>

ABC TV እና ROHA MEDIA በተመለከተ ከአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የተሰጠ መግለጫ!!

    • ከአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ለሚዲያዎች የተሰጠ የማስጠንቀቂያ መልዕክት!

    • ABC TV እና ROHA MEDIA በተመለከተ ከአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የተሰጠ መግለጫ !
    • የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል በአማራ ልጆች ውድ መስዋዕትነት እና ጀግንነት በድል እየተረማመደ ይገኛል። ትግል የሂደት ውጤት በመሆኑም ከትናንት የተሻለ ዛሬን እየገነባን ጠንካራ ተቋማዊ መሠረት በመጣል በሀቀኛ በጀግኖች የተከበበ ጠንካራ ተቋም መፍጠር ችለናል። የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ከተቋም ምስረታው ማግስት ጀምሮ አሁን አስከ ደረሰበት የአመታት የትግል ጉዞ ያስመዘገባቸው በርካታ ድሎች የመኖራቸውን ያክል ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎችን በማለፍ ዛሬም የአማራን ሕዝብ ነፃነት ለማወጅ በፀና መሠረት ላይ ቆሞ በመታገልና በማታገል ላይ ይገኛል።የአማራ ሕዝብ ትግል የአሸናፊነት መንገድ አንድነት ነው። የልዩነት መንገዶች ሊረዝሙ ወይም ሊዘገዩ ቢችሉም ከአንድነት የሚቀር ኃይል ግን የለም።
    • የአማራ ፋኖ ትግል መርህን መሠረት አድርጎ ወደ አንድ አታጋይ አደረጃጀት እንዲመጣም የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ፤እያደረገም ይገኛል።በተለይ ሸዋ የሃገረ-መንግስቱ እና የአማራ ፖለቲካ አምብርት(የፖለቲካ ማዕከል) በመሆኑ የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ከጠላት በልዩ ትኩረት የተከፈተበትን ጥቃት በመመከት ተጨባጭ ድሎችን እያስመዘገበ ይገኛል።የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ እነዚህን በርካታ ድሎች እያስመዘገበ ትኩረቱን ዋነኛ ጠላቱ ላይ አድርጎ እየታገለ ባለበት ወቅት ግን፤ የአማራ ፋኖ ትግል ውጤታማነት እረፍት የነሳቸው በውጭና በውስጥ በጠላትነት የተሰለፉ ሀይሎች በሙሉ ላለፉት አንድ አመት የታቀዱ የውክልና የሚዲያ ዘመቻ ከፍቶበውታል። ተቋሙ የተከፈቱበትን ያልተገቡ ዘመቻዎች በሆደ ሰፊነት እያለፈ በድል መገስገሱን ቀጥሏል። ነገር ግን መገንባት የማፍረስን ያክል ቀላል የሚመስላቸው የዚህ እኩይ ሴራ ባለቤቶች ትግሉን ለመከፋፈል አንጃነትን፣ አውራጃዊነትን እና ያልተገባ የጥቅም ትስስርን በማበረታታት ላይ ይገኛሉ።ለወትሮ የአማራ ተቋም ነን የሚሉ ሚዲያዎችም ተቋምና ተቋማዊነት ፣ምንነትና አስፈላጊነቱን ሳይረዱ የአማራን ሕዝብ ዋጋ የከፈለበትን ትግል ለቡድን ለመስጠት የልዩነት ገደል ማሚቶ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።የአማራ ሕዝብ ላለፉት 60 አመታት ተቋም አልባ በመሆኑ የፖለቲካ መገለል ፣ የጅምላ ግድያ ሰለባ ከመሆኑ ባሻገር በባለቤትነት ያስተዳድራቸው የነበሩ ነባር ርስቶችን ተነጥቆ አማራን መጥላት የፖለቲካ መሠረታቸው አድርገው በተነሱ ኃይሎች በርካታ ግፍ ፣በደልና ጭቆና ደርሶበታል።ትናንት ተቋም አልባ በመሆኑ ለዘርፈ ብዙ አደጋ የተጋለጠው የአማራ ሕዝብ ዛሬ በሀቀኛ ልጆቹ የደም ዋጋ አሸናፊነት ፤ የነፃውን ሕዝብ ነፃነት ለማወጅ  ጥቂት የትግል ሂደቶችን በመጠባበቅ ይገኛል። ነገር ግን ይህን ከነውስንነቱ በብዙ ዋጋና መስዋዕትነት ለድል ጫፍ የደረሰ የዋጋ ትግል በወገን ስም የተደራጁ ፣የጠላት አጀንዳ የተሸከሙ፣ ትግሉን ከመነገጃነት የዘለለ ዋጋ የማይሰጡ ፣ውግንናቸው ከወገን የመሠለ ዳሩ ግን የሚያወሩትን አንድነት  የማይኖሩ ከፋፋይ ሚዲያዎች መኖራቸውን ታዝበናል። ከእነዚህ መካከል ABC TV እና ROHA TV በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

      ABC TV እና ROHA TV የተባሉ ሚዲያዎች እና በውስጣቸው የሚሰሩ ባለሙያዎች/ጋዜጠኞች መርህን ጥሰው ከአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ በአንጃነት ያፈነገጡ ፣ ከኃላፊነት የተነሱ ፣ የዲስፕሊን ተጠየቅ ያለባቸው ግሰቦችንና ቡድኖችን ያልተገባ ሽፋን በመስጠት የትግሉን የአንድነት ሰበዝ እየመዘዙ የሸዋም ይሁን የአማራ አንድነት እንዳይሳካ እየሰሩ ይገኛሉ።

      ስለሆነም ሚዲያዎቹን የምትመሩና የምትደግፉ አካላት ይሕንን በአማራ ፋኖ አንድነት ላይ ፈተና የሆነውን አንጃነትን የሚያበረታቱ የትግል እንቅፋት የሆኑ ሚዲያዎች እና አንጃነትን የሚያበረታቱ ጋዜጠኞችን እንድታስቆሙ እየጠየቅን ፤ ይሕ የማይሆንና ከቀደመ ጥፋታችሁ የማትታረሙ ከሆነ ከአማራ ጠላት ከሆነው ከአገዛዙ የሚዲያ ተቋማት ተርታ መድበን የምንታገላችሁ መሆኑን እየገለፅን፤ በተመሳሳይ የጥፋት መስክ የተሰለፋችሁ ሚዲያዎችና ቡድኖችም ከመሠል ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እየጠየቅን፤ የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ደጋፊዎችና አባላት በተለይ ተቋሙ ይፋዊ ውክልና የሰጣችሁ ግሰቦችና ተቋማት በአማራዊ ጨዋነት በሁሉም ዘርፍ ለትግሉ እስተዋፆኦ  እንድታደርጉ በአክብሮት ልንገልፅላችሁ እንወዳለን።

      ሚዲያዎች የትግል አቅጣጫ መምሪያና ማሳለጫዎች እንጂ መነገጃዎች ሊሆኑ አይገባም!

  • ጥር 03/2017 ዓ.ም
  • የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ
Filed in: Amharic