግጦሽ¨ የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል።
¨ኧረ ወዳጃችን ሃብታሙ አሰፋ ምን ነካው?¨ ብዬ ሰዎችን ጠይቄ ”እኛም ገርሞናል’‘ ያላለኝ የለም።” ጸጥታ ማንን ገደለ? ለዛውም ቁጩ!?
እንዲያውም አንድ ሰው:–
”ሃብታሙ ዶርዜ ወይም ጉዴላ ነው። ሆኖም አማራ ሳይሆን፣ የአማራን ጉዳይ በጣም ያቦካል። ያምሳል። የአማራን ጉዳይ በበጎ ጎኑ ማማሰል እንጂ፤ በተቃራኒው ሲሆን ቅናት፣ ምቀኝነት፣ እናም ከጠላት በኩል የግድ ተከፋይነት መኖር አለበት። ሐብታሙ አማራ ጓደኞች አሉት እንጂ አማራ አይደለም። ምነው አማራ ጉዳይ ላይ እኝኝ አለ? ኢትዮጵያን ማቀንቀኑ ነበር የሚያዋጣው።” ብሎኛል። ልቦና ይስጠው። ወደ ቀልቡም ይመልሰው .. ከማለት ውጭ ምን ይባላል?

እስክንድርን የማውቀው በ¨ኦንላይን¨ አይደለም። ሲሳይ አጌናንም። ሲሳይ አሁን በሚያደርገውና እያደረገ ባለው ከሚያዝኑት ውስጥ ነኝ። ምንም ማድረግ አይቻልም። ሰው የመረጠውን ጎዳና የመከተል መብት አለው። ሌላው ምንም ይሁን ምንም፤ ሰው የሚያምንበትን አቋም ሆኖ ስመለከት በግሌ እፈልጋለሁ። አጭበርባሪ፣ አድርባይ፣ ሁሉም ጋር የሚጫወት ቀጣፊ ጥሩ አይደሉም። ሲሳይ የብልጽግና ደጋፊ ነው። ደጋፊነቱንም ለአብይም የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ቃል የገባና ለዚሁም ሜዳሊያ ያጠለቀ ነው። አለቀ።

እስክንድር ልዩ ነው። የጋዜጠኞችን ሰደት ያስቆመና ለሌሎች አርአያነትን ፈጥሮ እነ ተመስገን ደሣለኝን ”ትግላችን እስከ ቀራኒዮ” እንዲሉ ያሰኘ ጀግና።
እስክንድር ነጋ በኢትዮጵያ ውስጥ አገዛዞች አስፍነነዋል እያሉ የሚደሰኩርትን ዲሞክራሲንና ፍትህን እንዳልተገበረ እርቃናቸውን እንዲቀሩ ያደረገ ፅኑ ሰው ነው። እስክንድር ሁሉንም ውሸቶች ዕውነትንና ፈጣሪውን ይዞ ሲጋፈጥ በነጻ አይደለም። እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን መስዋዕትነት ከፍሎበታል። እንደሌሎች በገንዘብ፣ በቲፎዞ፣ በአገዛዙ አስተኳኪሾችና፣ ተኳሾች፤ ቲክቶከሮችና ”ተርብ-ግራሞች” (ቴሌግራም) የገነባው ስም አይደለም እስክንድራችን ያለው። የእርሱ ከሁላችንም ይለያል። በክፍለ ዘመን የሚሰጥ ስጦታ።
በሃያ ዕድሜዎቹ የጀመረው አቋሙና ትግሉ አንድ ዓይነት ነው። አይወላውልም። አይልመጠመጥም። አይሽለመጠመጥም። አያቃጥርም። አይፈትልም። በቃ ወንድ ነው። በእርግጥ ብዙ ወንዶች ነበሩ። በነበሩ ያለፉ። ለወራት ይዘመርላቸውና ወይም ለዓመታት ከዚያ ቃየል አቤልን ከገደለው የበለጠ ሴረኛና ደበኛ የሆኑ። ትግሉን የጀመሩት ሳያስቡት፣ ስያልሙት፣ ሳይከነክናቸው ወይም ”የኔ” ብለው ያልጀመሩት ይሆንና፤ በአቋራጭ ባገኙት ፍቅረ- ነዋይ ሲወድቁ ይገኛሉ። እስክንድር ይለያል። ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ወደ -ኋላ ዞር ብላችሁ ተመልከቱ። ወይም በዓይነ -ህሊናችሁ አስተውሉ። ለአፍታ። ስንቱን ዥዋ -ዥዌ ሲጫወት ትመለከታችሁ። ታዲያ እዚህ ሁሉ ዥዋ- ዥዌ ውስጥ እስኬው የለበትም። እንዲያውም በሰላም እስከመጨረሻው ሄዶ፤ ነገር ግን አሸንፎ ያልተሳካለትን ድል በሌላ ትግል ቀይሮታል። እስክንድር ይለያል።
በትግል ሜዳ አፈርን እፍ ብሎ፣ ውርጭንና ብርድን ተቋቁሞ፤ ረሐብና ጥምን ችሎ፤ ከዚያም መፍትሔው ጋር እደርሳለሁ ብሎ ማሰብና ማድረግ እስክንድርን ብቻ መሆን ይጠይቃል።
እኔ በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ስለፈሉት ኮተቶች አስቤ አላውቅም። ስለ እስክንድር ሳስብ። እስክንድርን መለስ ዜናዊ የሚፈራውና የሚያከብረው ሰው ነበር። እስክንድርን ሃይለማሪያም ደሳለኝ ያከበረው ነበር። እስክንድርን አሳሪዎቹም ገራፊዎቹም ያከብሩትም ይፈሩትም ነበር። ብርሓኑ ነጋ በዓለም ላይ ማንን ትፈራለህ ብትሉት ለሚስቱም ቢሆን የሚነግራት የሚፈራው እስክንድርን ነው። ምክንያቱም ውሽታሞች ዕውነተኛን ይጠየፋሉ። ብርሐኑ ደግሞ ቀጣፊና አጭበርባሪ ነው። ስለዚህም እስኬውን አይወደውም።
አብይ አህመድ:- ”ባልደራስ የሚባል ጨዋታ የምታመጣ ከሆነ ጦርነት እንገጥማለን” ያለው እስክንድርን ነው። እርሱን ተከትሎ ብርሃኑ ነጋ ”ይሄ ባልደራስ ምናምን የሚባል—” ሲል ያላገጠው እስክንድር ላይ ነው። በአምስት ዓመት ውስጥ የፈሉት ዩቱበሮች፣ ቲክቶከሮች፣ ቴሊቪዥኖች፣ መሰረት እስኪይዙ ድረስ ወይም በእግራቸው እስኪቆሙ ድረስ፤ ወይም ለአቅመ ገንዘብ (ሆድ) እስኪበቁ ድረስ የእስክንድር ስም የገቢ ማግኛቸው፤ የእስክንድርን ተግባራቶች ማውራትና ማወደስ የፕሮግራማቸው ግብ-አት ነበረ። የእስክንድር ጽናት ብቻ ነው በዚህ ዘመን ሊገለጽና ሊወደስ የሚችለው። አለያ ከመቶ ዓመት በፊት መሄድ ግድ ያላል። እንዲህ ያለ ሰው ለማግኘት። ለዚያ ነው እስክንድር ሲያልቅባቸው ቴዎድሮስ ምንሊክ እያሉ ሚያላዝኑት። ስለዚህም የዘመናችንን ወርቅ እንጠብቅ። ተወደደም ተጠላም፤ እስክንድር ነጋ የዘመናችን የጽናት ተምሳሌትና ምልክት ነው። አበቃሁ።
እስክንድርን ባለበት ሁሉ እግዚአብሔር እንዲጠብቀው የዘወትር ጸሎቴ ነው።
ግርማ እንድሪያስ ሙላት
Email:⇓
ethreference@gmail.com
girma077@gmail.com