ፋኖ በምሽግ ውስጥ
ፋኖና አርበኛ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው
አቅም እስከፈቀደ ድረስ ወደ ኋላ ቢቆጠር የአማራ ትውልድ ምንጩ አንድም ንግሥና ነው፥ ሌላም አርበኝነት ነው። በዚህ ሂሳብ በባንዳነት ትውልዳቸውን ከሻሩት በስተቀር ማናችንም አማሮች ልዑላን፣ ልዕልታት ወይም የአርበኞች ልጆች ነን። ከጎጃም እስከ ጎንደር፣ ከወሎ ቤተ አማራ እስከ ሸዋ ብሎም እስከ ሀረርጌና ጎሬ መላ ኢትዮጵያን ብንዞር የአማሮች የአርበኝነትና የአስተዳድር ታሪክ ጎልቶ እናገኘዋለን።
ለዛሬ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሤን ጨምሮ የሊቃውንት መብቀያ፣ የአርበኞች መፍለቂያ፣ አፄ አንበሳ ውድምን ጨምሮ የነገስታት መታገያ ወደ ሆነቺው ሸዋ መርሀቤቴ እናቅና። ፊታችንን ወደ መርሀቤቴ እንድናዞር የጋበዘን የአንድ ፋኖ ታሪክ ነው። ውድ አማሮች ሆይ፥ እነሆ ታሪኩ ተዘከሩልን:-
ቸርነት አሰፋ ይባላል። የተወለደው ሕዳር 7 ቀን 1992 ዓ.ም. ነው። አባቱ አቶ አሰፋ ዘርጋው ይባላሉ። ወላጅ እናቱም ወይዘሮ እቴቴ ባሕሩ ናቸው።
አርበኛ ቸርነት አሰፋ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት መርሐቤቴ አውራጃ ላይ ቤት ወረዳ ኮራ ወንጭት ችጉር ቀበሌ ተወልዶ ሲያድግ ከሰፊው የአማራ ሕዝብ የአርበኝነት ታሪክ በተጨማሪ የአምስት ወንድማማቾችን አስደናቂ የአርበኝነት ጀብዱ በቅርበት እየሰማ ነው ያደገው። 5ቱ ወንድማማች አርበኞች በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታሪክ በአምዱ የዘከራቸው ናቸው። በተለይም በድፍን መሬ “የሸንቁጥ ልጆች” እየተባለ ስማቸው እንደናኘ ነው። አባታቸው ደጃዝማች ሸንቁጥ ደራጅ ይባላሉ። በአድዋ ጦርነት የተፋለሙ ጀግና ነበሩ። የሸንቁጥ ልጆች ደግሞ በማይጨው መስመራዊ ጦርነትና በአምት አመቱ የሽምቅ ውጊያ ፋሽስት ጣልያንን ካርበደበዱ፣ አርበድብደውም ወደ መጣበት ከመለሱ አርበኞች መካከል ናቸው። ደጃዝማች ተሾመ፣ ደጃዝማች አበበ፣ ኃይሌ፣ ልጅ ይነሱ እና ልጅ ጥላሁን ይባላሉ። አርበኛ ቸርነት አሰፋ የእነዚህን ወንድማማቾች የጦር ሜዳ ጀብዱ ታሪክ ከእናቱ ጡት ጋር አብሮ እየጠባ ያደገ አማራ ነው።
በመሆኑም በመንፈስ ውርስ የተዛመተው ጀግንነት ቀጥሏል። የልጅነት አስተዳደጉ እንደ ብዙሃኑ የአማራ ሕጻናት ከአርበኝነት እና የውጊያ ጥበብ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነበር። ዛሬ አይደለም ሲረግጣቸው በሩቅ ሲያያቸው የጠላትን ሀሞት የሚያፈሱትን ዋርኝ ተራራና ገደልን፣ ኮራ ማርያም ተራራን፣ አባ አናጢ ተራራን እና ጌታ መስሪያ ተራራን በልጅ እግሩ ሲዘልባቸው አድጓል። ጠላት ፈፅሞ ማይረግጠውን የወንጭት ወንዝ ቆላማ አካባቢን በቀን፣ በጨለማ ተንቀሳቅሶ አድጎበታል። በእነዚህ የመሬት አቀማመጦች ወድቆ፣ ተነስቶ ማደግ ተፈጥሯዊ ኮማንዶነት ሊባል ይችላል።
በዚህ ገደል፣ ተራራ፣ አቀበትና ቁልቁለት በበዛበት ቀየ ከተለያዩ እንጨቶች ክላሽ እየሰሩ የተኩስ ጨዋታዎችን ይጫወቱ እንደነበር አብሮ አደጉ አርበኛ በለጠ ማሞ ያስታውሳል። ጭቃ በማድቦልቦል ቦምብ ይሰሩ እንደነበርም አጫውቶኛል። ቁልቋል በእሳት በመጥበስ ይፈጥሩት የነበረው ፍንዳታም የትዝታው አካል ነው። በዚህ መልኩ ተዋጊነትን ተክህኖ ያደገው ቸርነት አሰፋ ከእቃ እቃ ጨዋታ ወጥቶ እውነተኛውን የብረት ጠመንጃ ሲጨብጥ እንደ አባቶቹ ምሽግ ሰባሪ ለመሆን በቅቷል።
ቸርነት ወደ አርበኝነት እስከገባበት ጊዜ ድረስ ተማሪ ነበር። ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በዚያው በመርሐቤቴ ኮራ ወንጭት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። የሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን ደግሞ በአለም ከተማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን በዚያው በዓለም ከተማ የአርበኞች መታሰቢያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመከታተል ላይ ሳለ ወደ አርበኝነት ገባ።
ጊዜው እብሪተኛው የወያኔ ሰራዊት በአማራ ላይ የወረራ ጦርነት የከፈተበት በመሆኑ የአማራ ወጣቶች በፋኖነት ራሳቸውን በየቀያቸው እያደራጁ መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ጀመሩ። አርበኛ ቸርነት አሰፋም በ2013 ዓ.ም. የአማራ ፋኖ በመርሐቤቴ በሚል ስያሜ መሰባሰብ ሲጀመር ከመጀመሪያው ዙር ሰልጣኝ ፋኖዎች መካከል ነበር። የአጭር ጊዜ ስልጠናውን እንዳጠናቀቀ ሕዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ደቡባዊ ወሎ ቤተ አማራ ካላላ ግንባር ዘመተ። ከወያኔ ሰራዊት ጋር በመፋለም የአርበኝነት “ሀ” “ሁ”ን ጀመረ። በዚህም በወቅቱ ምስራቅ አማራ ፋኖ ይባል በነበረው አደረጃጀት ስር በመሆን እስከ ራያና አላማጣ ድረስ ተዋግቷል።
ከድል በኋላ በወርሃ ጥር 2014 ዓ.ም. ወደ መርሐቤቴ ተመለሰ። ሆኖም ከጦርነት መልስ ወደ ሰላማዊ ሕይዎቱ አልተመለሰም። ወያኔን ካስተነፈሰ በኋላ አማራን ለመውጋት ቋምጦ ወደ ነበረው የቤተ መንግስቱ ኦነጋዊ ሃይል ፊቱን አዞረ። ወርሀ ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. ብልፅግናን ለመታገል እንቅስቃሴው ተጀመረ። አርበኛ መከታው ማሞን ጨምሮ ከጓዶቹ ጋር በመምከር ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ይፋት ቀጣና ከራሳ በቅርብ ርቀት በአማራ እና በአፋር መስተዳድሮች አዋሳኝ በምትገኘው ሙቅ ውሀ ጫካ ገባ። ሌላ ትግል ጀመረ።
አርበኛ ቸርነት አሰፋ ከብልፅግና ወራሪ ሰራዊት ጋር የነፍስ አድን ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ በሻለቃ አዛዥነት፣ በብርጌድ አዛዥነት እና በክፍለ ጦር የዘመቻ አዛዥነት ተዋግቶ በማዋጋት በርካታ ጀብዱዎቹን ፈፅሟል።
በነበረን የአጭር ጊዜ ትውውቅ ቸሬ ደርባባ፣ ለውሳኔ የማይቸኩልና የማያመነታ ንግግረ ቁጥብ ሰው ነበር። “ከሚያስፈልገው በታች ተናገር። የተግባር ሰው ሁን” የሚለውን የሮበርት ግሪኔ የአመራር ፍልስፍና የተላበሰ ይመስላል። ቸርነትን የማስታውስበት አንድ የቅርብ ገጠመኝ አለኝ። ወደ ሰፈርንበት ከተማ ለመግባት ጠላት እየገሰገሰ የተጠጋን መሆኑን የሚገልጽ የተሳሳተ መረጃ ምሽት 4 ሰዓት ገ ofደማ ደረሰን። ወሬው በስፋት በመሰራጨቱ የከተማው ሰላማዊ ኗሪ ሕዝብ የቻለውን ያህል የቤቱን ዕቃ በአህያ እየጫነና እየተሸከመ ከፋኖ ቀድሞ የፋኖ ሰፊ ግዛት ወደ ሆነው ቀጣና ተመመ። ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ ህሙማን ሁሉ የጨለማ ጉዞውን ተጋፍጠውታል። ገደል ላይ እየወደቀ የሚነሳው፣ የሚያደናቅፈው፣ የጣርማ በር ብርድ የሚያቀጠቅጠው በርካታ ነው።
በዚህ ሂደት የመረጃው ትክክለኛነት እየተጣራ፣ የደፈጣ ምሽጎች እየተጠናከሩ እኛም ወደ ከተማዋ ዳርቻ ወጥተን ገዥ ቦታ ያዝን። ስለመረጃው ሰፊ መረጃ ለማግኘት ፊታቸውን ጠላት መጣበት ወደተባለው አቅጣጫ ያዞሩ እና ለተጨማሪ ቅኝት የወጡ ጓዶችን ፍለጋ የሰው እንቅስቃሴ ወደ ማይታይበት ጸጥ ያለ ከተማ ሁለት ሆነን በደረቅ ሌሊት መግባት ጀመርን። ቼሬ እና ጥቂት ጓዶቹ ከከተማ ሲወጡ እኛ እንደገና ለመግባት ስገሰግስ በደን በተሸፈነው የመኪና መንገድ ላይ ተገናኘን። በፍፁም መግባት እንደሌለብን ነግሮን እኛም በድጋሜ ወደ ተራራችን ተመለስን። በዚህ ጊዜ ያሳየው ወታደራዊ ጥንቃቄና ሓላፊነት የተሞላበት ርምጃ ትዝ ይለኛል። ለተጨማሪ ቅኝት ጠላት መጣበት ወደ ተባለው አቅጣጫ የዞሩትና አብረውኝ የሚንቀሳቀሱት የፕሬስ ጓዶቼ እስኪመለሱልኝ ድረስ ከእኔ ላለመለያት ያደረገው ሁሉ ከጓዳዊነት በዘለለ ጥልቅ ወንድማማቻዊ ፍቅርን የተሞላ ነበር።
አርበኛ ቸርነት አሰፋ የጠላትን እንቅስቃሴ በጥብቅ የሚከታተል ጥንቁቅ ወታደር ነበር። ከምድሩ በተጨማሪ በሌሊት ሰማዩን ሲቃኝ ያድራል። በተደጋጋሚ የሌሊት የድሮን ቅኝት መረጃዎችን ለዜና ግብዓት በሚሆን መልኩ በሌሊት ደውሎ ሲነግረኝ ቆይቷል። ይህ ሰላማዊው ማህበረሰብ መረጃውን አስቀድሞ ሰምቶ እንዲጠነቀቅ ከሚል እሳቤ ነው። በቅርቡ በመንዝ ማማ ምድር ባሽ ከተማ ላይ የጠላት ሰራዊት ንፁሃን ተፈናቃዮችን በሌሊት በድሮን ሲጨፈጭፍ ቸርነት ቀድሞ የደረሰ አስክሬን አንሺ ነበር።
ሰራዊት ሲመራና ሲያዋጋ ከፊት ቀድሞ ምሽግ እየሰበረ ነው። በአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ መሐመድ ቢሆነኝ ክፍለ ጦር ውስጥ ኮኮብ ዲሽቃ ተኳሽ እንደነበር ጓዶቹ ይናገራሉ።
በቅርቡ በተጉለትና ቡልጋ ከሰላ ድንጋይ ከተማ በቅርብ ርቀት ሳሲት ላይ በተደረገ ውጊያ የሠራው የጦር ሜዳ ጀብዱ ሲታወስ የሚኖር ነው። ዲሽቃን እንደ ክላሽ አነጣጥሮ በመተኮስ የጠላትን ዙ 23 በባሩዱ አቃጥሏል። በዚህም የጠላትን የማጥቃት ብቻ ሳይሆን የመከላከል አቅም ጭምር አሽመድምዷል።
ፋኖ አርበኛ ቸርነት አሰፋ ባለፈው ሕዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንዝ ማማ ምድር ሞላሌ ከተማ መገንጠያ እየተባለ በሚታወቀው ስፍራ በተደረገ የማጥቃት ውጊያ የጠላትን ምሽግ ሰብሯል። ራሱን የሀገር መከላከያ ሰራዊት እያለ ከሚጠራው ወራሪ ጦር አዋጊ ኮሎኔል ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ከተፋተገ በኋላ ከአፈር ጋር ቀላቅሎታል።
ይህ የምሽግ ውስጥ ጀብዱ ወደ ፊት ሲያበራ ይኖራል። በዚህ ውጊያ ዲሽቃና ላንድኩሩዘር መኪናን ጨምሮ በርካታ የነፍስ ወከፍ መሳሪያወችን ከእነጥይቶቻቸው ማርኮ ለደጀኑ ክፍል ጦር አስተላልፏል። በደረት ትጥቁ ካዝና ውስጥ የተሰገሰጉ ጥይቶቹን ሁሉ በጠላት ላይ አንድዷቸዋል። በደረቱ የነበሩ ቦምቦችን ጨርሶ ወደ ኋላ ከነበሩ ጓዶቹ ጭምር በመቀበል በፈጠረው ፋታ የለሽ የፍንዳታ ማጥቃት የጠላትን ምሽግ ድብልቅልቅ አድርጎታል። ገና ከልጅነቱ ጭቃ እያድቦለቦለ ቦምብ አወራወርን የቀሰመው አርበኛ ቸርነት የጠላት ተዋጊዎችን እንደ በሶ ጭብጦ እሳት የተሞላ ቦምብ አስገምጧቸዋል።
ፈሪ ምሰሶ ነው ዘላለም ይኖራል፥ ጀግና ብርሌ ነው ወድቆ ይሰበራል! እንዲሉ ይህ ጀግና በተወለደ በ25 ዓመቱ በክብር ተሰውቷል። የእነ መከታው ማሞን ካምፕ ተሰናብቶ የእነ አባ ኮስትር በላይ ዘለቀን፣ የእነ ራስ አበበ አረጋይን፣ የእነ ፊታውራሪ ገብርየን፣ የእነ ጀኔራል አሳምነው ፅጌን ካምፕ ተቀላቅሏል። ሰማዕታትን በደም ያጸና መላክ እርሱንም እስከመጨረሻው በደም አፅንቶታል።
ቸ ር ነ ት አ ሰ ፋ ዘ ር ጋ ው መጭው ትውልድ በቅብብሎሽ ሲዘክረው የሚኖር ስም ይሆናል!