>

ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌን ከጎዳና የታደጋቸው የመቄዶንያው ዶ/ር ብንያም በለጠ!!

ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌን ከጎዳና የታደጋቸው የመቄዶንያው ዶ/ር ብንያም በለጠ!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

(ነፍሰ ኄር ኮ/ል ካሣሁን የወታደራዊ መረጃ እና ደኅንነት ከፍተኛ መኮንን ነበሩ)፤

1.  ምክንያተ-ጽሕፈት፤

የመቄዶንያው በጎ ሰው፣ ዶ/ር ብንያም በለጠ- ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባደረገው ቆይታው፤ በአያት 49/ፀበል አካባቢ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን ማእከልን ለማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሁሉ የዕርዳታ እጆቹን እንዲዘረጉለት ተማጽኗል፡፡

‹‹ወገን ቢረዳዳ ችግርም አይጎዳ፤ ኀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለኀምሳ ሰው ጌጡ ነው፤›› የሚለውን ሀገሪኛ ብሂላችንን መሠረት በማድረግ የመቄዶንያው ብንያም ያስተላለፈው የተማሕጽኖ መልእክት፤ ቀድሞ የመቄዶንያ የአረጋውያን ማእከል ኗሪ የነበሩ አንድ ትልቅ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ሰውን አስታወሰኝ፤ ኮ/ል ካሣሁን ትርፌ!!

2.  ኮ/ል ካሣሁን ትርፌን በጨረፍታ፤

መቄዶንያ ተስፋቸው ጨልሞባቸው በጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ በርካታ ወገኖቻችንን ከአስከፊ ሕይወት የታደገ፤ ለስንት አረጋውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሰብአዊ ፍቅርን የለኮሰ፤ የመኖር ተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ፤ የበጎነትና የፍቅር ማሳያ የሆነ ተቋም ነው፡፡ ታዲያ መቄዶንያ ከጎዳና ሕይወት ከታደጋቸውና የመኖርን ተስፋ ከቀጠለላቸው የሀገር ባለውለታ ከሆኑት ሰዎች መካከል ደግሞ፤ የወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ከፍተኛ መኮንን የነበሩት ነፍሰ ኄር፣ ሌተናል ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌ አንዱ ናቸው፡፡

ኮ/ል ካሣሁንን ለማግኘት ዕድሉን ያገኘሁት ከጥቂት ዓመታት በፊት በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ መርጃ ማእከል ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በአስተባበሪነት ስመራ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ በመቄዶንያ የበጎ ፈቃድ አግልግሎት ቆይታዬ ወቅት ሌተናል ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌን ቃለ-መጠይቅ አድርጌያቸው ነበር፡፡

ለዛሬ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ቃለ-መጠይቅ ያደረኳቸውን- የወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ከፍተኛ መኮንን የነበሩትን፤ ነፍሰ ኄር ሌተናል ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌን የሕይወት ጉዞ ከታሪክ ማስታወሻዬ በጥቂቱ አካፍላችሁ ዘንድ ወደድኹ፡፡

ኮ/ል ካሣሁን በግርማዊ ቀዳሚ ኃ/ሥላሴ እና በወታደራዊው ደርግ ዘመን መንግሥታት የወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ከፍተኛ መኮንን ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግ መላው ሀገሪቱን ሲቆጣጠርም መንግሥት ሙያዊ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ ከተደረገላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ወታደራዊ የጦር መኮንኖች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

ኮ/ል ካሣሁን በመከላከያ ሚ/ር መስሪያ ቤት አካል በመሆን በወቅቱ የነበረውን ጦር በወታደራዊ መረጃና ደኅንነት መስክ ለሁለት ዓመታት ያህል አሠልጠነዋል፡፡ ከመንግሥት የተሠጣቸውን ግዴታቸውን ከፈጸሙ በኋላም ጡረታቸው ተከብሮላቸው ከመከላከያ መስሪያ ቤት በክብር ተሰናበቱ፡፡ ኮሎኔሉ ከዚህ በኋላ የስለላ መጻሕፍትን በመተርጎምና በግል ጋዜጦች ላይ የውጪ ዜናዎችን በመተርጎም ሥራ ላይ ነበር የተሰማሩት፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ የትዳር አጋራቸውን በድንገት ያጡት ኮሎኔል ካሣሁን ባጋጠማቸው የጤና መታወክ፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅልና ሱስ የተነሳ ወደ ጎዳና ሕይወት ወጡ፡፡ ኮሎኔል የጎዳና ኑሮአቸውንም በአዲስ ከተማ አካባቢ በሚገኘው በዳጃዝማች ገነሜ ትምህርት ቤት አጥር ሥር ነበር ያደረጉት፡፡ በዛም የአካባቢው ወጣቶች እንደ ነገሩ በሠሩላቸው የላስቲክ ቤት ውስጥ ለ2 ዓመት ያህል ኖረዋል፡፡

በወቅቱ የመቄዶንያ የአረጋውያን ማእከል የበጎ ፈቃድ አገልጋይና የአዲስ ከተማ የመስናዶ ት/ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሰላማዊት ለማእከሉ በሰጠችው ጥቆማ መሠረት ኮ/ል ካሣሁን ከጎዳና ተነስተው ወደ መቄዶንያ ማእከል ገቡ፡፡ ወደ መቄዶንያ ማእከል እስኪገቡ ድረስ ስለ ኮ/ል ካሣሁን ምንም የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡

ከወገባቸው በታች መንቀሳቀስ የማይችሉት ኮ/ል ካሣሁን ትርፌ ወደ ማእከሉ ከገቡ በኋላም ለተወሰነ ጊዜያት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት በተሸከርካሪ ወንበር/wheelchair ላይ ሆነው በሰው ድጋፍ ነበር፡፡ የመቄዶንያን ቤተሰባዊ ፍቅርና እንክብካቤ፣ የአማኑኤል ሆስፒታል ሐኪሞችን የሕክምና እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ያገኙት ኮ/ል ካሣሁን ትርፌ በ3 ወራት ውስጥ ጤናቸው ተሻሽሎ፤ በአካልም በመንፈስ ጠንካራ ሆነው በእግራቸው መራመድ ጀመሩ፡፡

የኮሎኔል ታሪክም፤ ‹‹የጎዳና ተዳዳሪው የወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ከፍተኛ መኮንን ኮ/ል ካሣሁን ትርፌ!›› በሚል አርእስት በተለያዩ የሕትመት ሚዲያዎች ላይ ለንባብ በቃ፡፡

ይህ የኮ/ል ካሣሁን ታሪክ በሪፖርተር ጋዜጣ በወጣ ማግሥት፤ ‹‹ኮ/ል ካሣሁን ትርፌን የት ናቸው፤ እባካችሁ አሳዩን!!›› የሚሉ ጎብኚዎች የመቄዶንያን ግቢ አጨናነቁት፡፡ ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች፣ የኪነ-ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ታዋቂ ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች… ይገኙበታል፡፡

3.  ኮ/ል ካሣሁን ትርፌ እና የሕወሓቱ አቦይ ስብሐት ነጋ በመቄዶንያ …

ይቀጥላል …

ይህንና ሌሎች የኮ/ል ካሣሁን ትርፌን የተመለከቱት ታሪካዊ መረጃዎችን በቀጣይ እስከ መቄዶንያ የገቢ ማሰባሰቢያ እለት ድረስ በከታታይ ለማስነበብ እሞክራለሁ፡፡

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለዶ/ር ብንያም በለጠ/ለመቄዶንያ የአረጋውያን ሕንጻ ግንባታ፤ ‹‹የእገዛ ጥሪ!›› መልእክቱን ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሁሉ በማስተላለፍ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ አብረነው እንቁም፡፡

ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍም፤ ‹‹ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በፈጣሪ/በአምላክ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች፤ አረጋውያንን/ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ መጎብኘት፤ ማጽናናት…፤›› ነው እንዲል፡፡ (ያዕቆብ ፩፤፳፯)

ቅዱስ ቁርዓንም፤ ‹‹እነዚያ ገንዘቦቻቸውን በሌሊት እና በቀን በድብቅም በግልጽም የሚለግሱ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፤ በእነርሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነርሱም አያዝኑም፡፡ ይላል፡፡
(ሱራ አል-በቀራ 2፤274)

ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!!

ከዚህ ጽሑፍ ጋር አባሪ/አታች ያደረኳቸው ምስሎቹ ኮ/ል ካሣሁን ትርፌ በጎዳና ሕይወት በነበሩበትና ጊዜና በኋላም ወደ መቄዶንያ ከገቡ በኋላ ያላቸውን ለውጥ የሚያሳይ ነው!!
Filed in: Amharic