የረሃብተኞች የጣር ድምጽና የሠማዕታት ደም ጩኸት ለፍትህ ያልቆሙትን ሁሉ ያውዳል
ከበየነ
በሞጆ፣ ሎሜ ወረዳ የመልዓከ-መንክራት ቀሲስ ወልደ እየሱስ አያሌው እስከነቤተሰባቸው በግፍ የመገደል ዜና በሰማን ሰሞን በዚሁ ወረዳ ሌሎች ስምንት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በተመሳሳይ ሁኔታ ተገደሉ የሚል ሌላ ዜና ተሰራጨ። እግዚአብሄር በአምሳሉ በፈጠራቸው የሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለው ዘግናኝና ሰቆቃዊ ዜናዎች እንደ ዋጋ ንረትና ገንዘብ ማሽቆልቆል ከቁብ የማይቆጠሩ ወሬዎች ሆነዋል። የንጹሃን ደም ከመቃብር በላይ ሲጮህ እየተሰማ በርካቶች ጆሮ ዳባስ ልበስ ብለዋል። ባለፉት ስድስት ዓመታት በእንዲህ ዓይነቱ ዘግናኝ አገዳደል የተሰዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን መነኮሳት፣ ባህታውያን፣ ካህናትና ምዕመናን እጅግ ብዙ ቢሆኑም ሕዝብ አሁንም የጋራ ቁጣ አላሰማም። ራሱን “ብልጽግና” ብሎ የሚጠራው “የጫካ ፕሮጀክትና የኮሪዶር ልማት” መንግሥት ወደ አራት ኪሎ ከመጣ ጀምሮ በኦሮምያና ከቁጥጥር ውጭ በሆኑ ወረዳዎች የሚገደሉት ኦርቶዶክሳዊ ክርስትያናትና አምሃራ ነገዶች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው።
እንደሚታወቀው ባሁኑ ሠዓት ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ፣ ከምዕራብ ጫፍ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ኢትዮጵያን ማስተዳደር የሚችል ኃይል ያለው ተፈሪ መንግሥት ባለመኖሩ ከእገታ እስከ ግድያ፣ ከዘረፋ እስከ ቤት ፈረሳ፣ ከስርቆት እስከ ብክነት፣ ከሙስና እስከ ሃገር መሸርሸር፣ ከፍጅት እስከ ጦርነት – የተንሠራፋው ታላቅ መቅሰፍት የሃገሪቱ ማህበራዊ ምጣኔ ኃብታዊ ገጽታ ሆኗል። ወገኖቼ አስቡት! የመሬት ላራሹ ጥያቄ – አንድ አብዮት (ONE REVOLUTION) ካፈነዳ – ዛሬ በመላ ኢትዮጵያ ላይ ያጠላው እርዛት፣ ረሃብ፣ ስደት፣ የኑሮ ውድነት፣ የግብር ቁለላ፣ የመኖር ዋስትና መነፈግ፣ የሕግ ተፈጻሚነት አለመኖር፣ የፍትህ መዛባት፣ የልጆች የትምህርት ገበታ መነፈግ፣ የነጻነት እጦት፣ ዘረኝነት፣ ሥራ አጥነት፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ሥር የሰደደ ድህነት፣ የሥነ-ልቦና አበሳ፣ የሽንገላው ብዛት – ሺህ አብዮቶች (TEN THOUSAND REVOLUTIONS) አያፈነዱምን?
በተቃውሞ ታምሳ፣ በአስራ ሰባት ዓመታት ጦርነት ቆስላ በግፍ ወደቧን ተነጥቃ ተፈጥሮ ካደላት የባህር በር የተነጠለችው ታላቂቱ ኢትዮጵያ 14 ጠቅላይ ግዛቶች ነበርዋት። ኤርትራ በወያኔ ደባ ተገንጥላ 13 ቀሩ። አሁን ላይ ትግራይ፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ በጌምድር እና ሸዋን መንግሥት ተብዬው አያስተዳድራቸውም፣ ግብርም አይቀበልም። እነዚህ የኢትዮጵያን ሰሜን-ምዕራብ ከፍተኛ መሬቶች (North-Western Highlands) የሚያካልሉት 5 ጠቅላይ ግዛቶች አብዛኛዎቹ ወጣ ገባ አስቸጋሪ ገመገም (rugged massif) የሆነ አዳጋች የመሬት አቀማመጥ (fierce topography) ለብሰዋል። የኢትዮጵያ ቅድመ ታሪክ መነሻ – የነገሥታት መናገሻ የሆነውን ሰሜን ኢትዮጵያን ግብር ማስገበር ሳይቻል “የኢትዮጵያ ንጉሥ ነኝ” ማለት – convince and confuse – የተባለው “የሰው መሳይ በሸንጎ”፣ ከንቱ ፖለቲካ (futile politics) የመጨረሻ ምዕራፍ ነው።
ከሃገሪቱ መልክዓ-ምድር ከግማሽ መቶኛውን በላይ የሚሸፍነው ሰሜን ኢትዮጵያ ከማዕከላዊ መንግሥት ተፅዕኖ ውጭ ነው። ቀሪውን መቶኛ የሃገሪቱን ምድር የሚያካልሉት ጠቅላይ ግዛቶች ከፊል ወለጋን ሳይጨመር የአገሪቱን ጠቅላላ ግብር በግዳጅ እንዲከፍሉ ታዘው በገቢዎች መሥሪያ ቤቶች ቁም ስቅል ያያሉ። በአዲስ አበባ ዙርያ እንዲሁም በሩቅ ርቀት ያሉ ትላልቅና ትናንሽ ከተሞችም ያልሠሩትን ያላተረፉትን ግብር (revenues) እንዲከፍሉ ታዘዋል። መብትን በሚጋፋው፣ ህግ በማያየው፣ ፍትህ ባልዳሰሰው የሰቆቃ አለንጋ የሚገረፈው ይህ ግብር ከፋይ ሕዝብ – ሺህ አብዮት – ቢያፈነዳ ይበዛበታል? የሰለሞናዊ ስርወ-መንግሥት ወራሽ አስተዋዩን፣ ሚዛናዊ ንጉሥ የገረሰሰ አብዮት እንደምን በክፉዎች ላይ ፍላፃውን መወርወር ተሳነው?
ሕጻናት፣ ልጆች፣ ደሆችና ጭቁኖች ፍትህ (justice) ተነፍገው ይጮሃሉ (cry of the neglected poor and oppressed)። እንደ መልዓከ-መንክራት ቀሲስ ወልደ እየሱስ ቤተሰብ አያሌው የታረደው ሁሉ ደሙ ይጮሃል። እነዚህ ድምጾች ኢ-ፍትሃዊ ገዥዎችን (injustice autocrats) ያሳድዳሉ፣ አታሞ መችዎችና ውታፍ ነቃዮችም (injustice collaborators) መደበቅያ ያጣሉ። በግፍ የተገደሉ አምሃሮች ደም ጩኸት ነፍሰ ገዳዮችን መቀመቅ አውርዷል። ወዮ! በሉ ግፈኞች – አብዮት ፈነዳም አልፈነዳም – የደሆች እንባና የኦርቶዶክስ ምዕመናን ደም ጩኸት በክፉ ገዥዎች ላይ ታላቅ ሠይፍ ይዞ ይመጣል። የረሃብተኞች የጣር ድምጽና የሠማዕታት ደም ጩኸት ለፍትህ ያልቆሙትን ሁሉ ያውዳል።
ዘረኛውን ብልጽግና ፓርቲን እና በቀዳዳ ባሊ ውሃ እንደማፍሰስ ያለውን ራስን የማታለሉን convince and confuse ፍሬ-ቢስ ሃሳብ የቀመሩትን – ድርብ ስለት (double-edge) ያላቸው ሁለት ተወርዋሪ ድምጾች ይገረስሷቸዋል። አንደኛው ድምጽ የሚያሳርዷቸውና የሚያስገድሏቸው ንጹሃን ኦርቶዶክስ ክርስትያናትና አምሃራ ነገዶች አስፈሪ “የደም ድምጽ” (blood Cries) ሲሆን ሁለተኛው ከሰሜኑ ተራራማ መሬቶች ተወንጭፎ አሉበት የሚወረወረው የጥይት አሩር “ነጎድጓዳማ መብረቃዊ ድምጽ” ነው። ሁለቱም ድምጾች በሠራዊት ብዛት፣ በታንክና መድፍ ጋጋታ፣ በጦር አውሮፕላን እና ድሮን ውካታ አይመለሱም።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን፣
አሜን